TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
56.9K photos
1.42K videos
205 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#Amhara #Merawi

በአማራ ክልል ፤ በየጊዜው በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በመንግሥት የፀጥታ ኃይል መከላከያ እና በ " ፋኖ " ታጣቂ ኃይሎች መካከል ግጭቶች ይደረጋሉ።

በእነዚህ ግጭቶችም በሁለቱም በኩል ከሚሞተው የግጭቱ ተካፋይ ባለፈ ንፁሃን ሰዎች ሰለባ እየሆኑ እንዳለ በተደጋጋሚ ተገልጿል።

ምንም እንኳን #መንግሥት ፤ " ከእውነታው ያፈነገጠ እና ሚዛናዊነት የጎደለው " ብሎ ቢያጣጥለውም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮኒሽን  (#ኢሰመኮ) ይፋ አድርጎት በነበረው ሪፖርት በክልሉ ፦

- የአንድ ዓመት ከሰባት ወር #ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች በድሮን መገደላቸው / የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው።

- በከባድ መሣሪያ ድብደባ ምክንያት #ሲቪል_ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱ።

- በመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት #ከሕግ_ውጪ የሆኑ ግድያዎች እንደሚፈፀሙ።

- ከዚህ ቀደም ግጭቶች በተካሄደባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ ፦
" ፋኖን ትደግፋላችሁ "
" ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ "
" መሣሪያ አምጡ "

" የተኩስ ድምጽ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ " በሚልና ይህንን በመሰሉ ምክንያቶች ከሕግ ውጭ የሆኑ በርካታ #ግድያዎች መፈጸማቸውን በይፋ ማሳወቁ አይዘነጋም።

ከሰሞኑን ዳግሞ በሰሜን ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል፣ ሰኞ ጥር 20/2016 ዓ/ም የነበረውን ውጊያ ተከትሎ በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል።

አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ገለጻ ፤ በሰሞኑ ተኩስ እሳቸው የሚያውቋቸው ብቻ 15 ወጣቶች መገደላቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ግን ፤ " የሟቾቹን ቁጥር በዚህ ወቅት ለመግለጽ መሞከር የጥቃቱን አድማስ ያሳንዋል እንጂ አይገለጸውም" ብለዋል።

እኚሁ ነዋሪ በግፍ የተገደሉ ንጹሐን ሰዎችን ቁጥር በሂደት እንጂ አሁን ሁሉንም ማወቅ እንደማይቻል ገልጸው ፤ " የዚህ ህዝብ ጭፋጨፋ ግን መቼ ነው የሚያበቃው? " ሲሉ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ለቢቢሲ አማርኛው አገልግሎት ቃላቸውን የሰጡ ነዋሪዎች፣ የሆስፒታል ሰዎችና የአይን እማኞች በከተማው ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ነዋሪዎች ግድያው የተፈጸመው በቤታቸው እና በመንገድ ላይ በተገኙ ሰላማዊ ሰዎች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

አንድ የህክምና ባለሙያ 13ት ሰዎች ከአስፓልት ዳር መገደላቸውን እንደሚያውቁ ተናግረው በአጠቃላይ በከተማዋ በዚያ ዕለት 85 ሰዎች መገደላቸውን አመልክተዋል።

አንድ የአይን እማኝ በርካታ ቀብሮች ላይ መገኘታቸውን ጠቅሰው የሟቾችን ቁጥር " ከ100 በላይ ነው " ብለዋል። ጥቃቱ በተፈጸመ ማግስት ጠዋት ላይ 48 አስከሬን መቆጠራቸውን ተናግረው ፤ " ከማርዘነብ ሆቴል እስከ በረድ ወንዝ ድረስ ግራ እና ቀኝ አስከሬን ብቻ ነበር " ብለዋል።

የሟቾችን ቁጥር 115 ገደማ የሚያደርሱ አንድ የዐይን እማኝ ደግሞ መከላከያ ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ ስታዲየም እና ጤና ጣቢያ በተባሉ ሰፈሮች " ከ6 ዓመት ህጻን እስከ 75 ዓመት አዛውንት " ድረስ ግድያ ተፈጽሟል ብለዋል።

የሆስፒታል ሠራተኛ የሆኑት የዐይን እማኝ በከተማዋ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የ6 ወር ነፍሰ ጡርን ጨምሮ 25 ሰዎች ቆስለው መጥተው " የተረፈ የለም " ሲሉ ገልጸዋል።

" 24ቱ ሆስፒታል የመጡት ሞተው ነው። አንዲት የ6 ወር ነፍሰ ጡር ሴት ከነ ነፍሷ መጥታ ሆስፒታል እንደደረሰች አርፋለች። አጠቃላይ 25 ነበር የመጡት " ብለዋል።

ቃላቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ፤ #በመርዓዊ_አስተዳደር ህንጻ ውስጥ በነበሩት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የፋኖ ታጣቂዎች ሰኞ ጠዋት ድንገተኛ ጥቃት ፈፀመው እንደነበርና ለዚህ ምላሽ " የበቀል እርምጃ " በመወሰዱ ነው ለበርካታ ሰዎች ግድያ ምክንያት የሆነው ብለዋል።

ስለ ግድያው ምን ምላሽ እንዳለቸው ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ ያቀረበላቸው የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ  መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር)፣ " ስብሰባ ላይ ነኝ መልሸ ልደውል " ብለዋል።

መንገሻ (ዶ/ር) ይህን ያሉት እንዲያብራሩ የተፈለገውን ጥያቄ በዝርዝር ከሰሙ በኋላ ሲሆን፣ በድጋሚም ስልክ ሲደወል ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም።

እንዲሁም፣ " እባክዎ ስልክዎን ያንሱና በኮሚዩኒኬሽን በኩል ያለውን የመርዓዊ ጉዳይ ማብራሪያ በመስጠት ኃላፊነትዎን ይወጡ " የሚል የፅሑፍ መልዕክት (SMS) ቢላክላቸውም ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

በተጨማሪ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፦
* የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ምክትል፣
* የክልሉና የሰሜን ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት፣
* የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ስለጉዳዩ ምን ምላሽ እንዳለቸው ለማወቅ እና ሃሳባቸውን ለማካተት ስልክ ቢደውልም ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ኮሚሽን ( #ኢሰመኮ ) ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ፤ " መረጃው ደርሶናል (የመርዓዊ ጉዳይ) ። እያረጋገጥን ነው " ብለዋል።

አክለው ፣ "የጸጥታ ጉዳይ ስለሆነ ትንሽ መንቀሳቀስና መረጃ መሰብሰብ አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል ሊዘገይ ይችላል። ግን እያጣራን ነው" ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል።

@tikvahethiopia