TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.4K photos
1.47K videos
209 files
4.03K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ🔝

በተማሪዎች መካከል ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በሚያነሳሱ አካላት ላይ መንግስት አስፈላጊውን #እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠየቁ።

ተማሪዎች የተሳሳተ መረጃን ሳያረጋግጡ ለሌሎች ከማስተላለፍ ተግባር መቆጠብ እንደሚገባቸውም የሐይማኖት አባቶች አስገንዝበዋል።

በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል ሰሞኑን በተፈጠረው አለመግባባት ዙሪያ ከተማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር  ትናንት በዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ውይይት ተካሄዷል፡፡

በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል የ2ኛ ዓመት የማኔጅመንት ተማሪ ሐና ይመር እንደገለፀችው በተቋሙ ሁከትና ግርግር የሚፈጥሩ አካላት የማንኛውንም ብሔር እይወክሉም፡፡

”የተከሰተው ችግርም የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት ያሰቡ ሐይሎች ተግባር እንጂ የተማሪው ፍላጎት ባለመሆኑ ድርጊቱን እናወግዛለን” ብላለች።

በግቢው ጸብ ሲፈጠር ወደ ቡድንና #ብሔር የመቀየሩ ነገር እየጎለበተ ስለሚገኝ ተማሪው ከዚህ ዓይነቱ ተግባር #ሊቆጠብ እንደሚገባም ጠቁማለች፡፡

ተቋሙም በትምህርታቸው ተገቢውን ውጤት ሳያገኙ ተሰናብተው እያለ ተመዝግበው የሚገኙ ተማሪዎችና  #በጥበቃ ስራ ላይ አድሏዊ አሰራር የሚፈጽሙ የጸጥታ ሐይሎችን ተግባር መገምገም እንደሚገባው ተናግራለች።

”ወንጀለኛ ተማሪ ብሔርን #አይወክልም፤ ጥፋት የፈጸሙ የየትኛውም ብሔር ተማሪዎች ለህግ መቅረብ አለባቸው” ያለው ደግሞ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪ ፉዓድ መሀመድ  ነው፡፡

ተማሪዎችም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ለማደፍረስ የሚጥሩ አካላትን ተግባር ማውገዝና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራን ማጠናከር እንደሚገባቸው አሳስቧል፡፡

የ3ኛ ዓመት የህግ ተማሪ ሙፍቲ መንዛ እንደተናገረው ተግባሩ በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የታቀደ ሴራ በመሆኑ ተማሪው ተግባሩን ማውገዝ ይገባዋል፡፡

”ዩኒቨርሲቲውም አመራሩ፣ አገልግሎት ሰጪውና ሌሎች አካላት በተማሪዎች መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑ አሰራሮችን ሊገመግም ይገባል” ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሐይማኖት አባት መላዓከ ሰላም ማንደፍሮ በበኩላቸው “ተማሪው የሀይማኖት አባትና የአገር ሽማግሌዎች የሚያስተላልፉትን መልዕክት በተግባር ማዋል ይገባል፤ በተለይ ደግሞ  ተማሪዎች የተሳሳተ መረጃን ሳያረጋግጡ ለሌሎች ከማስተላለፍ መቆጠብ አለባቸው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

”በተማሪዎች መካከል ልዩነትን የሚፈጥሩ አካላት ተግባር የሐይማኖት አባቶች ያወግዛሉ” ያሉት ደግሞ ሼህ አብዱለጢፍ መታን ናቸው፡፡

ተማሪዎችም ቀያቸውን ለቀው ለመጡለት የመማር ማስተማር ዓላማ ቅድሚያ ሰጥተው እኩይ ተግባራትን በጋራ መዋጋት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ  የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳድሩ የክልልና የፌዴራል ግንኙነት አማካሪ አቶ #ባዘዘው_ጫኔ እና የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ በተቋሙ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ማዘናቸውን ገልፀዋል፡፡

ድርጊቱ እንዳይባባስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ የግቢው ማህበረሰብ፣ የጸጥታ አካላትና ተማሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ተግባሩ የተማሪዎች አለመሆኑን በመረዳት ሁሉም የተቋሙ ተማሪ አንድነትን በማጠናከርና አኩሪ እሴቶችን በማጎልበት እኩይ ተግባሮች መታገልና የፍቅር መቻቻልና የይቅርታን ባህልን ማዳበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተወካይ ፕሬዝዳንት ዶክተር #ጀማል_ዩስፍ ችግሩ የተፈጠረው በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ የማይፈልጉ አካላት በተማሪዎች መካከል ልዩነት በመፍጠር የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ያቀዱት ሴራ መሆኑን ገልፀዋል።

ተማሪዎችም በአመራሩም ሆነ በጸጥታ አስከባሪ ሐይሎች ላይ ያነሷቸው ችግሮችን ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የጥፋቱ አካል የሆኑ ተማሪዎች በህግ እንደሚጠየቁም ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የተቋሙ፣ የፌዴራልና የክልል ተወካይዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌሎች፣ የጸጥታ አካላትና ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን በእለቱም እርስ በርስ ተጋጭተዋል የተባሉት ተማሪዎች #እርቅ ፈጽመዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ህዳር 11 ቀን 2011 ዓ ም ከምሽቱ 1 ሰዓት በተከሰተ አለመግባባት በአምስት ተማሪዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል።

ምንጭ፦ ኢዜአ
@tsegabwolde @tikvahethiopia