TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.8K photos
1.49K videos
211 files
4.06K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#AI

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰሩ የታዳጊ ሴቶች የእርቃን ምስሎች ስፔን ውስጥ ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠሩ ሲሆን ፖሊስ ምርመራ ላይ ነው።

በደቡባዊ ስፔን ውስጥ የምትገኘው አልመንድራሌሆ ከተማ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰሩ የታዳጊ ሴቶች እርቃን ምስሎች ከእነርሱ እውቅና ውጭ በማኅበራዊ ሚዲያ ከተዘዋወሩ በኋላ ድንጋጤ ውስጥ ገብታለች ሲል ቢቢሲ በድረገፁ አስነብቧል።

እርቃን ምስሎቹ የተሰሩት ሙሉ ልብስ ለብሰው የተነሱትን የታዳጊዎቹን ፎቶ በመጠቀም ነው።

በርካታ ምስሎቹ የተወሰዱትም ከታዳጊዎቹ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ነው።

ምስሎቹ ከተወሰዱ በኋላም አንድ ግለሰብ እርቃኑን ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ምናባዊ ምስል የሚፈጥር መተግበሪያ በመጠቀም የታዳጊዎቹ ምስል እርቃን እንዲቀር ተደርጓል።

እስካሁን ዕድሜያቸው በ11 እና በ17 ዓመት መካከል የሚገኙ 20 ታዳጊ ሴቶች፣ የዚህ ድርጊት ሰለባ መሆናቸውን በመግለጽ በደቡብ ምዕራብ ግዛቷ ባዳጆዝ ውስጥ በምትገኘው አልመንድራሌሆ ከተማ እና አቅራቢያው ሪፖርት አድርገዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩት ሐሰተኛ የእርቃን ምስሎች በታዳጊ ሴቶቹ ላይ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን አሳድረዋል።

የተወሰኑ ታዳጊዎች ከቤታቸው ለመውጣት እንደተሳቀቁ ተነግሯል።

ይህ ጉዳይ ወደ አደባባይ የወጣው ከታዳጊዎቹ ሴቶች መካከል የአንዷ እናት በሆነችው የማሕጸን ሐኪም ማሪያም አል አዲብ ምክንያት ነው።

አዲብ ማኅበራዊ ሚዲያዋን በመጠቀም ባወጣችው መልዕክት ምክንያት ጉዳዩ የስፔን ሕዝብ መነጋጋሪያ መሆን ችሏል።

አዲብ ታዳጊ ሴቶችንና ወላጆችን ለማረጋጋት ስትል በማኅበራዊ ሚዲያ ባጋራችው ቪዲዮ " የወጡት የAI ምስሎች የተፈጠሩት በበጋ ወቅት ቢሆንም ጉዳዩ ወደ አደባባይ የወጣው በቅርብ ቀናት ነው " ብላለች።

" ምን ያህል ሕጻናት ምስሎቹ እንደነበራቸው አናውቅም። ምስሎቹ የወሲብ ፊልም በሚጫንባቸው ገጾች ላይ ተጭነው እንደሆነም አናውቅም ነበር። ይህ ሁሉ ስጋት ነበረብን " ብላለች።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰሩ የታዳጊ ሴቶች እርቃን ምስሎችን ባማውጣት የተጠረጠሩ ታዳጊዎች ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 14 የሚደርስ ነው።

ፖሊስ ድርጊቱን እየመረመረ ሲሆን ምስሎቹን በመፍጠር ሒደት ውስጥ አሊያም በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ #ዋትስአፕ እና #ቴሌግራም በማጋራት ተሳትፈዋል ያላቸውን ቢያንስ አስራ አንድ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ታዳጊ ወንዶችን መለየቱን አስታውቋል።

መርማሪዎች ታዳጊ ወንዶቹ ሐሰተኛ ምስሎችን በመጠቀም ታዳጊ ሴቶቹን #በማስፈራራት ማግኘት የፈለጉት ነገር ስለመኖሩ ለማወቅ ምርመራ እያካሄዱ ነው።

#BBC

@tikvahethiopia
#አሜሪካ

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አንደኛ ዓመትን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

አንቶኒ ብሊንከን ምን አሉ ?

- ብሊንከን በደፈናው #ኢትዮጵያ እና #ኤርትራ ጠብ ከሚያጭሩ ድርጊቶች እንዲቆጠቡና የአካባቢውን አገራት ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር አለባቸው ብለዋል።

- የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ሙሉ ለሙሉ መውጣትን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

- ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረቱን ጨምሮ የተወሰዱ በጎ እርምጃዎችን አሜሪካ እንደምትደግፍ አሳውቀዋል።

- ህወሓት ኃይሎቹ ከባድ መሳሪያቸውን ፈትተው ተዋጊዎች ማሰናበት በተጀመረበት ጊዜ በትግራይ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፍን ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል። ለዚህም የኤርትራ ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ መውጣት አለባቸው ብለዋል።

- ብሊንከን አሜሪካ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉት ግጭቶች እንደሚያሳስባት ገልጸዋል። ያለው ነገር  በቀላሉ ሊታወክ የሚችለውን የኢትዮጵያን ሰላም አደጋ ላይ እንደጣለው አመልክተዋል።

- በአገሪቱ በተለያዩ ወገኖች የቀጠለው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና ጥቃት፣ " የመርዛማ ንግግሮች " መስፋፋት በጦርነቱ ምክንያት የሳሳውን ማኅበራዊ ትስስር የበለጠ እየሸረሸረው መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ፦
🔹አስተማማኝ የሽግግር ፍትሕ፣
🔹ሐቀኛ እና አካታች ብሔራዊ ምክክር በመላዋ አገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱትን ግጭቶች ለመፍታት ውይይት እንዲደረግ አስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል።

#BBC
#SecretaryofStateAntonyJBlinken

@tikvahethiopia
#Kenya

የጎረቤት ኬንያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ብሔራዊ መታወቂያ ካርድ ለማውጣት ዜጎች ክፍያ እንዲፈጽሙ መንግሥት ያወጣውን መመሪያ #አገደ

የኬንያ መንግሥት ይህን መመሪያ ማውጣቱን ተከትሎ ዜጎች ቅሬታቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ማጋሬ ጊኬንይ የተባሉ ሐኪም ናቸው መንግሥት አዲሱን መመሪያ ያወጣው “ድንገተኛ እና ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ” ነው ሲሉ የሕዝብ ድምፅ በማሰባሰብ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት።

የተሰበሰበው የሕዝብ ድምፅ እንደሚለው በአዲሱ መመሪያ መሠረት፤ በርካታ ዜጎች መታወቂያ ካርድ በቀላሉ ማግኘት አይችሉም።

ከዚህ ቀደም በነፃ ይሰጥ የነበረው ብሔራዊ መታወቂያ ካርድ አሁን 1 ሺህ ሺልንግ [370 ብር ገደማ] እንዲሆን መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አዟል።

መታወቂያ ለማሳደስ ደግሞ ኬንያዊያን 2 ሺህ ሺልንግ እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል።

ኬንያዊያን እያሻቀበ ባለው የኑሮ ግሽበት ምሬታቸውን እየገለጡ ባሉበት ወቅት ነው መንግሥት ገቢውን ለማሳደግ ሲል ዜጎች ከዚህ ቀደም በነፃ አሊያም በርካሽ የሚያገኟቸውን አገልግሎቶች በበለጠ ክፍያ እንዲሆን ያደረገው።

በርካታ ኬንያዊያን በሚከፍሉት ግብር አማካይነት ተግባራዊ እየሆኑ ላሉ የመንግሥት ግልጋሎቶች ተጨማሪ ክፍያ መጠየቃችን ተገቢ አይደለም እያሉ ናቸው።

አዲሱ መመሪያ መታወቂያ ካርድ ብቻ ሳይሆን ፓስፖርት፣ የጋብቻ ወረቀት፣ የሥራ እና የመኖሪያ ፈቃድ እንዲሁም የልደት እና ሞት ምስክር ወረቀት ለማውጣትም ክፍያ ይጠይቃል።

አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት አሊያም ለማሳደስ ይጠየቅ የነበረው ክፍያ 50 በመቶ ሲያድግ የልደት እና ሞት ወረቀት ለማውጣት የሚጠየቅ ክፍያ በአራት እጥፍ አድጎ 200 ሺልንግ ገብቷል።

መንግሥት በተጨማሪ ዜግነት አሊያም የመኖሪያ ፈቃድ ለማስጠት የሚጠይቀውን ክፍያ እጥፍ አድርጎታል።

ከኬንያዊያን ዜጎች በውጭ ሃገር የተወለዱ ልጆች የኬንያ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቁት ክፍያ 1 ሚሊዮን ሺልንግ ሆኗል።

በደንገት የተጫኑት የክፍያ መመሪያዎች አቅም የሌላቸው ዜጎች የመንግሥትን ግልጋሎት ተጠቅመው አስፈላጊ ወረቀት ለማግኘት ሊቸገሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ጭሯል።

ባለፈው ዓመት መስከረም ወደ ሥልጣን የመጡት የፕሬዝደንት ሩቶ መንግሥት በርካታ የግብር ዓይነቶችን ዜጎች ላይ የጣለ ሲሆን የነዳጅ ዋጋ ከፍ እንዲልም አድርጓል።

የብሔራዊ ፓርክ መግቢያ ዋጋን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት አገልግሎቶች ክፍያ ከፍ እንዲልም ሆኗል።

ባለፈው ሳምንት የገቢዎች መ/ቤት ባለሥልጣናት ወደ ኬንያ የሚመጡ ዜጎችም ሆኑ ጎብኝዎች ከ500 ዶላር በላይ ተመን ያለው ዕቃ ይዘው ከተገኙ ይቀረጣሉ ብሏል።

ፕሬዝደንት ሩቶ እስካሁን ስለ ዋጋው ጭማሪ ያሉት ነገር ባይኖርም ሐሙስ ዕለት ለሃገሪቱ ዜጎች ባስተላለፉት መልዕክት ኬንያዊያንን ከዕዳ ጫና ለማላቀቅ " ቀላል ያልሆኑ ግን አስፈላጊ " ውሳኔዎችን ለመውሰድ ተገድጃለሁ ብለዋል።

#BBC

@tikvahethiopia
ቪድዮ፦ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በረራ ላይ ሳለ #መስኮቱ_መገንጠሉን ተከትሎ አንድ የአሜሪካ አየር መንገድ አውሮፕላኑን ከበረራ አግዶታል።

የአሜሪካው አላስካ አየር መንገድ በቁጥር 65 የሆኑ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖቹን አግዷል።

እገዳው በበረራ ወቅት የአንደኛው አውሮፕላን መስኮት ተገንጥሎ አውሮፕላኑ በአስቸኳይ ለማረፍ ከተገደደ በኋላ ነው።

አርብ ዕለት በኦሬጎን ግዛት ከፖርትላንድ ከተማ ተነስቶ ወደ ካሊፎርኒያ ሲበር የነበረው አውሮፕላን የገጠመውን አደጋ ተከትሎ ከ35 ደቂቃዎች በረራ በኋላ በመነሻው ለማረፍ ተገዷል።

አየር መንገዱ በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩት 177 ተሳፋሪዎች እና ሠራተኞች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው አውሮፕላኑ #በሰላም አርፏል ብሏል።

የአደጋው መንስዔ እስኪጣራ ድረስ ሁሉንም 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች በጊዜያዊነት ከበረራ እንዳገደ አየር መንገዱ አስታውቋል።

ይህ ቦይንግ ሰራሹ አውሮፕላን ባለፉት ዓመታት መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

ከአምስት ዓመት በፊት #በኢትዮጵያ እና #ኢንዶኔዢያ ባጋጠመ አደጋ ምክንያት ከበረራ ታግዶ የነበረው ይህ ማክስ 737 ዝርያ መሆኑ ይታወቃል። #BBC

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#EHRC የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በአማራ ከልል ምዕራብ ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ በ20/05/2016 ዓ.ም በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖች መካከል በነበረ ግጭት ከፍተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንደደረሱት ባወጣው መግለጫ አሳውቋል። በእዚህ ግጭት ምክንያት በመርዓዊ ከተማ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ እንደነበር…
#USA #ETHIOPIA #MERAWI

በአማራ ክልል መርዓዊ ከተማ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ በማድረግ ግድያ የፈጸሙ ላይ ምርመራ ተደርጎ ለፍርድ እንዲቀርቡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጠየቁ።

አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በኤምባሲው የX ገጽ ላይ ባወጡት መልዕክት በመርዓዊ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በሚመለከት የወጡ ሪፖርቶች የአሜሪካ መንግሥትን እንደሚያሳስበው ገልጸዋል።

አምባሳደር ማሲንጋ፣ የክስተቱን አሳሳቢነት ከመግለጻቸው ባሻገር " የግድያውን ፈጻሚዎች ለሕግ ለማቅረብ " ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ተቆጣጣሪዎች ምንም ገደብ ሳይደረግባቸው ወደ ሥፍራው እንዲንቀሳቀሱ እንዲፈቀድላቸው እንዲሁም በግድያው ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በአገሪቱ ባሉት የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ በሌሎችም ቦታዎች ላይ " በመንግሥት እና ከመንግሥት ውጪ በሆኑ ኃይሎች በተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች እና ጥቃቶችን መፈጸማቸውን የሚያመልክቱ በርካታ የሚረብሹ ሪፖርቶች " እየወጡ መሆናቸውንም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

" ኃይል ሳይሆን ውይይት ብቸኛው አማራጭ ነው"ም ሲሉ አሳውቀዋል። #USEmbassy #BBC

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#Update የአማራ ክልል መንግሥት ምን አለ ? ዛሬ የአማራ ክልል መንግሥት ይፋዊ መግለጫ ሰጠ። የክልሉ መንግሥት ፥ " ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ መማር የተሳነው ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሓት) የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል " ሲል ከሷል። " ህወሓት የአማራ ክልል ተማሪዎችን መማሪያ መጽሐፍ እንደ ሰበብ ተጠቅሞ በይፋ ጦርነት ማወጁና…
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት  አቶ ጌታቸው ረዳ ከ ' ቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ' ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር።

በቃለምልልሱ ፥ ባለፉት ሳምንታት በአማራ እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የነበረው ግጭት በ " የሚሊሻ አባላት " መካከል እንጂ መደበኛ ኃይሎች የተሳተፉበት አልነበረም ብለዋል።

" አማራ ክልል በኩል የነበሩ ሚሊሻዎች የተለያዩ አስጊ እንቅስቃሴያዎችን ሲያደርጉ ነበር። በእኛ በኩል ያሉ የሚሊሻ አባላት ምላሽ ሰጥተዋል " ሲሉ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ያወጣውን መግለጫም  " መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ " ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱ #ተፈጻሚ_እንዳይሆን እያደረገ ያለው " ሕጋዊ የልሆነ የአማራ አስተዳደር ነው " ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ ጌታቸው በዚሁ ቃለ ምልልስ ፥ በሰላም ስምምነቱ መሰረት በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉትን ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከስምምነት መደረሱን አስታውሰዋል።

" ሕጋዊ ያልሆኑ አስተዳደሮችን ለማፍረስ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር አብረን እየሠራን ነው። ከአማራ ክልል ጋርም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ አብረን እየሠራን ነው " ብለዋል።

" የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚሹ አካላት እንዳሉ ግን በጣም እርግጠኞች ነን " ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ ጌታቸው እነዚህ አካላት እነማን እነደሆኑ በግልጽ በስም ጠርተው አልጠቀሱም።

#BBC #FocusonAfrica

@tikvahethiopia
" ሰላም እና ፍትህ ለማስፈን ያጠፋ መጠየቅ አለበት " - አቶ ጌታቸው ረዳ

በማህበራዊ ሚዲያ " ህወሓት ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ሊዋሃድ ድርድር እየተካሄደ ነው " የሚሉት መረጃዎች ፍጹም ሐሰተኛ ናቸው ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ለ ' ቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ' ተናግረዋል።

ብልፅግና እና ህወሓት ንግግር ማድረግ መጀመራቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው "  እነዚህ ንግግሮች ከውህደት ጋር የተያያዙ አይደሉም " ብለዋል።

" የቅርብ ጊዜው ንግግራችን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ስለማድረግ ነው። ውህደት አጀንዳም ሆኖ አያውቅም " ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ አሁን ላይ ከጠ/ሚ ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር ስላላቸው የስራ ግኝኑት በተመለከተ ፥ " ጥሩ የሥራ ግንኙነት ነው ያለን። የራሳችን የሆነ ልዩነት አለን። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አመለካከቶች አሉን " ብለዋል።

" የፕሪቶሪያው ስምምነት #አብረን_እንድንሠራ ዕድል ስለሰጠን፤ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችን ምንም ይሁኑ ምን አብረን እንድንሠራ አስችሎናል። ይህም ወደፊት ይቀጥላል ብዬ አስባለሁ " ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ፤ አቶ ጌታቸው በጦርነቱ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ በሙሉ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብለዋል።

" ማንም ሰው ቢሆን፤ እኔን ጨምሮ መጠየቅ አለብን። ማንም ነጻ እንዲሆን መፈቀድ የለበትም። ሰላም እና ፍትህ ለማስፈን ያጠፋ መጠየቅ አለበት " ሲሉ ገልጸዋል።

#BBC #FocusonAfrica

@tikvahethiopia
#USA

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሜክሲኮ በኩል ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን ለመቆጣጠር ያለመ አዲስ እና መጠነ ሰፊ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ዛሬ ይፋ እንደሚያደርጉ ተነግሯል።

ውሳኔው የአሜሪካ ኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት በየዕለቱ ከሚመለከቱት በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ ተጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በላይ አመልካቾች የሚቀርቡ ከሆነ ጥያቄያቸውን ሳይመለከቱ በቀጥታ ከአገር እንዲባረሩ ማድረግ የሚያስችል ሥልጣን ይሰጣል።

ይህም ድንበር ላይ ያሉ ባለሥልጣናት አሜሪካ የሚገቡ #ስደተኞች ቁጥርን እንዲገድቡ እንደሚያስችላቸው ተነግሯል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ባለፉት 4 ዓመታት ውስጥ ከ6.4 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ለመግባት እንደሞከሩ ተነግሯል።

ይህም እስካሁን ከታየው ከፍተኛው ነው።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ፤ ባይደን አሁን ላይ በ1952 የወጣውን በአሜሪካ ጥገኝነት የማግኘት ሥርዓትን ለመገደብ የሚያስችለውን ሕግ ለመጠቀም እያሰቡ እንደሆነ ዘግበዋል።

212 (ኤፍ) በመባል የሚታወቀው ሕግ ወደ አሜሪካ የሚገቡ የውጭ ዜጎች " ለአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም አስጊ የሚሆኑ ከሆነ " ፕሬዝዳንቱ " እንዳይገቡ ማገድ "  የሚያስችለው ነው።

#BBC
#USA #Immigration

@tikvahethiopia
#Malawi

ዛሬ የማላዊውን ምክትል ፕሬዝዳንት ሳውለስ ቺሊማን እና ሌሎች 9 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውሮፕላን ተሰውሯል።

እንደ አገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት መረጃ አውሮፕላኑ የማላዊ መከላከያ ኃይል ንብረት ነው።

ጥዋት ከሀገሪቱ ዋናው ከተማ ሊሎንዌ ከተነሳ በኋላ " ከራዳር ዕይታ ውጪ " ሆኗል። ምን ውስጥ ይግባ አይታወቅም።

የአገሪቱ የአቪዬሽን ባለሥልጣናት ከአውሮፕላኑ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ሞክረው ነበር ግን አልቻሉም።

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትም #የፍለጋ እና #ነፍስ_የማዳን ተልዕኮ እንዲካሄድ አዘዋል።

ም/ ፕሬዝዳንቱ መንግሥትን ወክለው በአንድ የቀድሞ የም/ቤት አባል የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ነበር በረራ የጀመሩት።

አብረዋቸው በርካታ የፓርቲያቸው ባለሥልጣናት ነበሩ።

Credit : #BBC

@tikvahethiopia
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
ቪድዮ ፦ የአሜሪካንን ገመና ለዓለም ሁሉ ያጋለጠው ' ዊክሊክስ ' የተሰኘው ድረገጽ መሥራች ጁሊያን አሳንጅ ለዓመታት ከዘለቀው የፍርድ ቤት ሙግት በኋላ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በደረሰው ስምምነት ከእስር ተለቋል።

አሳንጅ ለአምስት ዓመታት ያህል በዩናይትድ ኪንግደም እስር ላይ የነበረ ሲሆን አሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጣት ስትሞግት ነበር።

ከፍተኛ ምስጢራዊ ወታደራዊ መረጃዎችን ለዓለም ይፋ በማድረግ ክስ የቀረበበት አሳንጅ ጥፋተኝነቱን ማመኑን ተከትሎ ከዩኬ ከእስር ቤት በነጻ ተሰናብቷል።

ዩኬን ለቆም ወደ አውስትራሊያ ሄዷል።

ዊክሊክስ ከጦርነት ፣ ከስለላና ከሙስና ጋር የተያያዙ ምሥጢራዊ እንዲሁም መንግሥታዊ ሪፖርቶችን ጨምሮ ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰነዶችን ለዓለም ይፋ አድርጓል።

#StellaAssange
#BBC

@tikvahethiopia