TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.4K photos
1.43K videos
206 files
3.95K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
" የአላቂ እቃዎች እጥረት በጣም ትልቅ ፈተና ሆኖብናል " - የልብ ሕሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል

የአላቂ እቃዎች እጥረት የህፃናት ታካሚዎችን ወረፋ እየጨመረው መሆኑን፣ አሁንም ድረስ በአቬሬጅ አራት ዓመት ለሚሆን ጊዜ ወረፋ እየጠበቁ ያሉ ወደ 8,000 የሚጠጉ ህፃናት እንዳሉ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ለቲክህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

የማዕከሉ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ባልደረባ ዶ/ር ዳዊት እሸቱ በሰጡን ቃል፣ " የአላቂ እቃዎች እጥረት በጣም ትልቅ ፈተና ሆኖብናል" ብለዋል።

በማዕከሉ አጣዳፊ ትኩረት የሚሻው ፈታኝ ጉዳይ ምንድን ነው ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ አቅርቧል።

ዶ/ር ዳዊት ፥ " እያጋጠመን ያለው አንዱና ትልቁ ፈተና የአላቂ እቃዎች ነው። የምንሰጣቸው አገልግሎቶች በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ አገልግሎት ላይ ለሚውሉ እቃዎች በተለያዩ ምክንያቶች እጥረት አለ " ብለዋል።

" የአላቂ እቃዎች እንደልብ አለመገኘት የታካሚ የወረፋ ጊዜን እየጨመረው ይገኛል። አሁንም ወደ 8,000 የሚጠጉ ህፃናት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ " ሲሉ ገልጸዋል።

" አቬሬጅ የወረፋ ጊዜ አራት ዓመት እየደረሰ ነው ። በዋናነኝነት ከምንጠቀማቸው እቃዎች በተጨማሪ በዬቀኑ አክቲቪቲው ላይ የሚውሉ ለኦፕሬሽንና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ መድኃኒቶች/የአላቂ እቃዎች እጥረት በጣም ትልቅ ፈተና ሆኖብናል " ብለዋል።

በአቬሬጅ ለአራት ዓመት ወረፋ እየጠበቁ ያሉ ህፃናት ቢያንስ በምን ያክል ጊዜ ነበር ህክምና ማግኘት የነበረባቸው ? ስንል ላቀረብነው ጥያቄ " በዓመት እስከ 500 ታካሚዎችን እናስተናግዳለን። በሙሉ አቅማችን ግን ብንሰራ እስከ 1500 ህፃናትን መድረስ እንችላለን " ሲሉ መልሰዋል።

" ችግሩ ግን በዓመት 1,300 ያህል አዳዲስ ታካሚዎች ይኖራሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ከ20 ሺሕ በላይ ህፃናት በተፈጥሮ ከሚመጣ የልብ ችግር ጋር ይወለዳሉ ይባላል በዓመት። ስለዚህ ይሄ ችግር ውጪ አገር ቶሎ ነው መፍትሄ የሚሰጠው አገልግሎቱ አቬሌብል ስለሆነ። ወዲያው ቢሆን ይመረጣል "  ነው ያሉት።

እጥረት እየተስተዋለባቸው ያሉ የእቃ አይነቶች ምንድን ናቸው ? ስንል ላቀረብነው ጥያቄ ዶ/ር ዳዊት እሸቱ ፦

" ለልብ ህክምና የሚያስፈልጉ መድኃኒቶች አሉ። እንደ የደም ማቅጠኛ አይነት መድኃኒቶች ናቸው። ሁለት አይነት አገልግሎቶችን ነው የምንሰጠው በኛ ማዕከል። 

አንደኛው ደረት ተከፍቶ የሚሰራው ቀዶ ህክምና ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በደም ስር ውስጥ ተኪዶ የልብ ጥገናው የሚካሄድበት አገልግሎቶች ናቸው። እያንዳንዳቸውም የሚጠቀሟቸው ማተሪያሎች አሉ።

በቀዶ ህክምናው ኦክስጂኔተር የሚባል አለ። የልብና የሳንባውን ሥራ ተክቶ የሚሰራው ማሽን ላይ የሚገጠም ነው። እሱ ማተሪያል ለአንድ ጊዜ ነው አገልግሎት ላይ የሚውለው። ለአንድ ታካሚ ለአንዴ ነው የሚሆነው።

ካትላብ ላይ ደግሞ በደም ስር ውስጥ ዋየሮች የተለያዬ የዋጋ ሬንጅ አላቸው። እነርሱን እኛ ጋ አጥበን እስከ 4፣ 5 ጊዜ ደጋግመን እንጠቀማቸዋለን።

ስለዚህ በዋነኝነት እነዚህ ማተሪያሎች፣ ከዚያ ደግሞ የተለያዩ ኬሚካሎች ሁሉ አላቂ ከምንላቸው እቃዎች ውስጥ ይካተታሉ
" ሲሉ መልሰዋል።

የልብ ሕሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ላለፉት 35 ዓመታት አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል።

በመጀመሪያዎቹ 20 ዓመታት ህክምና ሲሰጥ የነበረው ወደ ውጪ በመላክ ነበር። በዚህም ወደ 2,600 ገደማ ህፃናት ውጪ ሂደው እንደታከሙ፣ ላለፉት 15 ዓመታት ደግሞ አሁን ባለው ማዕከል አገልግሎት እየሰጠ ነው።

በአጠቃይ እስካሁን 9,000 ህፃናት የልብ ቀዶ ጥገና እንደተደረገላቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስረድቷል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
#Amhara

🔴 “ ስለፓለቲካ ምንም የማያውቁ፣ ሮጠው የማያመልጡና ሰርተው የማይበሉ አረጋዊያን ላይ መድፍ መወርወር ሊወገዝ ይገባል ” - ነዋሪዎች

🔵 “ ፈቃደኝነት እንዲኖራቸው የሚፈለጉ ኃይሎች ቢያንስ ድርድር እንደሚፈልጉ በመግለጫ የተደገፈ ሀሳብ ቢሰጡ ህዝቡ ከስቃይ እፎይ ይል ነበር ” - ካውንስሉ

ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረውና ልጓም ባጣው በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ መካከል በሚደረገው የተኩስ ልውውጥ ሳቢያ የንጹሐ ስቃይ ተባብሶ መቀጠሉን አሁንም የገፈቱ ቀማሾችና የዓይን እማኞች ገልጸውልናል።

ንጻሃን ዜጎች እየተጎዱ ያሉት በምድር በሚደረግ የተኩስ ልውውጥ ከዚህም አለፍ ሲል በአየር ላይ በሚካሄድ ጥቃትም ጭምር ነው።

ሰሞኑን በክልሉ በከባድ መሳሪያ ጨምር የታገዘ የተኩስ ልውውጥ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው አዊ ዞን በንጹሐን ላይ ከባድ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት መድረሱ ታውቋል፡፡

በዞኑ ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ ቲሊሊ ከተማ ዙሪያ በ ‘ፋኖ’ እና መከላከያ መካከል የሚደረገው የተኩስ ልውውጥ በንጹሐን ላይ የከፋ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ የተጎጂ ቤተሰቦችና ነዋሪዎች በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ተማጽነዋል።

ከቀናት በፊት ከእንጅባራ አቅጣጫ ተተኩሶ ቲሊሊ ከተማ ወጣ ብሎ ከአንድ የገጠር ቤት ላይ ያረፈ መድፍ በቤተሰብ አባላት ላይ ከባድ የአካል ጉዳት፣ በንብረት ላይም የከፋ ውድመት ማድረሱን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

“ ሰሞኑን ወደ ቲሊሊ መድፍ ተወርውሮ በንጹሐን ቤት ላይ አርፏል። አንዲት ሴት እግሯ ተቆርጧል። ህጻን ልጅም ተጎድታለች። ስድስት ከብቶች ተገድለዋል። ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ወድሟል ” ሲሉ አንድ የዓይን እማኝ ገልጸዋል።

ሌላኛው የተጎጂ ቤተሰብ፣ “ ከቲሊሊ ከተማ ወጣ ብሎ ነው የተወረወረው መድፍ ጉዳት ያደረሰው ” ሲሉ ተናግረዋል።

“ በወቅቱ በመከላከያና በፋኖ መካከል የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ ነበር። መድፉ የተተኮሰው ግን ከእንጅባራ አቅጣጫ ነው። እሳቱ አልበርድ ብሎ የሰፈር ሰው በልቅሶ፣ በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ነው ያለው ” ብለዋል።

“ የሞተ የለም። ከሁለቱ ሰዎች ውጪ ሌላ የተጎዳም የለም። ከብቶች ግን ሁሉም አልቀዋል ” ነው ያሉት።

ስለፓለቲካ ምንም የማያውቁ፣ ሮጠው የማያመልጡና ሰርተው የማይበሉ አረጋዊያን ላይ መድፍ መወርወር ሊወገዝ ይገባል ሲሉም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ድርጊቱ የተፈጸመው ማክሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ/ም ከቀኑ 7: 30 ገደማ መሆኑን አስረድተዋል።

በአካባቢው ባለው ሁኔታ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ንጹሐንን ይደበድባሉ ሲሉም ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

" ያለው ድባብም የሚመች አይደለም " ሲሉም ገልጸዋል።

በምዕራብና ሰሜን ጎጃም፣ በጎንደር፣ በሰሜን ወሎ የተለያዩ አከባቢዎች ሰሞኑን ተፈጸመ በተባለ በድሮንና ከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ የተኩስ ልውውጥ ቁጥራቸው ገና በውል የማይታወቅ ንጹሐን ሰዎች ግድያና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ነዋሪዎች በሀዘን ስሜት አስረድተዋል።

የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ‘ የፋኖ ኃይሎችን ትደግፋላችሁ ’ በማለት ንጹሃን ላይ ከሚያደርሱት ግድያና ድብደባ በተጨማሪ ፥ ታጣቂዎችም ‘ መንግስትን ትደፋላችሁ ’ በሚል በንጹሐን ላይ ግድያ መፈጸማቸው ከተጎጂ ቤተሰቦች የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር የንጹሐን ግድያ ፣ የአካል ጉዳት ፣ እገታ ፣ የትምህርትና የግብርና ሥራ መስተጓጎል እንዳስከተለ ይታወቃል ፤ እየደረሰ ያለው ዘርፈ ብዙ ጉዳትም ሊቀለበስ አልቻለም። ሁለቱንም ተዋጊ ኃይሎች ለድርድር እንዲቀራረቡ ከማድረግ አንፃር ተስፋ ይኖር ይሆን ? ሲል የአማራ ክልል የሰላም ካውንስልን ጠይቋል።

ካውንስሉ ምን ምላሽ ሰጠ ?

" በሁለቱም ወገኖች በኩል ድርድርና ምክክር መደረግ አለበት ብለን ነው የተነሳበውና ይሄንኑ ወደ ተግባር ለማሸጋገር በመንግስት በኩል ፈቃደኝነት እንዳለ ገልጸናል፡፡

ፈቃደኝነት እንዲኖራቸው የሚፈለጉ ኃይሎች ቢያንስ ድርድር እንደሚፈልጉ በመግለጫ የተደገፈ ሀሳብ ቢሰጡ ህዝቡ ከስቃይ እፎይ ይል ነበር፡፡

' የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል ' እንዲሉ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ሌሎች አክተሮችም ስላሉ ግድያው፣ ሌብነቱ፣ እገታው ከዚሁ የመነጨ ነው፡፡ 

የእርስ በእርስ ጦርነት ከባድ ችግር ነው የሚያስከትከለው፡፡ ወደፊትም እንዲህ አይነቱ ነገር እጅግ በጣም ዘግናኝ የሆነ መጥፎ ነገር ሁሉ ያመጣል።

ይሄ እንዳይመጣ ወደ ድርድር እንዲመጡ ነው ለሁሉም አካላት ጥሪ ያደረግነው፡፡ የሆነው ሆነና እንደ ጠቅላላ ጉባዔ የምንለው ነገር አለና ያኔ ለሁሉም ጥያቄዎች ዝርዝር ማብራሪያ እንሰጣለን፡፡

ይህንኑ ጉዳይ በሚመለከት ሰሞኑን ስብሰብ እንደርጋለን፡፡ የሰላም ካውንስሉ የራሱን ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቷል፡፡ ከእሁድ በኋላ ጠቅላላ መግለጫ የምንሰጥ ነው የሚሆነው በዚያን ጊዜ ጠቅላላ ህዝቡ እንዲያውቀው የምናደርገው ጉዳይ አለ "
ብሏል።

(የካውንስሉን የጉባዔ ውጤትና ለሚቀርቡት እሮሮዎች የተሻለ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ በቀጣይ መረጃ የምናደርሳችሁ ይሆናል)

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#AddisAbaba “በክፍት ቤቶች ባለቤቶቻቸው አድሰው የፈለጉትን አገልግሎት ሊያውሉት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው ማስታወቂያው የወጣው” - ኮርፖሬሽኑ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን " የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤቶች እስከ ጥቅምት 30/2017 ድረስ ወደ ቤታችሁ ግቡ " በሚል ባወጣው ማሳሰቢያ ዙሪያ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጠው ዝርዝር ምላሽ ምንድን ነው ? የኮርፖሬሽኑ ማብራሪያ ፦ “ ማስታወቂያው…
#AddisAbaba

" አሁንም አንዳንድ የቤት ባለቤቶች ወደ ቤታቸው ለመግባት ምንም እንቅስቃሴ እያደረጉ አይደለም ፤ ይህ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ነው " - ኮርፖሬሽኑ

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በተለያዩ ጊዜያት በእጣ እና በጨረታ ተላልፈው ነዋሪ ያልገባባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች አስመልክቶ እስከ ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም ድረስ የቤት ባለቤቶቹ ወደ ቤታቸው የማይገቡ ከሆነ በህግ አግባብ ውል የሚቋረጥ መሆኑን ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡

በዚህም በርካታ የቤት ባለቤቶች ወደ ቤታቸው የገቡ ወይም ለመግባት ዕድሳት ላይ ስለመሆናቸው አደረኩት ባለው የአካል ምልከታ የተገነዘበ መሆኑን ገልጿል።

አሁንም ግን አንዳንድ የቤት ባለቤቶች ወደ ቤታቸው ለመግባት ምንም እንቅስቃሴ ያላደረጉ ፤ ነዋሪ ያልገባባቸው ቤቶች እንዳሉ መለየቱን አመክክቷል።

በኮርፖሬሽኑ የቀረበውን ጥሪ ተቀብለው ቤታቸውን አድሰው ለመግባት የጊዜ እጥረት ላጋጠማቸው አንዳንድ የቤት ባለቤቶች የተሰጠውን የጊዜ ገደብ አራዝሟል።

እስካሁን ድረስ ወደቤታቸው ለመግባት ምንም ይነት እንቅስቃሴ ያላደረጉ እንዲሁም ቤት ለማደስ የጊዜ እጥረት ያጋጠማቸው የቤት ባለቤቶች እስከ ህዳር 30 2017 ዓ.ም ወደ ቤታቸውን እንዲገቡ ለመጨራሻ ጊዜ አስጠንቅቋል።

በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማይገቡ ነዋሪዎች የሽያጭ ውላቸው የሚቋረጥ እና በቤታቸው ውስጥ ለሚፈጸም ማንኛውም ህገወጥ ድርጊት ተጠያቂ የሚሆኑ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አሳስቧል።

ከዘህ ቀደም ኮርፖሬሽኑ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ሰጥቶት በነበረው ማብራሪያ ፥ ማስታወቂያው የወጣበት ዋናው ምክንያት ሰዎች ‘ ተቸገርን፣ ክፍት በሆኑ ቤቶች ወንጀል እየተሰራ ነው፣ እየተዘረፍን ነው፣ ሴቶች እየተደፈሩብን ነው፣ የጸጥታ ስጋትም እየሆኑብን ’ ብለው ቅሬታ ስላቀረቡ እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል።

ቤቶቹ ቼክ ሲደረጉ ደግሞ እጣ ወጥቶባቸዋል፤ ውል ተፈጽሞባቸዋል፣ ግን ሰው አልገባባቸውም፡፡

" ስለዚህ ነዋሪው ተቸግሯል፡፡ የጸጥታ ኃይሉም ጥያቄ እያነሳ ነው " ብሎም ነበር።

" የቤት ባለቤቶች ቤታችሁን አድሳችሁ ግቡ " የተባለውም የግድ እራሳቸውን እንዳይሰለ አስረድቶ ነበር።

" ቢፈልጉ አድሶ ማከራየት መብት ነው፡፡ የራሳቸው ቤት እስከሆነ ድረስ፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ ሰው በቤቱ ይኑርበት ነው የኛ ጥያቄ፡፡ አካራይ አታከራይ የኛ መልዕክት ሊሆን አይገባም፡፡ ግን ቤቱን ኦውን ያድረጉ " ነው የሚል ማብራሪያ ነበር ኮርፖሬሽኑ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጠው።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#ትግራይ

" ቡድኑ ለስልጣን ሲል ማንኛውም ዓይነት ጥፋት ከመፈፀም ወደ ኋላ እንደማይል በተደጋጋሚ እየታየ ነው " - የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር

የትግራይ ጊዚያዊ አስተደደር ዛሬ ህዳር 1/2017 ዓ.ም የፅሁፍ መግለጫ አውጥቷል።

በዚህም " በአንደኛው ገፅ ልዩነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረሩ ሄደዋል በሌላኛው ገፅ ደግሞ የጊዚያዊ አስተዳደሩ እቅዶች የማደናቀፍ እና የማዳከም የተቀናጀ ዘመቻ ሲደረግ ቆይቷል አሁንም ቀጥሏል " ሲል ገልጿል።

በተለይም ከነሀሴ 2016 ዓ/ም ጀምሮ በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እና በግልፅ የታየው ልዪነት መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄያዎች በተቀናጀ መልኩ እንዳይፈቱ ከባድ እንቅፋት ፈጥረዋል ብሏል።

የጊዚያዊ አስተዳደሩን እቅዶች በተቀናጀ መልኩ የሚያደናቅፈው ህጋዊ ያልሆነ ጉባኤ ያካሄደው ቡድን ከፍተኛ አመራር ነው ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ " ደርጊቱ ህዝቡ ተስፋ እንዲቆርጥ ሆነ ተብሎ የሚደረግ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው " ሲል አውግዞታል። 

" የቡድኑ ተግባር የጊዚያዊ አስተዳደሩ እቅዶች ከማደናቀፍ በዘለለ ይፋዊ ወደ ሆነ የመንግስት ግልበጣ እና ስርዓት አልበኝነት ማስስፋፋት ከፍ ብሏል " ሲል ከሷል።

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በመቐለ ከተማ  ፣ በሰሜናዊ እና ማእከላዊ ዞኖች የታዩት የመንግስት ግልበጣና ስርዓት አልበኝነት ምልክቶች የቡድኑ ህግ አልበኝነት ማሳያ ናቸው ሲል አስረድቷል።

" ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የመንግስት የአመራር እርከን ከላይ እስከ ታች ለመቆጣጠር ጨርሰናል " የሚል የማደናገሪያ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል።

" የቡድኑ ማደናገሪያ በአጉል ተስፋ ራስን ከማታለል የዘለለ ቅንጣት ሀቅ እንደሌለው መታወቅ አለበት " ያለው አስተዳደሩ " ቡድኑ ለስልጣን ሲል ማንኛውም ዓይነት ጥፋት ከመፈፀም ወደ ኋላ እንደማይል በተደጋጋሚ እየታየ መጥቷል " ሲል ገልጿል።

" ' ከሰራዊት አመራሮች ተግባብተናል ' በሚል እየነዛው ያለው ማደናገሪያ ለጠባብ የስልጣን ፍላጎቱ ማሟያ ነው " ብሏል።

" በትግራይ ህልውና የቆመው ሃይል ከመጠቀም እንደማይመለስም ማሳያ ነው " ሲል አክሏል።

" ቡድን " ሲል የገለፀው አካል በሃይማኖት አባቶች የተጀመረው ነገሮች በውይይት የመፍታት ሂደት እንደማይቀበል በአደባባይ ገልፀዋልም ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል።

የጊዚያዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮቼ አሁንም ነገሮች በሰከነ አኳሃን በሰላም እና በውይይት ለመፍታት ዝግጁ ናቸው ብሏል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች የጀመሩት የሰላምና የውይይት ጥረት እንዲሳካ ሁሉም ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርቧል።

በቅርቡ የትግራይ ሃይማኖት አባቶች የህወሓት አመራሮች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በንግግር እንዲፈቱ ለማድረግ ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እና አቶ ጌታቸው ረዳ እና አመራሮቻቸውን በአካል አገናኝተው ነበር።

ከዚህ መድረክ በኃላ በወጡ የተለያዩ ፎቶዎች በርካቶች " ችግሩ በንግግር ሊፈታ ነው " በሚል ብዙ ተስፋ አድርገው ነበር።

በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት ትናንት በትግራይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አባቶች አማካኝነት ሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ያደረጉት የፊት ለፊት ግንኙነት ከብፁአን የሃይማኖት አባቶች ተግሳፅና ምክር የዘለለ ውጤት እንደሌለው ተናገረ።

የደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ህወሓት ዛሬ ምሽት አጭር መግለጫ አውጥቷል።

አንዳንድ ሚዲያዎች ደግሞ " ለእርቅና ሽምግልና ተስማምተዋል " የሚል መረጃ እስከማሰራጨትም ደርሰው ነበር።

በኃላ በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት ፥ " በብፁአን አበው የተዘጋጀው ፊት ለፊት የማገናኘት መርሃ ግብር ልዩነቶች በህግ ፣ ተቋማዊ ስርዓት ማእከል በማድረግ ህዝብን ከአደጋ መታደግ በሚችል የሰለጠነ ሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችን እንድንፈታ ያለመ የምክርና የተግሳፅ መድረክ ነበር " ሲል አሳውዋል።

" ብፁአን አበው ላቀረቡልን ምክርና ተግሳፅ ያለንን ክብርና ድጋፍ ገልፀናል ፤ ከዚህ በዘለለ የተለያዩ አካላትና ሚዲያዎች ' ለእርቅ እና ሽምግልና ተስማምተዋል ' በማለት የሚያሰራጩት መረጃ ከእውነት የራቀ ነው " ሲል ነበር የገለጸው።

በቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ አባል ተዘጋጅቶ የተላከ።

#TikvahEthiopiaFamilyAA #Tigray #Mekelle

@tikvahethiopia
#AddisAbaba

" ያለደረሰኝ አትሽጡ አልን እንጂ እቃ እንወርሳለን ያለ አካል የለም " -የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ " በከተማዋ በርካታ ነጋዴዎች በግብር ከፋይነት ተመዝግበው ደረሰኝ የማይሰጡ በመሆናቸው እና ችግሩም በጣም እየሰፋ በመሆኑ ወጥነት ባለው መንገድ ህጉን እንዲያከብሩ እና ወደስርዓት እንዲገቡ ለማድረግ እየሰራው ነው " ሲል ገልጿል።

ቢሮው የታክስ ኢንተለጀንስ እና ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ነጋሽ የቁጥጥር ስራው ከዚህ ቀደምም የነበረ ቢሆንም በዘመቻ መልክ ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

ዘመቻ ሲባል ፦
- ወደ ቫት ስርዓት ውስጥ ያልገቡትን ማስገባት ፣
- ፈቃድ የሌላቸው ፈቃድ እንዲያወጡ ማድረግ፣
- ደረጃቸው ደረሰኝ መስጠት የሚገባቸው ሆኖ ሳለ የማይሰጡትን ደረሰኝ አስፈቅደው እና አሳትመው መጠቀም እንዲጀምሩ ማስቻልን ያካትታል።

የቁጥጥር ስራው በተለይም በገበያ ሞሎች ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ታውቋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም አንዳንድ ነጋዴዎች እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ " ንብረት ለመውረስ እና ሱቆችንም ለመዝጋት ነው " በሚል ሱቃቸውን ዘግተዋል ንብረትም ወደ ሌላ ቦታ አዙረዋል።

ቃላቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡ  በመርካቶ አካባቢ የሚሰሩ ነጋዴዎች  " ከምንም በፊት ያሉትን ችግሮች ማወቅ ይገባል። ቸርቻሪውን ማነጋገር ያስፈልጋል። ችግሮቹን ለመቅረፍ መሰራት አለበት። " ብለዋል።

" ነጋዴው ከአስመጪ እቃ ሲገዛ አስመጪው ከዋጋው በታች ደርሰኝ ይሰጣል አልያም ጭራሽ ላይሰጥም ይችላል ፤ ምንም  አይነት የግዢ ደረሰኝ ባላገኘበት ' ነጋዴው ሱቅ ውስጥ ያለዉን ንብረት እንወርሳለን ' ማለት ትክክል አይደለም " ሲሉ አክለዋል።

" መንግሥት ታች ያለው ነጋዴ ላይ ጣቱን ከመቀሰር አስመጪዎቹን ደረሰኝ እንዲሰጡ ማድረግ እና ቸርቻሪውን ማወያየት ያስፈልጋል " ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አንዳንድ የራሳቸው የገቢዎች ሰዎች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ቸርቻሪዎችን ማስጨነቅ እንደሚቀናቸው ቃላቸውን የሰጡ አንዳንድ ነጋዴዎች ጠቁመዋል።

ያለ ደረሰኝ ግብይት በሚፈጸምበት ወቅት የገንዘብ ድርድር ሁሉ እንደሚያደርጉና ያሉ ችግሮች ስር የሰደዱ እንደሆኑ ገልጸዋል።

" ከምንም በላይ ያለ ደረሰኝ ግብይት እንዳይኖር ከላይ ጀምሮ መስራት እንደሚገባ ነጋዴው በደረሰኝ ከገዛ በደረሠኝ እንደሚሸጥ ከላይ ግን እጃቸው የረዘመ ሰዎች ስላሉ መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ " አመልክተዋል።

ሁኔታዎችን በመጠቀም በህግ ሰበብ ከነጋዴው ገንዘብ የሚቀበሉና ሙስና የሚሰሩ ህገወጥ ተግባራትንም የሚያባብሱ በገቢዎች አካባቢ ያሉ ሰዎች እንዲታረሙ መሰራት እንዳለበት አክለዋል።

ዛሬ በመርካቶ " ያለ ደረሰኝ ለምን ሸጣችሁ " በሚል ንብረት ይዘው የሄዱም እንዳሉ በመጠቆም በዚህ ምክንያት ሱቆች ተዘግተው እንደነበር ጠቁመዋል።

ሌላ አንድ በቲክቫህ ኢትዮጵያ የሃሳብ መለዋወጫ መድረክ ሃሳባቸውን ያካፈሉ ዜጋ ፥ አስመጪዎች እና አምራቾች ለጅምላ ነጋዴ እና ቸርቻሪ ያለደረሰኝ ስለሚሸጡ ያለደረሰኝ የተገዙ እቃዎች እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

" ነጋዴዎች እቃዎቻቸው ሳይወዱ ደረሰኝ ስለሌላቸው እንዳንወረስ ብለው ወደ ሌላ ቦታ ያሸሻሉ ሱቅም ለመዝጋት ይገደዳሉ  " ብለዋል።

" ዋናው ስራ መጀመር ያለበት ከአስመጪዎች እና አምራች ኢንዱስትሪዎች መሆን አለበት ፤ እነሱን በሚገባ ከተቆጣጠሩ እና እርምጃ ከወሰዱ በኋላ በተዋረድ ጅምላ ነጋዴዎች እና ቸርቻሪዎችን መቆጣጠር ይገባል " ብለዋል።

" የችግሩ ምንጭ ከሆኑት አስመጭዎች እና አምራች ኢንዱስትሪዎች ጠበቅ ያለ እርምጃ መወሰድ አለበት " ሲሉ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

" በዛሬው ዕለት በመርካቶ አካባቢ ንብረት ሊወረስ ነው፤ ሱቃችን ሊዘጋ ነው " የሚል ውዥንብሮች በመፈጠራቸው አንዳንድ ነጋዴዎችን ግርታ ውስጥ መክተቱ ተናግሯል።

ስለ ጉዳዩ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የታክስ ኢንተለጀንስ እና ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ነጋሽን አነጋግሯል።

ዳይሬክተሩ ምን መለሱ ?

➡️ " ጠዋት ሱቆች ሁሉ ተዘግተዋል " ተብሎ ተወርቶ በአካል ዞሬ አይቻለሁ የተወሰኑ ሱቆች የተለያዩ ቦታዎች ላይ የተዘጉ የሚመስሉ አሉ ነገር ግን መደበኛ ሥራ ቀጥሏል።

➡️ " በዚህ ደረጃ ተዘግቷል ለማለት እይቻልም ተዘጋ የሚባለው ምን ያህል ሱቅ ሲዘጋ ነው ? አንድ ቤት ሁለት ቤት ተዘግቶ ይሆናል ነገር ግን አብዛኛው እየሰራ ነው።

➡️ ህገ ወጥነትን ማስቀጠል የሚፈልግ አካል  አለ። ሆን ብሎ ' የሆነ ነገር ተሰርቷል፣ ሊሰራ ነው ' የሚል ውዥንብር መፍጠር የሚፈልግ አካል እንዳለ ነው የተረዳሁት።

➡️ ቁጥጥር ሊደረግ ነው በተለይ አስመጪ እና አከፋፋይ ላይ ሲባል ቸርቻሪ ላይ ስጋት የሚፈጥሩ አሉ፣ በትላንትናው ዕለትም የሚሸሹ ነጋዴዎች ገጥመውናል ያለፍቃድ ይነግዱ የነበሩ ናቸው ብንጠየቅ መልስ የለንም በሚል ስጋት ነው። ሱቃቸውን ቢዘጉም እነሱ ናቸው የሚሆኑት።

➡️ ተዘግቷል የሚለውንም እርግጠኛ መሆን ይፈልጋል በእርግጥ የተዘጋ ነው ወይስ ነጋዴው በsocial ችግር ሱቃቸውን ዘግተው ስለሌሉ ነው የሚል ጥርጣሬ የሚያጭር ስለሆነ የተዘጉ አይደሉም ወደሚል ድምዳሜ ነው የደረስነው።

➡️ ይርጋ ሃይሌ የገበያ ሞል ላይ ከ15 ቀን በፊት ኮንትሮባንድ ስለነበረ ጎምሩኮች በርብረዋል ደረሰኝ የሌለውን ወርሰዋል ደረሰኝ ያለውን ጥለው ወጥተዋል።

➡️ የገበያ ሞሉ ላይ እቃዎችን መለየት አስቸጋሪ ስለነበር እና ሰዎቹም ተባባሪ ስላልነበሩ ለጊዜው ታሽጎ ነበር። በአሁኑ ሰዓት ሀሉም ተከፍተዋል። የቀረ ካለ በንግድ ቢሮ በኩል ፈቃድ ያልነበረው በመሆኑ በተወሰደ እርምጃ ነው።

➡️ ታሽገው የነበሩ አብዛኛው ሱቆች ተከፍተዋል። እስካሁን ያልተከፈተ ካለ ፈቃድ ስላላወጣ ነው የሚሆነው በተረፈ እቃ የሚወረሰው ኮንትሮባንድ ሲሆን ብቻ ነው።

➡️ ሁሉም ሰው ደረሰኝ ስለማይሰጥ የሚመለከተው ብቻ ነው ደረሰኝ እንዲሰጡ የሚጠበቀው መስጠት የሚጠበቅባቸው ነጋዴዎች ደረሰኝ እየሰጡ ግብይታቸውን ይቀጥሉ።

➡️ " እቃችሁ እየተወረሰ ነው፣ ሊወረስብን ነው" የሚሉ አካላት እቃቸው ምን ስለሆነ ነው የሚወረሰው ? እንደዚህ የሚሉ አካላት ኮንትሮባንድ ስለሆነ ይመስላል።

➡️ ያለደረሰኝ አትግዙ ፣የሚሸጥላችሁን ጠቀሙ እኛ ደግሞ ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈጽምን አካል እንቆጣጠራለን ብለናል የምንከታተላቸውም ለዛ ነው።

➡️ እቃ ለመውረስ የህግ መሰረት ያስፈልጋክ። እቃ የሚወረሰው የታክስ እዳ ማካካሻነት ከተያዘ ብቻ ነው።

➡️ ግብይት ላይ ያለ እቃን የታክስ ማካካሻ ብለን የምንወርስበት ምክንያት የለንም። ክፍተት ያለበትን ነጋዴ ለማወናበድ የሚሮጥ ሌላ ጥላ የሚፈልግ አካል የሚያወራው ወሬ ነው።

➡️ " ያለደረሰኝ አትሽጡ " አልን እንጂ እቃ እንወርሳለን ያለ አካል የለም። ይህም ለነጋዴዎች በደብዳቤ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
#ትኩረት🚨

" የጤና ተቋሙ ሳይፈርስ ከላይ ያሉ አካላት አስቸኳይ ድጋፍ ቢያደርጉ መልካም ነው "  - ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘው የዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በክልሉ ተፈጥሮ ከነበረው ጦርነት በፊት ለመድሃኒትና ለላብራቶሪ ግብዓቶች ይመደብለት የነበረው በጀት ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ነበር።

በሆስፒታሉ የመድኃኒት እና የላብራቶሪ መመርመሪያ ግብዓቶች እጥረት ስለማጋጠሙ በተደጋጋሚ ሲነገር ቢቆይም ችግሩን እስካሁን መቅረፍ እንዳልተቻለ ተነግሯል።

በሆስፒታሉ ላይ ላጋጠመው እጥረት ለዩኒቨርሲቲው ይመደብ የነበረው በጀት በግማሽ መቀነሱ እንደምክንያት ይነሳል።

ለሆስፒታሉ ለመድኃኒትና ለላብራቶሪ መመርመሪያ ግብዓቶች አቅርቦት በ2016 በጀት ዓመት ተመድቦለት የነበረው 18.9 ሚሊየን ብር ሲሆን ለ 2017 በጀት ዓመት የተመደበለት ደግሞ 30 ሚሊየን ብር ብቻ ነው።

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዓይደር ኮምፕረንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስተዳደር እና ልማት ዳይሬክተር ዶ/ር ኃይለስላሴ በርኸ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ሆስፒታሉ በ2016 በጀት ዓመት ከ ኢትዮጵያዊ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በብድር የወሰደው መድኃኒት ከ 60-70 ሚሊየን ብር ይደርሳል ብለዋል።

በብድር የወሰደውን የመድኃኒት ክፍያ ሆስፒታሉ መክፈል ባለመቻሉ 14.3 ሚሊየን ብር ከጤና ሚንስቴር ለመድኃኒት አቅራቢ ድርጅት እንዲከፈል ሆኗል።

ሆስፒታሉ የተወሰነ ክፍያ የከፈለ ቢሆንም ያልተከፈለ ከ 40 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ እዳ ከ 2016 ወደ 2017 በጀት ዓመት የተላለፈበት ሲሆን በዚህ ምክንያት ከዚህ በኋላ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት መድኃኒቶችን በካሽ እንጂ በብድር እንደማያገኝ ተነግሮታል።

ሆስፒታሉ ከውስጥ ገቢው እዳውን መክፈል ለምን ተሳነው ?

ዶ/ር ኃይለስላሴ እንደሚሉት በዓይደር ሆስፒታል የሚታከሙ ታካሚዎች ከ 80-90 በመቶ የነጻ ታካሚዎች ናቸው።

" ከፍለው መታከም የማይችሉ ታካሚዎች የደሃ ደሃ መሆናቸውን ከወረዳቸው ያጽፋሉ ወረዳውም ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በሚገባው ውል መሰረት ጤና ቢሮው ከእኛ ጋር ውል ያስራል ያከምናቸውን ታካሚዎችም በ3 ወር ወይም በ6 ወር ለሆስፒታሉ ይከፍላል" ብለዋል።

ስለዚህ የምናክማቸው ታካሚዎች እነርሱ በቀጥታ ባይከፍሉም ከጤና ቢሮው ክፍያው እንዲፈጸም የሚደረግ በመሆኑ ነጻ ናቸው ማለት አይደለም ብለዋል።

ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ በተጠቀሰው መንገድ ሲያክም ቆይቶ ክፍያው እንዲፈጸምለት ለጤና ቢሮው ጥያቄ ቢያቀርብም "በትግራይ የምዕራብ እና የደቡብ አካባቢዎች የሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎች በትግራይ ስር ስላልሆኑ እና በርካታ መጠለያ ጣቢያዎች በመኖራቸው እንዲሁም ታካሚዎችም ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ በመሆናቸው ከየትም አምጥቼ ገንዘብ መሰብሰብ አልቻልኩም " የሚል ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት ሆስፒታሉ ከጤና ቢሮው ሊከፈለው የሚገባ በርካታ ሚሊየን ብር ስለቀረበት መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ላይ ያለበትን የ40 ሚሊየን ብር በላይ እዳ መክፈል እንዳልቻለ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በኩልም የማይገኙ እንደ የስነ-ልቦና እና የካንሰር መድሃኒቶች ፣ ካቴተር ፣ ለመስፋት የሚያገለግሉ ስቲቾች (Stitches) እንዲሁም እንደ ማግኒዢየም ሰልፌት ያሉ መድኃኒቶችም መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በአገልግሎቱ በኩል አይገኙም የተባሉትን መድኃኒቶች ለመግዛት ወደ ሌሎች አቅራቢዎች ለግዢ ጨረታ ይወጣል ፤ ከውጭ ሲገዛ በጣም ውድ በመሆኑ ሳቢያ ሆስፒታሉ ለመድኃኒት ካለው ትንሽ በጀት ጋር ተደምሮ ለገንዘብ እጥረት እንዳጋለጠው ጠቁመዋል።

አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጫና ጋር ተደምሮ ከዚህ በፊት ለዓመት ያስገዛ የነበረ ገንዘብ ለሁለት እና ሦስት ወርም አይቆይም ብለዋል።

ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሆስፒታሉ እዳውን መክፈል እንደተሳነው ገልጸዋል።

" በካሽ ካልሆነ በብድር ይሰጥ የነበረ መድኃኒት ከዚህ በኃላ እንደሌለ ከአገልግሎቱ ተነግሮናል " ብለዋል።

በዚህም ሳቢያ በሆስፒታሉ በተለይም የስነ አዕምሮ ፣ የማደንዘዣ እና ለመስፋት የሚያገለግሉ ግብዓቶች እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ማጋጠሙን ተሰምቷል።

በሆስፒታሉ የማይገኙ መድኃኒቶችን ታካሚዎች ከውጭ በውድ ዋጋ እንዲገዙ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

እንደሆስፒታሉ መረጃ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስነ አዕምሮ መድኃኒቶች ፍላጎት እየጨመረ ነው።

ሆስፒታሉ ካለበት የበጀት እጥረት በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የባለሞያዎች ፍልሰት እንዳጋጠመው የተሰማ ሲሆን ከህክምና ት/ቤቱ ብቻ ከ300 በላይ ሐኪሞች መሰደዳቸውን ተናግረዋል።

አብዛኛዎቹ ባለሞያዎች የተሰደዱት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ነው።

ዶክተር ፥ " አብዛኛው ሃኪም የሄደው ወደ ሶማሊያ፣ ፑንትላንድ እና ሶማሊላንድ ነው ለመኖር አስቸጋሪ ቢሆኑም የሚከፈላቸው ክፍያ ጥሩ ስለሆነ ለመኖር አዳጋች ወደ ሚባሉ ቦታዎች እየተሰደዱ ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ ለህክምና ባለሞያዎች ያልተከፈለ የ17 ወር ደሞዝ እና የ22 ወር የትርፍ ሰዓት ክፍያ እስካሁን እንዲከፈል አልተደረገም።

በሆስፒታሉ ስላጋጠመው እዳ በቀጣይ ምን ታስቧል ? ለሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ " ምንም እንኳን በጽሁፍ ያቀረብነው ጥይቄ ባይኖርም ጤና ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲያደርግልን ወይም የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የእዳ ስረዛ እንዲያደርግልን ለመጠየቅ እያሰብን ነው " ብለዋል።

" ሆስፒታሉ ከሚገኝበት ውስብስብ ችግር ምክንያት የጤና ተቋሙ ሳይፈርስ ከላይ ያሉ አካላት አስቸኳይ ድጋፍ ቢያደርጉ መልካም ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

በመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በኩል የማናገኛቸው መድኃኒቶች አሉ ስለሚለው ቅሬታ እና ሆስፒታሉ ስላለበት እዳ ምን ታስቧል ? የሚለውን በሚመለከት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የመቀሌ ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ገብረማርያምን አነጋግረናል ምላሻቸው በቀጣይ ይቀርባል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
" መኪናው አስፓልት ዳር ቆሞ ቢገኝም ውስጥ የነበረው እቃ ግን ተዘርፎ ተወስዷል " - አመልካቾች

ከሰሞኑን አንድ ዝርፊያ በአዲስ አበባ ተፈጽሟል።

ከላይ በምስሉ ላይ የሚታየው ታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 - 00434 አ.አ የሆነ እቃ ጫኝ አይሱዙ መኪና ከነጫነው እቃ በተደራጁ ዘራፊዎች ተወስዶባቸው እንደነበር ባለቤቶቹ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

ከጫነው እቃ ጭምር የተዘረፈውን መኪና ያዩ ወገኖችም እንዲያፏልጓቸው ብዙ ሲጥሩ ከቆዩ በኃላ ንብረቱ ተወስዶ መኪናው ግን ሃና ማርያም አካባቢ መንገድ ዳር ቆሞ ተገኝቷል።

ዝርፊያው እንዴት ተፈጸመ ?

መኪናው ከቀናት በፊት ከኮዩ ፈጬ የንግድ እቃ ጭኖ መርካቶ ለማራገፍ መንገድ ይጀምራል።

ሳር ቤት ኪንግስ ሆቴል አከባቢ ሲደርስ ግን የወታደር ሬንጀር ልብስ የለበሱ እና የታጠቁ
ሰዎች በአባዱላ መኪና መንገድ በመዝጋት መኪናውን ያስቆሙታል።

በተጨማሪም ልክ የህግ አስከባሪ አካላት (ወታደር) እንደሆኑ በማስመሰል ሹፌሩን " መንጃ ፍቃድ አምጣ " ብለው ጠይቀው ህገወጥ እቃ እንደጫነ ጥቆማ ደርሷቸው ያስቆሙት መሆኑን እና መኪናው ለፍተሻ የሚፈለግ መሆኑን ይገልጻሉ።

ሹፌሩም የጫነው እቃ መርካቶ የሚራገፍ የንግድ እቃ መሆኑን ገልፆ እቃው የተገዛበትን ደረሰኝ በማሳየት ጭምር ለማስረዳት ይሞክራል።

ይሁንና ግን ልክ እንደ ህግ አስከባሪ / ወታደር ልብስ ለብሰውና ታጥቀው እና ተደራጅተው የመጡት ዘራፊዎች " መኪናው ፖሊስ ጣቢያ ተወስዶ መፈተሸ አለበት " በማለት ሹፌሩን እያዋከቡ እና እየደበደቡ አውርደው ወደያዙት አባዱላ መኪና ያስገቡታል።

የእነርሱ ሹፌር ደግሞ ወደ አይሱዙው ገብቶ መኪኖቹ ፊት እና ኋላ ሆነው እየተከታተሉ ይሔዳሉ፡፡

ይሁንና ግን ቡልጋሪያ አከባቢ ሲደርሱ አይሱዙው ወደ ሌላ አቅጣጫ ሲያመራ ሹፌሩን የጫነው አባዱላ ደግሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ ይዞራል።

በዚህ ሰዓት ሹፌሩ " ህግ ቦታ እየወሰድንህ ነው አላላችሁኝም ወይ ? ለምንድነው መኪናው ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚሔደው ? " የሚል ጥያቄ ሲያነሳ ውስጥ ያሉት ዘራፊዎች ሹፌሩን እራሱን እስከሚስት ድረስ በመደብደብ እና በማፈን ጭምብል አልብሰው በፍጥነት እየነዱ ይጓዛሉ።

በዚህ ሁኔታ ለረጅም ርቀት ከተጓዙ በኋላ ኃጫሉ መንገድ ወደ ጋርመንት መሔጃው ጋር ሹፌሩን ከመኪናው አውርደው ጥለውት ይሰወራሉ።

ሁኔታው ከተፈጠረ በኋላ አከባቢው ላይ የደረሱ ሰዎች ሹፌሩን አፋፍሰው ጤና ጣቢያ ያደረሱ ሲሆን ሹፌሩም አራሱን ከመሳት ከነቃ በኋላ ጉዳዩን ወንጀሉ ለተፈፀመበት አከባቢ ፖሊስ ጣቢያ አመልክቷል።

ከቀናት በኃላ በተደረገ ፍለጋ መኪናው ሃና ማርያም አስፓልት ዳር ቆሞ ሊገኝ ችሏል።

ለቲክቫህ ኢትዮጵያ መኪና ከጫነው እቃ ጭምር እንደተዘረፈባቸው የገለጹት አመልካቾች ፥ " ምንም እንኳን መኪናው ቆሞ ቢገኝም ውስጥ ተጭኖ የነበረው ከ3.4 እስከ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት እቃ ተዘርፎ ተወስዷል " ብለዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እስካሁን የተያዘ ሰው እንደሌለ ጠቁመዋል።

ሌሎች ወገኖች መሰል ነገር እንዳይፈጸምባቸው በማለት ይህንን ጉዳይ ለጥንቃቄ ይረዳ ዘንድ ማጋራታቸውን ገልጸዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
🔈 #የመምህራንድምጽ

🔵 "የሁለት ወራት ደመወዝ አልተከፈለንም። ቤተሰብ እንዴት እናስተዳድር?" - የደቡብ ወሎ ዞን መምህራን

🟢 " የሚመለከተው ኮማንድ ፓስቱን ስለሆነ በወረዳ በኩል እንዲፈቱ አነጋግረናል " - የዞኑ መምህራን ማኀበር

በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ የሚገኙ መምህራን የሁለት ወራት የደመወዝ ክፍያ ስላልተፈጸመላቸው የከፋ ችግር ላይ በመሆናቸው አማረዋል።

ክፍያው ያልተፈጸመላቸው በክልሉ ባለው የሰላም መደፍረስ ሳቢያ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ባለመገኘታቸው ' ሳታስተምሩ ደመወዝ አይከፈላችሁም ' በሚል መሆኑን አስረድተዋል።

" የሁለት ወራት ደመወዝ አልተከፈለንም። ቤተሰብ እንዴት እናስተዳድር ? " ሲሉ ጠይቀው፣ ከዚሁ ትንሽ ደመወዝ ብሶ ባለመከፈሉ ችግር ላይ በመውደቃቸው የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጧቸው በአጽንኦት ጠይቀዋል።

የቀረበው ቅሬታ እንዲቀረፍ ምን እየተሰራ እንደሆነ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ የቀረበለት የዞኑ መምህራን ማኀበር፣ " የሚመለከተው ኮማንድ ፓስቱን ስለሆነ በወረዳ በኩል እንዲፈቱ አነጋግረናል " የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

" መምሪያ ኃላፊው ጋ ተነጋግረናል። በዚያ በኩል እየገመገሙ መስራት የሚችሉና መምህራን ያልገቡባቸው ትምህርት ቤቶቸ ከሆነ የግድ የማይከፈል መሆኑን፤ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከሆነ ግን እንዲከፈል እየተደረገ እንደሆነ ነው " ብሏል።

በትምህርት ቤት ቢገኙም ተማሪ ባለመገኘቱ ብቻ ስላላስተማሩ ደመወዝ እየተከፈላቸው  ቅሬታ ለሚያቀርቡት መምህራን ምላሽ እንዲሰጥ ላቀረብንለት ጥያቄ በሰጠን ምላሽ ደግሞ፣ " ትምህርት መምሪያን አነጋግሩ " ብሏል።

የቀረበውን ቅሬታ በመግለጽ ምላሽ እንዲሰጡ ለሳምንት የጠበቅናቸው የዞኑ ትምህርት መምሪያና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ጉዳዩን በጽሞና ከሰሙ በኋላ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በተጨማሪ፣ መምህራን እያቀረቡት ያለውን የደመወዝ አለመከፈል ቅሬታ ሰምቷል? ስንል ጥያቄ ያቀረብንለት የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር (ኢመማ) ማብራሪያ ሰጥቷል።

ማኅበሩ ፦

" በአካባቢው ካለው ችግር አንጻር ፎርማል ሆኖ የመጣልን ነገር የለም። ግን በወግዲ ወረዳ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎችም እስከ ለሁለት ወራት እየተከፈለ አይደለም ከባንክም ከሌላም  ኬዝ ጋር በተያያዘ።

እንደተባለው መምህራን እየተጎዱ ነው። በይበልጥ ጉዳዩ የክልሉን መምህራን ማኅበር ይመለከታል። ፎርማል ሆኖ ወደኛ ቢመጣ ወደ ፌደራል መንግስትም ልንወስደው እንችላለን፡፡

ፎርዛትማተር መንግስት 'የክልሎቹ ማንዴት ነው' ነው የሚለን፡፡ ከዚህ ቀደም የትግራይ ክልል መምህራን መጥተው ያን ያህል ሲንገላቱ የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር ነበር ለሻይ ሲላቸው የነበረው።

አማራ ክልል አይነት የጦርነት ሁነት ላይ ስለሆነ ፎርማሊ በሕግ አግባብ የሚጠየቅ ድርጅት የለም፡፡ በዚህ ነው የተቸገርነው "
ነው ያለው።

በጸጥታው ችግር ትምህርት ቤቶች ስለተዘጉ ሳያስተምሩ ደመወዝ እንደማይፈጸምላቸው እንደተነገራቸው ነው መምህራኑ የሚገልጹት፤ ይህ አግባብ ነው ? በሚል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላቀረበው ጥያቄ የማኀበሩ ፣ " ልክ አይደለም " የሚል መልስ ሰጥቷል።

" ተማሪ እስከመጣላቸው ድረስ አላስተምርም ያሉ መምህራን ካሉ ነው እንጂ መምህራኑ ትምህርት ቤት ቁጭ ብለው ተማሪ እየጠበቁ ነገር ግን በጸጥታ ችግር ተማሪ ካልመጣላቸው ማንን ነው የሚያስተምሩት ? " በማለት ጉዳዩ ልክ ያልሆነበትን ምክንያት በመጠይቅ አስረድቷል፡፡

" ጸጥታውን ማስከበር ያለበት እኮ የመንግስት አካል ነው " ያለው ማኀበሩ፣ " የራሱን ሥራ እንዴት መምህራን ላይ ይጥላል? ትክክል የማይሆነው ይሄ ነው፡፡ መምህራን ትምህርት ቤት ላይ ከሌሉ ትክክል ነው ደመወዛቸው መክፈል አይገባም የት እንዳሉ አይታወቅምና " ብሏል።

" ነገር ግን ማኀበረሰቡ ልጆችን ትምህርት ቤት ልጆቹን አልክም ብሎ ከሆነ መምህራን ደግሞ ትምህርት ቤታቸው ላይ ሆነው እንዴት ነው የማይከፈሉት። ይሄ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን መቱት አይነት ነገር ነውና ትክክል አይደለም " ሲል አክሏል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#ሳህለወርቅ_ዘውዴ

“ አቅጣጫዬን አሳይቻለሁ፤ በዛ መሠረት ለመስራት ሞክሬአለሁ ” - የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዜዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

በበጎ ፈቃድ የተሰባሰቡ ሴቶችና የሴት መሪ ድርጅቶች በጋራ በመሆን በቅርቡ የሥራ ዘመናቸውን ላጠናቀቁት ለቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሸራተን አዲስ ሆቴል ዛሬ የምስጋና ፕሮግራም አዘጋጅተው ነበር።

በዚሁ መርሀ ግብር አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ፣ የሴቶች ማኀበራት መሪዎችና በሌሎች የሥራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ ሴቶች ተገኝተዋል።

ፕሮግራሙ ከተዘጋጀበት ዓላማ አኳያም ለቀድሞ ፕሬዜዳንቷ “ በጣም ውድ ” እና “ ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ” የተባለለት የሀገር ቅርስ ጭምር የተቀረጸበት የስዕል ስጦታ የተበረከተላቸው ሲሆን፣ “ ከሚገባው ቦታ አስቀምጠዋለሁ ” በማለት ስጦታውን ላበረከቱላቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በመርሀ ግብሩ ባደረጉት ንግግር ደግሞ፣ “ የዛሬ 6 ዓመት ገደማ ያደረኩት ንግግር የ18 ደቂቃ ነበር። ጥቂት ጊዜ ነው የነበረኝ ለመዘጋጀት። የደረሰብኝም አልገባኝም ነበር ” ሲሉ አስተውሰዋል የቀድሞ ፕሬዜዳንቷ።

“ ሴቶች የሚለውን ቃል 29 ጊዜ፣ ሰላም የሚውን ቃል 30 ጊዜ ተናግሬ ነበር ” ያሉት ሳህለወርቅ፣ “ ለራሴ አልዋሽም፣ ለሌላም አልዋሽም። አቅጣጫዬን አሳይቻለሁ፣ በዛ መሠረት ለመስራት ሞክሬአለሁ ” ሲሉም አክለዋል።

“ ተያይዘን መስራት አለብን። ጡረታ የሚባለውን ነገር አሁን ነው የጀመርኩት ግን እረፍት የለም። ጡረታም ተወጥቶ እንደማይታረፍ የቀደሙኝ እያሳዩኝ ነው። ላደረጋችሁልኝ በጣም ነው የማመሰግነው ” ነው ያሉት።

የቀድሞዋ ፕሬዜዳንት ከዚህ ቀደም፣ “ ‘የሰው ልጅ ሆዱ ሲከፋው ጊዜም እንደ ሰው ሲገፋው፣ መሄጃ መውጫ ሲጠፋው ዝምታ ብቻ ነው ተስፋው’ ይላል ማህሙድ ‘ዝምታ ነው መልሴ’ን ሲያዜም ” ብለው፣ “ አንድ ዓመት ሞከርኩ ” የሚል ፅሑፍ በX (ቲዊተር) ገጻቸው አጋርተው ነበር።

በወቅቱም ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ይህንን ምስጢር አዘል የሆነ ፅሑፋቸውን በተመለከተ ግን ዛሬም የሰጡት ማብራሪያ የለም።

የቀድሞዋ ፕሬዜዳንት ሳልለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ ሴት የኢትዮጵያ ፕሬዜዳንት ሆነው ለ6 ዓመታት 4ኛ የኢትዮጵያ ፕሬዜዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው፣ የሥልጣን ዘመናቸው በመጠናቀቁ ኃላፊነታቸውን ለፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ማስረከባቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
#OFC

“ አሁንም ቢሆን ሀገራዊ ምክክሩ በሚሄድበት አቅጣጫ እርካታ የለንም ” - ኦፌኮ

ከዚህ ቀደም በምክክሩ እንደማይሳተው ገልጾ የነበረው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) አሁንም እየተሳተፈ እንዳልሆነ፣ ኮሚሽኑ በሚሄድበት አቅጣጫ እርካታ እንደሌለው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጿል።

ፓርቲው ከዚህ ቀደም በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፍ ቢጋበዝም በምክክሩ እንዳልተገኘ አስታውሷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በበኩሉ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራውን መቀጠሉን እየገለጸ ነው፤ አሁንስ ፓርቲው ከኮሚሽኑ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት አላሰበም ? ከምክክሩ የወጣበት ምክንያትስ ምንድን ነው ? ምላሽስ አላገኘም ? ሲል ጥያቄ አቅቧል።

ፓርቲው ምን ምላሽ ሰጠ ?

“ በእርግጥ ከዚህ ቀደምም ጥሪ ተደርጎልን ነበር። ችግሩ ከዝግጅት ጀምሮ ያለው እንቅስቀሴ አሳታፊ አልነበረም።

ሲጀመር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ 'ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ይሆናል’ ተባለ፣ ከዚያ ተመልሶ ‘ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሆናል’ ተባለ። 

ይሄ ልዩነቱም አልታየንም። ምክንያቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በገዢው ፓርቲ የተሞላ ስለሆነ ገልተኛነቱ ያን ያክል አስተማማኝ እንዳልሆነ ነው የምንረዳው። 

ምክንያቱም የሌሎች ተሳትፎ ወይ የለም ወይ በጣም አናሳ ነው፤ ኢንሲግኒፊካንት የሚባል ደረጃ ማለት ነው።

የኛ ሀሳብ ፓለቲካዊ ውይይቶች በፓለቲካ ኃይሎች መካከል መካሄድ ይኖርባቸዋል፣ ሁሉንም ኃይሎች አካታች መሆን አለበት የሚል ነው።

እኛ ሕዝብ ማወያየትን አንጠላም ወይም አናናንቅም ነገር ግን ከሕዝብ ጋር ከመድረሱ በፊት ወይም እየደረሰም እያለ ሌሎች የፓለቲካ ኃይሎች ሊነጋገሩበትና ሊፈቷቸው  የሚገቡ ነገሮች አሉ። 

ለምሳሌ በተለያዩ አካባቢዎች የኛ ፅሕፈት ቤቶች ተዘግተው ባሉበት፣ አባሎቻችንን ሰብስበን ማነጋገር ባልቻልንበት ሁኔታ፣ ለሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳ መፍጠር የሚባለው ነገር ውስጥ መሳተፍ አስፈላጊ አይደለም።

እንደገናም ጦርነት እየተካሄደ ሀገራዊ ምክክር ብሎ ነገር ምንድን ነው? ይሄ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነገር ነው።

ይሄን እርስ በእርስ የሚጋጨውን ነገር የሆነ ጋፕ ስጡት፣ ለመነጋገር፣ ለመወያየት እድል ይሰጠው አገር እየተጠበቀ አገር ቢነጋገርበት ጥሩ ይሆናል በሚል ጥያቄ አቅርበን ነበር።

ይሄን የኛን ሀሳብና ጥያቄ ምንም ከዚህ ግባ አላሉትም። ምናልበት የተሻለ ነገር ቢያመጡ እኛም አጨብጭበን እንቀበላቸዋለንና እንዲሄዱ ነው የተውናቸው።

ኦፌኮ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ፓርቲዎች አሉ እንደዚህ ያደረጉ። ጊዜና መነጋገር የሚፈልጉ፣ አንድ ወገንን ብቻ ተጠያቂ ከማድረግ እንድንቆጠብ የሚያደርጉ ነገሮች አሉ።

ስለዚህ ነገሮቹ መፍትሄ ካላገኙና የተወሰነ አቅጣጫ ካልተቀመጠላቸው እንዲያው ለመሳተፍ ተብሎ የምንሳተፍበት ምክንያት አይኖርም። 

አሁንም ቢሆን ሀገራዊ ምክክሩ በሚሄድበት አቅጣጫ እርካታ የለንም። እርካታ ቢኖረንና ብንሳተፍበት ጥሩ ነበር ”
ብሏል።

ለቀረበበት ትችት ምላሽ እንዲሰጥ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ለጊዜው በተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ መሆኑን በመግለጹ ምላሹን እንደሰጠ የሚቀርብ ይሆናል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia