TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
205 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
የአምቦ ከተማው እርቅ‼️

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከዛሬ ጀምሮ #የተኩስ_ማቆም ውሳኔ አሳልፈዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኦነግ ሰራዊት በጥቂት ቀናት ውስጥ ካለበት ጫካ ወጥቶ ወደ ካምፕ እንዲገባም ውሳኔ አሳልፈዋል። መንግስት እና ኦነግ ውሳኔዎችን ያሳለፉት የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት በዛሬው እለት በአምቦ ከተማ ባዘጋጀው የእርቅ ስነ ስርአት ላይ ነው።

በዛሬው እለት በተዘጋጀው የእርቅ ስነ ስርዓት ላይ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲቄዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ወጣቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና የአምቦ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል። በመድረኩ ላይም መንግስት እና ኦነግ በኦሮሞ ባህል መሰረት ኮርማ በሬ በማረድ በይፋ የእርቅ ስነ ስርአት ፈጽመዋል።

ሁለቱም አካላት ከዚህ በኋላ ወደ ደም #መፋሰስ እንደማይገቡ እንዲሁም ያለፈውን ነገር በመተው ስለወደፊቱ ብቻ በጋራ ለመስራት በእርቅ ስነ ስርዓቱ ቃል ገብተዋል። በመድረኩ ላይ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከስምምነት የደረሱባቸው ዝርዝር የውሳኔ ነጥቦች ይፋ ተደርጓል።

ዝርዝር ስምምነቱንም የቴክኒክ ኮሚቴውን በመወከል የፖለቲካ ተንታኝ እና አክቲቪስት አቶ ጀዋር መሃመድ ያቀረቡ ሲሆን፥ ሁለቱንም አካላት በማነጋገር በዝርዝር ውሳኔው ላይ መደረሱን አስታውቀዋል። በዚሀም መሰረት ከዛሬ ጀምሮ በመንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር መካከል ጦርነት መቆሙን አስታውቀዋል።

ወደ ግጭት የሚያስገቡ ትንኮሳዎችን ሙሉ በሙሉ መከልከሉን እንዲሁም አንዱ በሌላው ላይ ከዚህ በኋላ መግለጫ ማውጣት ሙሉ በሙሉ መከልከሉንም ገልፀዋል። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሰራዊት ካለበት ቦታ በሙሉ ትጥቅ ፈትቶ ወደ ካምፕ እንዲገባ መወሱን እና ይህም ከበቂ ጥበቃ ጋር በክብር አቀባበል ወደ ካምፕ እንዲገቡ እንዲደረግ መወሰኑንም ገልፀዋል።

ሰራዊቱን ወደ ካምፕ የማስገባት ስራም በ20 ቀን ውስጥ መጠናቀቅ እንዳለበት ተወስኗል ያሉት አቶ ጃዋር፥ ከእዚህም ውስጥ 10 ቀናት ዝግጅት የሚደረግበት፤ ቀሪው 10 ቀናት ደግሞ ሰራዊቱ ወደ ካምፕ የሚገባበት ነው ብለዋል። ወደ ካምፕ የማስገባት ሂደቱም በሶስት ደረጃዎች ተከፋፍሎ ይካሄዳል ያሉ ሲሆን፥ በዚህም የመጀመሪያም ወደ ወረዳ ከተሞች እንዲሰባሰቡ፣ በመቀጠል ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ እንዲገቡ ማድረግ በመጨረሻም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት አቀባበል ማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህ ወቅት ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑን እና ይህን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም አካል ላይ መንግሰት ህግን የማስከበር ስራ እንዲሰራ ተፈቅዶለታል ብለዋል። የኦነግ ሰራዊት ካምፕ ከገባ በኋላም አጠቃላይ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጎ የመንግስት የፀጥታ አካላት መቀላቀል ለሚፈልጉ እንደሚያሟሉት መስፈርት እንዲቀላቀሉ መወሰኑንም አስታውቀዋል።

ከዚህ ውጭ ያሉት ደግሞ እንደየፍላጎታቸው በፈለጉት ዘርፍ ስልጠና ወስደው እንዲሰማሩ ድጋፍ እንደሚደረግም አስታውቀዋል። ወደ ካምፕ የገባው ሰራዊትን አያያዝም የቴክኒክ ኮሚቴው በየጊዜው እየሄደ የሚጎበኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሰራዊት አባላት እስካሁን ላጠፉት ጥፋት ይቀርታ መደረጉንም የቴክኒክ ኮሚቴው ተወካይ አቶ ጀዋር አስታውቀዋል። ኤፍ ቢ ሲ እንደዘገበው ከላይ የተዘረዘሩትን ስምምነቶች ጥሶ የተገኘ ማንኛውም አካል ላጠፋው ጥፋት ተጠያቂ እንደሚደረግም ነው የገለፁት።

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ያዘጋጀው የእርቀ ሰላም መድረክ ባሳለፍነው ማክሰኞ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል ማዕከል መካሄዱ ይታወሳል። በመድረኩ ላይም የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በመካከላቸው የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል።

እንዲሁም የኦነግን የታጠቀ ሰራዊት ትጥቅ ለማስፈታት እና ሰራዊቱን ወደ ካምፕ ለማስገባት እንዲሁም ሌሎች ስምምነት ላይ የተደረሱ ጉዳዮችን ለማስፈፀም 71 አባላት ያለው የቴክኒክ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፥ የቴክኒክ ኮሚቴውም ከምሁራን 11፣ ከአባ ገዳዎች 54፣ ከኦዲፒ 3 እንዲሁም ከኦነግ 3 አባላት ያለው ነው።

ምንጭ፦ ኢ.ፕ.ድ
@tsegabwolde @tikvahethiopia