TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.3K photos
1.47K videos
209 files
4.03K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
" እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሁሉ የቀይ ባህር ተልማችንንም ዕውን አድርገን ወሽመጣቸውን ዳግም እንቆርጠዋለን " - ሀገር መከላከያ ሰራዊት

የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ባሰራጨው አንድ ፅሁፍ ፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሀገር ስኬት ሁሌም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጿል።

ሰራዊቱ ባወጣው ፅሁፍ ፤ ስማቸውን በግልፅ ያልጠራቸው እና " #እነሱ " ሲል የጠራቸው አካላት " እንደ ጦስ ዶሮ ዙሪያችንን እየዞሩ የብሄራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጫ መንገዶች ሁሉ ለመዝጋት ከመፍጨርጨር ቦዝነው ያወቁበት የታሪክ አጋጣሚ የለም " ብሏል።

" አንዳንዴ ከራሳቸው ስኬት በላይ የእኛ በጠና መቸገርና መጎሳቆል በእጅጉ የሚያረካቸው እስኪመስል ድረስ ሀገራዊ የተስፋ ብርሃናችንን ለማጨለም ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም " ሲል ገልጿል።

" አባይን ለሺህዎች ዘመናት ለብቻቸው እንዳሻቸው ሆነውበታል። ለምተው አድገው ሀገራቸውን በጠንካራ መሠረት ላይ አቁመውበታል " ያለው ሰራዊቱ " እኛ ይህ ለምን ሆነ የሚል በከንቱ ምቀኝነት ብቻ ተነሳስተን ያደረግነው አንዳችም ነገር የለም " ሲል አስረድቷል።

" ለኢትዮጵያም ሆነ ለእነሱ ወንዝ ብቻ ያልሆነው አባይ እነሱን ሲያስውብ እኛን ሲያገረጣ ለብዙ ጊዜያት ቆይቷል " ያለው ሰራዊቱ ፤ " እውነት ከእነሱ ቅጥ ያጣ ስጋትና ራስ ወዳድነት በሚመነጭ ሴራ እየተጎነጎነልን በዚህም ዋጋ ከፋዮች ሆነን መቆየታችን ስናስበው የሚተናነቀን መራር እውነት ነው " ብሏል።

ኢትዮጵያ ጥቅሟን በሌሎች መጉዳት ላይ መመስረት እንደማትፈልግም ገልጾ ሁሌም " ማንም ሳይጎዳ እኔም በድርሻዬ ልጠቀም " በሚል መርህ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ይህን ማረጋገጥ መቻሏን አስታውሷል። በዚህም እነዚህ አካላት ወሽመጣቸው መቆረጡን ገልጿል።

ይህን ተከትሎ ፤ " ከቀጠና እስከ አህጉር፣ ከአህጉር እስከ ዓለም አቀፍ ተቋማት ብዙ ማስነው ሊያስቆሙት ያልቻሉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ አሁን ' የተበላ እቁብ ሆኖባቸዋል ' " ብሏል

" እነዚሁ አካላት አሁን ደግሞ የሶማሊያ ' አዛኝ ቅቤ አንጓች ' ሆነው ብቅ ብለዋል " ያለው ሰራዊቱ " የህዳሴ ግድቡስ እሺ ከአባይ ጋር ተያያዘ እንበል። ከወዳጅ ጎረቤታችን ሶማሌላንድ በቀይባህር የባህር በር እና የባህር ሃይል ቤዝ እንዲኖረን በምትኩም ሶማሌላንድን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምንሰጠው ኖሮን ተስማማን። ታዲያ እንዴት ቀይባህር ውስጥም አባይ ሊታያቸው ቻለ ? ... ይህ ታሪካዊ ጠላትነት ካልሆነ ምን ይባላል ? " ሲል ጠይቋል።

መከላከያ ባወጣው ፅሁፍ ፤ " የማይመጡበት የለም " ያላቸው እነዚህ አካላት " ከውስጥ በብሄር፣ በሃይማኖት በሌላም እንድንናቆር፣ ሁሌም በአዙሪት እንድንዳክር.. ይተጋሉ። መቼም አይተኙልንም " ብሏል።

" እኛም እንደ ታላቁ የህዳሴው ግድባችን ሁሉ የቀይ ባህር ተልማችንንም ዕውን አድርገን ወሽመጣቸውን ዳግም እንቆርጠዋለን። እኛ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሀገራችን ስኬት ሁሌም ዝግጁ ነን " ሲል አሳውቋል።

#FDREDefenseForce

@tikvahethiopia