TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.6K photos
1.49K videos
211 files
4.05K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
" ግድያው የተፈጸመበት ወጣት ደረጀ አማረ ተስፋ ይባላል ፤ የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ቤተሰቦቹ የሄደ ነበር " - ነዋሪዎች

ቁጣን ስለቀሰቀሰው የደራው አሰቃቂ ግድያ ነዋሪዎቹ ምን አሉ ?

ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ አንድ ወጣት በታጣቂዎች ተይዞ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከታየ በኋላ በርካቶችን አስቆጥቷል።

ጉዳዩን በሚመለከት ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ቃላቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች " ግድያው የተፈጸመው በአካባቢው ላይ በሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

ድርጊቱ የተፈጸመው ከ2 ወራት በፊት እንደሆነም ገልጸዋል።

ግድያው የተፈጸመበት ወጣት ማነው ?

ዳንኤል ገመዳ የተባለው ግለሰብ ወደ ሰሜን ሸዋ ደራ አካባቢ አምርቶ የሟችን ቤተሰቦች ማነጋገሩን ገልጿል።

ግድያው የተፈጸመበት ወጣት ደረጀ አማረ ተስፋ እንደሚባል እና የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ቤተሰቦቹ የሄደ እንደነበር አስረድቷል።

በአሰቃቂው ቪዲዮ ላይ ከሚታየው የ10ኛ ክፍል ተማሪ በተጨማሪ ጓደኛው ከማል ሁሴን በአንድ ቀን መገደላቸው ተነግሯል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ በከጀማ ተራራ ሸሽተው ነበር። ደረጀ እና ሌሎች ግን በቀያቸው የቆዩት በበረት ታስረው የሚገኙትን እንስሳትን ለመጠበቅ ነበር።

በአካባቢው የነበሩ ታጣቂዎች ደረጀ እና ከማል ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የደረጀ አባት የሆኑትን አቶ አማረ ተስፋ ቶላን አግኝቼ አነጋግሬያለሁ የሚለው ዳንኤል፣ " ያን ቀን አሳድደው እግሩን ተኩሰው መትተው ከያዙት በኋላ ሳርኩላ ወደ ሚባል ቦታ ወሰዱት። እዚያ ቦታ ነው የፋኖ ታጣቂዎች በብዛት የሚንቀሳቀሱት " ይላል።

ደረጀ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሎ አስከሬኑ ለአውሬ የተጣለው እዚያ ቦታ መሆኑን የተናገሩት አባትየው፣ የልጃቸውን መገደል ቢሰሙም አስከሬኑን አግኝተው መቅበር አለመቻላቸውን ጨምሮ ገልጿል።

የደረጀ እናት እና አባት በልጃቸው ሞት ምክንያት አእምሮ ጤናቸው መቃወሱ ተገልጿል።

" የደረጀ እናት አእምሮአቸው ተጎድቷል እና አትናገርም። ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም። ለማንም አይመልሱም። " ነው የተባለው።

ደረጀ ለቤተሰቡ ታናሽ ልጅ ሲሆን ወንድሞቹ እና እህቶቹ አግብተው ከቤት በመውጣታቸው እናት አባቱን ለማገዝ በቤት ያለ ብቸኛ ትንሽ ልጅ መሆኑ ተመላክቷል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ምንድነው ?

የግፍ ግድያውን የተመለከቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዛሬ ሰልፍ ወጥተው ነበር።

ምግባቸውንም ትተው በመውጣት ሀዘናቸውንና ቁጣቸውን ገልጸዋል።

ፍትህ እንዲሰፍን ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና ወንጀለኞችም የፍትህ አደባባይ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

#ኢሰመኮ : የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን እንደሰማ ገልጾ ማጣራት መጀመሩን እና የደረሰበትን ውጤት ወደፊት እንደሚያሳውቅም ገልጿል።

የደራ ህዝብ እያየው ያለው የከፋ መከራ ምን ይመስላል ?

በደራ ሰላምና ደህንነት ከጠፋ ቆይቷል።

በቀጠናው በሰላም ወጥቶ መግባት ቅንጦት ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ሰዎች በግፍ ይገደላሉ ፤ የሚጠየቅ አካል ግን የለም።

ለአብነት ከሳምንታት በፊት ገንዳ አረቦ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሀጂ አህመድ መስጅድ ኢማም ሼይኽ ሙሀመድ መኪን ታግተው ከነበሩት 12 የሚሆኑ የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ጋር በሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸው መነገሩ የቅርብ ትውስታ ነው።

ሌሎች በርካታ ግፍ እና ግድያዎች ሲፈጸሙም ቆይቷል።

በአካባቢው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (መንግሥት ሸኔ የሚላቸው) ታጣቂዎች፣ እንዲሁም የፋኖ ታጣቂዎች፣ የመንግሥት ታጣቂዎች  ይንቀሳቀሳሉ።

ህዝቡ ሰላም ከተጠማ ዓመታት አልፈዋል። ግፍ ፣ በደል ፣ ሰቆቃ መመልከት የዕለት ተዕለት ሁኔታው ሆኗል።

ዛሬ ይህ እጅግ አሰቃቂ ቪድዮ ወጥቶ በዚህ ልክ መነጋገሪያ ሆነ እንጂ በአካባቢው የሚፈጸመው ግፍ፣ የሚካሄደው ግድያ እጅግ አስከፊ ነው።

ብዙ ጊዜ ስለ አካባቢው ሁኔታ  ቢነገረም ይህ ነው የሚባል መፍትሄ አልመጣም።

ሰላም ወዳዱ ህዝብ በተለያየ አቅጣጫ በታጣቂዎች የሚያየው መከራ በቃላት የሚገለጽ አይደለም።

የአካባቢው ነዋሪዎች " መንግሥት ተቀዳሚ ስራው የሆነውን የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ስራ እየሰራ አይደለም " በሚል ብዙ ጊዜ ቅሬታቸው አቅርበዋል። አሁንም ቢሆን እያቀረቡ ነው።

#Oromia #Dera #BBC_Afaan_Oromoo

@tikvahethiopia