TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
205 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
🔈 #የሐኪሞችድምጽ

" በህክምና ሞያ ብቻ 10 ዓመት በላይ ተምረናል እድሜያችን ወደ ጎልማሳነት ተጠግቷል ቤተሰብ ማስተዳደር ፣ ለልጆቻችን ወተት እና ዳይፕር መግዣ እስከማጣት ድረስ ነው ያቃተን "  - ሐኪም

በማዕከላዊ የኢትዮጵያ ክልል፣ ሃዲያ ዞን የሚገኘው ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ የሚያስተምሩ ሐኪሞች ፦
➡️ የ4 ወር ዲዩቲ (የትርፍ ሰዓት ስራ ክፍያ)፣
➡️ የ14 ወር የኦቨር ሎድ ክፍያ (Over load) 
➡️ የ2016 የአንዋላይዜሽን (Annualization) ክፍያ ስላልተከፈላቸው ማስተማራቸውን ለመቀጠል እንደሚቸገሩ ለዩኒቨርሲቲው በጻፉት ደብዳቤ አሳውቀዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተውና ለዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች የተጻፈው ደብዳቤ በቁጥር 48 የሚሆኑ መምህራን ሐኪሞች ፊርማቸውን አስፍረውበታል።

ከማህጸንና ጽንስ፣ ከውስጥ ደዌ ፣ ከሰርጀሪ እና ከህጻናት ህክምና ክፍል የተወጣጡ ናቸው።

በጻፉት ደብዳቤ ሐኪሞቹ የማስተማር ሂደቱ ላይና የተጠራቀሙ ልዩ ልዩ ክፍያዎችን በሚመለከት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትና ሌሎች ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች በተገኙበት ተደጋጋሚ ውይይቶችን ቢያደርጉም መፍትሄ ባለማግኘታቸው እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ይገልጸል።

በመሆኑም ከ05/02/17 ጀምሮ የማስተማር ስራቸውን በጊዜያዊነት እንዳቆሙና ለሚፈጠረው ማንኛውም ችግር ሃላፊነት እንደማይወስዱ ለዩኒቨርሲቲው አሳውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ለመምህራኑ ደብዳቤ ምላሹን በደብዳቤ የሰጠ ሲሆን የማስተማር ስራቸውን በመደበኛነት እንዲቀጥሉ እና ይህን የማያደርጉ መምህራን ሐኪሞች ላይ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታ አቅራቢ ሐኪሞችን በስልክ በማነጋገር ሃሳባቸውን ተቀብሏል።

በሆስፒታሉ የሚያስተምሩ የጤና ባለሞያዎች " የዲዩቲ ወይም የትርፍ ሰዓት ክፍያው ጨምሮ ሌሎችም ክፍያዎች እንዲከፈላቸው ተደጋጋሚ የሆነ ሙከራ ቢያደርጉም ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ማስፈራሪያ እየደረሰን ይገኛል " ብለዋል።

የህክምና ሞያ በባህሪው ከመደበኛ የስራ ሰዓት በተጨማሪ የምሽት እና የአዳር ሰዓትን ጨምሮ ለተጨማሪ ሰዓታት እንዲሰሩ የሚያስገድድ ሲሆን በሆስፒታሉ የሚያስተምሩ ሲኒየር ሐኪሞች ባለፉት 4 ወራት የሰሩበት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ስላልተከፈላቸው ለከባድ የኢኮኖሚ ጫና መዳረጋቸውን ነግረውናል።

ካነጋገርናቸው መካከል አንደኛው ሐኪም ፦

" በህክምና ሞያ ብቻ 10 ዓመት በላይ ተምረናል እድሜያችን ወደ ጎልማሳነት ተጠግቷል ቤተሰብ ማስተዳደር ፣ለልጆቻችን ወተት እና ዳይፕር መግዣ እስከ ማጣት ድረስ ነው ያቃተን።

እኛ ትርፍ ነገር አልጠየቅንም ኑሮ ውድነቱ የሚታወቅ ነው በደሞዝ ብቻ መኖር አልቻልንም ለልጆቻችን የምንቋጥረው ምግብ ከአቅም በላይ ሆኖብናል።

መሰረታዊ ፍላጎታችንን እናሟላ የሰራንበተን ክፈሉን ነው ያልነው " ብለዋል።

እንደ ሐኪሙ ገለጸ የኑሮ ውድነቱ በተለይም አነስ ያለ ደሞዝ በሚከፈላቸው ነርሶች ላይ ከፍቷል።

ምግብ ሳይበላ መጥቶ በስራ ላይ ሳለ ራሱን ስቶ የወደቀና የቤት ኪራይ የሚከፍለው አጥቶ ቴሌቪዥኑን ያስያዘ ነርስ በሆስፒታል አለ ነው ያሉት።

በሚሰሩበት እና በሚያስተምሩበት በዋቻሞ ዪኒቨርሲቲ ስር የሚገኘው የንግሥት እሊኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕረንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አመራሮችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲውን ሃላፊዎችን ቢያናግሩም መፍትሄ እንዳጡ ነግረውናል።

ቃላቸውን ለቲክቫህ የሰጡ ሐኪሞች " መኖር አልቻልንም " ሲሉ ክብደቱን አስረድተዋል።

ከተጠራቀመው የትርፍ ሰዓት ክፍያ ውስጥ የአንድ ወር ክፍያ ባለፈው ወር እንደተከፈላቸው ገልጸው ነገር ግን ዘግይቶ ስለተከፈለ " ከብድራችን አላለፈም ሁላችንም በብድር ነው የምንኖረው " ብለዋል።

" የብድር አዙሪት ውስጥ ገብተናል ደሞዝ እንቀበላለን ያልቃል ከዛ እንበደራለን፣ ብድር እንከፍላለን እንደዚህ ነው እየኖርን ያለነው " ሲሉ አስረድተዋል።

በተጨማሪ ሐኪሞቹ ፦

- የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ችግራቸውን ከመፍታት ይልቅ ሰዎችን ለይቶ ማስፈራራት ላይ እንደተጠመዱ ፤ የዲፓርትመንት ሃላፊዎችን ለይቶ በማስፈራራት " እናንተ ናችሁ እያሳመጻቹ ያላቹት የሙያ ፈቃዳቹ ይነጠቃል " እስከማለት እንደደረሱ፤

- ለሆስፒታሉ፣ ለተማሪው ፣ለማህበረሰቡ እና ለሰራተኞች የሚያስብ ሃላፊ እንዳጡ ፤

- ተወካዮች ከዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳዊት ሃየሶ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ፕሬዝዳንቱ " ችግሩ ያለው ግቢያቹ ውስጥ ነው የሆስፒታሉ የውስጥ ገቢ የት እንደሚሄድ አላውቅም የውስጥ ገቢው የተጠየቀውን ክፍያ መክፈል መቻል አለበት " ማለታቸውን፤

- ለቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሐብታሙ አበበ ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም ችግራቸው ሳይፈታ ፕሬዝዳንቱ በሙስና እና ሐብት ምዝበራ ወንጀል ተጠርጥረው ሐምሌ 15/2016 ዓም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፤

- ከትምህርት ሚኒስቴር ሊያማክሩ የመጡ በትምህርት ሚኒስትር ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የተወከሉ ሰዎች ባሉበት ስብሰባ ላይ አዲስ ፕሬዝዳንት ስለሆነ ጊዜ እንዲሰጠው ፣ ነገሮችን አስተካክሎ እና አይቶ የእነሱን ክፍያ በቅድሚያ እንዲከፈል እንደሚያደርጉ እንደነገሯቸው እና እስካሁን መታገሳቸውን ጠቁመዋል።

ነገር ግን እስካሁን ከመፍትሄ ይልቅ ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጻዋል።

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አያኖ ሻንቆ ምን ምላሽ ሰጡ ?

ስራ አስኪያጁ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃን ፥ መምህራኑ የጠየቁት ክፍያ ያልተከፈላቸው መሆኑን አምነዋል።

" አልከፍልም ያለ ሰው የለም ለምንድነው ስራ የሚያቆሙት ? የዲዩቲ እና ኦቨርሎድ ክፍያ ከደሞዝ ጋር አይገናኝም ለደሞዛቸው መስራት አለባቸው የትርፍ ሰዓት ክፍያ ግን ሲሰሩ ብቻ ነው መክፈል የሚቻለው አሁን ላለመግባት ከወሰኑ በቀጣይ ያልሰሩበት ይቆረጥባቸዋል " ብለዋል።

" በአንድ ጊዜ ያልተከፈለውን ክፍያ ሁሉ ለመክፈል የሆስፒታሉ በጀት የማይበቃ በመሆኑና ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ስለሌለ የሚመጣውን ገንዘብ ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ ሰጥተን ነው የምንከፍለው በጀቱን እየጠየቅን ነው ሲፈቀድ እንከፍላለን አንከፍልም ያለ የለም " ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም " ይህን መሰል ችግር እኛ ጋር ብቻ አይደለም ያለው እናንተ ጋር ስለደረሰ ነው እንጂ በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ችግር አለ " ያሉ ሲሆን " በእኛ በኩል በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ችግሩ ይፈታል ብለን እናስባለን " ብለዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM