TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.7K photos
1.49K videos
211 files
4.06K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ደመወዝ

" ለግል ድርጅቶች ሠራተኞችም የደመወዝ ማስተካከያ የሚደረግበት አቅጣጫ እንዲሰጥ ለመንግስት ጥያቄ ቀርቧል " - ኢሠማኮ

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት ይፋ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ ለመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ ይደረጋል በተባለው ልክ፣ ለግል ድርጅቶች ሠራተኞችም ማስተካከያ የሚደረግበት አቅጣጫ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቧል።

የኢሠማኮ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አህመድ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃል ፤  " በመንግሥት በጀት ለሚተዳደሩት የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ እንደሚደረግ ቢገለጽም፣ የግል ድርጅቶችና ተቋማት በራሳቸው በጀትና ትርፍ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑናቸው፣ በትርፋቸው ላይ ተመሥርተው ለሠራተኛ የደመወዝ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ከመንግሥት አቅጣጫ እየተጠበቀ ነው " ብለዋል።

" የሠራተኞችና የደመወዝ ዝቅተኛው ወለል እንዲወጣ እየወተወትን ነው " ሲሉም ተናግረዋል።

የመንግሥት እና የግል ሠራተኞች አንዱ የተሻለ አንዱ የወደቀ የሚባል ክፍያ ሊኖር አይገባም ሲሉ አክለዋል።

" መንግሥት ይህን ጉዳይ ሊዘነጋው አይችልም የሚል እምነት ቢኖረንም፣ መሰል አገራዊ አጋጣሚዎችና ቀውሶች በሚኖሩበት ጊዜ ባለሀብቶችንና ተቋማትን የሚመለከቱ ማሻሻያዎች በማድረግና ውይይቶች በማካሄድ አቅጣጫዎች ሊሰጡበት ይገባል " ሲሉ ተናግረዋል።

" ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ለአገርም አይጠቅምም፣ የኢንዱስትሪ ሰላም አይኖርም፣ ሠራተኛውም ተረጋግቶ ሥራውን ማከናወን አይችልም " ብለዋል።

አቶ አያሌው፣ " ጉዳዩ እጅግ በጣም አሳሳቢ ስለሆነ መንግሥት አቅጣጫ የማይሰጥበት ከሆነ ኢሠማኮ ጥያቄውን በጽሑፍ ለመንግሥት ያቀርባል " በማለት አስረድተዋል፡፡

" ሠራተኛው በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ምክንያት በልቶ ማደር አልቻለም፣ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አልቻለም፣ ይህን ማንም ያውቀዋል ሚስጥር አይደለም፣ አሠሪዎቹ ለሚያሠሯቸው ዜጎች ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ መክፈል አለባቸው " ብለዋል፡፡

የሠራተኛ መብት መከበር እንዳለበት " የሚያረጋግጥ ወጥ የሆነ ሕግ ያስፈልጋል " ያሉት አቶ አያሌው፣ " የሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልና ሌሎች የሠራተኞች መብቶችና ጥቅማ ጥቅሞች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መንግሥት ለምን እንዳዘገያቸው አልገባኝም " ሲሉ ገልጸዋል።

" የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጉዳይ ላይ አሁንም መንግሥት የዘነጋው ይመስላል " ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ኢሠማኮ ተጨማሪ ጥያቄ ሊያቀርብ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

አክለው ፥ ከመንግሥት ተቋማት በተሻለ የሚያተርፉት የግል ተቋማት፣ ከመንግሥት የደመወዝ ጭማሪ ጋር እኩል ላለመጨመር ትልቁ ችግር የአስተሳሰብ ጉዳይ እንጂ፣ የገንዘብ እጥረት አይደለም በማለት ለዜጎች ማዘን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ለራስ ብቻ ከማግበስበስ ዕሳቤ በመውጣት ምርታማ ሠራተኛን ለማፍራት፣ አሁን  ተመጣጣኝ የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ ብዙ ነው የሚያሰኝ አለመሆኑን ገልጸዋል።

#EthiopianReporter #Salary #Ethiopia

@tikvahethiopia