TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.7K photos
1.49K videos
211 files
4.06K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
የጥናት ሪፖርቱ ይፋ ሊደረግ ነው...

ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ #ተቃውሞ የቀረበበት ንብረትነቱ የሚድሮክ ጎልድ የሆነው #የለገደምቢ ወርቅ ማውጫ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ጥናት ሪፖርት በመጪው ሳምንት ይፋ እንደሚያደርግ፣ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚድሮክ ጎልድ ኩባንያ በለገደምቢ ወርቅ ለማምረት የሚጠቀምበት ኬሚካል በአካባቢውና በማኅበረሰቡ ጤና ላይ ቀውስ እንደፈጠረ በመግለጽ፣ የሻኪሶ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ በማሰማታቸው የማዕድን ሚኒስቴር ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን እስኪጣራ የኩባንያው የማዕድን ምርት ፈቃድ ከአንድ ዓመት በፊት ማገዱ ይታወሳል፡፡

ሚያዝያ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር አቶ #ሳሙኤል_ሁርቃቶ፣ በገለልተኛ ባለሙያዎች በሚድሮክ ጎልድ ኩባንያ አሠራር ላይ ሲካሄድ የነበረው ጥናት ሪፖርት #በመጪው ሳምንት ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የአካባቢ ተፅዕኖ ጥናት ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስጠንቶ የነበረ ቢሆንም፣ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡ ሚኒስቴሩ የሚድሮክ ጎልድን ፈቃድ #ካገደ በኋላ ከኩባንያው ኃላፊዎች፣ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ተወካዮችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ተጨማሪ ጥናት በገለልተኛ ወገን እንዲከናወን ከስምምነት ላይ መድረሱ ይታወሳል፡፡

የካናዳ መንግሥት ለማዕድን ሚኒስቴር በሚሰጠው የድጋፍ ፕሮግራም፣ በለገደምቢ ወርቅ ማውጫ ላይ ለሚካሄደው ጥናት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ጥናቱ በካናዳ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንደተካሄደ ታውቋል፡፡ በጥናቱ ግኝት ላይ ተመርኩዞ ሚኒስቴሩ የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ሚድሮክ ጎልድ ሥራው በመቋረጡ ለከፍተኛ ኪሳራ እንደተዳረገ በመግለጽ፣ ጥናቱ በአፋጣኝ እንዲሠራ ሲወተውት መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በማዕድን ኩባንያዎችና በአካባቢ ማኅበረሰቦች ስለሚፈጠሩ ግጭቶች የተናገሩት አቶ ሳሙኤል፣ አንዳንድ ኩባንያዎች የማኅበረሰብ አቀፍ ሥራ እንደማያከናውኑ ከክልል መንግሥታት ጋርም ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከፌዴራል መንግሥት የማዕድን ሥራ ፈቃድ የተሰጣቸው ኩባንያዎች በክልል ውስጥ ደሴት ሆነው የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ከክልል መንግሥት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አያደርጉም፡፡ ክልሉም ምን እንደሚሠሩ አያውቅም፡፡ ልክ ችግር ሲፈጠር ኩባንያዎቹ የክልሉን መንግሥት ያናግራሉ፤›› ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ ይህን አሠራር ለመለወጥ ሚኒስቴሩ በማዕድን ኩባንያዎችና በክልል መንግሥታት መካከል መልካም የሥራ ግንኙነት ለመፍጠር እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ክልሎች የማዕድን ኩባንያዎች የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች አውቀው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በማኅበረሰብ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ሊነገሩ የሚገቡ መልካም ሥራዎች የሠሩ ኩባንያዎች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

ሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማውጫን በ1989 ዓ.ም. ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ በጨረታ በ172 ሚሊዮን ዶላር መግዛቱ ይታወሳል፡፡ የወርቅ ማውጫው በዓመት አራት ቶን ወርቅ የማምረት አቅም አለው፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር
@tsegabwolde @tikvahethiopia