TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
205 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
#Update " ድርጅቱ ጉባኤውን እንዳያካሂድ እንቅፋት የሚሆን ከድርጅቱ የተፈለፈለ ከፍተኛ አመራር አለ " - ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችን ለሁለት የከፈለውና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድም እውቅና የተነፈገው የህወሓት 14ኛ ጉባኤ መክፈቻ ዛሬ ተደርጓል። የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በመክፈቻው ባሰሙት ንግግር ምን አሉ ? ሊቀመንበሩ " ድርጅቱ ህጋዊ…
#TPLF

' ህወሓት ' ውስጥ እየሆነ ያለው ምንድነው ?

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከትግራዩ ጦርነት በፊት እንደ ህጋዊ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ስር ተመዝግቦ ይንቀሳቀስ ነበር።

ነገር ግን  ቦርዱ ፓርቲው " ኃይልን መሰረተ ያደረገ የአመጽ ተግባር ላይ ተሰማርቷል " በሚል ሰርዞታል።

የተወካዮች ምክር ቤትም ፓርቲውን " ሽብርተኛ ድርጅት " ሲልም ፈርጆት ነበር።

ደም አፋሳሹና አስከፊው ጦርነት እንዲያበቃ ፕሪቶሪያ ላይ ስምምነት ሲፈረም አንዱ ፈራሚ ይኸው ህወሓት ነበር።

በስምምነቱ ላይ ፓርቲው የተለጠፈበት የሽብርተኝነት ፍረጃ እንደሚፋቅ በግልጽ ሰፍሯል።

በዚህ መሰረት ከወራት በፊት ድርጅቱ ከሽብርተኛነት ተሰርዟል።

ነገር ግን የምዝገባው ጉዳይ ሌላ ነው።

ክፍፍሉ እና ' የቀደመ ህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ' ጥያቄ ምንድነው ?

ህወሓት የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኃላ በውስጥ የኃይል ሽኩቻ ላይ ነበር።

አመራሮቹም ቀስ በቀሰ በሂደት የለየለት መከፋፈል ውስጥ ገብተዋል።

ምንም እንኳን በይፋ ባይወጣም ግልጽ ክፍፍል ይታይ ነበር።

ይህም በአቶ ጌታቸው ረዳ እና በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ቡድኖች መካከል ነው።

ባለፉት ወራት እጅግ በርከታ ስብሰባዎች ተደርገው የነበረ ቢሆንም ልዩነቶች ግን እየሰፉ እንጂ እየጠበቡ ሲሄዱ አልታዩም።

ከአንድነት ይልቅ መከፋፈሉ እና ሽኩቻው ጨምሮ ታይቷል።

በዚህ ሂደት ላይ ግን ህወሓት ፥ " ህጋዊ ሰውነታችን ወደነበረበት እንዲመለስ " የሚል ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ ይቀርባል (ሚያዚያ ወር ላይ)።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን አንድ በአመጽ ተግባር ላይ ተሳትፎ የሰረዘውን ፓርቲ የቀደመው ህልውና መመለስ የሚያስችልበት የሕግ ድንጋጌ የለውም። በዚህም ጥያቄውን ሳይቀበለው ይቀራል።

ህወሓትንና ሌሎችንም ለመመዝገብ በሚል አዋጅ እስኪሻሻል ተደርጓል።

ህወሓትም ዳግም " ህጋዊው ሰውነቴ ወደነበረበት ይመለስ " ሲል በሊቀመንበሩ ዶ/ር ደብረጽዮን በኩል ጥያቄ ያቀርባል።

በእርግጥ ሁሉም አመራሮች " የነበረው ህልውና ይመለስ " የሚለው ላይ ልዩነት የላቸውም።

የተሻሻለው አዋጅም ግን በአመጽ ተሳትፎ ለተሰረዘ ፓርቲ የቀደመ ህልውናውን መመለስ የሚያስችል የህግ ድንጋጌ አልያዘም።

ይህን ተከትሎም ቦርዱ " #በልዩ_ሁኔታ " በሚል ፓርቲውን መዝግቦታል።

ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልም ወደ አዲስ አበባ ሄደው ከምርጫ ቦርድ የተሰጠውን " በልዩ ሁኔታ " መመዝገቡን የሚገልጽ ህጋዊ የሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ፈርመው ወስደው መቐለ ሄደዋል።

ከዚህ በኃላ መቐለ ሄደው በሰጡት መግለጫ " እኛ ይሄን አንቀበልም ፤ የጠየቅነው ሌላ የተሰጠን ሌላ ነው " ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

" እኛ እንደዛ አልነበረም የተነጋገርነው ፤ የተባልነውም እንደዛ አልነበረም " የሚል ነገር አንስተዋል።

የእውቅና ምስክር ወረቀቱን ፈርመው ከወሰዱ በኃላ  " ከምቀደው ብዬ ነው ይዤው የመጣሁት " ብለዋል። ምዝገበውን እንደማይቀበሉት እና እንደተመዘገቡም እንደማይቆጠር ነው የገለጹት።

እነ አቶ ጌታቸው ረዳ በምስክር ወረቀቱ ጉዳይ ምንድነው አቋማቸው ?

- በምዝገባ ጉዳይ ለምርጫ ቦርድ የተላከው ደብዳቤ ማእከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው በግለሰቦች የተላከ ነው።

- የተወሰኑ ግለሰቦች ናቸው ከድርጅቱ አሰራር ውጪ በቡድን በመሆን የፈረሙት እንጂ እኛ ለምዝገባ ብለን የፈረምነው ማንኛውም ሰነድ የለም።

- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ' ህወሓት ' ን አስመልክቶ ለተወሰኑ ግለሰቦች የሰጠው እውቅና #የተጭበረበረ በመሆኑ ዳግም ሊያጤነው ይገባል ... የሚል ነው።

ጉባኤው ?

የህወሓት ፅህፈ ቤት እና ማህተምን የተቆጣጠረው የነ ዶ/ር ደብረጾን ገ/ሚካኤል ቡድን ክፍፍሉ እና ከምርጫ ቦርድ ጋር ያለው ልዩነት ሳይፈታ ለጉባኤ ዝግጅት ሲያደርግ ነበር።

በጣም አጭር ጊዜ ውስጥም የጉባኤ ተሳታፊ ለይቶ ጉባኤ ማካሄድ ጀምሯል።

ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው አንዱ የህወሓት ቁጥጥር ኮሚሽን " አካሄዱን የጠበቀ አይደለም " በማለት ራሱን አግልሏል።

አቶ ጌታቸው ያሉበት 14 የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት " እኛ የለንበትም " ብለው ራሳቸውን አግልለዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደግሞ ባለው አሰራር አንድ ህጋዊ ፓርቲ ጠቅላላይ ጉባኤ ከማድረጉ ከ21 ቀናት በፊት ለቦርዱ ማሳወቅ እንዳለበት ይገልጻል።

በመሆኑንም ፤ የቦርዱን አሰራር ያልተከተለ ፣ ቦርዱ ባልተገኘበት የሚደረግ ጉባኤ ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን እውቅና እንደማይሰጥ አሳውቋል።

ህወሓት ግን መቐለ ላይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በርካታ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሌሉበት ጉባኤ እያካሄደ ነው።

ጉባኤ ማድረግ ምድነው ጥቅሙ ?

አንድን ጉባኤ ህጋዊ የሚያደርገው በሚመለከተው አካል እውቅና አግኝቶ አሰራሩን ተከትሎ ሲካሄድ ነው።

የፓርቲዎችን ጉዳይ የሚመለከተው ምርጫ ቦርድ በመሆኑ " አካሄዱ ትክክል አይደለም። እውቅናም አልሰጥም " ባለበት ሁኔታ ጉባኤ ቢደረግ ተሰብስቦ ከመበተን ውጭ ውጤት የለውም የሚሉ አሉ።

ዶ/ር ደብረጽዮን ግን ፥ " ህወሓትን አድኖ ህዝብ ከጥፋት መታደግ የጉባኤው ዋነኛ አላማ ነው " ብለዋል።

" የድርጅቱና የህዝቡ የተሟላ ድህንነት ማረጋገጥ በሚችል መልኩ በዴሞክራሲያዊ ውይይትና ክርክር ብቃት ያላቸው አመራሮች መምረጥ ይገባል "ም ብለዋል።

" የአሁኑ ጉባኤ ለድርጅቱ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው " እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው ፍጹም መግባባት ሳይሰረግበት እየተካሄደ ያለ መሆኑን ያነሳሉ።

የጉባኤው ውጤት ምን ሊሆን ይችላል ?

ጉባኤ ማድረግ ምን ችግር ላይፈጥር ይችላል።

ጉባኤውን ተከትሎ የሚተላለፉ ውሳኔዎች እውቅና ስለማያገኙ ሌላ ጭቅጭቅ እና ልዩነት መፍጠሩ ይጠበቃል።

ጉባኤው ላይ በእነ አቶ ጌታቸው እና ቡድናቸው ምትክ ሌሎች የመምረጥ ነገር ካለ ይበልጥ ነገሩ ይከራል።

አቶ ጌታቸውም " #ይቃወሙናል " የሚሏቸውን አመራሮች ለማስወገድ የሚደረግ ጉባኤ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጉባኤው የሚያመጣው የግጭት ስጋት አለ ?

በትግራይ ፖለቲካውን የሚከታተሉ አካላት አሁን ላይ በተጨባጭ የሚታይ የግጭት ስጋት የለም ባይ ናቸው።

ጉባኤውን ተከትሎ ምርጫ ተደርጎ ፤ አመራሮችን የማስወገድ ነገር ከመጣ ግን በሂደት ጭቅጭቁና ንትርኩ መጨመሩ እንደማይቀር ያነሳሉ።

በፓርቲው ጉዳይ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለው ልዩነት የመስፋት እድል ሊኖረው እንደሚችል ይገልጻሉ።

በፓርቲው ያሉት አንጃዎች የራሳቸው ደጋፊ ስላላቸው ልዩነታቸው በሰፋ ቁጥጥር በሂደት ወደ ኃይል እርምጃ እንዳይሄዱ ያሰጋል።

አሁን ላይ ግን በተጨባጭ የሚታይ የግጭት ስጋት ግን የለም።

#ትግራይ : ትግራይ ከአስከፊው ጦርነቱ በቅጡ ሳታገግም ፣ ብዙ ተጎጂ ባለበት ፣ ገና ተጠያቂነት ባልተረጋገጠበት ፣ ብዙ እገዛ የሚፈልግ ባለባት ፣ ተፈናቃይ ተሟልቶ ባልተመለሰበት ... ሌሎችም ብዙ ስራዎች ባልተሰሩበት ይህ የጉባኤ እና ምዝገባ ጉዳይ የህዝብ አጀንዳ እንዲሆን መደረጉ በርካቶችን ያስቆጣ ሆኗል። ይህ ጉዳይ ቀስ በቀስ በሂደት መሄድ እንደሚችልና መቅደም ያለባቸው ህዝባዊ ጉዳዮች መቅደም እንደነበረባቸው የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው።

#TikvahEthiopia

@tikvahethiopia