TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.5K photos
1.43K videos
206 files
3.95K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
የIMF ሰዎች እዚህ ኢትዮጵያ ናቸው።

ብሉምበርግ የዜና ወኪል ፤ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ለኢትዮጵያ ሊሰጥ በሚችለው ድጋፍ አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ የድርጅቱ ባለሥልጣናት አዲስ አበባ ይገኛሉ ብሏል።

በእርስ በርስ ጦርነቱ ሳቢያ ኢትዮጵያ ከIMF ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር የነበራት ግንኙነት ተቀዛቅዞ መቆየቱ ይታወሳል።

እንደ ብሉምበርግ ዘገባ የተቋሙ የባለሙያዎች ቡድን ኢትዮጵያ ከIMF ሊደረግላት ስለሚችለው ድጋፍ አስፈላጊውን “ቴክኒካዊ ሥራ ለማከናወን” ነው አዲስ አበባ የሚገኘው።

ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተ ውይይት እና አስፈላጊውን ሁኔታ እንዲያመቻቹ የተላኩት የIMF ባለሥልጣናት ለ10 ቀናት ያህል ይቆያሉ።

ቃላቸውን ለሮይተር የዜና ወኪል የሰጡ የIMF ቃል አቀባይ በበኩላቸው ፤ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላት ተቋሙን እንደጠየቀች ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ፤ " ሊሰጥ የሚችለው ድጋፍ አገሪቱ ለምታካሂደው አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ እና ምጣኔ ሀብቷን በማረጋጋት ለሰብአዊ ድጋፍ፣ ለሥራ ፈጠራ እና ለድህነት ቅነሳ የሚውል ይሆናል " ብለዋል።

የIMF ባለሥልጣናት በዚህ ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ የሚያደርጉት ቴክኒካዊ ውይይት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና በተቋሙ መካከል ሰብአዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮችን ለማሻሻል የተደረገ ንግግር ተከታይ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መካከል ሲካሄድ የነበረው የድጋፍ፣ የብድር ስረዛ እና ሽግሽግ ንግግር በከፊል በትግራይ ሲካሄድ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር።

ብሉምበርግ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ጦርነቱ ያስከተለውን ውድመት መልሶ ለመገንባትና የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመሸፈን አስፈላጊ ለሆኑ የገቢ ምርቶች ክፍያ ለመፈጸም ድጋፍ ያስፈልጋታል።

ጦርነቱ ካስከተለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ባሻገር በአፍሪካ ካሉ የመዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች መዳረሻ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን እና ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተነሳ ከዓለም ባንክ (World Bank) አንዲሁም ከIMF የምታገኘውን ድጋፍ ገትቶት መቆየቱን አስታውሷል።

በጦርነቱ እና በዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር የገጠማት ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ከመመዝገቡ በላይ እጥረትም ተከስቷል።

#ቢቢሲ #ብሉምበርግ #ሮይተርስ

@tikvahethiopia