TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
58K photos
1.44K videos
208 files
4.01K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#አብን

አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ታፍሰው #ታሰሩብን" ሲል የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ አቤቱታ አሰማ። ሃያ ስምንት እንደሚሆኑ አብን ያሳወቃቸው አባላትና ደጋፊዎቹ የታሠሩት የመሪዎቻቸውን ጉዳይ ለመከታተል አዲስ አበባ፤ አራዳ ምድብ ችሎት ተገኝተው በነበረ ጊዜ መሆኑንም አብን ገልጿል። “የታሠሩብን ‘አማራነት እና እውነት አይታሰርም’ የሚል ሸሚዝ የለበሱ ናቸው” ሲሉ የንቅናቄው የፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በለጠ ካሣ ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። የተያዙት ሰዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው የሦስት ሺህ ብር ዋስ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውንም አቶ በለጠ አመልክተዋል።

ምንጭ፦ የአሜሪካ ድምፅ
@tsegabwolde @tikvahethiopia
#አብን

በእነ አስጠራው ከበደ እና በእነ ሲያምር ጌቴ መዝገብ የተከሰሱት የአብን አባላትና አመራራሮች በብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ተፈቀደላቸው ሲል አብን በፌስቡክ ጉፁ አሳወቀ። ከታሰሩ ከ1 ወር በላይ የሆናቸውና በእነ አስጠራው ከበደ መዝገብ የተከሰሱት 26ቱ የአብን አመራሮችና አባላት ዛሬ ማለትም ሐምሌ 23/2011 ዓ.ም 8:00 ላይ ለ3ኛ ጊዜ አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው የነበረ ሲሆን እያንዳንዳቸው በ1ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ወስኗል ብሏል ንቅናቄው። በሌላ በኩል በእነ ሲያምር ጌቴ መዝገብ የተከሰሱት ሲያምር ጌቴ በ3ሺህ ብር እንዲሁም ሌሎች እያንዳንዳቸው በ2 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን ንቅናቄው በፌስቡክ ገፁ ገልጿል።

@tsegabwolde @tikvahethiopia
#አብን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በእነ አስጠራው ከበደ እና በእነ ሲያምር ጌቴ መዝገብ የተጠረጠሩ የአብን አመራሮችና አባላት በዋስ እንዲወጡ የተሰጠውን ውሳኔ ውድቅ እንዳደረገ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/አብን/ በፌስቡክ ገፁ ገለፀ።

በእነ አስጠራው ከበደ እና በእነ ሲያምር ጌቴ መዝገብ የተከሰሱት የአብን አመራሮችና አባላት በብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም አቃቢ ሕግ ይግባኝ የጠየቀ ሲሆን ይግባኙን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የተፈቀደውን ዋስትና መብት ውድቅ በማድረግ ውሳኔ ሰጥቷል፤ ችሎቱ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ/ም መዝገቡን ቀጠሯል ሲል ንቅናቄው ገልጿል።

@tsegabwolde @tikvahethiopia
#አብን

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና ሌሎች ሶስት ሰዎች ላይ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ ቀሪ የምርመራ ስራዎችን አጠናቆ የተጠርጣሪዎቹን የወንጀል ተሳትፎ ለይቶ እንዲያቀርብ ለጳጉሜ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓም በተከሰተው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የግድያ ወንጀል ላይ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ትናንት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል። መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉበትን ወንጀል ለማጣራትና ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ሲጠይቅ፤ ተጠርጣሪዎቹ ”በቁጥጥር ስር የዋልነው በፖለቲካ አቋማችን ነው” በማለት ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ👇
https://telegra.ph/ABN-08-10

Via #ENA
@tsegabwolde @tikvahethiopia
"የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ የኖረ ፣ ክፉ ደጉን በጋራ ያሳለፈ፣ የተጋባ፣ የተዋለደ፣ የተዋሃደ ሕዝብ ነው!" #አብን

የኢሬቻ በዓልን በተመለከተ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ:-

ከሁሉም በማስቀደም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ወንድም ለሆነው የኦሮሞ ሕዝብ እንኳን ለኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን ይገልፃል። የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ የኖረ ፣ ክፉ ደጉን በጋራ ያሳለፈ፣ የተጋባ፣ የተዋለደ፣ የተዋሃደ ሕዝብ ነው። ሃቁ ይህ ሆኖ እያለ ባለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ የተፈጠሩት ጥራዝ ነጠቅና በአማራ ጥላቻ የሰከሩ ብሔርተኞች የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት የጨቋኝና የተጨቋኝ ፤ አለፍ ሲልም የቅኝ ገዢና ተገዢ አድርገው በማቅረብ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀውን ጠንካራ ትስስር ለማላላት ቢሰሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ዛሬም እንደትላንቱ የአማራ ሕዝብ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በጋራ አርሶ፣ ነግዶ፣ ሰርቶ፣ ተጎራብቶ ፣ እየተጋባና እየተዋለደ፣ በሃዘን በደስታው እየተገናኘ አብሮ እየኖረ ነው።

ተጨማሪ የንብቡ👇
https://telegra.ph/ETH-10-04-3

@tsegabwolde @tikvahethiopia
#አብን

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዶ/ር በለጠ ሞላን በድጋሚ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ።

አቶ መልካሙ ሹምዬ ደግሞ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።

የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ ፤ ፓርቲው ለ3 ቀናት የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ሲያካሂድ እንደቆየና የሥራ አስፈፃሚ አባላቱን በአዲስ በማደራጀት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት፦

👉 ዶ/ር በለጠ ሞላ - ሊቀመንበር
👉 አቶ መልካሙ ሹምዬ - ምክትል ሊቀመንበር
👉 ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ - የውጭ ግንኙነት ኃላፊ
👉 አቶ ዩሱፍ ኢብራሒም - የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ
👉 አቶ ክርስቲያን ታደለ - የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ክፍል ኃላፊ
👉 አቶ ጋሻው መርሻ - የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ
👉 አቶ ጣሂር መሐመድ - የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ
👉 ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም - የአብን ጽ/ቤት ኃላፊ
👉 አቶ ሐሳቡ ተስፋየ - አደረጃጀት ጉዳዮች ኃላፊ አድርጎ የሥራ አስፈፃሚውን በአዲስ አደራጅቷል።

ከተመረጡት የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚዎች መካከል ሦስቱ አዲስ መሆናቸው ተገልጿል።

ፓርቲው ዛሬ 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአማራ ክልል መዲና ባህር ዳር ማካሄድ መጀመሩን #ኢብኮ / #አሚኮ ዘግቧል።

@tikvahethiopia
#አብን

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ከድርጅት ህገ-ደንብ እና አሰራር ውጭ በመሆን አፍራሽ ድርጊቶችንና የዲሲፕሊን ጥሰቶችን ፈፅመዋል ባላቸው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ላይ የእርምት ውሳኔ ማሳለፉን አሳውቋል።

የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በ29/8/2014 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ነው በፓርቲው መዋቅር የተለያዩ የሃላፊነት እርከኖች ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ የዲሲፕሊን እና ድርጅታዊ መርህ ጥሰቶችን በተመለከተ ተወያይቶ የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ የተለያዩ ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ያሳወቀው።

ፓርቲው በዚህ ውሳኔው የንቅናቄው የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው ሲሆን " የንቅናቄው ከፍተኛ አመራር ሆነው ሳለ ፣ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው በተለያዩ አፍራሽ ድርጊቶች ላይ የተሳተፉ ሲሆን ፣ ከዚህ ቀደም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሁለት ጊዜ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል " ሲል ገልጿል።

" ይሁን እንጂ አሁንም በንቅናቄው ሥራ አስፈፃሚነታቸውም ሆነ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው በጋራ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ተገዥ ባለመሆን እና ንቅናቄውን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ አንጃኞች ጋር ሕብረት በመፍጠርና ፣ ንቅናቄው የሃሳብና የተግባር አንድነት እንዳይኖረው በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ስተለገኙ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ተወስኗል " ብሏል።

በሌላ በኩል ፤ ፓርቲው 10 የመካከለኛ አመራሮች እና አባላትን ከድርጅቱ ያገደ ሲሆን ለሁለት የቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

(ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ከላይ በደብዳቤው ተያይዟል)

@tikvahethiopia
#አብን #አቶ_ክርስቲያን_ታደለ

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሩና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ ፤ የአብን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አመራሮች ፣ አባላት፣ ደጋፊዎች ማዋከብ እና አፈና እየደረሰባቸው መሆኑን በመግለፅ ይህ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል አሉ።

ደርሷል ስላሉት ማዋከብ እና አፈና ፣ መቼ ? የት ? እንዴት ? እነማንን ? ስለሚሉ ዝርዝር ጉዳዮችን በግልፅ የሰጡት ማብራሪያ የለም።

አቶ ክርስቲያን በተረጋገጠው የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ፥ " አብን ዝቅ ሲል የአባላቱና ደጋፊዎች፥ ከፍ ሲልም የንቅናቄውን ዓላማ የሚጋሩ ኢትዮጵያውያን ንብረት መሆኑን ገዥው የብልጽግና ፓርቲና ያዋቀረው መንግስት በውል ሊያውቁት ይገባል " ብለዋል።

አክለውም " የተፎካካሪ ፓርቲ የውስጥ ጉዳይ የፓርቲው አባላትና በየደረጃው ያለው ሕጋዊ መዋቅር ጉዳይ ነው። የአብን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አመራሮችን፣ አባላትንና ደጋፊዎችን ማዋከቡ በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል " ሲሉ ገልፀዋል።

" እየተደረገ ያለው አፈናና ውርክቢያ ማንንም አይጠቅምም፤ በተለይ ደግሞ ገዥውን ፓርቲ አይጠቅምም " ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።

አቶ ክርስቲያን ፤ " አብን በሕዝብ ምርጫ በራሱ መንግስት ለመሆን የሚታገል ፓርቲ እንጂ የገዥው ፓርቲ ሁሉንም የመጠቅለል ስካር መደገፊያ ምርኩዝ አይደለም " ሲሉ ፅፈዋል።

አቶ ክርስቲያን ታደለ ከጥቂት ቀናት በፊት የፓርቲያቸው ስራ አስፈፃሚ ከህገደንብ እና አሰራር ውጭ በመሆን አፍራሽ ድርጊቶችን እና የዲሲፕሊን ጥሰቶችን ፈፅመዋል በሚል የመጨረሻ ያለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው እንደነበር ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ አቶ ክርስቲያን ፤ መሰል ውሳኔዎችን ለመወሰን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሥልጣን የሌለው መሆኑን መግለፃቸው አይዘነጋም።

@tikvahethiopia
#አብን

የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራሮቹ ያቀረቡትን ስራ መልቀቂያ አልቀበልም አለ።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል።

በስብሰባው በተለይ በፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር በለጠ ሞላ በኩል " አሁን ላሉ በርካታ ጉዳዮች ላለፉት 4 አመታት በከፍተኛ አመራርነት ያገለገልን አመራሮች ለቀን በአዲስ እንተካ " የሚለውን ሃሳብ ፓርቲው ጊዜ ሰጥቶ የተወያየበት መሆኑን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጣሂር ሞሀመድ ተናግረዋል።

ሆኖም ሊቀመንበሩ ያቀረቡትን የመልቀቂያ ሃሳብ ማዕከላዊ ኮሚቴው አልቀበልም ብሏል።

አሁን እየታየ ላለ ችግር የመፍትሄ አካል ለመሆን አዳዲስ አመራሮችን ወደፊት በማምጣት እንተካካ የሚለውን ሃሳብም ፓርቲው ሀምሌ 18/2014 በሚያካሂደው ስብሰባ በጥልቀት እንደሚያየውና እስከዛም ፓርቲው በትኩረት ስራውን እየሰራ እንደሚቀጥል ተገልጧል።

የፓርቲው ውስጣዊ አንድነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ የህዝብ ግንኙነት ኀላፊው አቶ ጣሂር ሞሀመድ " ማህበረሰቡ ውስጥ ላሉ ልዩ ልዩ ሃሳቦችና ለድርጅቱም አቅምና ውስጣዊ አንድነት የሚበጁትን ሃሳቦችና ውሳኔዎች የምናሳልፍበት ስብሰባ ሀምሌ 18 ይካሄዳል " ብለዋል።

#AMC

@TIKVAHETHIOPIA
#አብን

" ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ለቅቂያለሁ " - አቶ ክርስቲያን ታደለ

አቶ ክርስቲያ ታደለ ከአብን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት መልቀቃቸውን አሳወቁ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ እና የአብን አመራሩ አቶ ክርስቲያን ከሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት መልቀቃቸውን የገለፁት በተረጋገጠ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ነው።

አቶ ክርስቲያን በመልዕክታቸው " ከግንቦት 1፣ 2014 ዓ/ም ጀምሮ እንደሥራ አስፈፃሚ ተወስነው መሰራት የነበረባቸው ጉዳዮች ለውጥ ፈር በሆኑ ጥቂት ግለሰቦች ምክንያት ከስነስርዓት ውጭ እየተወሰኑ በመሆኑ የእኔ በስም ብቻ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተብሎ መቀጠል ትክክል አለመሆኑን ተረድቻለሁ " ብለዋል።

" የቤት ኅመማችንን በቤት ተነጋግረን እንቀርፋለን በሚል በዝምታ ቆይቻለሁ " ያሉት አቶ ክርስቲያን " በየደረጃው ባሉ የመዋቅራችን አባላትና አመራሮች ዘንድም ለምን ኃቁን አትነግረንም የሚል ወቀሳ አድርሶብኛል " ሲሉ አስረድተዋል።

አክለውም ፤ ለተቋም ማዕከላዊነትና ወንድማማችነት እሴት በሚል በዝምታ መቆየታቸውን ድርጅቱን ከማዳን ይልቅ እንዲፈርስ የመተባበር ያህል በመሆኑ እያደር ስጋት እንደፈጠረባቸው በዚህም ከስራ አፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ለመልቀቅ እንደወሰኑ ገልፀዋል።

እንደአብንን መስራችነታቸው እና ፓርቲውን ወክሎ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል እንደማሆናቸው እንዲሁም እንደ አንድ አማራ ንቅናቄው " ወደ ቀደመ ሥፍራውና ትክክለኛው የትግል መስመር ለመመለስ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ አንዳችስ እንኳን የምቆጥበው ነገር እንደማይኖረኝ አረጋግጣለሁ " ብለዋል።

(ሙሉ መልዕክታቸው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#Update ዛሬ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ያቀረቡትን የ6 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ተከትሎ፤ ከም/ቤት አባላት ጥያቄዎች ቀርበው ነበር። የም/ቤት አባል ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ " ከአንዳንድ ክልሎች በከፍተኛ መጠን ወደ ከተማዋ ይገባሉ " የተባሉ " ፍልሰተኞችን " በተመለከተ "ከአንዳንድ ክልሎች " የሚለው አገላለጽ ምን ማለት ነው? ክልሎቹ ቢገለጹ " ሲሉ ጠይቀዋል። " ከአንዳንድ…
#አብን

አብን የፌዴራል መንግስቱ/ገዢው ብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከንቲባን ከስልጣን እንዲያስነሳ እና ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠየቀ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ( #አብን ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዛሬ ለምክር ቤት ያቀረቡትን ሪፖርት አጥብቆ አውግዟል።

ፓርቲው ከንቲባ አዳነች አበቤ ዛሬ ለአዲስ አበባ ከተማ ም/ ቤት ባቀረቡት ሪፖርት " ከአንዳንድ ክልሎች የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት መንግስትን በመጣል በኃይል ስልጣን ለመቆጣጠር ያለመ ነው " ሲሉ ሪፖርት ማቅረባቸውን ከተለያዩ ሚዲያ ዘገባዎች እና ከውስጥ ምንጮቻችን አረጋግጠናል ብሏል።

ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ይህን ማለታቸው አደገኛ ከፋፋይ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ነው ያለ ሲሆን ይህም አገረ መንግስቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና በማናቸውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው የዓለም አቀፍ ወንጀል ጥሪ ነው ሲል ገልጾታል።

አብን ፤ ዜጎች በነፃነት ተዘዋውረው የመስራት እና የመኖር ሰብዓዊ መብት ያላቸው መሆኑ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥምምነቶች ድንጋጌዎች እና በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግስት ጭምር የተረጋገጡ ተፈጥሯዊ መብቶች ናቸው ብሏል።

ፓርቲው በመግለጫው ፤ ከንቲባዋ " የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ " እየተባለ በሚጠራው ጽንፈኛ እና በአንድ ወቅት መንግስት ራሱ " የሽብርተኞች መጠቀሚያ ነው " ብሎ በፈረጀው ሚዲያ በተከታታይ የወጡ ቅስቀሳዎች ቅጥያ የሆነ አደገኛ የወንጀል ቅስቀሳ አድርገዋል ሲል ከሷል።

" ዓለም አቀፍ ከተማን በከንቲባነት እመራለሁ ከሚል የመንግስት ባለስልጣን እንዲህ ዓይነት አደገኛ ቅስቀሳ በሪፖርትነት መሰማቱ እስካሁን ሲፈፀሙ ለነበሩ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች እና እየታወጀ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ከለላ የሚሆን አደገኛ የወንጀል ድርጊት ጥሪ ነው " ሲል ፓርቲው ገልጿል።

አብን በመግለጫው ፤ " ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ይኼንን አደገኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ትኩረት በመስጠት አስቀድሞ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ታሪካዊ ጥሪ እያደረግን፤ በተለይ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ይኼንን ባያደርግ በሩዋንዳ የፈፀመውን ታሪካዊ ስህተት የሚደግመው መሆኑን ማስረገጥ እንሻለን " ብሏል።

በሌላ በኩል ፥ የፌደራል መንግስቱ ሆነ ገዥው የብልጽግና ፓርቲ ይኼንን አደገኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ያደረጉትን ግለሰብ ከስልጣን እንዲያነሳና ለፍርድ እንዲያቀርብ ጥሪ እናቀርባለን ያለ ሲሆን " መሰል ድርጊት በድጋሚ እንዳይፈፀም መንግስታዊ ማረጋገጫ ጭምር እንዲሰጥ ጥሪ እናቀርባለን " ብሏል።

@tikvahethiopia
#አብን #ኢዜማ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በሀገራዊ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የመጀመሪያ ዙር ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ላይ አስታውቀዋል።

በቀጣይም #በሚያግባቡ_ሀገራዊ_ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን ለማድረግና #የጋራ_አቋም ለመያዝ ከስምምነት ላይ መደረሳቸውንም ገልፀዋል።

ሁለቱ ፓርቲዎች የ " ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ / ህወሓት " ን ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዝን በቅድሚያ የተቃወሙ ፓርቲዎች ናቸው።

ፓርቲዎቹ ተቃውሟቸውን በየተናጠል ባወጡት በመግለጫ አሳውቀዋል።

ይህ ከተሰማ ከሰዓታት በኃላ ነው ሁለቱ ፓርቲዎች በሚያግባቡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን ለማድረግና የጋራ አቋም ለመያዝ ከስምምነት ላይ እንደደረሱ የተነገረው።

@tikvahethiopia
#አብን

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ ፤ መንግሥት በአማራ ክልል ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በቀጥታ በመወያየት ለተፈጠሩት ችግሮች እልባት የመስጠት ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳሰበ።

ፓርቲው ፤ በተለይ ለሀገራቸው ሉዓላዊነትና አንድነት በጋራ ተሰልፈው መስዋዕትነት የከፈሉት የአማራ ልዩ ሀይል፣ ፋኖ እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ቅራኔ ውስጥ እንዳይገቡና ለግጭት እንዳይዳረጉ በከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብሏል።

" መንግስት የክፉ ቀን አጋሩ ከነበሩትና በእውነትም ከሕዝብና ከሃገር ፍላጎትና ጥቅም በተፃራሪ የመቆም ተሞክሮ፣ ዝንባሌና ታሪክ ከሌላቸው የአማራ ገበሬዎች፣ ወጣቶችና ፋኖዎች ጋር ያልተገባ ግብግብ ውስጥ መግባት የለበትም " ያለው አብን አሁን ያለው ችግር በውይይት እና ምክክር ሊፈታ የሚችል መሆኑን አስገንዝቧል።

በሌላ በኩል ፓርቲው የተለያዩ የፖለቲካ አጀንዳዎቻቸውን በሸፍጥ ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ አካላት ባልተገባ መልኩ የአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው እንደሚቀርቡ ሊታወቅ ይገባል ብሏል።

አብን ፤ የአማራ ሕዝብ ድንገተኛ ወዳጅ እና ወኪል በመሆን ግጭት ለማስነሳት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አመልክቶ ፤ እነዚህ አካላት ይህን ድርጊታቸውን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ አሳስቧል።

