TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.6K photos
1.44K videos
206 files
3.97K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ለጥንቃቄ_ከጠቀማችሁ

1. በአዲስ አበባ ከተማ የሜትር ታክሲ አገልግሎት የምትሰጡ ወንድም እህቶቻችን እባካችሁ ጥንቃቄ አድርጉ።

ማክሰኞ ምሽት 4 ሰዓት ገደማ ወደ ጎተራ ማሰለጫ መውረጃ ወይም በተቃራኒ ወደ ቄራ የሚወስደው መስቀለኛ መንገድ አካባቢ አንድ አገልግሎት ሰጪን 3 ተሳፋሪ መስለው የገቡ ወንበዴዎች መሃል አስፓልት ፣ በብዛት መኪና በሚመላለስበት መንገድ ላይ ከውስጥ እቃ ይዘው ሲሮጡ መመልከቱን አንድ የቤተሰባችን አባል መልዕክት አጋርቶናል።

ሹፌሩ ከመኪና ውስጥ አልወረደም ነበር። ምናልባት ቢወርድ ሌላ የነሱ ተባባሪዎች መኪናውን ይዘው ለመጥፋት አስበውም ሊሆን ይችላል ብሏል።

እነዚህ 3 ሰዎች ሁለቱ ከኋላ አንዱ ከፊት የነበሩ ሲሆን በፍጥነት የመኪናውን በር ከፍተው እቃ ይዘው ሲሮጡ ነው የተመለከታቸው።

" ፈጣሪ ነው የሚጠብቀን ነገር ግን በተለይ ምሽት ላይ ስንሰራ የምንጭናቸውን ሰዎች ፦
- ማንነት፣
- ስልክ ቁጥር ፣
- የምንሄድበትን ቦታ ፣
- የሰዎቹን ሁኔታ ድርጊታቸውን፣
- ንግግራቸውን በደንብ እንከታተል። ውስጣችን ጥሩ ስሜት ካልተሰማውም ይቅርብን " ብሏል።

ህይወታቸውን ለማሻሻል፣ ቤተሰባቸውን ለመደገፍ ፣ ልጆቻቸውን ለማኖር ሲሉ ብርድ እና ፀሀይ እየተፈራረቀባቸው ቀን ፣ ምሽት ፣ ለሊት ሳይሉ የሚሰሩ ወገኖቻችንን ፈጣሪ ከክፉ ይጠብቃቸው።

ዘራፊዎችም ዛሬ ላይ ተይዘው ነገ የሚለቀቁ ከሆነ ከወንብድና ተግባራቸው ስለማይመለሱ እጅግ ጠንካራ ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል።

የሰረቁበትን ቀን እንዲረግሙ የሚያደርግ ቅጣት ሊጠብቃቸው ይገባል።

ሰው ለልጆቹ ፣ ለቤተሰቦቹ ለራሱ ህይወት ሲል ከባድ ዋጋ እየከፈለና በሰላም ጥሩ ሰራተኛ ዜጋ ሆኖ ሀገሩን ህዝቡን እያገለገለ ካለ በበቂ ሁኔታ ከወንጀል ሊጠበቅ ይገባዋል።

2. በመኪና ተደራጅተ የሚዘርፉ ዛራፊዎች አሁንም በከተማው አሉ።

በቅርቡ ፥ መካኒሳ አካባቢ አንድ ግለሰብ በገዛ ሰፈሩ ያውም ጠዋት ላይ በ " ቪትዝ " ተሽከርካሪ የመጡ ወንበዴዎች አንገቱን በማነቅ ንብረቱን ዘርፈው መሬት ላይ ጥለውት ጠፍተዋል።

" አውቶብስ ተራ " አካባቢ በተመሳሳይ አንድ ወጣት በ ' ቪትዝ ' ተሽከርካሪ ላይ በመሆንና ውሃ በመድፋት " ና እንጥረግልህ " በማለት ለመዝረፍ ሙከራ አድርገዋል ፤ ምንም እንኳ ክፉ ሃሳባቸው ባይሳካም።

እነዚህ ባለመኪና ወንበዴዌች ምናልባት ብዙ ቦታ መሰል ተግባራትን እየፈጸሙ ይሆናል።

ከወራት በፊት ሩወንዳ አካባቢ ለሊት በ ' DX መኪና ' ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወንበዴዎች አንድን ግለሰብ ሞባይል ስልክ በገጀራ አስፈራርተው መዝረፋቸውን ነግረናችሁ ነበር።

መኪና የምታከራዩ ወይም መኪና ለሰው የምትሰጡት ሰዎችም ጥንቃቄ አድርጉ ማነው ፣ ለምን አገልግሎት እየተጠቀመ ነው የሚለውን አጣሩ።

ፖሊስ ይህንን ጉዳይ ከምንጩ ለማድረቅ መስራት አለበት።

በከተማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመንገድ ትራፊክ መብራት ላይ ስርቆት በጅጉ ቀንሷል። ይህ አበረታች ተግባር ጭራሽ መኪና ይዘው ለዝርፊያ በተሰማሩ አካላት ላይም መቀጠል አለበት።

ሰዎች ቀንም ይሁን ማታ ሳይሳቀቁ መንቀሳቀስ እንዲችሉ መደረግ አለበት። ህግ ቀን ቀን ብቻ የሚሰራ ማታ የማይሰራ እስኪመስል ድረስ ዘራፊዎች የሚያደርጉን እንቅስቃሴ መገታት መቻል አለበት።

3. የጸጥታ አካላትን የሚመስል ልብስ ለብሰው የሚዘርፉም አሉ።

አንድ የቤተሰባችን አባል በመንገዱ የገመጠውን አጋርቶናል።

ድርጊቱ የተፈጸመው በዚህ ወር  አለርት ሆስፒታል አካባቢ ነው።

መኪናውን እያሽከረከረ በሚሄድበት ወቅት የጸጥታ ኃይል ልብስ የሚመስል የለበሱ በግሩፕ የተሰባሰቡ ሰዎች (8-10) ድቅድቅ ያለ ጨለማ ውስጥ ሆነው ሊያስቆሙት ይሞክራሉ።

ነገር ግን እውነተኛ እና ትክክለኛ የጸጥታ አካላት ሰዎች እንዳልሆኑ ይጠረጥራል። ምክንያቱም ከዚህ ቦታ በፊት (ብዙም ሳይርቅ) ሌላ የደህንነት ፍተሻ ተፈትሾ ነበር።

እንዚህ ሰዎች ቁም ያሉት ቦታ ድቅድቅ ጨለማ እና የሚያስፈራ ስለነበር ወደፊት ትቷቸው ሲሄድ ሁለት የተጎዱ ሰዎች መሬት ላይ ተኝተው ተመልክቷል። ሌላ መኪና ስላልነበረና ለህይወቱም በመስጋቱ በፍጥነት ከቦታው ርቆ ሄዷል።

ምናልባት እነዚህ ሰዎች ለፍተሻ ብለው መኪናቸውን አስቁመዋቸው ዘርፈዋቸው ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬውን ገልጿል።

የፖሊስ የደህንነት ፍተሻ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ከየትኛውም አካል ፍቃድ ሳያገኙ ለመሰል እንቅስቃሴ የሚሰማሩ ካሉ አጥንቶ እርምጃ መውሰድ ይገባል። የማያዳግም አስተማሪ ቅጣትም መቀጣት ይገባል።

ሌላው የየትኛውም የሀገሪቱ የጸጥታ ልብስ በሲቪል ሰዎች / አባል ባልሆኑ ሰዎች እየተለበሰ በማኛውም መንገድ ሚዲያ ላይም ጭምር መታየት የለበትም። ሁሉም ሰው ለፍቶ ነው የክብር ልብሱን የሚለብሰውና ማንም እየተነሳ የጸጥታ ልብስ እየለበሰ መታየት ሌላውም ይህን እንዲለማመድ መደረግ የለበትም ፤ ልብሱም መከበር አለበት።

#TikvahEthiopiaFamilyAddisAbaba

#ቲክቫህኢትዮጵያ
#አዲስአበባ

@tikvahethiopia