TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.7K photos
1.49K videos
211 files
4.06K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
አቶ ጌታቸው አሰፋ‼️

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ከነገ ጀምሮ በሀዋሳ ያደርጋል። አራቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችም ከድርጅታዊ ጉባኤው በፊት የፓርቲዎቻቸውን ሊቀ መንበር፣ ምክትል ሊቀ መንበር፣ የማዕከላዊ እና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫን አካሂደዋል።

የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) መጠሪያውን ወደ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በተመሳሳይ መልኩ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ደግሞ ወደ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) መቀየራቸው ይታወሳል። ሁለቱ ፓርቲዎች ከስማቸው ባሻገር የአርማ ለውጥም አድርገዋል። በሌላ በኩል ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) የቀድሞ ስማቸውን እና አርማቸውን ይዘው ቀጥለዋል።

ኦዴፓ፣ አዴፓ እና ዴኢህዴን በርካታ የቀድሞ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሎቻቸውን በአዲስ እና ወጣት አባሎች ተክተዋል። ይህ በእንዲህ
እንዳለ ህውሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አድርጎ የመረጣቸው ግለሰቦች ነባር እና ከሞላ ጎደል የድርጅቱ ታጋዮች መሆናቸው አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

በተለይ ደግሞ የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ #ጌታቸው_አሰፋ ከዐሥራ አንዱ የድርጅቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ ሆነው መመረጣቸው ብዙዎች ህወሓት #ከለውጡ ራሱን ገሽሽ እያደረገ ስለመሆኑ እንደ አንድ ማሳያ አድርገው ወስደውታል።

ለመኾኑ አቶ ጌታቸው አሰፋ ወደ ሥራ አስፈጻሚ መምጣታቸው አሁን ባለው የለውጥ አውድ ምን ፖለቲካዊ ትርጉም ይሰጣል?

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የሰጡት የህወሓት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቀድሞ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን አቶ #ጌታቸው_ረዳን እንዲህ ብለዋል፦

''ጌታቸው አሰፋ #ጎበዝ መሪ መሆኑን አውቃለሁ። ጎበዝ #ኢህአዴግ መሆኑን አውቃለሁ። ጎበዝ #ህወሓት መሆኑን አውቃለሁ። ህወሓት ሲወስን በሚዲያ #ሃሜት ላይ ተመሥርቶ አይደለም የሚወስነው'' በማለት በቀድሞው የደኅንነት ሹም አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ የሚቀርቡ ወቀሳዎችን አጣጥለዋል።

አቶ ጌታቸው ጨምረውም ''ይፋዊ መግለጫ ሳይኖር ሚዲያዎች ሃሜት ሲያወሩ ነበር። ሃሜት ላይ ተወስነን ውሳኔ የምናስተላልፍ ቢሆን ኖሮ ሃገር #ይጠፋል። ክስ ስለመመስረቱም የማውቀው ነገር የለም። አቶ ጌታቸው አሰፋን ፈልጎ ህውሓት ጋር የመጣ አካል የለም።'' በማለት አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ ክስ አለመመሥረቱን አመላክተዋል።

አቶ ጌታቸው አያይዘው እንደሚሉት ከሆነ አቶ ጌታቸው አሰፋ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ የመመረጥ ፍላጎት አልነበራቸውም።

''ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ መግባትም አልፈለገም፤ ሲሪየስሊ [አጥብቆ] ነው የተከራከረው። ጉባኤው ግን ከማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እንዲገባ ወሰነ። ማዕከላዊ ኮሚቴው ደግሞ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ውስጥ መግባት አለበት ብሎ ወሰነ።'' ይላሉ አቶ ጌታቸው ረዳ።

"አቶ ጌታቸው አሰፋ በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ወደ ሀዋሳ ይሄዳሉ ወይ?" ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ ጌታቸው ረዳ ሲመልሱ ''የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በጉባኤው እንዲሳተፍ ይጠበቃል። እንደማንኛው የኮሚቴ አባል ሀዋሳ ላይ ልታይዋቸው ትችላላችሁ።

እንደማንኛውም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ተሳትፎ ማድረግ ስላለብን አንዳንዶቻችን ያው መንገድ ላይ ነን። ለምሳሌ አውሮፕላን ካመለጠኝ ልቀር እችላለሁ'' ብለዋል።

ይህ አገላለጽ 'አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይገኙ ይችላሉ' የሚለውን ያመላክት እንደሆነ ከቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው ረዳ፣"እኔ የእያንዳንዱ ሰው ስኬጁል አላወጣም። ሁላችንም ተበትነን ነው ወደ ሀዋሳ እየሄድን ያለነው፤ ጌታቸውም በራሱ ጊዜ ስኬጁሉን አሬንጅ ያደርጋል፤ ካገኘሁት እነግራችኋለሁ" ሲሉ በቀልድ የታጀበ ምላሽ ሰጥተዋል።

ነገ በሚጀመረው የኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የድርጅቱ ሊቀ መንበር ማን ሊሆን ይችላል ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ''አሁን ያሉት ሊቀ መንበር ላለፉት 5 ወይም 6 ወራት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። እስካሁን የሠሩት ሥራ ተገምግሞ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገናል ወይስ አያስፈልገንም የሚለው የጉባኤው ውሳኔ ነው የሚሆነው'' በማለት መልሰዋል።

ህወሓት ማንን በእጩነት ለማቅረብ እንደተሰናዳ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው ረዳ ፓርቲዎች እንደማይመርጡ አስረድተዋል። ''ህወሓት፣ ብአዴን
ወይም ኦህዴድ ዕጩዎችን አያቀርቡም። ፓርቲዎች አይደሉም ዕጩዎችን የሚጠቁሙት። ከ180ዎቹ የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት ግለሰቦችን ለሊቀ መንበርነት ለጉባኤው ጥቆማዎችን ይሰጣሉ። ከዚያም ምርጫ ይካሄዳል። ድምጽ ያገኘ ያሸንፋል።'' ብለዋል።

በግንባሩ ጉባኤ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው፤ ''የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አፈጻጸም ላይ መቀዛቀዝ ይታያል።

ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት እሱን እንዴት አድርገን ነው በፍጥነት የምናስቀጥለው የሚለው ትልቁ አጀንዳ ነው። ወደ ሃገር እንዲገቡ የተደረጉ ተፎካካሪ፣ ተቃዋሚ የሚባሉ ፓርቲዎች ወደ ሃገር ከገቡ በኋላ አንዳንዱ 'አሸንፌ ነው የመጣሁት' ይላል። ሌላኛው 'ወደሽ ሳይሆን ተገደሽ ነው የተቀበልሺኝ' ይላል። ይህ ዓይነት ስሜት የሚፈጥረው #የሰላም እና #የመረጋጋት ዝብርቅርቅ አለ። ይህን ለመሰሉ ጉዳዮች ጉባኤው #ምላሽ ይሰጣል። ይህ የሁላችንም አጀንዳ ነው'' ብለዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ የአማርኛው አገልግሎት
@tsegabwolde @tikvahethiopia
#የካቲት2010

የ2010 ዓ/ም በተለይም የካቲት ወር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በርካታ ክስተቶች የተስተናገዱበት ፤የካቲት 8 ደግሞ ታሪካዊ ቀን ተብሎ ሊመዘገብ የሚችል ነው።

ለረጅም ዓመታት በእስር ቤት እንዲማቅቁ የተፈረደባቸው ፖለቲከኞች ፣ የሃይማኖት አስተማሪዎች፣ በርካታ ወጣቶች ከእስር እንዲፈቱ የተደረገበት ፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ ያስገቡበት ወር ነው።

ከብዙ ትውስታዎች በጥቂቱ ፦

- መላው ሀገሪቱ ከፍተኛ ጭንቀት እና ውጥረት ውስጥ የነበረችበት ወቅት ነበር።

- በበርካታ ከተሞች በተለይ በኦሮሚያ ክልል እና አማራ ክልል እንዲሁም በደቡብ ክልል የወጣቶች የ #ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ላይ ተቃውሞ እጅግ የበረታበት ነበር። ተቃውሞው እስረኞች እንዲለቀቁ፣ ፍትህ እንዲሰፍን፣ መንግስት ዜጎችን መግደል እንዲያቆም ሲጠየቅበት የነበረ ነው።

- በተለይ በኦሮሚያ ክልል እጅግ በርካታ ከተሞች ፣ በአማራ ፣ በደቡብ ክልሎች በሚገኙም ከተሞች መንግስትን በመቃወም የስራ ማቆም እና ቤት የመቀመጥ አድማ የተደረገበት ወር ነበር።

- መንግስት እስረኞችን ለመፍትታ የወሰነበት በዚህም ፦ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ (በወቅቱ) ጉዳያቸው በህግ ተይዞ የነበሩ 329 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ የወሰነበት በአጠቃላ 746 እንዲፈቱ የተባለበት ወር ነበር።

- እነ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ፣ አቶ አንዱአለም አራጌ፣ አቶ አበበ ቀስቶ እና አቶ እስክንድር ነጋ የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ አንፈርምም ያሉበት ወር ነው።

- ከሰባት እስከ ሃያ ሁለት አመታት እስር የተበየነባቸው የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት አንዳችም ያጠፋነው ጥፋት የለም በሚል "የምንጠይቀውም ይቅርታ የለም " የይቅርታ ፎርም አንፈርምም ያሉበትም ወር ነው።

- የ2010 የካቲት ወር የኦፌኮው ከፍተኛ አመራር አቶ በቀለ ገርባ ፣ አቶ ጉርሜሳ አያና፣ አቶ አዲሱ ቡላላ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ጌቱ ጋሩማ፣ አቶ ተስፋዬ ሊበን እና አቶ በየነ ሩዳ ከእስር የተለቀቁበት ነው።

- የዞን ዘጠኞቹ (የቀድሞ) እነ አቶ በፍቃዱ ኃይሉ ፣ አቶ አጥናፍ ብርሃኔ እና አቶ ናትናኤል ፈለቀ ክስ የተቋረጠበት ወር ነበር የካቲት 2010 ዓ/ም።

- እነ አቶ አዱአለም አራጌ ፣ አቶ እስክንድር ነጋ ፣ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ፣ አቶ ኦልባና ለሌሳ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ ፣ አርቲስት ሴና ሰለሞን ፣ አርቲስት ኤልያስ ክፍሉ ፣ ወ/ሮ ጫልቱ ታከለ ፣ ወ/ሮ እማዋይሽ ፣ አቶ ማሙሸት አማረ፣ ኦኬሎ አኳይ (የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዘዳንት)፣ አቶ አንዱአለም አያሌው ፣ እነ አቶ ብርሀኑ ተክለያሬድ ከእስር የተለቀቁበት ወር ነበር።

* የካቲት 8 / 2010 (በዛሬዋ ቀን) የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እና ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡበትና ይህንኑም በመግለጫ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያሳወቁበት ቀን ነበር።

- በ2010 የካቲት ወር የሚንስትሮች ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በሁሉም ሀገሪቱ ክፍል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የወሰነበት እና ወደ ምክር ቤት የመራበት ነበር።

- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ስብሰባ የካቲት 23/2010 ዓ/ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በ395 ድጋፍ፣ በ88 ተቃውሞ እና በ7 ድምጸ ታእቅቦ ያፀደቀበት። በኃላም የተፈጠረው የቁጥር ስህተት መነጋገሪያ ነበረበት በወቅቱ አፈጉባኤ የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ ህዝብን " ይቅርታ " የጠየቁበት ወር ነበር።

- የአዋጁ መታወጅ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲከሰት ያደረገም ነበር። በነበሩ ግጭቶች ቀደም ብሎ በወሩ ውስጥ በነበሩ ተቃውሞዎች በርካታ ወጣቶች የተገደሉበት ነበር።

- የአማራ ክልል በጎንደርና ጭልጋ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የ224 ተጠርጣሪዎች ክስ ያቋረጠበት።

- የጎንደሯ ወጣት ንግስት ይርጋ ከእስር የተፈታችበት ወር ነው (የካቲት 13 ቀን 2010) ።

- የኢትዮጵያ መንግስት ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌን (አሁን በህይወት የሉም) ጨምሮ 18 ሰዎች በይቅርታ እንዲፈቱ የወስነበት ወር ነው።

- የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አደርገዋል ተብለው የተከሰሱት ኮሎኔል አንተነህ ደምስ፣ ኮሎኔል አለሙ ጌትነት፣ ብ/ጀነራል አሳምነው ፅጌ (አሁን በህይወት የሉም)፣ ብ/ጀነራል ተፈራ ማሞ ከእስር የተፈቱት በዚሁ የካቲት ወር ነው።

- የኦህዴድ (የቀድሞ የኢህአዴግ አባል ድርጅት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠበት ወር ነው። (ዶክተር ዐቢይ የአሁን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር /የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዜዳንት ናቸው)

- ሱማሌ ክልል 1500 እስረኞችን ከእስር የፈታበት ነው።

- የቀድሞው ሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበሩት አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከእስር የተፈቱበት ወር ነው። እሳቸው ሁለት ጊዜ "ፈርመው እንዲወጡ" ተብሎ ሲጠየቁ ወንጀል እንዳልፈፀሙ በመግለፅ የይቅርታ ፎርም ላይ አልፈርምም ብለው ነበር። (አሁን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው)

(ከላይ የዘረዘርናቸው በቲክቫህ ኢትዮጵያ ገፃችን በየካቲት ወር 2010 ላይ ከተለዋወጥናቸው በርካታ መረጃዎች / በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት በወሩ ውስጥ ከታዩ ክስተቶች ጥቂቶቹን ያስታወስንበት ነው)

#TikvahFamily

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
" ፍ/ቤቱ የሚያስከስሳቸው ጉዳይ የለም በማለት በነፃ አሰናብቷቸዋል " - ጠበቃ በሙሉ ታደሰ

አቶ ዘመነ ካሴ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ዛሬ ጠዋት ከባሕር ዳር ማረሚያ ቤት ከእስር መፈታታቸውን ጠበቃቸውን ዋቢ በማድረግ ዶቼ ቨለ ሬድዮ ጣቢያ ዘግቧል።

አቶ ዘመነ " በህግ ማስከበር ሥራ ላይ የነበረን ሰው #ገድለዋል " በሚል ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት መስከረም 11 ቀን 2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ነበር።

ጉዳያቸውን ሲመለከት የቆየው የባሕር ዳር እና አካባቢው ፍ/ቤት አቶ ዘመነን " የሚያስከስሳቸው ጉዳይ ባለመኖሩ " ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም በነፃ እንዳሰናበታቸው ጠበቃቸው አቶ በሙሉ ታደሰ ተናግረዋል።

በመጀመሪያዎቹ  የጊዜ ቀጠሮዎች ወቅት ሌሎች ግለሰቡ የተጠረጠሩባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ክሱ በዋናነት ከግድያ ወንጀል ጋር የተያያዘ እንደነበር ጠበቃው ተናግረዋል፡፡

አቶ ዘመነ ካሴ ወደ ፍ/ ቤት እንደማይሄዱ ካሳወቁ በኋላ አብዛኛውን የፍርድ ሂደታቸውን በሌሉበት በባህርዳር እና አካባቢው ፍርድ ቤት ሲካሄድ መቆየቱን የሬድዮ ጣቢያው ዘገባ አመልክቷል።

አቶ ዘመነ ካሴ በቀድሞ የ " አርበኞች ግንቦት 7 " ውስጥ በአባልነትና በአመራር ውስጥ የነበሩ እና ረጅም ጊዜ በኤርትራ በርሀ ውስጥ በመሆን " #ኢህአዴግ " መራሹን አገግዛ ሲታገሉ ያሳለፉ ፤ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎም ውጭ ያሉ የታጠቁ አካላት ትጥቃቸው አውርደው ወደ ሀገር ሲገቡ ወደ ሀገር የገቡ ሲሆን ወደ ሀገር ከገቡ በኃላ በፋኖ አደረጃጀት እንቅስቃሴ ውስጥ በፊት መስመር ላይ ከሚታወቁ ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ለአንድ የውጭ ሚዲያ በሰጡት ቃል ፤ በአማራ ክልል በጎጃም አካባቢ የሚንቀሳቀውና እራሱን " የአማራ ሕዝባዊ ኃይል ፋኖ " በማለት የሚጠራው ቡድን ሰብሳቢ እንደሆኑ ተናግረው ነበር።

@tikvahethiopia
#Ethiopia

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዜዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃለማርያም ሀገር ጥለው ከወጡ ዛሬ ድፍን 33 ዓመት ሆኗቸዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪ ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ/ም ነው ከሀገር የወጡት።

የድርግ ውድቀትን እና የ #ኢህአዴግ ወደ አዲስ አበባ መቃረብን ተከትሎ ከሀገር እንደወጡ የሚነገርላቸው ኮ/ሌ መንግሥቱ ኃለማርያም በአንድ ወቅት ፤ " እኔ ኮብልዬ አልወጣሁም " ሲሉ ነበር ቃላቸውን የሰጡት።

ኬንያ የሄዱትም ' #አሰብ ' በሻዕብያ በመያዙ ለመልሶ ማጥቃት የሚሆን ሌላ በር እንዲኖር ከኬንያ፣ ከጅቡቲ እና ሰሜን ሶማሊያ መንግስታት ጋር ለመነጋገርና ለመመለስ እንደነበረና ይህም ጥብቅ ሚስጥራዊ ጉዞ እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ጥዋት 2:20 ወደ ኬንያ ጉዞ እንደጀመሩ እዚህ ስብሰባ መጀመሩና ኬንያ እንዳሉ ከቀን 7:00 ሰዓት ከስልጣን እንደወረዱ እንደሰሙ ገልጸው ነበር።

በራሳቸው አንደበትም ፥ ምንም አይነት #ገፊ ምክንያት በሌለበት በአሻጥር ከሀገር እንዲወጡ መገደዱን ነው በአንድ ወቅት ሲናገሩ የተደመጡት።

ዛሬ ላይ ሀገር ጥለው ከወጡ 33 ዓመት የደፈናቸው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በዚምባቡዬ ውስጥ ይኖራሉ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዜዳት ከዓመታት በፊት ፦
° በዘር ማጥፋት ፣
° በግድያ፣
° ከህግ ውጪ ሰዎችን በማሰር
° ንብረትን በመውረስ ጥፋተኛ ተብለው በሌሉበት #የሞት ፍርድ ተወስኖባቸዋል።

@tikvahethiopia