TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57.1K photos
1.42K videos
206 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
🇪🇹 #NationalDialogue 🇪🇹

እናት ፓርቲ ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግልጽ ደብዳቤ ጻፈ።

ፓርቲው ለኮሚሽኑ በጻፈው ደብዳቤ ፤ " ኢትዮጵያ ሕልውናዋን በመፈታተን ደረጃ ላይ ከደረሰው ቀውስ ብቸኛው መውጫ መንገድ ሁሉን አቀፍ #አገራዊ_ምክክር ማድረግ ፤ እንደ አገር በዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሆነ በጽኑ እናምናለን " ብሏል።

" የምክክር ኮሚሽኑ በክልል ደረጃ የአጀንዳ ልየታ ውይይቶችን ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንና ለዚሁ በአዲስ አበባ ከተማ ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ/ም ጀምሮ በተከታታይ ቀናት በሚደረጉ ስብሰባዎች የአጀንዳ ልየታ የሚያደርግ ጉባዔ መጥራቱ ይፋ ተድርጓል ፤ ጥሪው ለእኛም ደርሷል " ብሏል።

" የሚደረገው ምክክር ስልጣንን የጨበጠ አካል #በቀጥታም ሆነ #በስውር የሚመራው ውይይት መሆን እንደሌለበት እናምናለን " ሲል አስገንዝቧል።

ፓርቲው ፤ " በእኛ እሳቤ ይህ ምክክር በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት በመሠረታዊ መልኩ እስከ ማሻሻል አስፈላጊ ከሆነ እስከ መለወጥ ድረስ የሚያዘልቅ እንደሆነ ብናምንም በሥራ ላይ ያለው የአሸናፊዎች ሕገ መንግሥት ዓይነት ተግባር እንዳይፈጸም እና እንደ አገር ዳግም ስህተት እንዳንሠራ ከፍተኛ ሥጋት አለን " ሲል አሳውቋል።

" አገር ልትመክርበት ይገባል ብለን የምናስባቸው የምክክር አጀንዳዎች ፦
➡️ ወቅት የማይለውጣቸውና ወጥነት ያላቸው፣
➡️ መንግሥት ብንሆን ልንተገብራቸው ይገባል ብለን ያስቀመጥናቸው ነጥቦች ስለሆኑ ከአጀንዳ ልየታው ጋር ምንም ችግር የሌለንና ይህንኑ ያቀረብን መሆናችንን ኮሚሽኑ እንዲያውቀው የአገራችን ሕዝብም እንዲረዳልን እንወዳለን " ብሏል።

እናት ፓርቲ ፥ " አጀንዳዎቻችንን የማቅረቡ ሂደት እንደተጠበቀ ሆኖ በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው የምክክር መድረክ ፦

1ኛ. አገር በከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባለችበት ሁኔታ ምክክርም ጦርነትም በአንዴ ማድረግ የማይቻል መሆኑ፣ ከአገራት ተሞክሮ እንዲህ ባለ ሁኔታ የሚደረግ ምክክር ውጤታማ እንደማይሆን ታውቆ በተቃራኒ ወገን የተሰለፉ ወንድማማቾችን እያጨራረሰ የሚገኘው የእርስ በርስ ጦርነት በድርድር ፖለቲካዊ መፍትሄ ሳይበጅለት ፤

2ኛ. በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በየእሥር ቤቱ ታጉረው ባሉበትና ፍትሕ ተነፍጓቸው የሰቆቃ ሕይወት በሚገፉበት፤

3. የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ለምክክሩ ጭምር ጉልህ አስተዋጽዖ ማድረግ የሚችሉ ወገኖቻችን ያለ ፍርድ በየእሥር ቤቱ በሚማቅቁበት፤

4ኛ. አገር በአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ባለችበት፤

5ኛ. በምክክሩ ከመሳተፍ ራሳቸውን ከመጀመሪያ ጀምሮ ከሂደቱ ያገለሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምክክር ማምጣት ባልተቻለበትና በመሳሰሉ ምክንያቶች ምክክሩ አገራችን በእጅጉ የምትሻውን አገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ያስገኝላታል ብለን አናምንም። " ሲል አሳውቋል።

" እነዚህ ሁኔታዎች አጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ምክክር እስከሚደረግበት ባለው ጊዜ በቀዳሚነት መፍትሄ አግኝተው ሊፈቱ ካልቻሉና ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ በምክክሩ ለመሳተፍ እንቸገረለን " ሲል ገልጿል።

(ፓርቲው ለኮሚሽኑ የላከው ሙሉ ደብዳቤ ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia