TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.6K photos
1.43K videos
206 files
3.96K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#AddisAbaba

" ፈተናውን ብዙዎቹ ሊያልፉ ይችላል የሚል ግምት ነው የተያዘው " - የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሚኖሩ ዳይሬክተሮች እና ቡድን መሪዎች መካከል #ተመሳሳይ የብሔር ማንነት ያላቸው አመራሮች ብዛት ከ40 በመቶ እንዳይበልጥ ሊያደርግ መሆኑ ተሰምቷል።

በቅርቡ ለሚተገብረው #የሠራተኞች_ድልድል ሲባል ከ14 ሺህ በላይ የከተማ አስተደደሩ ሠራተኞች ነገ አርብ ታኅሣሥ 12/2016 ዓ.ም. ለፈተና ይቀመጣሉ።

ከማዕከል እስከ ወረዳ ያሉት ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ባለፉት ሳምንታት ከሠራተኞቹ ጋር ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል ተብሏል።

163 ሺህ ገደማ ሠራተኞች በስሩ ያሉት አስተዳደሩ ፤ በሚተገበረው ለውጥ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል የከተማዋን የመንግሥት ሠራተኞችን በአዲስ መልኩ መደልደል የሚለው ይገኝበታል።

ለለውጡ ትግበራ ተብሎ የተዘጋጀ #የሥልጠና_ሰነድ ምን ይላል ?

-አሁን በመጀመሪያው ዙር ድልድል እንዲተገበርባቸው የተመረጡት አስራ ስድስት (16) ተቋማት ናቸው። ከእነዚህም መካከል ፦

* የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር፣
* ቤቶች ልማት እና አስተዳደር፣ ትራንስፖርት፣
* ፐብሊክ ሰርቨሲ እና ሰው ሀብት ልማት፣
* ፕላን እና ልማት፣
* ሥራ እና ክህሎት፣
* ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮዎች
* ቤቶች ኮርፖሬሽን፣
* ኅብረት ሥራ ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎች የከተማይቱ ኤጀንሲዎች እና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ይገኙበታል።

- የተዘረዘሩት መስሪያ ቤቶች ድልድል የሚደረግባቸው በማዕከል ቢሮዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ላይ ባሉ ጽህፈት ቤቶቻቸው ጭምር ነው።

የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ጣሰው ገብሬ ምን አሉ ?

° ከላይ የዘረዘሩት መስሪያ ቤቶች ለመጀመሪያው ዙር ትግበራ የተመረጡት ብዙ ተገልጋይ የሚያስተናግዱ እንዲሁም ብልሹ አሰራር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብዙ መጓደል ያለባቸው በመሆናቸው ነው።

° የሠራተኞች ድልድል ከመከናወኑ በፊት የእነዚህ መ/ቤቶች ሠራተኞች ለፈተና ይቀመጣሉ።

° ፈተና ለመስጠት የታቀደው የሠራተኞቹን የብቃት ደረጃ ለማረጋገጥ ነው።

° ፈተናው የባህሪ እና የቴክኒክ ምዘናዎችን የያዘ ነው። የሚሰጠው የቴክኒክ ምዘና ሠራተኞቹ ከሚሠሩት ሥራ ጋር ግንኙነት ያለው ነው። የባህሪው ፈተና ደግሞ አገልግሎት አሰጣጡን የሚፈታተኑ የባህሪ ችግሮች ስላሉ ያንን ክፍተት ለመሙላት አመላካች እንዲሆን ተስቦ የተዘጋጀ ነው።

° የምዘና ፈተናው የተዘጋጀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጋራ ትብብር ነው።

° ፈተናው የሚሰጠው በዩኒቨርስቲ / በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው።

° እስካሁን ባለው መረጃም ነገ ፈተናውን የሚወስዱ ሠራተኞች ቁጥር ከ14 ሺህ በላይ ነው።

° ፈተናውን የማያልፉ ሠራተኞች እንዳይኖሩ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ እንዲያጠኑ ተነግሯል። ፈተናው ለማለፍ በሚያስቸግር መንገድ በጣም የተወሳሰበ፣ አብስትራክት እና ንድፈ ሀሳባዊ የሆነ ሳይሆን የሠራተኞችን አቅም ለመለካት አመላካች ሆኖ ነው የተዘጋጀ ነው።

° ብዙዎቹ ሊያልፉ ይችላል የሚል ግምት ነው የተያዘው።

የሪፎርም ሥልጠና ሰነዱ ምን ይላል ?

- የከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎች ፈተናውን ለማለፍ ከ50 በመቶ በላይ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል።

- ከዚህ የማለፊያ ውጤት በታች የሆነ ነጥብ ያገኘ ባለሙያ ከደረጃው ዝቅ ብሎ ባሉት የአስተዳደር እርከኖች ላይ ይመደባል።

- ለዳይሬክተሮች እና ለቡድን መሪዎች የተቀመጠው የፈተና ማለፊያ ነጥብ 60 በመቶ ነው። ይህን ነጥብ የማያስመዘግቡ አመራሮች ለዳይሬክተርነት ወይም ለቡድን መሪነት ኃላፊነት #መወዳደር_አልችሉም

ዶ/ር ጣሰው ገብሬ ፦

ሠራተኞች ፈተናውን ማያልፉ ከሆነ ዝቅ ተደርገው ሊመደቡ ይችላሉ። ድልድሉ ሲያልቅ ሌሎች አማራጮች ታይተው ምን ሊደረግ እንደሚችል የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ መፍትሄ ይፈለግላቸዋል።

በአዲስ መልኩ #ሠራተኞች ሲደለደሉ ከፈተናም በተጨማሪ ሌሎች መስፈርቶችን ይኖራሉ።

- ሰነዱ የሠራተኞች ድልድልን በተመለከተ " ትኩረትን የሚሹ አዳዲስ ጉዳዮች " በሚል ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ጉዳይ ነው።

- ድልድሉ ሲከናወን " ሕብረ ብሔራዊነትና አካታችነት በጥንቃቄ " መተግበር እንዳለበት በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

- " አካታችነትና ፍትሐዊነትን " በሚመለከተው የሰነዱ ክፍል ላይ በዳይሬክተርነት እና ቡድን መሪነት የሥራ መደቦች ላይ አመራሮች ሲመደቡ " የሜሪት ሥርዓት " ይጠበቃል።

- የአመራሮች ድልድል "የብሔር ብሔረሰብ ስብጥርን ባካተተ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ " ይከናወናል።

- በመ/ቤቱ ካሉ የሥራ መደቦች መካከል በተመሳሳይ ማንነት የተያዙት ከ40 በመቶ መብለጥ የለባቸውም።

- መ/ቤቶቹ ድልድሉን ሲያከናውኑ ይህንን #የብሔር ስብጥሩን ለመጠበቅ እንዲችሉ " ብቃት ያላቸውን ሠራተኞች ከሌሎች መ/ ቤቶች በመለየት በዝውውር እንዲሟሉ " ይደረጋል።

ዶ/ር ጣሰው ገብሬ ፦

ከ40% መብለጥ የለበትም በሚል የተቀመጠው አሠራር፤ የሚተገበረው የቡድን መሪዎች እንዲሁም የዳይሬክተሮች ድልድል ላይ ብቻ ነው።

በዚህ ድልድል ወደ #ሠራተኛው የወረደ እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም። የድልድል ደንቡ ውስጥም የለም።

የተመሳሳይ ማንነት ያላቸው ከተወሰነ ፐርሰንት በላይ መሆን የለበትም የሚለው ለዳይሬክተሮች እና ለቡድን መሪዎች ነው።

ከተማዋ የአገሪቱ ዋና ከተማ ናት። ብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ያሉባት ስለሆነች ያንን ሥዕል የሚያሳይ እንዲሆን መደረግ ስላለበት የተቀመጠ ነገር ነው።

ይህ የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርምና የሠራተኞች ድልድል እስከ ታኅሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ለማጠናቀቅ በጊዜያዊነት ዕቅድ ተይዟል።

ይህ መረጃ #ባለቤትነቱ የቢቢሲ አማርኛ አገልግሎት ነው።

@tikvahethiopia