TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.7K photos
1.49K videos
211 files
4.06K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#መልዕክት

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፦

" . . . ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚአብሔር ከሌለ ፍትሕ ይጐድላል፣ ፍትሕ ከጐደለ ብሶት ይፈጠራል፣ ብሶት ካለ ሰላም ሊኖር አይችልም።

በሁሉም የዓለማችን ክፍል ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚብሔር እየተዘነጋ በመሄዱ ቀውሱ ተባብሶ ይታያል፤ የሰው ልጅ ኑሮ በየትም ይሁን በየት በስጋት የተሞላ ሆኖአል፤ የሚወራው ሁሉ ስለ ግጭት ስለአየር ብክለት ስለ ረኃብና እልቂት ሆኖአል።

ዓለም የጉልበተኞችና የባለ ሀብቶች ብቻ እንድትሆን የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ ከባድ የፍትሕ መዛባት አጋጥሞአታል፤ የዝቅተኛው ማኅበረ ሰብ ሰብአዊ መብት ተዘንግቶአል፤ ከዚህ አኳያ ዓለም በዚህ እስከ ቀጠለች ድረስ ሰላም የማግኘቷ ዕድል በጣም አጠራጣሪ ነው።

የክርስቶስ ልደት ያስተማረን ግን እንደዚህ አልነበረም፤ ጌታችን የተወለደው በተዋበና ምቹ በሆነ የሀብታም ቤት ሳይሆን #በከብቶች_በረት ነበረ፤ የተገለጠውም ለባለሥልጣኖች ሳይሆን ዝቅተኞች ለሚባሉ እረኞች ነበረ፤ ልዑላኑ ሰማያውያንና ትሑታኑ ምድራውያን በአንድነት አገናኝቶ ስለ #ሰላም በጋራ እንዲዘምሩ አደረገ፤ አሳዳጅ ሳይሆን ተሳዳጅ ሆኖ በግብጽ አገር በመንከራተት አደገ፤ ይህን ሁሉ ያደረገው እኛ እሱን እያየን እንደ ሰንደቅ ዓላማ እንድንከተለው ነበር።

ጌታችን ከባለሥልጣናቱና ከባለሀብቶቹ ይልቅ በድሆቹ ደረጃ የተወለደው ለድሆቹና ለዝቅተኞቹ ትኩረት እንድንሰጥ ለማስተማር ነው። የእኛ ድርጊት ግን #ግልባጩ ሆኖ እየተስተዋለ ነው፡፡

እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ክርስቲያን ነኝ ብሎ፣ በስመ እግዚአብሔር ተሰይሞ፣ መስቀልን በአንገቱ ተሸክሞ የእሱ መሰል በሆነው ወይም መስቀል በተሸከመው ወንድሙ እና እኅቱ እንዲሁም በመሰል ፍጡር ላይ ያለ ርኅራኄ ሲጨክን መታየቱ ነው፤ እንዲህ እየሆነ እንዴት ሰላም ይምጣ? እግዚአብሔርስ እንዴት በረከቱ ይሰጣል? ይህ እጅግ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን  ምእመናንና ምእመናት!

እኛ ኢትዮጵያውያን ከእንዲህ ዓይነቱ የሃይማኖትና የሞራል ዝቅጠት በአስቸኳይ መውጣት አለብን፤ ጠቡ፣ መለያየቱ፣ መጨካከኑ፣ ለኔ ለኔ መባባሉ ከረምንበት፤ ሆኖም ያመጣልን ነገር ቢኖር ሁለንተና ውድመት ብቻ ነው። ያስገኘልን ትርፍ ይህ መሆኑ እያወቅን በዚሁ ልንቀጥል አይገባም።

ሰው ችግሩን በልቡ እያወቀ በዓይኑ እያየ እንዴት ገደል ውስጥ ይገባል ? ዕርቅና ይቅርታ ማንን ጐዳ ? ሰላምና አንድነት ማንን አከሰረ ? ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በሆነውም ባልሆነውም ከመተላለቅ ለምን ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በእኩልነትና በስምምነት መኖር አቃተን ?  ሦስት ሺሕ ዘመናት አብረው የኖሩ ሕዝቦች እንዴት ችግራቸውን በጠባይና በብልሐት ማስወገድ አቃታቸው ? ይህ ከቶ ሊሆን አይገባም።

ሁላችንም ሰከን ብለን እናስብ፤ ለሁሉም የማሰቢያና የመመካከሪያ ጊዜ ፈጥረን ችግሩን በስፍሐ አእምሮ እንፍታው፤ችግርን በምክክርና በይቅርታ መፍታት አማራጭ የሌለው ጥበብ ነው። የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ልኂቃን በዚህ ተግተን ልንሰራ ይገባል፤ መንግሥትና የፓለቲካ ፓርቲዎችም ለዚህ የበኩላቸውን ድጋፍ ያድርጉ፤ በዚህም ሰላማችንን እንመልስ፡፡ "

(ሙሉ መልዕክታቸው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia