TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.4K photos
1.47K videos
209 files
4.03K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
" ዜጎች አሁን በየዕለቱ እያሻቀበ ባለው #የኑሮ_ውድነት ራሳቸውን ሊያኖሩ የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ካልተቻለ አገርንም አደጋ ላይ ይጥላል " - ኢሰማኮ

የሰራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የመትከል ጥያቄ እየተንከባለለ የመጣና የኢትዮጵ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) ጭምር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀረበበት በኢትዮጵያ ያሉ ሠራተኞችን ለምሬት የዳረገ ግን ምላሽ ያልተቸረው ጉዳይ መሆኑን ብዙዎች ሲያወሱ ይደመጣሉ።

ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን ያቀረቡ አንድ ሠራተኛ ፤ " በአዲስ አባባ ከ3,000 ብር በታች የቤት ኪራይ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። ለዛውም በኮምፒስታቶን የተጠጋገነ ቤት ነው። የወር ደመወዜ ደግሞ 3,000 ብር ነው። ታዲያ በዚህ ደመወዝ እንዴት መኖር ይቻላል ? " ሲሉ አማረዋል።

አክለውም ፤ " ምንም እንኳ ለኑሮ ውድነቱ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የደመወዝ ወለል አለመተከልም አንዱና ዋነኛው መንስኤ ነው። በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም መንግሥት ግን የአንድ ሰሞን አጀንዳ ከማድረግ በዘለለ መጽትሄ እየሰጠ አይደለም " የሚል ወቀሳ አቅርበዋል።

እኝህን ቅሬታ አቅራቢ ለአብነት ጠቀስን እንጂ እሮሮው በበርካቶች ዘንድ በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል። 

የቅሬታ አቅራቢዎችን እሮሮ መነሻ በማድረግ ቲክቫህ ለኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) የስራ አስፈፃሚ አባል እና የኢንድስትሪ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዲርብሳ ለገሰ ተከታዮቹን ጥያቄዎች አቅርቧል።

* የኑሮ ውድነት በየዕለቱ እየጨመረ በሚስተዋልበት ሁኔታ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጥያቄ ግን ከቀጠሮ ባለፈ ለምን መፍትሄ አይሰጠውም ?

* ጉዳዩን በተመለከተ ከዚህ በፊት ለጠ/ ሚኒስትሩ ያቀረባችሁት ጥያቄ አሁንስ ከምን ደረሰ ?

* ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጥያቄ መፍትሄ ሳይሰጠው እየተንከባለለ የመጣ ጥያቄ ነው። አሁንስ ቢሆን እየተንከባለለ እንደማይቀጥል በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል ?

* ጠቅላይ ሚኒስተሩ አቅጣጫ የሰጡበት ጉዳይስ በተግባራዊነቱ ምን ያክል እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

አቶ ዲርብሳ ለገሰ ምን ምላሽ ሰጡ ?

- ለኑሮ ውድነት የራሱ የሆነ ፋክተር ስላለው ይኸኛውም አንደኛው ነው በሚል አንስተንላቸዋል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ። በአሁኑ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ የከበደው ቢኖር ሠራተኛው ነው። 

- የዚህ ጥያቄ እየተንከባለለ መሄድ ሠራተኞችን ብቻ ሳይሆን የሚጎዳው አገርንም ይጎዳል በእኛ እምነት ለማንም አይጠቅምም።

- ዜጎች አሁን በየዕለቱ እያሻቀበ ባለው የኑሮ ውድነት ራሳቸውን ሊያኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ካልተቻለ #አገርንም_አደጋ_ላይ_ይጥላል

- ይህ ጉዳዩ ትኩረት አግኝቶ እንዲኬድበት አቅጣጫ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ በተለያዩ የሥራ መደራረብ ምክንያቶች አቅጣጫውን የተቀበሉ አካላት ባለመኖራቸው ነው እንጂ ባሉበት ቦታ ሆነው ክትትል እያደረግን እንገኛለን።

- በኢትዮጵያ ለኑሮ ውድነቱ የሠራተኛ ደመወዝ ማነስ ብቻ አይደለም። የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ግን ይህም እንደ አንድ ፋክተር ስለሚሆን ይህንንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተናል።

- በኢትዮጵያ #ሰላም_እስከሌለና #ሰላም_መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ ለኑሮ ውድነት በሌላ መንገድ ተገቢና ዘላቂ ምላሽ መስጠት ይገባል ተብሎ አይገመትም። 

- አሁን ሠራተኞች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ይደርሱባቸዋል። #መፈናቀል#መንገላታት ይደርስባቸዋል።

- መዘግየቱ ተገቢነት እንደሌለው ፣ ጉዳቱም ለሁላችን እንደሚሆን መንግሥትም ሊገምተው እንደሚገባ በየዕለቱ፣ በየጊዜው ማሳሰባቸን አይቀርም፣ ክትትል እናደርጋለን ውጤቱንም እናሳውቃችኋለን።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፤ ከሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ባገኘው መረጃ ፦

* ሚኒመም ዌጅን በተመለከተ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ።

* #ዓለም_አቀፍ_አማካሪዎችንም ጭምር በማካተት ልምዶችንና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ለማስታረቅ የሚችያስችል ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ሲጠናቀቅ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ መረጃ ይሰጣል።

ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል #ያልተተከለላቸው አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት (3) የአፍሪካ አገራት ብቻ ሲሆኑ ፣ የሠራተኞች የመነሻ የወለል ደመዎዝ ተጠንቶ የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም በ2011 ዓ.ም በወጣው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ላይ ተደንግጓል።

ኢሰማኮ ፦
° ጥናት በማጥናት ለሥራና ክህሎት ጨምሮ ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በደብዳቤ ቢያቀርብም መፍትሄ እንዳልተሰጠው፣
° በ2015 ዓ.ም የሜይዴይ በዓል ጥያቄውን ሰላማዊ መልስ እንዲሰጠው በሰላማዊ መንገድ ለማንሳት ቢሞክርም ሰልፉ እንደተከለከለ፣
° ባሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርጎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  አቅጣጫ እንዳስቀመጡ መግለጹ የሚታወስ ነው።

መረጃው በአ/አ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።

@tikvahethiopia
#መልዕክት

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፦

" . . . ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚአብሔር ከሌለ ፍትሕ ይጐድላል፣ ፍትሕ ከጐደለ ብሶት ይፈጠራል፣ ብሶት ካለ ሰላም ሊኖር አይችልም።

በሁሉም የዓለማችን ክፍል ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚብሔር እየተዘነጋ በመሄዱ ቀውሱ ተባብሶ ይታያል፤ የሰው ልጅ ኑሮ በየትም ይሁን በየት በስጋት የተሞላ ሆኖአል፤ የሚወራው ሁሉ ስለ ግጭት ስለአየር ብክለት ስለ ረኃብና እልቂት ሆኖአል።

ዓለም የጉልበተኞችና የባለ ሀብቶች ብቻ እንድትሆን የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ ከባድ የፍትሕ መዛባት አጋጥሞአታል፤ የዝቅተኛው ማኅበረ ሰብ ሰብአዊ መብት ተዘንግቶአል፤ ከዚህ አኳያ ዓለም በዚህ እስከ ቀጠለች ድረስ ሰላም የማግኘቷ ዕድል በጣም አጠራጣሪ ነው።

የክርስቶስ ልደት ያስተማረን ግን እንደዚህ አልነበረም፤ ጌታችን የተወለደው በተዋበና ምቹ በሆነ የሀብታም ቤት ሳይሆን #በከብቶች_በረት ነበረ፤ የተገለጠውም ለባለሥልጣኖች ሳይሆን ዝቅተኞች ለሚባሉ እረኞች ነበረ፤ ልዑላኑ ሰማያውያንና ትሑታኑ ምድራውያን በአንድነት አገናኝቶ ስለ #ሰላም በጋራ እንዲዘምሩ አደረገ፤ አሳዳጅ ሳይሆን ተሳዳጅ ሆኖ በግብጽ አገር በመንከራተት አደገ፤ ይህን ሁሉ ያደረገው እኛ እሱን እያየን እንደ ሰንደቅ ዓላማ እንድንከተለው ነበር።

ጌታችን ከባለሥልጣናቱና ከባለሀብቶቹ ይልቅ በድሆቹ ደረጃ የተወለደው ለድሆቹና ለዝቅተኞቹ ትኩረት እንድንሰጥ ለማስተማር ነው። የእኛ ድርጊት ግን #ግልባጩ ሆኖ እየተስተዋለ ነው፡፡

እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ክርስቲያን ነኝ ብሎ፣ በስመ እግዚአብሔር ተሰይሞ፣ መስቀልን በአንገቱ ተሸክሞ የእሱ መሰል በሆነው ወይም መስቀል በተሸከመው ወንድሙ እና እኅቱ እንዲሁም በመሰል ፍጡር ላይ ያለ ርኅራኄ ሲጨክን መታየቱ ነው፤ እንዲህ እየሆነ እንዴት ሰላም ይምጣ? እግዚአብሔርስ እንዴት በረከቱ ይሰጣል? ይህ እጅግ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን  ምእመናንና ምእመናት!

እኛ ኢትዮጵያውያን ከእንዲህ ዓይነቱ የሃይማኖትና የሞራል ዝቅጠት በአስቸኳይ መውጣት አለብን፤ ጠቡ፣ መለያየቱ፣ መጨካከኑ፣ ለኔ ለኔ መባባሉ ከረምንበት፤ ሆኖም ያመጣልን ነገር ቢኖር ሁለንተና ውድመት ብቻ ነው። ያስገኘልን ትርፍ ይህ መሆኑ እያወቅን በዚሁ ልንቀጥል አይገባም።

ሰው ችግሩን በልቡ እያወቀ በዓይኑ እያየ እንዴት ገደል ውስጥ ይገባል ? ዕርቅና ይቅርታ ማንን ጐዳ ? ሰላምና አንድነት ማንን አከሰረ ? ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በሆነውም ባልሆነውም ከመተላለቅ ለምን ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በእኩልነትና በስምምነት መኖር አቃተን ?  ሦስት ሺሕ ዘመናት አብረው የኖሩ ሕዝቦች እንዴት ችግራቸውን በጠባይና በብልሐት ማስወገድ አቃታቸው ? ይህ ከቶ ሊሆን አይገባም።

ሁላችንም ሰከን ብለን እናስብ፤ ለሁሉም የማሰቢያና የመመካከሪያ ጊዜ ፈጥረን ችግሩን በስፍሐ አእምሮ እንፍታው፤ችግርን በምክክርና በይቅርታ መፍታት አማራጭ የሌለው ጥበብ ነው። የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ልኂቃን በዚህ ተግተን ልንሰራ ይገባል፤ መንግሥትና የፓለቲካ ፓርቲዎችም ለዚህ የበኩላቸውን ድጋፍ ያድርጉ፤ በዚህም ሰላማችንን እንመልስ፡፡ "

(ሙሉ መልዕክታቸው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia
#መልዕክት

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ፦

" . . . የክርስቶስን መወለድ በአግባቡ ለማክበር ለሰው ልጆች ሕይወት፣ ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያንና ለእርሱ ቅዱስ ስፍራዎች ክብርን እንስጥ፡፡

ከራስ ወዳድነት መንፈስ እንውጣ በመላው አገራችን #ሞት_ይብቃ#ሰላም_ይስፋፋ፡፡

የተራቡ ፣ የተጠሙ ፣ የታረዙ ፣ የተበደሉ፣ የታመሙና የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን እናስታውስ፡፡

ከጎናቸው እንሁን እንርዳቸው እናጽናናቸው፡፡ ለኛ ምን ይደረግልን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ምን እናድርግ እንበል፤ መጠጊያ ለሌላቸው መሸሸጊያ እንሁንላቸው፡፡

የሚገለሉ ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው እናድርግ፡፡  ዘመዳቸው እንሁን፡፡ ምክንያቱም የልደት በዓል ክርስቶስ ዘመዳችን እንደሆነ የሚያበሥረን በዓል ነውና፡፡

በልደት ምስጢር ማንም እንግዳ ሊሆን አይገባውም፡፡

እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ ጠንካራ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ በግብጽ ባርነት ሳላችሁ በመገለል፣ በመማረር ኖራችኋል፡፡ ስለሆነም እንግዳ እንዳታማርሩ ይላል፡፡ ይህ ትልቅ የፈጣሪ ትዕዛዝ ነው፡፡ ሁላችንም ልናቀርበው የሚገባው ጥያቄ የሚከተለው ነው፡፡

‹‹እንግዳ አባርሬ ይሆን››? እንግዳን ከሚያዋርድ ሐሳብ፣ ትምህርት፣ መልዕክት ጋር ተባብሬ ይሆን? የእኔ ባሕል ሙሉ ስለሆነ ሌላውን መጫን፣ ማግለል አለብኝ ብዬ ይሆን ? ይህ ዓይነት ሐሳብ ከእግዚአብሔር ቃል እንደሚርቅ ተረድቼ ይሆን? ከእንደዚህ ዓይነት ሐሳብ ለመውጣትስ ምን ማድረግ ይገባኛል ልበል፡፡ 

ከዚህ ሐሳብና ይህ ዓይነት ሐሳብ ከሚገለጥባቸው ተግባራት ነፃ መውጣት የምንችለው ወደ ገና በዓልና ወደ ትንሣኤ ምስጢር ስንቀርብ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ሰማይና ምድር ከእኛ ጋር አብረው ለታላቁ ጌታ ታላቅ የምስጋና መዝሙር ይዘምራሉ፡፡ "

(ሙሉ መልዕክታቸው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#ኢትዮጵያ #ሰላም

#ሰላም_ከሌለ_ሁሉ_ነገር_የለም!

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፦

" ... በምድር ላይ ሰላም ካልነገሰ በቀርን መቼም ምንም ነገር ሊሆን አይችልም። ሰላም ዓለምን የሚገዛ ነው ፤ ሰላም ከሌለ ሁሉ ነገር የለም። ሰላም ካለ ሁሉ ነገር አለ።

ለሰላም የሚሆን ዋጋ በዓለም ላይ አይገኝም። ብርም ይሁን ፣ ወርቅም ይሁን አልማዝም ይሁን #አይመጥነውም። ለሰላም የሚሆን ዋጋ አይመጥነውም ይሄ ሁሉ።

ሰላሙን የምናመጣው እኛው ነን ፣ የምናባርረውም እኛው ነን።

ሰላም በምድር መንገስ አለበት። ሰላም በምድር ካለ ሁሉም ነገር አለ ፦
- ሀብት አለ
- ትምህርት አለ
- ስልጣኔ አለ
- ድሃ በጉልበቱ፣ ሃብታም በሀብቱ ፣ የተማረም በእውቀቱ ሀገርን ያቀናል እራሱም ይኖራል።

ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር እንደሌለ የታወቀ ነው።

ስለ ሰላም #መጸለይ ምንጊዜም አስፈላጊ ነው። ሰላም በሶስት ፊደል የተወሰነች ብትሆንም ዓለምን #የምትገዛ ሰላም ናት። ሰላም ዓለምን ይገዛል ምክንያቱም ሁሉም ነገር የሚስተካከለው በሰላም ስለሆነ።

ስለ ሰላም ምንጊዜም ቢሆን #ሁሉም_ኢትዮጵያዊ በያለበት ጸሎት ማድረግ አለበት፤ በጸሎት ሁሉም ነገር ይገኛልና። "

የፎቶ ባለቤት፦ ፎቶግራፈር አቤል ጋሻው + ኢጃት (አዲስ አበባ ቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል - ' የአእላፋት ዝማሬ ' - በኢትዮጵያ ጃንደረባው ትውልድ)

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
" የባሕር በር ጉዳይ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው " - ኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ምን አሉ ? " ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ከዓላማው ውጪ የሆኑ የተሳሳቱ መረጃዎች ተሰራጭተዋል። የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን…
#ኢትዮጵያ🇪🇹

" ... ለሶማሊያ በችግር ጊዜ ብዙ ድጋፍ ያላደረጉ #አንዳንድ_ተዋናዮች ራሳቸውን እንደ እውነተኛ ወዳጆቿ አድርገው ለማሳየት እየሞከሩ ነው " - አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ምን አሉ ?

- ኢትዮጵያ ለሶማሊያ #ሰላም እና #ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት በውድ ልጆቿ #ደም እና #ላብ በግልፅ አሳይታለች።

- ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድንበር ተጋርተው የሚኖሩ ጎረቤቶች ብቻ ሳይሆኑ የጋራ የሆነ ቋንቋ፣ ባህል እና ህዝብ የሚጋሩ ወንድማማች ሀገራት ናቸው።

- ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን የሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ጠንካራ ናቸው ፤ እጣ ፈንታችን የማይነጣጠል ነው።

- ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ለኢትዮጵያ የንግድ ግንኙነት የሚሆን የባህር አገልግሎት የሚሰጥ የትብብር እና አጋርነት ስምምነት ነው። ስምምነቱ በየትኛውም ሀገር ላይ ሉዓላዊነትን የሚጥስ / የሚገዳደር / በግዳጅ የየትኛውንም ሀገር ሉዓላዊነት የሚረግጥ አይደለም።

- እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ለሶማሊያ በችግር ጊዜ ብዙ ድጋፍ ያላደረጉ አንዳንድ ተዋናዮች ራሳቸውን እንደ እውነተኛ ወዳጆቿ ለማሳየት እየሞከሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ያነሳሳቸው ለሶማሊያ ያላቸው ወዳጅነት ሳይሆን #ለኢትዮጵያ_ያላቸው_ጥላቻ / የጠላትነት ስሜት መሆኑ ግልጽ ነው።

- እነዚህ ተዋናዮች አጀንዳቸው የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ፣ መረጋጋት እና ደህንነት አይደለም። ሊዘሩ የፈለጉት #አለመግባባት እና #ትርምስን ነው። እየታየ ያለው ነገር ውጥረት የሚያባብስ እንዲሁም ደግሞ አጋጣሚውን ለመጠቀም ለሚፈልጉ የውጭ ተዋናዮች ፍላጎት ብቻ የሚያገለግል ነው።

- ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመስረተ ሁሉን አቀፍ ቀጠናዊ ትስስርን ለመፍጠር ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር በትብብር መንፈስ ለመስራት እየጣረች ነው።

- ኢትዮጵያ ውጥረትን ከሚፈጥሩና ከሚያባብሱ መግለጫዎች፣ ንግግሮች እና ትርክቶች ይልቅ ቀጣይነት ያለው ውይይት ማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ በጽኑ ታምናለች።

#AmbassadorRedwanHussien #X

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
ረመዷን ነገ ይጀምራል። በሳውዲ አረቢያ የረመዳን ወር መግቢያ ጨረቃ በመታየቷ የታላቁና ቅዱሱ የረመዳን ወር ጾም ነገ ሰኞ ይጀምራል። @tikvahethiopia
#ረመዷን

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዜዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ፦

" ታላቁ የረመዳን ወር የእዝነት፣ የመተሳሰብ፣ የምህረት ወር በመኾኑ ደካሞችን፣ ችግረኞችን፣ ተፈናቃዮችን እንዲሁም ወላጅ አልባ ሕጻናትን በመርዳትና ማዕዳችንን በማካፈል በመተሳሰብና አላህን በመለመን ልናሳልፈው ይገባል።

የረመዳን ወር የእዝነት፣ የምህረትና ከእሳት ነጃ የምንወጣበት፣ አላህ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የዒባዳ ወር ይሁንልን።

መንፈሳዊ ልዕልና የሚኖረው #ሰላም ሲኖር በመኾኑ፣ ለሀገራችን ሰላም እና ለሕዝባችን ደኅንነት ዱዐ ልናደርግ ይገባል።

ለመላው ሙስሊም ማኀበረሰብ እንኳን ለ1445 ዓ.ሂ /2016 የረመዷን ወር በሰላም አደረሳችሁ። "

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
" ከእንግዲህ በሽፍትነት / rebel በመሆን መንግሥትን መጣል አይደለም ፤ መነቅነቅ አይቻልም " - ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፤ " ከእንግዲህ በኃላ በሽፍትነት / rebels በሚመስል ነገር መንግስትን መጣል አይደለም መነቅነቅ እንኳን አይቻልም " አሉ። ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ይህን ያሉት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ እና ታማኝ ግብር ከፋይ ባለሀብቶችን ሰብሰበው በመከሩበት ወቅት ነው።…
" በቅርቡ 5 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ በአንድ ባንክ ተልኮ ይዘናል " - ዶ/ር ዐቢይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሁለት ቦታ (ከመንግስት ጋር እና ጫካ መንግስትን ለመጣል ከሚታገሉ ጋር) የሚጫወቱ አንዳንድ ባለሃብቶች አሉ ሲሉ ተናገሩ።

ይህን የተናገሩት ከታማኝ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ምክክር ባደረጉበት ወቅት ነው።

ባለሃብቶቹ በምክክር መድረኩ ስለ #ሰላም ጉዳይ ያነሱ ሲሆን ጠ/ሚስትሩም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ ፤ " ሰላም ተብሏል እውነት ነው አስፈላጊ ነው " ብለዋል።

" ድሮ ሀብታሞች አዝማሪ ቀጥረው ያጫውቱ ፣ ይገጠምላቸው ነበር ድሃው እራት እየበላ በግጥም ይተባበራል ፤ አሁን ድገሞ ሀብታሞች #ዩትዩበር ይቀጥራሉ ድሃው በላይክ እና ሼር ይተባበራቸዋል እነዚህ ሰዎች እንደፈለጉ ሲያተረማምሱ ይውላሉ " ሲሉ ተናግረዋል።

" ዩትዩበሮቹን ባንቀልብ ወደ ስራ ወደ ኢንድስትሪ ይገቡ ነበር ፤ ለዚህ አስተዋጽኦአችን ምንድነው ብሎ ስራ ፈጣሪው ባለሃብቱ ግብር ከፋዩ ቢያስብ ጥሩ ነው " ብለዋል።

" እኛ እና እናተ ከተባበርን ሙስና ይቀንሳል፣ አገልግሎት ሊሻሻል ይችላል " ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ " ጫካ ላሉ ሰዎች ብር ባለመላክ ብትተባበሩም እንዲሁ ይቀንሳል " ሲሉ ተናግረዋል።

" አንዳንድ በተለያየ ቦታ ሚታገሉን ሰዎች እስከ 10 ቤት በአባቱ፣ በወንድሙ  ያለው ሰው አለ፤ በረሃ ታጋይ አታጋይ የሚባል ሰው። በጣም ሃብታሞች ናቸው እዛ ተቀምጠው መነገድ የሚቻል ከሆነ ሰላም ጋር ምን አመጣቸው ሰላም ከመጣ ንግድ የለም ማለት ነው " ብለዋል።

" ቤት አላቸው፣ በተለያየ አካውንት ባንክ ውስጥ ገንዘብ አላቸው በቅርቡ እንኳን 5 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ መጥቶ ይዘናል በአንድ #ባንክ ፣ ከፍተኛ ብር ይንቀሳቀሳል " ሲሉ ገልጸዋል።

" ሃብታሞች ማወቅ ፣ መብለጥ ፣ መላቅ ስለሚመስላቸው እዚህም ይጫወታሉ እዚያም ይጫወታሉ፤ እዚህ እኛን ' የተከበራችሁ ' ይላሉ እዛ ሄደው ' እንደናተ ጀግና የለም ' ይላሉ በዚህ ሰዎቹ እየተታለሉ እንደ ስራ መስክ ይዘውት ሀገር ያምሳሉ ወጣቶች ያልቃሉ ... ችግር አለ " ብለዋል።

" እናተም ልክ የድሃ ቤት እንደምትገነቡት ሁሉ በዚህም በኩል ችግሮች እንዲፈቱ ከልባችሁ ብታግዙ ያለው ነገር ይቀንሳል " ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ምንም እንኳን ስም ባይጠቅሱም ከሀገር የወጡ ባለሃብቶች እንዳሉ ገልጸዋል።

" የሆኑ የሆኑ ሰዎች ጠፍተው ይሄዳሉ ከዚህ። ከቆየ በኃላ ስንሰማ ለምንድነው የጠፋው ሚስተር X ጥሩት ወደሀገሩ ይመለስ ሲባል ሚስተር X አይፈልግም ያደረጋቸው ትራዛክሽኖች ሁሉ ይታወቃሉ ብሎ ስለሚያስብ አይፈልግም " ብለዋል።

" እኛ እንደ መንግስት አንድም ባለሃብት ከሆነ ክልል ጋር ግጭት ስላለ ከሀገር ውጣ ያልነው የለም " ሲሉ ተደምጠዋል።

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#አጣዬ

“ የሰው ሕይወት በእነርሱም በእኛም ጠፍቷል። የሟቾች ቁጥር እንደ አጣዬ ከተማ ወደ 10 ደርሷል። በጣም በርካታ ቁስለኞች አሉ ” - የአጣዬ ከተማ ከንቲባ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማና በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን በታጣቂዎች መካከል ተከፈተ የተባለው የተኩስ ልውውጥ ከሰሞኑ ይልቅ ዛሬ (ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ/ም) አንፃራዊ #ሰላም እንዳሳዬ፣ በነበረው የተኩስ ልውውጥ ግን በሁለቱም ወገኖች የንጹሐን ሕይወት እንዳለፈ የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ ተመስገን ተስፋ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

Q. ቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰላሙ ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ፣ የተኩሱ ሂደት ምን ይመስል እንደነበር፣ የጉዳት መጠኑ ምን ያክል እንደሆነ ለከንቲባው ጥያቄ አቅርቧል።

አቶ ተመስገን ተስፋ፦

“ ተኩሱ ሁለት ቀናት በዙሪያው ሲካሄድ ቆይቷል። ወደ ከተማው ከገባ በኋላ ደግሞ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ውጊያው ተካሂዷል።

መከላከያ ገብቶ ከቆመ በኋላም ተራራ ላይ በመሆን በመተኮሱ የተገደሉ ንጹሐን አሉ። የሰው ሕይወት በእነርሱም በእኛም ጠፍቷል። በጠቅል የሟቾች ቁጥር እንደ አጣዬ ከተማ ወደ 10 አካባቢ ደርሷል። ቁጥራቸው ባይታወቅም እጅግ በጣም በርካታ ቁስለኞች ናቸው ያሉት።

Q. ቲክቫህ ኢትዮጵያ በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን በኩል “ ፋኖ ታጣቂዎች ጥቃት አደረሱብን ” በአማራ ክልል በኩል ደግሞ “ የሸኔ ታጣቂዎች ጥቃት አደረሱብን ” የሚሉ ሀሳቦችን ነዋሪዎቹ በየፊናቸው እየገለጹ ይገኛሉ። እንደተባለው “ የፋኖ ታጣቂዎች ” ም ሆኑ የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው ጥቃት አድራሿቹ ? እውነታው ምንድን ነው? ሲል ጠይቋል።

አቶ ተመስገን ተስፋ፦

“ በከተማችን ላይ የፋኖ ታጣቂ የለም። ከእነርሱም ጋር ግጭት አልፈጠረም። ምናልባት የፋኖ ታጣቂ የሚባለው ችግሩ ከመንግሥት ጋር ነው። መንግሥትን ካልሆነ በስተቀር የኦሮሚያን ብሔር በዚህ ቦታ ሂዶ ተጋጨ የሚል እንደ ከተማችን የለም። ችግሩ የተፈጠረው በእኛ በከተማው ታጣቂዎችና በእነርሱ መካከል ነው።

ዞሮ ዞሮ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች በአንድ ገበያ የሚገበያዩ፣ ተስማምተው የሚኖሩ፣ በማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ ስለሆኑ፣ አማርኛ ተናጋሪው ኦሮሞው ላይ፣ ኦሮምኛ ተናጋሪውም እንደ ህዝብ ጥቃት ያደርሳል፣ ፈልጎ ይዋጋል ብለን አናስብም።

ልዩ የሆነ ቡድን፣ ፀቡ እንዲነሳ የሚፈልግ (ምናልባት ደግሞ ከዚያ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችል) ቡድን አለ። እሱም ደግሞ ኦረምኛ ተናጋሪ ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው ‘ሸኔ’ ነው።

ስለዚህ የእኛ ፍረጃ አሁን የኦሮሞ ሕዝብ የአማራን ሕዝብ ወጋው ሳይሆን፣ የኦሮሞ ‘ሸኔ’ አማርኛ ተናጋሪውን በከተማው ላይ መጥቶ ወግቷል የሚል ግምገማ ነው ያለን።

Q. ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንዲቻል መንስኤውን ማወቅ ያስፈልጋልና የሰሞኑ ተኩስ መነሻው ምን ነበር ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ አቅርቧል።

አቶ ተመስገን ተስፋ፦

“ እንደ አጠዬ ከተማ ነዋሪ፣ እንደ ከተማ አመራር መነሻው ይሄ ነው የሚል ነገር የለም። ግጭቶቹ የተካሄዱት በወሰን ብቻ ሳይሆን በከተማው መሀል ላይ ነው። ድንገት ገቡ ተወረረ ከተማው።

ከንጹሐን ሞት በተጨማሪ ሆቴሎች፣ ሱቆች ተዘርፈዋል። አረጋዊያን፣ ሴቶች፣ ህፃናት ከከተማ ወጥተው ወደ ገጠራማው ክፍል ተፈናቅውለዋል። አጣዬ ከተማ ያሉት ወንዶችና የጸጥታ አካላት ብቻ ናቸው።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አካባቢውን መከላከያ ተቆጣጥሯል። አንጻራዊ የሆነ ሰላም አለ። ”

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በኩል ስለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም። ፈቃደኛ ሆነው የሚሰጡት ማብራሪያ ካለ በቀጣይ ይቀርባል።

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Update

ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጦችን ሲያስተናግዱ በቆዩት በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች ውስጥ ካለፉት 3 ቀናት ወዲህ አንጻራዊ የሚባል #ሰላም መኖሩን የአካባቢውን ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ ቪኦኤ ዘግቧል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ፤ የአጣዬ ከተማ አስተያየት ሰጭዎች ፣ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መኖሩን አመልክተዋል። ለደኅንነታቸው ሲሉ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች የተፈናቀሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ግን በአሳሳቢ ችግር ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

አልፎ አልፎ ግን የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ አመልክተዋል፡፡

አንድ የሰንበቴ ከተማ ነዋሪ ፥ " መንገድ ዝግ ነው መንቀሳቀስ አልቻልንም። የጅሌ ጥሙጋና የአርጡማ ፋርሲ ወረዳዎች ተቆራርጠናል። ተረጋግቷል የሚባለው በሁለቱም ወረዳዎች መንግሥት ሰላም አስፍኖ መንገዶች ሲከፈቱ ነው። አሁን መንገድ አልተከፈተም ሰውም ችግር ውስጥ ነው " ብለዋል።

ነዋሪዎች ዘላቂ የሆነ ሰላም እንዲመጣ የፌደራል መንግሥቱ መፍትሔ እንዲያፈላልግ ነዋሪዎቹ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ጥሪ አቅርበዋል።

ሰሞኑን በነበረው የተኩስ ልውውጥ የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ ንብረት ወድሟል።

@tikvahethiopia
#ትግራይ

ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ምን አሉ ?

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች በክልሉ ለሚገኙ ሚድያዎች መግለጫ ሰጥተው ነበር።

በዚህም ወቅት ፥ " በፕሪቶሪያ ውል ያልተፈፀሙት እንዲተገበሩ እየሰራን እንቀጥላለን " ብለዋል። 

" የፕሪቶሪያ ውል የፈረምነው የተለያዩ የትግራይ ቦታዎች ከክልሉ አስተዳደር ውጭ በነበሩበት በርካታ ወገኖች ከቄያቸው በተፈናቅሉበት ጊዜ ነበር " ያሉት ጄነራሉ " የውሉ ተዋዋዮች በህገ-መንግስት መሰረት የትግራይ ግዛታዊ አንድነት እንዲረጋገጥ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ ተስማምተዋል " ብለዋል። 

" የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ውልን በጥንቃቄ መተግበር ይገባል " ሲሉ ገልጸዋል።

" አሁን በመታየት ያለው ውጤት የጦርነቱ ውጤት እንጂ የጦርነቱ መነሻ አይደለም " ሲሉ ገልጸዋል።

" የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ትግራይ በሃይል የተያዘባት መሬት ሙሉ በሙሉ መልሳ የተማላ ቁመናዋ መያዝ ፤ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ እንዲተገበሩ ያስገድዳል ይህ እንዲሆን ደግሞ በሃይል በተያዙ ቦታዎች ያሉ ታጣቂዎች መውጣትና ህጋዊ ያልሆነው አስተዳደር መፍረስ አለባቸው " ብለዋል።     

" ህጋዊ ያልሆኑ አስተዳደሮች ማፍረስና ታጣቂዎች ትጥቃቻውን ማስፈታት የፕሪቶሪያ ውል የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን ቀጥሎ የሚደረገው ሁሉ #ሰላም ከተረጋገጠ በኋላ የሚሆን ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

" ተፈናቃዮች ሲመለሱ ክብራቸው ተጠብቆ ፣ የሚያስፈልጋቸው መሰረተ ልማት ሁሉ ተሟልቶ ሰብአዊ ድጋፍ ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች በማድረግ መሆን አለበት "  ያሉት ጀነራሉ  " አስተዳደርን በሚመለከት ቀበሌዎችና ወረዳዎችን የሚያስተዳድሩ ጊዚያዊ  አስተዳደሮች ራሱ ህዝቡ ይመርጣል " ብለዋል።  

ዘላቂ መፍትሄ በሚመለከት ምን አሉ ?

" የፌደራል መንግስት ' አከባቢዎቹ በፌዴራል ስር ቆይተው #ሪፈረንደም ይካሄድ ' የሚል አቋም ያለው ሲሆን በእኛ በኩል ደግሞ በአከባቢው ጊዚያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ ወደ ትግራይ ይመለሱ የሚል አቋም ነው ያለው፤ ይህ የአቋም ልዩነት እስካሁን አልተፈታም እንዲፈታ ደግሞ ቀጣይ ሰላማዊ ትግል እናደርጋለን " ብለዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyMekelle

Photo Credit - Tigrai & DW TV
                                          
@tikvahethiopia