TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.7K photos
1.44K videos
207 files
3.97K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
ቴሌግራም

በአዲስ አበባ ከተማ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች የብሔራዊ ፈተና መልሶችን በቴሌግራም ለማዘዋወር ሲሞክሩ መያዛቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና መሰጠት ከተጀመረበት ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ ቴሌግራምን ጨምሮ የተለያዩ የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።

ትናንት ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. የተጀመረው የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም እየተካሔደ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሐረጓ ማሞ "ጥቃቅን" ችግሮች መታየታቸውን ገልጸዋል። ችግሮቹ ፈተናውን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ አይደሉም ያሉት ወይዘሮ ሐረጓ በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ለፈተና የተቀመጡ ተማሪዎች "በቴሌግራም አፕልኬሽን ተጠቅመው መልሶቹን ለማዘዋወር ሲሞከር ወዲያው በቁጥጥር ሥር እንዲውል" ተደርጓል ሲሉ ለዶይቼ ቬለ «DW» ተናግረዋል። በውስን የኢንተርኔት ግንኙነት ውስጥ ግልጋሎት መስጠት የሚችለው የቴሌግራም የመልዕክት መለዋወጫ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። ከትናንት ጀምሮ ይኸው የቴሌግራም የመልዕክት መለዋወጫ #ባልታወቀ ምክንያት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ግልጋሎት መስጠት #አቁሞ ነበር። ኩነቱ መተግበሪያው በኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ግልጋሎት እንዳይሰጥ ታግዶ ይሆን የሚል ሥጋትም አጭሮ ነበር።

የቴሌግራምም ይሆን የኢንተርኔት ግልጋሎቶች በኢትዮጵያ ግልጋሎቶቻቸው የተቆራረጠበትን ምክንያት አገልግሎት አቅራቢው ኢትዮ-ቴሌኮም በይፋ አልገለጸም።

በርካታ ኢትዮጵያውያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ግልጋሎቱ ለብሔራዊ ፈተናው ደኅንነት ተብሎ ሳይቋረጥ እንዳልቀረ ጠርጥረዋል። የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠባቸው አካባቢዎች መካከል ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ጀምሮ ወደ ሥራ ተመልሷል። በአዲስ አበባ፣ በመቐለ፣ በቦረና፣ በባሕር ዳር፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በስልጤ ዞን ዳሎቻ አካባቢዎች የተቋረጠው የኢንተርኔት ግልጋሎት ሥራ ከጀመረባቸው መካከል ይገኙበታል። ዶይቼ ቬለ በአዲስ አበባ የተወሰኑ አካባቢዎች ቴሌግራም መስራት መጀመሩን ቢያረጋግጥም በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም እንደቆመ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ደርሰውታል።

በአዲስ አበባ የፈተና መልስ #በቴሌግራም በኩል ለማዘዋወር የተሞከረበትን ትምህርት ቤት ጨምሮ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት የተቆጠቡት ወይዘሮ #ሐረጓ "ይኸንን ያደረጉ ግለሰቦች ማንነት፤ የት ቦታ እንደተፈጸመ፤ የት ቦታ እንደተያዘ #በቅርብ ሪፖርት ይደረጋል የሚል ዕምነት አለኝ" ሲሉ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሐረጓ "ማንኛውንም የኤሌክትሮኒክ መሳሪያ በፈተና ክፍል ውስጥ ይዞ መገኘት እንደማይገባቸው ለፈታኞችም ለተፈታኝ ተማሪዎችም ተነግሯቸዋል። ያልተፈቀዱ ነገሮች ይዞ መግባት በራሱ አንድ ወንጀል ነው። ሁለተኛ ይዘው በገቡት መሳሪያ ፈተናውን ለሌላ ወገን ለማስተላለፍ መሞከር ደግሞ ሌላ ሁለተኛ የደምብ ጥሰት ነው" ብለዋል። የዘንድሮው የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከሰኔ 03 እስከ ሰኔ 05 ቀን 2011 ዓ.ም ይሰጣል። እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ሰኔ 6፣7፣10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሔዳል። በዚህ አመት 1,277,533 ተማሪዎች የ10ኛ ክፍል እንዲሁም 322,317 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ መመዝገባቸውን የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ መረጃ ይጠቁማል።

ምንጭ፦ DW
@tsegabwolde @tikvahethiopia