TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.6K photos
1.43K videos
206 files
3.97K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ረቂቅአዋጅ

የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ለማሻሻል የወጣው ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል።

የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ምን ይዟል ? ምን ዋና ዋና ማሻሻያ ተደርጓል ?

🔵 ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የስራ አመራር ቦርድ አሰያየም እና አወቃቀር ጋር በተያያዘ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

በአዋጁ የተዘረጋው የቦርድ አሰያየምና አወቃቀር የተንዛዛ እና ረጅም ሂደትን የሚከተል መሆኑ ከዘርፉ ተለዋዋጭ ሁኔታ አንጻር አብሮ የማይሄድ መሆኑ፣ ይህም ባለሥልጣኑ መደበኛ ተልእኮዎችንና አስቸኳይ ውሳኔዎችን ከመስጠት አንጻር የመፈጸም አቅሙን የሚያስተጓጉል መሆኑ፣ እንዲሁም በነባሩ አዋጅ የተካተተው የቦርድ አባላት ስብጥር ከባለሥልጣኑ ሬጉላቶሪ ሚና ጋር በተያያዘ የጥቅም ግጭትን የሚፈጥር ሆኖ መገኘቱ እንደክፍተት ተገልጿል።

የተደረጉ ማሻሻያዎች ፦

" አንቀፅ 9/5/ሀ/ የቦርዱ አባላት ለመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ቅርበትና አግባብነት ካላቸው የተለያዩ አካላት እና የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ይሆናሉ " በሚል በረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ የተደረገበት ሲሆን የቦርድ አወቃቀር ላይ አስቻይ ያልሆኑ ገደቦች እንዲሻሻሉ ተደርጓል፡፡

🔵 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የስራ አመራር ቦርድ በወሳኝ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

በረቂቁ ማብራሪያ ላይ ፥ " በመርህ ደረጃ የባለሥልጣኑ ስራ አመራር ቦርድ ባለሥልጣኑን በፖሊሲ የሚመራ አካል ቢሆንም፣ በአዋጁ አንቀፅ 13(2) መሰረት በዕለት ተዕለት የሚከወኑ የሬጉላቶሪ ሥራዎች በቦርድ እንዲከናወኑ ተደርጓል " ይላል።

" በተጨማሪም የሀገርን ደህንነት ወይም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ የሚያደፈርስ ዘገባ በማናቸውም መገናኛ ብዙሃንና በማናቸውም ጊዜ ቢሰራጭ በአንቀፅ 81 መሰረት ፈቃድ የማገድ፣ የመሰረዝና አለማደስን የተመለከተ አስተዳደራዊ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ለቦርድ ተሰጥቷል " ሲል ያብራራል።

" ስለሆነም አዋጁ ቦርዱ ከሚጠበቅበት የፖሊሲ አቅጣጫ ሰጪነት ሚና ውጭ በዕለት ተዕለት የሬጉላቶሪ ተግባርና ሃላፊነት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡  ይህም ባለሥልጣኑ በህግ የተሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ መስጠት እንዳይችል ገድቦታል " ይላል።

" በተመሳሳይ የሚዲያውን አውድ ታሳቢ ያላደረገ የውሳኔዎች መዘግየት በዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ በሀገር ደህንነት ላይ አሉታዊ ጎኑ አመዝኖ ይታያል " ሲክ አክሏል።

የተደረጉ ማሻሻያዎች ፡-

" የፈቃድ አለማደስ፣ የፈቃድ ማገድ፣ ወይም የፈቃድ መሠረዝ የሚያስከትሉ ውሳኔዎችን የመወሰን ሥልጣን የባለሥልጣኑ ቦርድ ይሆናል" የሚለው ድንጋጌ ተሻሽሏል።

የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ከባድ የገንዘብ ቅጣት ወይም አንድ ፕሮግራም ማገድ ወይም መሰረዝ የሚያስከትሉ ውሳኔዎችን የመወሰን ሥልጣን
#የባለሥልጣኑ_ይሆናል፡፡

ረቂቁ " ባለሥልጣኑ የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ መሰረዝ፣ ከባድ የገንዘብ ቅጣት ወይም አንድ ፕሮግራም መሰረዝ የሚያስከትል ቅጣት የሚዳርግ ክስ ሲቀርብለት ባለፈቃዱ ወይም የምዝገባ የምስክር ወረቀት የተሰጠው መገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ላይ ያለውን ምላሽ በፅሁፍ በ7 የስራ ቀናት ውስጥ ለባለሥልጣኑ እንዲያቀርብ እድል ሊሰጠው ይገባል "  ይላል።

" በተወሰኑት ውሳኔዎች ቅር የተሰኘ ባለፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት የተሰጠው የመገናኛ ብዙሃን ውሳኔው በደረሰው በ14 የሥራ ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለቦርዱ ሊያቀርብ ይችላል፤ ቦርዱ አቤቱታው በደረሰው በ30 የሥራ ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለበት " በሚል በረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡

🔵 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አሿሿምን በተመለከተ ማሻሻያ ተደርጓል።

" የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በቦርዱ ተመልምሎ በመንግስት አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሰየማል " የሚለው ድንጋጌ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡

የተደረገው ማሻሻያ፡-

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል፡፡

🔵 ከብሮድካስት አገልግሎት ባለፈቃድ ግዴታዎች ጋር በተያያዘም ማሻሻያ ተደርጓል።

የረቂቁ ማብራሪያ ላይ " በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ከቀጥታ ሥርጭት ውጭ የማናቸውም ፕሮግራም ይዘት በጣቢያው ከመሠራጨቱ በፊት ሕግን የሚያከብር መሆኑን የማረጋገጥ፤ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ይህ ድንጋጌ በቀጥታ ስርጭት ወቅት ህገወጥ ይዘቶች ከተሰራጩ የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎችን ተጠያቂ የማያደርግ በመሆኑ፣ አስፈላጊውን ኤዲቶሪያል ጥንቃቄ እንዳያደርጉ ያደርጋል፡፡

በመሆኑም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በሚፃረር እና በሀገር ሉአላዊነት ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ እንደ ጦርነት ጥሪ እና የጥላቻ ንግግር የመሳሰሉ ይዘቶች እንዲሰራጩ መንገድ ይከፍታል፡፡

በመሆኑም ይህን ለመከላከል የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመውሰድ ማሻሻል አስፈልጓል " ብሏል።

የተደረገው ማሻሻያ፡-

የማናቸውም ፕሮግራም ይዘት በብሮድካስት አገልግሎት ጣቢያው ከመሠራጨቱ በፊት ሕግን የሚያከብር መሆኑን የማረጋገጥ፤ በሚል በረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia