TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.4K photos
1.43K videos
206 files
3.95K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
⚫️ #ኢትዮጵያ ⚫️

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ምን ያልተፈጸም ፤ ምንስ ያልተደረገ ግፍ አለ ?

እጅግ በጣም ሚያስደነግጠው እንዲሁም ፍጹም ከሰውነት ተራ እየተወጣ መሆኑን የሚያሳየው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ልክ ጀግንነት ፣ በጎ ተግባር፣ ፍቅርን ለትውልድ የሚያስተላልፉ ይመስል ግፍና ጭካኔያቸውን በቪድዮ ማስረጃ እራሳቸው ቀርጸው ለትውልድ እያስቀመጡ መሆናቸው ነው።

በእርግጥም እንዲህ እየቀረጹ ማስቀመጣቸው ህዝቡን ለሚፈልጉት ዓላማ ለማነሳሳትና እርስ በርስ ለማባላት፣ ህዝቡን ወደ ግጭት ለማስገባት ሊሆን ይችላል።

በጥላቻ የሚፈጽሙት የግፍ ተግባራቸው አላረካ ብሏቸው ፣ " እዩልን ምን ያህል አውሬ እንደሆንን " የሚለውን ለማሳየትም ይሆናል።

በሀገራችን ፦
🔴 ሰው ከነህይወቱ ሲቃጠል
🔴 በድንጋይ ተወግሮ ሲገደል
🔴 በጅምላ በጥይት ተደብድቦ ወደ ገደል ሲከተት
🔴 አስክሬን ሲጎተት
🔴 አስክሬን አደባባይ ላይ ሲጣል
🔴 ተዘቅዝቆ ሲሰቀል
🔴 በስለት ተቀልቶ ሲገደል
🔴 የጥይት በረዶ ሲዘንብበት ... ኧረ ብዙ ብዙ በቪድዮ ተቀርጾ አይተናል።

ይኸው ዛሬ የሰው ልጅ ልክ እንደ ዶሮ " በስመአብ " ተብሎ ሲታረድ በቁማችን አየን።

ይህ ጭካኔ በማስረጃ በቪድዮ ተቀርጾ የወጣ ነው ለመሆኑ ስንት በቪድዮ ያልተቀረጸ ፣ በየአካባቢው የተፈጸመ ግፍ ይኖር ይሆን ?

እነዚህ ግፍ ፈጻሚ ሰዎች ሰይጣናዊ ስራቸውን በቪድዮ ቀርጸው ማስቀረታቸው በቤተሰብ ፣ በህዝብ ላይ የማይረሳ ቂም፣ ቁርሾና ቁስል ለማኖር ይመስላል።

የትም ይሁን ማንኛውም የግፍ ድርጊት ሲፈጸም ግን የሚቀድመው ድርጊቱን ከልብ አዝኖ ማውገዝ  ነው። ፍትህ ተጠያቂነት እንዲሰፍን መጠየቅ ፤ ለፍትህ መታገል ነው።

ልክ ሰው በሞተ ቁጥር ያለ አንዳች ሀዘን እና መከፋት ወደ ፖለቲካ ንትርክ መግባትና የሰው ደም ፈሶ እንዲቀር ለማድረግ መሯሯጥ የግፍ ግፍ ነው።

ከዚህ ቀደም ብዙ ታዝበናል።

ሰው በግፍ ይገደላል ከዛም ሰዎች በየማህበራዊ ሚዲያ ይመጡና " የኔ ወገን ሰው አይገድልም፤ ፍጹም ነው ፣ ፃድቅ ነው ፣ እንዲህ እንዲያደርግ ተፈጥሮው አይፈቅድለትም " እያሉ ድርጊቱ ያራክሱታል።

ሌላው ወገን ይመጣና በሞተው ንጹህ ሰው ደም ፖለቲካ ይሰራል። በጅምላ ጥላቻውን ይተፋል። በዚህ መንገድ የስንት ሰው ደም ፈሶ ቀረ ?

ላለፉት ዓመታት ሰው በግፍ ይገደላል ከዛ የቀናት የማህበራዊ ሚዲያ አጀንዳ ሆኖ ያልፋል፤ ይረሳል። ከዛ ሌላ ግፍ ሌላ ግድያ ይፈጸማል።

አንዳንዱ እውነት ከልቡ አዝኖ ፤ አንዳንዱ ደግሞ የይስሙላ ያዘነ ይመስል ሸፋፍኖ በማህበራዊ ሚዲያው ይጽፋል ፤ ይለፍፋል። ከሰዓታት በኃላ ሁሉም ረስቶት ምንም እንዳልተፈጠረ ወደ ህይወቱ ይመለሳል። ማህበራዊ ሚዲያ ሲገባ ትዝ ሲለው ለቀናት ስሜቱን ይፅፍ ይሆናል።

እስከ ህይወት ፍጻሜ ድረስ በሀዘን የሚቃጠሉትና ልጃቸውን የማይረሱት እናት አባት፣ ወንድም ፣ እህት ቤተሰብ፣ ዘመዶች ናቸው።

በተለይ እናት እና አባት ሲያለቅሱ ነው የሚኖሩት።

ይህ አዙሪት መቆም አለበት። ደመ በፈሰሰ ቁጥር ቁርሾ ቂም እየተወለደ እንጂ ፍቅር አንድነት አይመጣም።

ልጆቹን የተነጠቀ ቤተሰብና አካባቢ እንደሌላው የማህበራዊ ሚዲያ አርበኛ የአንድ ቀን ሀዘን አድርጎ አያልፈውም። የተፈጸመበትን ግፍና በደል መቼም አይረሳውም ! ቂም በውስጡ ያድራል። ይህ በሀገር ህዝብ ትስስር ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ከባድ ነው።

ከምንም በላይ ለተጎዱ ወገኖች ፍትህ በማስፈን ፣ ሌላ የአንድ ሰው ደም እንዳይፈስ በማድረግ አዙሪቱን ማቆም ካልተቻለ የከፋ ነገር መምጣቱ አይቀርም።

እዚህች ምድር ላይ ነገ ሳይሆን ዛሬ የሰው ልጅ ደም መፍሰስ እንዲቆም ማድረግ ይገባል።

ፍትህ ሊሰፍን ፤ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ ይገባል።

ታጣቂም ሆነ አልሆነ ፤ የአካባቢው ፣ የክልሉ የመንግሥት አካል ሆነ አልሆነ ሁሉም በየድርሻው በየደረጃው ሊጠየቅ ይገባል።

እጅግ በጣም አስገራሚው ነገር በምንም አይነት መንገድና ሁኔታ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ ስራው ሊሆን የሚገባው እና ችግርም ሲፈጠር ለህዝብ የማሳወቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ከማህበራዊ ሚዲያው ጩኸት በኃላ ለመናገር ሲወጣ መታየቱ ነው።

ለመሆኑ የሚፈጸመውን የሚሰማው ከህዝብ ጋር በሚዲያ ነው ? ነዋሪው በሚዲያ ባይጮህ ላያወግዝ ነው ?

ቆይ ልክ እንደማንኛውም ሌላ አካል " አወገዝኩ " ብቻ ነው የሚባለው  ወይስ ስለተፈጸመ ግፍ በዝርዝር አጣርቶ ለህዝብ ወጥቶ መረጃ መስጠት ነው የሚገባው ? የመንግሥት ስራ ድርሻው ምንድነው ? ለስንቱ ፍትህ ለተነፈገ እያነባ ላለ ወገን ፍትህ ሰጠ ? ተጠያቂነትን አሰፈነ ? በደል የደረሰባቸውን ካሰ ? ዳግም ደም እንዳይፈስ ተከላከል ? እኚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ ይሻሉ።

ህዝብ በሀገሩ የሚሆነውን ሁሉ ያያል ፣ ይታዘባል፣ ይገመግማል ፣ ነጥብም ይይዛል።

በምንም አይነት ሁኔታ የሰው ደም አይፈስስ ፤ ደም ሲፈስ ቂምና ቁርሾ እንጂ ፍቅርና አንድነት አይወለድም።

#ቲክቫህኢትዮጵያ
#TikvahEthiopia
#ናውስ

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
⚫️ #ኢትዮጵያ ⚫️ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ምን ያልተፈጸም ፤ ምንስ ያልተደረገ ግፍ አለ ? እጅግ በጣም ሚያስደነግጠው እንዲሁም ፍጹም ከሰውነት ተራ እየተወጣ መሆኑን የሚያሳየው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ልክ ጀግንነት ፣ በጎ ተግባር፣ ፍቅርን ለትውልድ የሚያስተላልፉ ይመስል ግፍና ጭካኔያቸውን በቪድዮ ማስረጃ እራሳቸው ቀርጸው ለትውልድ እያስቀመጡ መሆናቸው ነው። በእርግጥም እንዲህ እየቀረጹ ማስቀመጣቸው…
የእውነት ያለቀስነው መቼ ነው ?

አሁን ላይ ጨምሮ ባለፉት ዓመታት ምን ያህል ግፍ ምን ያህል ጭካኔ ሀገራችን ውስጥ እንደተፈጸመ መናገር መቼም ለቀባሪው ማርዳት ነው።

ግን ግን እውነት አብረን ያለቀስንበት ቀን መቼ ነው ? ትዝ የሚለውስ አለ ?

አንዱ በሀዘን ተሰብሮ ሲያለቅስ አንዱ ይስቃል  ይደሰታል ፤ አንዱ ሲደሰት አንዱ ያለቅሳል። ሁሉንም አንድ የሚያደርገው የሰብዓዊነት ስሜትም እየታየ ጠፍቷል ፤ ሞቶ አፈር ለብሷል።

ለማዘን ቅድሚያ ጥያቄው " ማነው ? የትኛው ወገን ነው ? " ብሎ መጠየቅ ተለማምደነዋል። " የኔ " የምንለው ሲሆን ማልቀስ " የሌላው ነው " ብለን ስናስብ ምንም እንዳልተፈጠረ ማለፍ ከዛም ከፍ ሲል ግፉን ኖርማል ለማድረግ መሮጥ ስራችን ሆኗል።

ሌላው ይቅር ግፍና መጥፎ ተግባር ማውገዝ እንኳን ሂሳብ ተሰልቶ ጥቅምና ጉዳቱ ታይቶ፣ ጩኸቱንና የህዝቡን ቁጣ ተመልክቶ ሆኗል።

ከምንም በላይ የሚስፈራው ጭካኔና ግፍ ለሚፈጽሙ ግለሰቦች ያውም ከነማስረስረጃቸው ለሚታዩ ሰዎች ጥብቅና መቆም ለነሱ መከራከር ልምድ እየሆነ መምጣቱ ነው።

" እባካችሁ ነገሩ በደንብ ይጣራ " ማለት አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ሰው የግፍ ፈጻሚዎቹ ማንነት የኔ ወገን ነው ብሎ ካሰበ " በፍጹም እንዲህ አያደርጉም ፤ የተፈጠሩበት ተፈጥሮና ስነልቦና አይፈቅድም " ብሎ ድምዳሜ በመስጠት ሌላ ግፍ መፈጸም ተለምዷል።

በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራ ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ... በሌሎችም ክልሎች በመንግሥት ታጣቂዎች፣ መንግሥትን እንፋለማለን ብለው በወጡ ታጣቂዎች ፣ ፓለቲከኞች በሚሰሩት ጥላቻ የተመረዙ ከማህበረሰቡ በወጡ ሰዎች ለማየት የሚከብድ ብዙ ግፍ ተሰርቶ ያውም በቪድዮ ተቀርጾ ታይቷል ዛሬም እዚሁ መንደር አለ።

ድርጊቶቹ ይፋ ሲወጡ አብሮ በጋራ ከማዘን ፍትህን ከመጠየቀ ይልቅ የፈጻሚዎቹ ደጋፊ ሆነው የሚቀርቡ ሰዎች በዘመቻ ነገሩን ለማራከስ እና እንዳልተፈጸመ ለማሳየት የሚሄዱበት ርቀት እውን ነገ ለወጥ ይመጣል ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

በሌላኛው ጎራ በንጹህ ሰው ደም ጥቅም ያስገኝልኛል ያለውን ፖለቲካ ይጫወታል። ከበፊትም እጠላዋለሁ የሚለውን አካል መርጦ ሌላ እልቂት ይቀሰቅሳል።

በዚህም መሃል በርካቶች እንደወጡ ቀርተው ፍትህ አላገኙም።

ለማህበራዊ ሚዲያ ሰዎች እና ሰላም ያለበት ከተማ ለሚኖሩ ነገሩ የሁለት ቀን ግፋ ቢል የሶስት ቀን አጀንዳ ሆኖ ያልፋል። ከዛ ሌላ ግፍ ይፈጸማል።

እናት አምጣ የወለደችውን ፤ ለፍታ ያሳደገችውን ልጅ እያሰበች ዘላለም በለቅሶ ትኖራለች። ወዳጅ ዘመድ ግፉን እያሰበ አመለካከቱ ተቀይሮና በመጥፎ ስሜት ተሞልቶ ለሌላው እንዳያዝን ሆኖ ይኖራል።

የስንቱ ቤት በሀዘን ፣ የስንቱ ሰው ልብ በቂምና ቁርሾ ፤ ሳይወድ በግዱ በመጥፎ አመለካከት ተሞልቶ ይሆን ?

ይህ ነገር ማብቃት አለበት። ተስፋ የሚሰጥ ትንሽ ሰብዓዊነት ሊኖር ይገባል። ማንም ይሁን ማን ተጠያቂነት ሊፈጠር፣ ፍትህ ሊሰፍን ይገባል።

እናቶች የሞተው ልጆቻቸውን ባይመልስላቸውም ፍትህ ሲያገኙ ቢያንስ እንባቸው ይታበስ ተስፋቸው ይለመልም ይሆናል።

ፍትህ ሲገኝ ዜጎች በሀገራቸው ተስፋቸው ያብባል።

በምንም አይነት ሁኔታ በግጭት ፣ በጦርነት ሆነ በምንም መንገድ በምድሪቱ ደም አይፈሰስ ፣ ሰው አይበደል ፤ የሰው ደም በፈሰሰ ቁጥር ፤ በደል በተፈጸመ ቁጥር ቂም ጥላቻ፣ አለመተዛዘን እየተወለደ እየተስፋፋ ይመጣል።

ደስታውስ ይቅር እውነት አብረን መቼ ነው በጋራ ያለቀስነው ? ብለን እንጠይቅ። ከልብ እንኮንን፣ ሂሳብ አንስራ ፤ የሰው ደም ላይ ፖለቲካ አንቆምር ፤ ለፍትህ እንታገል ! ካልሆነ የሁላችን እጣ ፋንታ እንደወጡ መቅረት ፍትህ አለማግኘት ይሆናል።

#TikvahEthiopia
#ቲክቫህኢትዮጵያ
#ናውስ

@tikvahethiopia