TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.7K photos
1.44K videos
207 files
3.97K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ኑሮውድነት

በኢትዮጵያ ቋሚ ወርሃዊ ደመወዝ ያላቸውና ዝቅተኛ ተከፋይ ነዋሪዎች በየጊዜው የሚጨምረው የዋጋ ንረትን መቋቋም እየከበዳቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ አባባይ ዘመነ በአዲስ አበባ በአንድ የመንግሥት መ/ቤት ተቀጥረው ይሰራሉ።

ከጊዜ ወደጊዜ የኑሮው ጫና እየጨመአ ነው የሚሉት አቶ አባባይ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ በመንግሥት ሰራተኛ ደመወዝ ቤት ተከራይቶ፣ ምግብ ገዝቶ፣ የትራንስፖርት ከፍሎ ለመኖር ከአቅም በላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጫናው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ እንዳለው ሁሉ እኛም ላይ አለ የሚሉት አቶ አባባይ ፤ መንግሥትም ይህንን ያውቀዋል ብለዋል።

የሁለት ሴት ልጆች እናቷ አብዮት ሃብቴ ደግሞ የ1800 ብር ደመወዝተኛ እንደሆኑ ገልጸው አሁን ባለው ሁኔታ ኑሮውን መቋቋም ፍፁም እንደተሳናቸው ገልጸዋል።

የመንግሥት ምገባ ባይኖር (ቁርስ እና ምሳ) ደግሞ የከፋ ችግር እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ባለኝ ደመወዝ ወር መድረስ አልችልም ያሉት ወ/ሮ አብዮት " አንድ ኪሎ ከጥቁሩ ዝቅ ያለው ጤፍ 120 ብር ነው የምንገዛው በጣም ውድ ነው ፤ እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ያብርድልን እንጂ ኑሮ በጣም ከባድ ነው " ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ረ/ፕሮፌሰር ዶ/ር ሰውአለ አባተ ስለ ጉዳዩ ምን ይላሉ ?

- የብር የመግዛት አቅም በየጊዜው መዳከም ቋሚ ደመወዝተኞች በኑሮ ውድነቱ እንዲጎዱ አድርጓል።

- ደመወዛቸው ቋሚ ነው፤ ገንዘቡ ደግሞ የመግዛት አቅሙ ከዋጋ ንረት ጋር በተገናኘ እጅግ በጣም አዘቅዝቋል። የዛሬ ዓመት 100 ብር ይገዛ የነበረው የፍጆታ እቃ ዛሬ ምን ያህል ይገዛል ? ተብሎ ሲታሰብ የመግዛት አቅሙ ቀንሷል።

- ገቢያቸው ቋሚ ከሆነና ካልጨመረ የዋጋ ንረቱ በጨመረ ቁጥር የሚጠቀሙት የፍጆት መጠን እየቀነሰ ይመጣል። ቁርስ፣ ምሳና እራት ይበላ የነበረ ሰው ዛሬ ምናልባት ቁርስና እራት ብቻ ሊበላ ይችላል። እንጀራ ይበላ ከነበረ ዳቦ ብቻ ይበላ ይሆናል።

- በአጠቃላይ ቋሚ ደሞዝተኛ የሆኑ የመንግሥት ሰራተኞች እጅግ እየተጎዱ ናቸው። በቋሚ ገቢ ኑሮን መምራት ከባድ እየሆነ መጥቷል።

- የኑሮ ውድነት ጫናውን ለማቃለል የሚያስችል የደመወዝ ጭማሪ ቢደረግ ጥሩ ነው።

- መንግሥት 'ደመወዝ የማልጨምረው ዋጋ ንረትን ያባብሳል' በሚል ነው ግን የዋጋ ንረቱ እስካለ ድረስ ቋሚ ገቢ ያለው ሰራተኛ በአግባቡ የዋጋ ንረቱን ሊሸከምለት የሚችል የገንዘብ መጠን በደመወዝ ጭማሪ መልክ ማግኘት አለበት።

- አንዱ ዋጋን የሚያንረው መንግሥት በመንግሥታዊ ሚዲያዎች የሚያደርገው የፕሮፖጋንዳ ስራ ነው፤ 'ደመወዝ ተጨመረ' የሚል ዜና በተደጋጋሚ ሲሰራ ገበያው ይረበሻል። የደመወዝ ጭማሪ ሲደረግ በውስጥ የመንግሥት አሰራር ቢሆንና በሚዲያ ባይጮህ ተፅእኖው ያን ያህል ላይሆን ይችላል።

- በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የነዳጅ እጥረት፣ የአቅርቦት እጥረት የፍላጎት መጨመር የሚያመጣቸው የዋጋ ንረቶች እንደተጠበቁ ሆነው ይሄን ሊያሟላና የማህበረሰቡን ኑሮ ሊደጉም በሚችል መንገድ የደመወዝ ጭማሪ ቢደረግ ጥሩ ነው።

የመንግሥት ሰራተኛው አቶ አባባይ ግን ከደመወዝ ጭማሪው ይልቅ መንግስት ውድነቱን ለመቆጣጠር ቢሰራ መልካም ነው ይላሉ። ዋጋ ሲጨምር ሃይ ባይ ሊኖር ይገባል  ብለዋል። ተቆጣጣሪ ከሌለ ደመወዝ ቢጨመር ያለው ዋጋ ከዚህ ሊጨምር ይችላል ሲሉ ገልጸዋል።

በኑሮ ውድነትና ደመወዝ ጉዳይ የሰቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ስመኝ ውቤ፤ ጉዳዩ ሁሉንም እንደሚመለከት ገልጸው የተለየ ምላሽ እንደማይሰጡ ተናገረዋል።

ከዚህ ቀደም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ስለ ደመወዝ ጭማሪ በተመለከት ወደፊት በሂደት የሚታይ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል። #VOAAmH

@tikvahethiopia
" ህዝቡ በጣም ተቸግሮ ነው ያለ ዛሬ ፣ ሰው ውሎ የማይገባበት ፤ ያሰበበት ደርሶ የማይመለስበት ነው " - ወንድማቸው የተገደለባቸው ነዋሪ

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳና አካባቢው ተባብሷል በተባለ የታጣቂ ኃይሎች እገታና ግድያ ነዋሪዎች ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸውን ለቪኦኤ ሬድዮ በሰጡት ቃል አመልክተዋል።

አቶ አወቀ ሰጠኝ የተቡ የህዝብ ማመላለሽ ሚኒባስ አሽከርካሪ የሆነው ወንድማቸው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሰኔ 26 በስራ ላይ እያለ በታጣቂዎች ጥቃት መገደሉን አመልክተዋል።

በዕለቱ 18 ሰዎች አሳፍሮ ከጎንደር ተነስቶ መተማ እየተጓዘ ነበር።

' መቃ ' በተባለው ቦታ ላይ ነው ታጣቂዎች ጥይት ተኩሰው እሱን ጨምሮ 3 ሰዎች ሲገደሉ 14 ሰዎች ታግተው ወደ ጫካ ተወስደዋል።

ረዳቱ ሩጦ ማምለጡን አቶ አወቀ አስረድተዋል።

ሌላ ከኋላ የመጣ አንድ መኪናም ሰው ባይገደልም አስወርደው እንደሄዱ ጠቁመዋል።

" ሁል ጊዜ ግድያ፣ ሁል ጊዜ እገታ፣ ሞት በቃ በጣም የሚያሳዝን ነው ፤ ገላጋይ የሌለበት ሀገር ሆነናል " ሲሉ በሀዘም ስሜት ሆነው ተናግረዋል።

" ህዝቡ ተቸግሮ ነው ያለ ዛሬ ሰው ውሎ የማይገባበት ፤ ያሰበበት ደርሶ የማይመለስበት ፣ የሰው ህይወት የሚጨፈጨፍበት ሰዓትና ጊዜ ላይ ነው ያለን። ምንም የሚያድነን አላገኘንም፣ መንግስትም ሊያድነን አልቻለም " ብለዋል።

መተማ አጠቃላይ ሆስፒታል አስክሬን ክፍል ውስጥ ሰራተኛ የሆኑት  አቅልለው ገነቱ፥ ባለፈው ሳምንት በታጣቂዎች ተወስደው ከነበሩት መካከል እንደሆነ የተጠቆመ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ ቤተሰቡ ባለመቅረቡ ቀብሩ በማዘጋጃ ቤት መፈጸሙን ተናግረዋል።

አንድ ስሜ አይገለጽብኝ ያሉ የመተማ ወረዳ ነዋሪ ፥ በአካባቢው ግድያ እና እገታ ተባብሶ በመቀጠሉ ስራ ውሎ ወደ ቤት መግባት ፈታኝ እንደሆነ ገልጿል።

" እገታ ብቻ መበራከቱ ሳይሆን ሰዎችም ይገደላሉ " ያለው ይኸው ነዋሪ " የታገተ ሰው ብር የጠየቃል መክፈል የማይል አይመለስም " ሲል ተናግረዋል።

ከሰሞኑም ከመተማ ሆስፒታል አንድ አምፑላንስ ከነሹፌሩ መታገቱን ገልጿል። ለማስለቀቂያ 300 ሺህ መጠየቁን ተከትሎ በየመስሪያ ቤቱ እየተለመነ ነው ብሏል።

እገታ በመስፋፋቱ ነዋሪው፣ ሰራተኛው መንቀሳቀስ እንደቸገረው ጠቁሟል።

" በቃ ከቤት መስሪያ ቤት ከዛ ቤት እንጂ ከቤት መውጣት ከባድ ነው " ብሏል።

አንድ ከጎንደር መተማ የሚሰራ ሹፌር ደግሞ ፤ " ማንኛውም ሰው ወጥቶ ለመግባት ፣ ተንቀሳቅሶ ለመስራት ለመነገድም ሌላም የቀን ተቀን ስራ ለማከናወን በጣም ተቸግሯል። አስፈሪ ሁኔታ ነው ያለው። መንገዱ በጣም አስጊ ነው " ሲል ለሬድዮ ጣቢያው ተናግሯል።

#AmharaRegion
#VOAAmh.
#Metema

@tikvahethiopia