TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
59.4K photos
1.51K videos
215 files
4.12K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
" ከ10 ሄክታር በላይ የፓርኩ ክፍል በቃጠሎ ወድሟል " - የማዜ ብሔራዊ ፓርክ

ከትናትና በስቲያ ማምሻውን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ቁጫ ወረዳ የማዜ ብሔራዊ ፓርክ አከባቢ የተነሳዉ እሳት ሌሊቱን ሙሉ ሳይጠፋ ማደሩንና በፓርኩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የማዜ ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ጬማ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

በአከባቢው ከፓርኩ አቅራቢያ ከሚገኝ ሞርካ ቀበሌ አንድ አርሶ አደር የማሳ ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅት እያካሄደ ከነበረዉ ቃጠሎ የወጣ እሳት ምሽት 12 ሰዓት አከባቢ በፓርኩ ዙሪያ የሚገኝን 5 ሄክታር ቦታ ካወደመ በኋላ ከሌሊቱ 8 ሰዓት ገደማ የፓርኩን ክፍል ማዉደም መጀመሩን የገለፁት አቶ መስፍን ከወቅቱ ነፋሻማነትና የሰዓቱ ምቹ አለመሆን የእሳት ማጥፋትን ስራ ፈትኖት እንደነበር አስታዉቀዋል።

የእሳት ማጥፋት ስራዉ ከዛሬ ማለዳ ከ12 ሰዓት ጀምሮ በተደራጀ መልኩ በአከባቢው ነዋሪዎች፣ በፀጥታ መዋቅርና በእሳት አደጋ ብርጌድ ርብርብ ሲደረግበት ቆይቶ ከፓርኩ ዉጪ 5 ሄክታር ከፓርኩ ክፍል ደግም 10 ሄክታር በላይ ካወደመ በኋላ ረፋዱ አራት አከባቢ በቁጥጥር ስር መዋሉን አቶ መስፍን አስታዉቀዋል።

አቶ መስፍን አክለዉም እስካሁን በተደረገዉ ማጣራት ከፓርኩ ስነ ምህደር ዉድመት ባሻገር በአራዊቱ ላይ ጉዳት አለመድረሱን ገልፀዋል።

በእሳት ማጥፋቱ ስራ ከተሳተፉት የአከባቢዉ ነዋሪዎች ፣የፀጥታ መዋቅር አባላትና በሃይለማርያምና ሮማን ፋዉንዴሽን የተቋቋመው የእሳት አደጋ ብርጌድ በተጨማሪ ከወላይታ ወደ ሳዉላ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የግልና ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ሕዝቡን በማጓጓዝ ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ምስጋና አቅርበዋል።

የማዜ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ እና ጎፋ ዞኖች መካከል ቁጫ ወረዳ አከባቢ የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ 460 ፣ከሐዋሳ 235 እንዲሁም ከጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ 196 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል።

የፓርኩ አጠቃላይ ስፋት 220 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆንበሀገራችን በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘዉ የስዋይኔ ቆርኬ ጨምሮ አንበሳ፣አቦሸማኔ፣የቆላና ትልልቆቹ አጋዘኖች፣አምባራይሌና ከርከሮን ጨምሮ 39 የተለያዩ አጥቢ እንስሳቶች፣196 የአዕዋፋት ዝርያዎች እና ከ80 በላይ የእፅዋት አይነቶ እንደሚገኙበት ከማዜ ብሔራዊ ፓርክ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
በትራፊክ አደጋ የ6 ወጣቶች ሕይወት አለፈ።

በሲዳማ ክልል ደቡባዊ ሲዳማ ዞን አለታ ወንዶ ወረዳ " ሽቆ " ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ቡና ጭኖ ከሳይት ሲወጣ የነበረ የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 18766 ኦሮ የሆነ የጭነት መኪና ተገልብጦ የ6 ወጣቶች ሕይወት አለፈ።

ሁለት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱም ታእላውቋል።

የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ደህንነት ቁጥጥር ዳይሬክቶረት ዳይሬክተር ዋና ኢንስፔክተር ዳንኤል ሽንኩራ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፥ በመኪናዉ ላይ ሹፌርና ረዳቱን ጨምሮ አስር ሰዎች ነበሩ።

ስምንቱ ገዳ ተብሎ በሚጠራዉ ቦታ የቡና ሳይት የሚሰሩ ታዳጊ ወጣቶች እንደነበሩና በአደጋው ወቅት መኪናዉ ሲገለበጥ ቡናዉ በላያቸዉ ላይ በመጫኑ 6ቱ ወዲያዉኑ ሲሞቱ ሁለቱ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዉ የመጀመሪያ ሕክምና በአለታ ወንዶ ሆስፒታል ከተደረገላቸው በኋላ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ሀዋሳ መላካቸውን ዋና ኢንስፔክተር ዳንኤል አስታዉቀዋል።

ዋና ኢንስፐክተሩ ሹፌሩና ረዳቱ በአሁኑ ሰዓት በአለታ ወንዶ ወረዳ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆናቸዉን አረጋግጠዋል።

በክልሉ በቡና ምርት ወቅት የሚኖሩ እንቅስቃሴዎች ለትራፊክ አደጋዎች የመጋለጥ ዕድልን ከፍ እንደሚያደርጉ በትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ዙሪያ በሁሉም መዋቅሮች ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም በቸልተኝነትና ከልክ ባለፈ በራስ መተማመን በገጠሪቱ አከባቢዎች አደጋዎች እንደሚከሰቱ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
" ከአደጋው በህይወት የተረፈ የለም " - የሶባ ቦሩ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሶባ ቦሩ ወረዳ በወርቅ ቁፋሮ ስራ ላይ የነበሩ 8 ሰዎች ላይ አፈር ተደርምሶባቸዉ የሁሉም ሕይወት ማለፉን የወረዳዉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አሸናፊ ድንቆ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

አደጋው በትላንትናው ዕለት ከቀኑ 9 ሰዓት አከባቢ ' ቃንጣቻ ' ተብሎ በሚጠራዉ ቀበሌ በባህላዊ መንገድ የወርቅ ማዕድን በማዉጣት ስራ ላይ በነበሩ 8 ሰዎች ላይ መድረሱን ኃላፊዉ ገልጸዋል።

በአከባቢዉ የሚስተዋለዉ ባህላዊ የወርቅ አወጣጥ ስርዓትና በቸልተኝነት የሚደረጉ ሽሚያዎች ለናዳዉ ምክንያት ሊሆን ይችላል ያሉት ኃላፊዉ ሟቾቹ ሁሉም ወንዶች መሆናቸው አስታዉቀዋል።

የአስከሬን ፍለጋዉ ሂደት ፈታኝ እንደነበር ገልጸው አደጋዉ ከደረሰበት ሰዓት አንስቶ እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ድረስ በሰዉ ሃይልና በማሽን በመታገዝ የፍለጋ ስራዉ መከናወኑንና በዛሬው ዕለት የሁሉም የቀብር ሥነ ስርዓት መፈፀሙን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

አቶ አሸናፊ የጉጂ ዞን ሰባ ቦሮ ወረዳ በወርቅ ፣ ታንታሌም ፣ አምርላንድን በመሳሰሉ የማዕድን ሃብቶች የበለፀገ አካባቢ መሆኑንና ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ በርካታ ሰዎች በማዕድን ማዉጣት ስራ ላይ ተሰማርተው እንደሚሰሩ ገልፀዉ ከዚህ ቀደም አከባቢዉ ላይ መሰል አደጋዎች ተከስተዉ እንደማያውቁም ተናግረዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
" ለቅሬታችን ተገቢዉን ምላሽ ባለማግኘታችን ለርዕሰ መስተዳድሩ አቅርበናል " - የአረካ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ መምህራን

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን አረካ ከተማ በሚገኘዉ የአረካ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የሚሰሩ አሰልጣኝ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች አዲሱ የደሞዝ ማሻሻያ ክፍያ " አልተከፈለንም " ሲሉ ቅሬታቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አድርሰዋል።

በቁጥር ከአንድ መቶ በላይ የሆኑ የኮሌጁ አሰልጣኝ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በአድራሻ የፃፉትንና የተፈራረሙበትን የቅሬታ ደብዳቤ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስገብተዋል።

ሰራተኞቹ በሰጡት ቃልም " መንግስት ለኑሮ ዉድነት ማካካሻ በማለት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጥቅምት 1/2017ዓ/ም ጀምሮ ክፍያ የፈፀመ ቢሆንም እስካሁን የማሻሻያዉ ልዩነት አልተከገለንም " ሲሉ ገልፀዋል።

" ስራ ሳናቆም ተደጋጋሚ ቅሬታ ስናቀርብ ቆይተናል " የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ " ከዚህ ቀደም ከ2015 ዓ/ም ጀምሮ አብዘኞቻችን የተሰጠንን የደረጃ ዕድገት ክፊያ ተግባራዊ አልተደረገም በዚያ ላይ ይህ ሲጨመርበት ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እየዳረገን ነዉ " ብለዋል።

ኮሌጁ ስለ ጉዳዩ ምን ይላል ?

የአረካ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዲን አቶ ጻድቁ ሳሙኤል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል ፤ የደሞዝ ማሻሻያው አለመከፈሉ ትክክል መሆኑን አረጋግጠዋል።

" የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ በክልሉ ያሉ የሁሉም ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎችን መረጃ በአጭር ጊዜ ዉስጥ በመሰብሰብና በማደረጃት ክፍያዉን እንደሚፈፅም ምላሽ ስለሰጠ እየተጠባበቅን እንገኛለን " ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የደቡብ ኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮን ምላሽም ጠይቋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቢዮት ደምሴ በቢሯቸዉና በክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሃብት ልማት ቢሮ እጅ ያለዉ የሰራተኞች ቁጥር መረጃ ከ5 መቶ በላይ ሰዉ የቁጥር ልዩነት በማሳየቱ የማጣራቱ ስራ እስኪጠናቀቅ ክፍያው አለመፈፀሙን ተናግረዋል።

" አሁን ላይ ሁሉም ኮሌጆች መረጃዎችን አጠናቀዉ ወደ ፐብሊክ ሰርቪስ የመላኩ ስራ ስለተጠናቀቀ በአጭር ቀናት ዉስጥ ችግሩ ይፈታል " ሲቡ ያላቸዉን ሙሉ እምነት ገልፀዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክንክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ስር 35 ኮሌጆች መኖራቸዉን ከነዚህም ዉስጥ በወላይታ ዞን አረካ ከተማ በሚገኘዉ አረካ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ከ150 በላይ አሰልጣኝ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ስለመኖራቸዉ ከኮሌጁ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
ልታስመርቀዉ ከቤተሰቦቿ ተደብቃ የመጣች እጮኛዉን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የገደለዉ ግለሰብ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ጉርባ በሚባል ቀበሌ የገዛ እጮኛዉን ጭካኔ በተሞላበት መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት አንገቷን በመቁረጥ ሕይወቷ እንዲያልፍ ያደረገዉ ወጣት በፅኑ እስራት መቀጣቱን የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ም/ኢንስፔክተር ጋፋሮ ቶማስ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመዉ ነሐሴ 16/2016 ዓ/ም በአርባምንጭ ከተማ ጉርባ ቀበሌ ነው።

ተከሳሽ ዮናስ ጫፊቄ የተባለው ግለሰብ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ 1ኛ  ዓመት ተማሪ የሆነችዉን ሟች ሊዲያ ዮሐንስ እሱን ለማስመረቅ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ በመጣችበት ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት አሰቃቂ ድርጊቱን መፈፀሙን የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል።

ወጣቷ " እጮኛዬ ይመረቅልኛል " በሚል ደስታ ከቤተሰቦቿ ተደብቃ ተከሳሽ ተከራይቶ ወደ ሚማርበት  ቤት መጥታ በዋዜማዉ ለምረቃዉ የሚሆኑ የዲኮር፣ የዳቦና ለስላሳ መጠጦችና በቡና ዝግጅት ቤቱን አሰማምራ በምሽቱም ግቢ ዉስጥ ያሉ ተከራዮችን ጠርተዉ ከሸኙ በኋላ ሟች ሀገር ሰላም ብላ በተኛችበት ከሌሊቱ 7 ሰዓት ገደማ እራሷን መከላከል በማትችልበት ሁኔታ በቢላዋ አንገቷን አርዶ መግደሉን የምርመራ መዝገቡን ዋቢ አድርገው ፖሊስ አዛዡ ገልፀዋል።

ፖሊስ አዛዡ አክለው እንደገለጹት ፥ በወቅቱ በተደረገዉ ማጣራትም ሆነ በክስ መዝገቡ ላይ እንደሰፈረዉ ወንጀለኛው " ወደ ዩኒቨርሲቲ በሄድሽበት ሌላ የወንድ ጓደኛ ይዘሻል " በሚል ነው በር ዘግቶ አሰቃቂ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው።

ፖሊስ በዚህ ዘግናኝ ወንጀል ዙሪያ ተገቢዉን ማጣራትና ምርመራ አድርጎ ለዐቃቤ ሕግ ማቅረቡን አስታውቀዋል።

ዐቃቤ ሕግም ክስ በመመስረት ለፍርድ ቤቱ ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሙን የሰዉ፣ የሰነድና የህክምና ማስረጃዎችን በማቅረብ አስረድቷል።

በቀረቡ ማስረጃዎች እና ምስክሮች ግራ ቀኙን ሲያጣራ የቆየዉ የጋሞ ዞን ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት በቀን 29/5/2017 ዓም በዋለዉ ችሎት ተከሳሽ ዮናስ ጨፊቄ በተከሰሰበት በአሰቃቂ ሁኔታ ነብስ የማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን በማረጋገጥ በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑንም ኢንስፔክተር ጋፋሮ ቶማስ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
🔊 #የሠራተኞችድምጽ

" ቋሚ ሠራተኞች ሆነን ሳለ በደሞዝ ማሻሻያው አልተካተትንም " - የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ መንግስት ሠራተኞች

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙን ተከትሎ የሚከሰቱ የኑሮ ዉድነትና ተያያዥ ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ የመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ ማሻሻያ ተደርጎ ከጥቅምት ወር 2017 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

በሲዳማ ክልል፤ ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን፤ ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ የመንግስት ሠራተኞች ግን " ከ2012 ዓ/ም ጀምሮ በቋሚነት ተቀጥረን እየሰራን ያለን ቢሆንም በአዲሱ የመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ አልተካተትንም " ሲሉ ቅሬታቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስገብተዋል።

ቅሬታቸዉን ካደረሱን መካከል ፦
- በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን፣
- ማዘጋጃ ቤቶች፣
- በትምህርት ዘርፍ ፣
- በሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም በሕብረት ስራ ጽ/ቤቶች የሚሰሩ ሠራተኞች ናቸው።

" በወቅቱ በአግባቡ ማስታወቂያ ወጥቶ ተመዝግበንና ተወዳድረን ማለፋችን ተረጋግጦ የቋሚነት ደብዳቤ ተሰጥቶን ላለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ደሞዝ ሲከፈለን በቆየንባቸው መደቦች ላይ እየሰራን ባለንበት በአዲሱ የደሞዝ ማሻሻያ አለመካተታችን ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ዳርጎናል " ብለዋል።

" ለወረዳዉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሃብት ልማት ጽ/ቤት እና ለክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ቅሬታችንን በአካልና በፅሁፍ ብናቀርብም ተገቢዉ ምላሽ አልተሰጠንም ጉዳዩን ለኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ተቋም ለማቅረብ መረጃ እያደራጀን ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

ቃላቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡት ፤ የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰዉ ሃብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሃይሉ አቢኖ ፥ " በወረዳዉ በ2012 ዓ/ም የነበረው አግባብነት በሌለው ቅጥር በአንድ መደብ ሶስትና አራት ሰዎችን በተደራራቢነት የመቅጠር ሁኔታዎች አሁን ለተፈጠረው ችግር ዋነኛ ምክንያት ሆኗል " ሲሉ ገልጸዋል።

ከዞኑና የክልሉ ፐብልክ ሰርቪስ ጋር በመናበብ መፍትሔ እያፈላለጉ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በወቅቱ ይህን ተግባር የፈፀሙ አመራሮች እና የሰዉ ሃብት ልማት ኃላፊዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የሚናገሩት ኃላፊዉ በወረዳዉ በዚህ መልክ ተጠቀጥረዉ በአዲሱ የደመወዝ ማሻሻያ ያልካተቱና በቀጣይ መፍትሔ የሚፈለግላቸዉ 470 በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ዉስጥ የተለዩ ሰራተኞች ስለመኖራቸዉ አክለዋል።

የሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ፐብልክ ሰርቪስና የሰዉ ሃይል ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ በዛብህ ባርሶ በበኩላቸው በ2011 እና 2012 በአከባቢው ሕገወጥ ቅጥሮች መፈፀማቸውን ገልጸዋል።

በወረዳዉ አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ በአዲሱ ደሞዝ ያልተካተቱንና በወረዳው ቅጥር ያልተፈፀመባቸዉ ክፍት መደቦችን የመለየት ስራ መከናወኑን አንስተዉ በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ብቻ 407 ክፍት መደቦች መኖራቸዉን ለማወቅ መቻሉን ገልፀዋል።

የክልሉ የበላይ አመራሮች በሚያስቀምጡት አቅጣጫ መሰረት እነዚህን ሠራተኞች በነዚህ ክፍት መደቦች የመደልደልና ሌሎችም ሕጋዊ አመራጮች በመፈለግ በአጭር ጊዜ ዉስጥ እልባት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጉዳዩን እስከመጨረሻ ተከታትሎ መረጃውን ይልካል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
" በአደጋው ሁለት ሰዎች ወዲያዉኑ ሲሞቱ ስራ ላይ የነበረ አንድ ተረኛ የፖሊስ አባልን ጨምሮ በሶሰት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል" - የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ

ትላንት ምሽት 4 ሰዓት ገደማ መነሻዉን ሻሸመኔ ያደረገ ኮድ (3)  - B311533 AA የሆነ አይሱዙ የጭነት መኪና ሶዶ ከተማ ሲደርስ ባደረሰዉ የትራፊክ አደጋ  በሰዉ ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ም/ኮማንደር ሀብታሙ አሰፋ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

እንደ ፖሊስ አዛዡ ገለፃ ከኦሮሚያ ክልል አርሲ አከባቢ የግብርና ምርት / ሙሉ ቲማቲም / ጭኖ የነበረዉ ተሽከርካሪ ሶዶ ከተማ ' ሲዳር ቄራ ' በሚባለዉ አከባቢ በከተማዉ በሞተር ሳይክል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት ሰዎችን ገጭቶ ወዲያዉ ሕይወታቸዉ አልፏል።

በተመሳሳይ መልኩ የምሽት ተረኛ የነበረ አንድ የፖሊስ መርማሪም ጥሪ ተደርጎለት በሞተር ሳይክል ጥሪ ወደተደረገለት ስፍራ ሲንቀሳቀስ ይሄዉ ተሽከርካሪ ገጭቶት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የፖሊስ አዛዡ ገልጸዋል።

አደጋ አድራሹ ተሽከሪካሪ አራት የመብራት ፖሎችን ከገጨ በኋላ ዲች ዉስጥ ገብቶ የቆመ ሲሆን በአሽከርካሪዉና ረዳቱ ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰበት የፖሊስ መርማሪ በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገለት ሲሆን ቀላል ጉዳት የደረሰባቸዉ ሹፌሩና ረዳቱም በኦቶና አጠቃላይ ሆስፒታል በሕክምና ላይ መሆናቸዉን የከተማው ፖሊስ አዛዥ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

አጠቃላይ በአደጋዉ 2 የሞት፣ 1 ከባድና 2 ቀላል የአካል ጉዳት እንዲሁም 7 የንብረት ጉዳት መድረሱን አሳውቀዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
በመኖሪያ ቤት ዉስጥ በተነሳ የእሳት አደጋ የ3 ታዳጊ ልጆች ሕይወት አለፈ።

በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፤ ምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ፤ በንሳ ወረዳ ' ሞኮንሳ ' ተብሎ በሚጠራዉ ቀበሌ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ዉስጥ የተነሳ እሳት የ3 ታዳጊ ሕፃናትን ሕይወት ቀጥፏል።

ትላንት ሐሙስ ቀትር 8 ሰዓት አከባቢ እንደተነሳ በተነገረዉ በዚህ የእሳት አደጋ በቤቱ ዉስጥ ይጫወቱ የነበሩ 3 ሕፃናትና 3 የቤት እንስሳት መሞታቸዉን የወረዳዉ አስተዳዳሪ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል።

የእሳቱን ትክክለኛ መንስኤ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአካባቢውን ፖሊስ አነጋግረን ተጨማሪ መረጃ የምናደርስ ይሆናል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Update

የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፈሰር ፀጋዬ ቱኬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከቀረበባቸው ሁለት ክሶች በነፃ ተሰናበቱ።

የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፈሰር ፀጋዬ ቱኬ የሕግ ጠበቃቸው አቶ ገብረመድህን ተክሌ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደገለፁት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሀዋሳ ማዕከል ከቀረበባቸው ከባድ የሙስና ወንጀል እና በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም በሚል የቀረበባቸዉን ሁለት ክሶች ላለፉት አንድ ዓመት ሲከታተሉ ቆይዋል።

በዛሬዉ ዕለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐዋሳና አከባቢዋ ማዕከል በነፃ መሰናበታቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል።

ከቀድሞ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፈሰር ፀጋዬ ቱኬ በተጨማሪ ተመሳሳይ ክስ ተመሰርቶባቸዉ የነበሩት የቀድሞ የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበራ አሬራም በነፃ መሰናበታቸውን ጠበቃ ገብረመድህን ተክሌ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስታውቀዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
" ምርጫ ማሸነፌ እንደወንጀል ታይቶ 1 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ያለአግባብ ታስሪያሁ " - አቶ አማንያስ ጉሹና

ከሰሞኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤዉን አካሂዶ ነበር።

በዚህም ጉባኤ ላይ የኢዜማው ተመራጭ ጉባኤ እንዳይሳተፉ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ የዘይሴ ብሔረሰብ ተመራጭ የሆኑት አቶ አማንያስ ጉሹና " ያለአግባብ 4 ወራት ከታሰርኩ በኋላ ያለመከሰስ መብቴ ተነስቶ ለተጨማሪ 7 ወራት በእስር ላይ እንዲቆይና በምክር ቤት ጉባኤ እንዳልሳተፍና ከመንግስት ስራም እንዲሰናበት ተደርጌያለሁ " ሲሉ ቅሬታቸዉን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

አቶ አማንያስ ፤ " ብሔረሰቡ ያለዉን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የመዋቅር ጥያቄ በተለያዩ ጊዜያት ሲጠይቅ የቆዬ ቢሆንም ተገቢዉን ምላሽ ባለማግኘቱ በ6ኛ ሀገራዊ ምርጫ የኢዜማ ፓርቲን በመምረጡ ከምርጫዉ ማግስት ጀምሮ በፓርቲው በአባላትና አመራሮች ላይ የእስርና የማሳደድ ተግባር በይፋ ማካሄድ ተጀምሯል " ብለዋል።

" በአሁኑ ሰዓት ከ2 መቶ በላይ የፓርቲዉ አባላትና አመራሮች በጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት እየተመላለስን ነዉ " ሲሉ አስረድተዋል።

" ተወዳድረን ምርጫ ማሸነፋችን ሃጥያት ባልሆነበት በገዢዉ ፓርቲ አመራሮች በግልም ሆነ በብሔረሰቡ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እየደረሰብን ነዉ " የሚሉት አቶ አማንያስ " ለአብነትም የደቡብ ክልል ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደዉ 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ የዜይሴ ብሔረሰብ ያለተወከለበት እና ከሌሎች ብሔሮች ጋር በክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሌሎች ተሳታፊዎች ጋር ያልተሳተፈበት ጉባኤ ነዉ " ሲሉ ወቅሰዋል።

" በዚሁ የፖለቲካ ተፅእኖ ምክንያት ሀገሬን ለ17 ዓመታት ካገለገልኩበት የመምህርነት ሙያ እንድሰናበት ተደርጌያለሁ " ያሉት አቶ አማንያስ " ወደ ስራ ገበታዬ እንዲመልሱኝ ደጋግሜ ብጠይቅም 'ያለመከስ መብትህ ሳይነሳ መመለስ አትችልም' የሚል ምላሽ ከትምህርት አስተዳደር መዋቅሮች ተሰጥቶኛል " ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የኢዜማ ፓርቲ የሕግና አባላት ጉዳይ ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስዩም መንገሻን በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገራቸዉ ሲሆን " በዘይሴ ብሔረሰብ የሕዝብ ተመራጭ አቶ አማኒያስ ጉሹና ላይ የተፈፀመዉ ጉዳይ ኢ-ሕገመንግስታዊ ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

በወቅቱ ያለመከሰስ መብታቸዉ ሳይነሳ ታስረዉ መቆየታቸዉንና በአካባቢዉ ያለዉን የሰብአዊ መብት ረገጣና የፖለቲካ ተፅእኖ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በፅሑፍ ማሳወቃቸዉንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደአከባቢዉ ማቅናቱንና የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ አንስተዋል።

" ከስራ የተሰናበቱበትና ወደ ስራ እንዳይመለሱ የሚደረግበት አግባብ ከፍተኛ የፖለቲካ ተፅእኖ ያለበት ነዉ " ያሉት አቶ ስዩም ፤ የኢዜማ ፓርቲ በአከባቢው ያለዉን የፖለቲካ ጫናና ተያያዥ ጉዳዮችን ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በጽሑፍ አቅርቦ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ግብረሃይል ተዋቅሮ ቦታዉ ድረስ በመሄድ በሰጠዉ አቅጣጫ መሠረት አቶ አማንያስ በዋስ እንዲፈቱ መደረጉን ተናግረዋል።

አቶ አማንያስ " ወደ ስራ ገበታዬ እንዲመልሱኝ በተደጋጋሚ ብጠይቅም የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤትና የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ' ያለመከሰስ መብትህ እስካልተነሳ ድረስ መመለስ አንችልም ' ተብያለሁ " በሚል ላነሱት ቅሬታ ከከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ጽ/ቤትና ከጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
" በአስር ቀናት ዉስጥ የ19 ሰዎች ሕይወት አልፏል " - የኑዌር ዞን ጤና መምሪያ

በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን አኮቦ ወረዳ ከቀናት በፊት እንደተከሰተ በተነገረዉ የኮሌራ በሽታ በጥቂት ቀናት ብቻ 19 ሰዎች ሲሞቱ ከ280 በላይ ሰዎች ላይ በበሽታዉ መያዛቸውን የኑዌር ዞን ጤና መምሪያ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስታዉቋል።

ከደቡብ ሱዳን እንደገባ በተገመተዉ ይህ የኮሌራ በሽታ የካቲት 3/2017 ዓ/ም በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን ስር ከሚገኙ አምስት ወረዳዎች አንዱ በሆነዉ አኮቦ ወረዳ መከሰቱን የሚናገሩት የኑዌር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋትቤል ጌርማል በሽታዉ ቀስ በቀስም በቀሪዎቹ አራት የዞኑ ወረዳዎች በላሬ፣ በመኮይ፣ በዋንቱዋ፣ በጂካዎ ወረዳዎች መከሰቱን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል።

በሽታዉ አስቀድሞ የተገኘበት የአኮቦ ወረዳ የሀገራችን ጠረፋና ቦታና በየብስ (በመሬት ላይ) ትራንስፖርት የማይገገባበትና የስልክ አገልግሎት የለሌበት አከባቢ በመሆኑ መረጃ ለመሰብሰብም ሆነ አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማድረስ አዳጋች ማድረጉን ጠቁመዉ ከላይ በተጠቀሰዉ በበሽታዉ የተያዙ ሰዎች ቁጥር የአኮቦ ወረዳ መረጃ አለመካተቱን ገልፀዋል።

የጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቤል አስፋዉ በበኩላቸዉ በአሁኑ ወቅት በሽታዉ ከአምስቱ የኑዌር ዞን ወረዳዎች በተጨማሪ በጋምቤላ ከተማና የጋምቤላ ዙሪያ ወረዳ እንዲሁም በክልሉ ባሉ ሶስት የስደተኞች ካምፖች በበሽታዉ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸዉን ተናግረዉ በአሁኑ ወቅት የበሽታዉን ስርጭት መግታት ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን ገልፀዋል።

አሁን ላይ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚደረገዉን ርብርብ የባለሙያዎች ቁጥር ማነስና የአካባቢዎቹ መልካምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪ መሆን በተለይም በሽታዉ አስቀድሞ ወደተከሰተበት የአኮቦ ወረዳ ለመሄድ ብቸኛዉ አማራጭ የጀልባ ላይ ጉዞ በመሆኑና በአከባቢዉ የስልክ ኔትወርክ ባለመኖሩ በደቡብ ሱዳን ኔትወርክ መረጃ መለዋወጥ ስራዉ አዳጋች አድርጎታል ብለዋል።

ዶ/ር አቤል አክለዉም የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የበሽታዉን ስርጭት ለመግታት እንዲያግዝ 1.6 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው መድኃኒቶችና ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉንና የፌዴራልና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸዉን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
" በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር ቱርካናና ዳሰነች አከባቢ በተከሰተዉ ግጭት እስካሁን 5 ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል " - የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር

⚫️ " በአከባቢዉ ዛሬ ከማለዳዉ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 9 ሰዓት ከፍተኛ ተኩስ ነበር ! "


በጎረቤት ሀገር ኬንያ ቱርካና እና ኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች አከባቢ በአሳ ማጥመጃ ጀልባና መረብ ስርቆቶች እንደተነሳ በተገለጸ የአርብቶ አደሮች ግጭት ባለፉት ሶስት ቀናት 5 ኢትዮጵያዊያን መገደላቸውን የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስታውቋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ 28 ቀበሌዎች ከጎረቤት ሀገር ኬንያ ጋር ድንበር የሚጋሩ ሲሆን በአከባቢዉ በሁለቱ ሀገራት አዋሳኝ ላይ ከሚገኘው የቱርካና ሀይቅ አሳ በማስገር ስራ የአከባቢው አርብቶ አደሮች በጋራ ሲጠቀሙ የቆዩ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኦሞ ወንዝ መሙላቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ በኩል የአሳ ምርት መበራከቱንና የኬንያ አርብቶ አደሮች ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀዉ የመግባትና የአሳ ማስገሪያ መረብና ጀልባዎች (ዛተራ) የመስረቅ አዝማሚያዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የዳሰነች ወረዳ አስተዳዳር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስረድቷል።

ይህን ተከትሎም ባሳለፍነዉ ሳምንት በኬንያ ቱርካና ግዛት የአከባቢው አስተዳዳሪዎች ጋር በመነጋገር መግባባት ላይ በመድረስና ከሁለቱም አከባቢ አርብቶ አደሮች ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ተይዞ በነበረበት የኬንያ አርብቶ አደሮች ከትላንት በስቲያ ሁለት ኢትዮጵያዊያንን በትላንትናው ዕለት ደግሞ ሶስት የአንድ ቤተሰብ አባላትን መግደላቸዉን ተከትሎ የዳሰነች አርብቶ አደሮች አስከሬን ለመዉሰድና ለአፀፋ ተኩስ ከፍተዉ እንደነበር የወረዳዉ መንግስት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስታውቋል።

በዛሬዉ ዕለት በተለያዩ ተሽከርካሪዎች ታግዘዉ ከኬንያ በኩል በርከት ያሉ የታጠቁ ሃይሎች ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ እስከ ቀትር 9 ሰዓት ድረስ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብተዉ ሲታኮሱ መዋላቸዉን የገለፀው የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር የኬንያ ፓርላማ አባላት ወደ አከባቢው በመምጣት ተኩሱን ማስቆማቸዉንና ዜጎቻቸዉን ከኢትዮጵያ መሬት ማስወጣታቸውንና ከዳሰነች ወረዳና የዞን ፀጥታ መዋቅር ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ግጭቱ የተከሰተበት ቦታ ከደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ዋና ከተማ ኦሞ ራቴ 30 ኪሎሜትር ርቀት አከባቢ ሲሆን በተለይም በኬንያ ቱርካና ' ኮኮሮ '/ተብሎ በሚጠራዉ አከባቢና በኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ አሪኮ አከባቢ መሆኑም ተገልጿል።

የኬንያ አንዳንድ ሚዲያዎች ከ20 በላይ የሀገሪቱ አሳ አስጋሪዎች " በቱርካና ሀይቅ ላይ ከኢትዮጵያ በኩል ሜሪሌ አከባቢ በገቡ ታጣቂዎች ተገድለዋል " የሚል ዘገባ እየሰሩ ናቸው።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
" በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶአደሮች ተፈናቅለዋል " - የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር 🚨" አሁንም ከኬንያ ቱርካና ግዛት በኩል ዛቻዎች ስላሉ ስጋት ዉስጥ ነን ጥበቃና ከለላ ይደረግልን " - አርብቶአደሮች በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር ደቡብ ኦሞ ዳሰነች ወረዳና በኬንያ ቱርካና ግዛት አዋሳኝ አከባቢ ባለፉት ሁለት ቀናት በአሳ ማስገሪያ መረብና ጀልባ ስርቆቶች እንደተቀሰቀሰ በተነገረዉ ግጭት የበርካቶች…
" ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነዉ ፤ የአስክሬን ፍለጋዉም ተጠናክሮ ቀጥሏል " - የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ እና በሰሜን ኬንያ ቱርካና የድንበር አከባቢ ተከስቶ በነበረዉ ግጭት ምክንያት ስየስ ከተባለ የዳሰነች መንደር ተፈናቅለዉ የነበሩ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶአደሮች ወደ ቀያቸዉ መመለስ መጀመራቸዉን የዳሰነች ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሀቴ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

በቀጠናዉ በአሳ ማስገሪያ መረብና ጀልባ ስርቆቶች መነሻ እንደተቀሰቀሰ በተገለፀዉ ግጭት ከሁለቱም ሀገሮች ከ30 በላይ አርብቶአደሮች ሕይወት መጥፋቱን መዘገባችን አይዘነጋም።

ግጭቱን ተከትሎም ኬንያን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናት የቱርካና ሀይቅ ሰሜናዊ ጠረፍ ላለፉት አምስት ቀናት ከእንቅስቃሴ ዉጪ ሲሆን ከዳሰነች ወረዳ ስየስ መንደር በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች በአቅራቢያቸዉ ወደሚትገኘዉ ሌላ መንደር ተፈናቅለዉ ነበር።

በትናትዉ ዕለት የዳሰነችና የቱርካና አከባቢ አስተዳደሮች ባሉበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የተመራ ልዑክ ከኢትዮጵያ በኩል በኬንያ የቱርካና ካውንቲ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርና የአከባበው የፓርላማ ተወካይ የተመራ ልዑክ በሁለቱ ሀገራት የድንበር አከባቢ ተፈጠሮ የነበረዉን ግጭት በፍጥነት ለመፍታትና አከባቢውን ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ መነጋገራቸዉን ተከትሎ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸዉ የመመለስ እየተሰራ እንደሆነ አቶ ታደለ ሀቶ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በሀይቅ ዉስጥ የጠፉ አስከሬኖች የማፈላለጉ ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ያነሱት አቶ ታደለ በሁለቱም ወገን የተወሰዱ ንብረቶችን የማስመለስና በአከባቢዉ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ተጠናክረዉ በሚቀጥሉበት ዙሪያ ዉይይት ማድረጋቸዉን አስታዉቀዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyHW

@tikvahethiopia