የአማራ ሕዝብ እነዚህ አካላት የሚያደርጓቸውን አደንቋሪ የጥፋት ጥሪዎች ፈፅሞ እንዳይሰማ ሲል ፓርቲው አስገንዝቧል።

በተለይ የአማራ ወጣቶች፣ ፋኖዎች እና የልዩ ሃይል አባላት ፦
- የሕዝቡ ሰላም እና ደህንነት እንዳይናጋ፣
- የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዳይሰተጓጎሉ፣
- የልማት ስራዎች እንዳይኮላሹ፣
- በዋናነት ደግሞ ህዝብ ላይ ምንም አይነት አካላዊ እና የህይወት ጉዳት እንዳይደርስ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትም በጊዜያዊ ስሜት ሳይገፋ በሆደ ሰፊነት ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ተመሳሳይ ትጋት እንዲያሳይ አብን ጥሪ አቅርቧል።

አብን በመግለጫው ፥ " ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአማራ ሕዝብ ያሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዲዘነጋና በምትኩ በደራሽና ስሜታዊነት በተጫናቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያተኩር የሚገፋፉ እንቅስቃሴዎች፣ ከውስጥና ከውጭ የሚደረጉ የአፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳዎች ሰለባ እንዳይሆን ህዝባችንና የህዝባችን ወዳጆች ሁሉ አዎንታዊ እገዛ እንድታደርጉ እንጠይቃለን " ብሏል ።

የአማራ ህዝብ ግራ ቀኙን በአግባቡ መዝኖ በስሙ የሚነግዱ ኃይሎችን ይሁንታ ሊነሳቸው እንደሚገባ አብን ጥሪ አቅርቧል።

(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia
#አብን

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ አውጥቶ ነበር።

አብን በዚህ መግለጫው ፤ በየትኛውም አሰላለፍ እና አግባብ ስለአማራ ህዝብ የተሰለፉ ሀይሎች #ጦርነት ዘላቂ ጥቅምን ለማረጋገጥ አስቻይ እንዳልሆነ ሊገነዘቡት ይገባል ብሏል።

ይልቁን ጦርነት ህዝብን ለተደራራቢ የማህበራዊ ፣ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ድቀት ስለሚዳርግ ለሰላማዊ የፖለቲካ መፍትሄዎች ተገቢውን ስፍራ ሰጥተው ለክልሉ ሰላም መመለስ  ድርሻቸውን እንዲወጡ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

" የአማራ ህዝብ ከሌላው የሀገሪቱ ህዝብ ጋር ያለውን የወንድማማችነት እሴቶች ከሚንዱ ቅስቀሳዎች ፣ በራሱ እና በልጆቹ የተመሰረቱ ተቋማትን በተለይም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሚያጠለሹ መልዕክቶች እንዲሁም የአማራ ህዝብ ማህበራዊ ረፍት እንዲያጣ ከሚመኙ አካላት በስልት የሚሰጡትን አጀንዳዎች በመጸየፍ ወደ ሰላም መድረክ የሚያመሩ መንገዶችን ሁሉ ለመጥረግ አቅሙ የፈቀደውን ርብርብ እንዲያደርግ " ሲል አብን አሳስቧል።

(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia
#አብን

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር ከኃላፊነታቸው ለቀቁ።

የአብን ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ሹምዬ በገዛ ፍቃዳቸው ከድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርነት እና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት መልቀቃቸውን ለፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በፃፉት ደብዳቤ አሳውቀዋል።

ለምን እዚህ ውሳኔ ላይ ደረሱ ?

መልካሙ ሹምዬ ፤ በእስካሁኑ ቆይታቸው በግል እና በድርጅት ሥራዎች ያጋጠሙ ፈተናዎችን ለመቋቋም የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ነገር ግን ከአብላጫው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ያላቸው የአቋም ልዩነት እየሰፋ መሆዱን ጠቁመዋል።

የሃሳብ እና የአቋም ልዩነቱ ከሕዝቡን መብት ፣ ጥቅም እና ኅልውና መከበር አንጻር ያለው ትርጉም እና ውጤት ከፍ ያለ መሆኑን እንዳመኑበት ፤ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በኃላፊትነት መቀጠል የድርጅቱንና የሕዝቡን ጥቅም የሚያስከብር ሆኖ ባለማግኘታቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን አሳውቀዋል።

መልካሙ ሹምዬ ምንም እንኳን ከኃላፊነት በገዛ ፍቃዳቸው ቢለቁም የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ #አባልነታቸውን ይዘው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጻዋል።

@tikvahethiopia