TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.6K photos
1.44K videos
206 files
3.97K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ሽርካ

" በየቤቱ ይዘው በማገት ወደ ወንዝ አካባቢ ወስደዋቸው፤ አሰልፈው ነው የገደሏቸው " - ነዋሪዎች

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ ትላንት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች 9 ሰዎችን ከቤታቸው በመውሰድ መግደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች እና ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።

ግድያው የተፈጸመው ሐሙስ ኅዳር 19/ 2017 ዓ.ም. ከሌሊቱ 6፡00 አካባቢ መሆኑን ቤተሰቦች ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ 9 ወንዶችን ከቤታቸው ከወሰዱ በኋላ ወንዝ አካባቢ እንደገደሏቸው ገልጸዋል።

በወረዳው ሶሌ ፈረንቀሳ በተባለ ቀበሌ የተፈጸመው ግድያ " ሃይማኖት ተኮር " እንደሆነ ነዋሪዎች እና ቤተሰቦች አመልክተዋል።

" በየቤቱ ይዘው በማገት ወደ ወንዝ አካባቢ ወስደዋቸው፤ ዘጠኙን አንድ ላይ አሰልፈው ነው የገደሏቸው " ያሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ ከከሟቹች ውስጥ አንዱ የ42 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አጎታቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሟቾቹ " አንድ ሰፈር " የሚኖሩ ጎረቤቶች እና ዘመዳሞች እንደሆኑ የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪ ሰለባዎቹ " በሙሉ የእኛ ቤተሰቦች ናቸው " ብለዋል።

ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ አካባቢው ላይ እንደደረሱ የተናገሩ አንድ የተጎጂ ቤተሰብ ከሟቾቹ ውስጥ ወንድማቸው እንደሚገኝበት አረጋግጠዋል።

እኩለ ሌሊት ላይ ወደ መኖሪያ መንደሩ የመጡት ታጣቂዎች እያንዳንዱን ሟች ከየቤቱ ለቅመው ወደ ወንዝ ወስደው እንደገደሉ ተናግረዋል።

ስጋት ውስጥ የነበረው የአካባቢው ማኅበረሰብ በማግስቱ ዛሬ ተኩስ ወደተሰማበት አካባቢ ፍለጋ መውጣቱን የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ አስከሬን ወንዝ ዳር " እንዳለ ተረፍርፎ ተገኘ " ብለዋል።

በእርሻ እና እንጨት ሥራ የተሰማሩ ነበር የተባሉት የአራት ልጆች አባት ሟች ከሌሎች ሰለባዎች ጋር ፈረንቃሳ በተባለ ወንዝ አቅራቢያ ተገድለው ተገኝተዋል።

ከሟቾቹ መካከል ሁለት የ70 ዓመት አዛውንቶች እንደሚገኙ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከ45 ዓመት በታች የሆኑ እና በግብርና ሥራ የተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው ብለዋል።

የተገደሉት ሰዎች የቀብር ሥርዓት ዛሬ በሶሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል።

ነዋሪዎች በጥቃቱ ቀን ከአካባቢው ሌሎች አ5 ሰዎችም ታግተው እንደተወሰዱ ገልጸው እስካሁን ታጋቾቹ እንዳልተገኙ ተናግረዋል።

አንድ ቤተሰብ የታገቱት ሰዎችን አስከሬን እየጠበቀ እንደነበር ጠቁመው ተወሰዱበት በተባለው ቦታ ቢፈለጉም አስከሬናቸው አልተገኘም ብለዋል።

ሌላ ነዋሪ ግን ከወንዙ ተሻግሮ ቡርቃ በተባለ አካባቢ አራቱ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ጠቁመዋል።

ባለፉት ቀናት በአካባቢው ተመሳሳይ ግድያዎች እና እገታዎች እንደነበሩ የተናገሩ አንድ ነዋሪ የኅዳር 19ኙ ጥቃት " ሌላ ዙር ጥቃት ነው " ብለዋል።

" በግራ በቀኝ ግድያ አለ። ከሦስት ቀን በፊት ሦስት ወይም አራት ሰዎች ተገድለዋል " ብለዋል።

ወረዳቸው ግድያ እና እገታ በተደጋጋሚ የሚፈጸምበት መሆኑን አመልክተዋል።

የአካባቢው ነዋሪ በተደጋጋሚ ጥቃቶች " የተፈናቀለ ነው " ያሉ ሌላ ነዋሪው፤ አካባቢው ተረጋግቷል በሚል ሰብል ለመሰብሰብ ወደ ቀበሌው ያመሩ ሰዎችም የግድያው ሰለባ እንደሆኑ ተናግረዋል።

በአካባቢው የሸኔ ታጣቂዎች በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ የፀጥታ ኃይሎች ጥቃት በደረሰበት ሶሌ ፈረንቀሳ ቀበሌ " የጥይት ተኩስ " በሚሰማበት ርቀት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

" ያን ያህል ርቀት በሌለበት ቦታ ላይ ነው ሰው እየተገደለ፤ ሰው ሞተ የሚለውን የሚሰሙት። ሁለት ኪሎ ሜትር ቢሆን ነው። ቢያንስ ተኩስ ይሰማል። የደረሰልን ግን የለም " ብለዋል።

ዛሬ ረፋድ ቀብር ከተፈጸመ በኋላ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ጥበቃ እንሚያደርጉላቸው ቃል መግባታቸውን የተናገሩ የሟች ቤተሰብ፤ " እንቆጣጠራለን፤ ሕዝቡ ከእኛ ጋር ይሁን " ማለታቸውን ተናግረዋል።

ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የቢቢሲ አማርኛው ክፍል ነው።

@tikvahethiopia