TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
አዲስ የአስተዳደር መዋቅር‼️

3 ዞኖችና 44 ተጨማሪ ወረዳዎች የተካተቱበት አዲስ የአስተዳደር መዋቅር ረቂቅ አዋጅ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ቀረበ።

ረቂቅ አዋጁ የደቡብ ክልል ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 8ተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው #በዛሬው እለት የቀረበው።

አዲሱ ረቂቅ አወቃቀር የመንግስት አገልግሎትን ለወረዳ ማዕከላት ቅርብ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑ ታምኖበታል።

በአዲሱ የአስተዳደር እርከን መሠረት፣ ካሁን በፊት ልዩ ወረዳ የነበረው ሀላባ ወደ ዞንነት ሲያድግ ዌራ ዙሪያ፣ ድጆ ዌራና ድጆ የተባሉ ወረዳዎች እና ቁልቶ ከተማ አስተዳደር ይኖሩታል።

ጋሞ ጎፋ ዞን #ለሁለት ተከፍሎ ጋሞ እና ጎፋ ዞኖች እንዲዋቀር በረቂቅ አዋጁ ላይ ቀርቧል።

በረቂቅ አዋጁ መሰረት ጎፋ ዞን በስሩ ስምንት ወረዳዎች የሚኖሩት ሲሆን፥ ወረዳዎቹም ዲምባ ጎፋ፣ ገዜ ጎፋ፣ ዛላ፣ ኡባ ደብረ ፀሐይ፣ ኦይዳ፣ ሳውላ ከተማ፣ መለኮዛና ጋዳ ወረዳዎች እና ቡልቂ ከተማ በዞኑ አስተዳደር ተዋቅረዋል።

ለብቻው እንደ አዲስ የሚዋቀረው ጋሞ ዞን ደግሞ 13 ወረዳዎች የሚኖሩት ሲሆን፥ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ፣ አርባ ምንጭ ከተማ፣ ደራማሎ፣ ቁጫ፣ ዲታ፣ ካምባ፣ ምዕራብ አባያ፣ ጨንቻ፣ ቦንኬ፣ ሰሜን ቦንኬ፣ ጋርዳ ማርታ፣ ቦረዳ እና ምዕራብ ቁጫ የተባሉ ወረዳዎችን ያቀፈ ይሆናል።

በረቂቅ አዋጁ ከሰገን ሕዝቦች ዞን ወጥቶ በዞንነት እንዲደራጅ የውሳኔ ሀሳብ የቀረበበት ኮንሶ ዞን ደግሞ፣ በስሩ ካራት ከተማ አስተዳደር፣ ካራት ዙሪያ፣ ሰገን ዙሪያና ከና የሚሉ የወረዳ መዋቅሮች ተካተዋል።

በክልሉ ነባር ዞን አስተዳደሮች ተጨማሪ አዲስ የወረዳ አስተዳደር እርከኖች እንዲቋቋሙ በረቂቅ አዋጁ ላይ ቀርቧል።

በሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን አስተዳደር የሚገኙ የቡርጂ፣ አማሮ፣ ዴራሼና አሌ ወረዳ አደረጃጀት በቀጣይ ከሕዝብ ጋር ያለው ውይይት ሲጠናቀቅ የክልል ምክር ቤቱ በሚሰጠው ውክልና መሠረት በመስተዳድር ምክር ቤት እንደሚወሰን ተገልጿል።

በቤንች ማጂ ዞን የተጨማሪ የአዲስ የዞንና የወረዳ አደረጃጀት ጥያቄ በቀጣይ ከሕዝብ ጋር ያለው ውይይት እንደተጠናቀቀ ይወሰናል ተብሏል።

ከቀድሞ የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር የቀረበው የኤዞ ወረዳ መሆን ጥያቄ እና በከንባታ ዞን የቀረበው የአዲሎ ወረዳ ጥያቄም በተመሳሳይ የክልል ምክር ቤቱ በሚሰጠው ውክልና መሠረት በመስተዳድር ምክር ቤት እንደሚወሰን ተገልጿል።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት በዛሬው ውሎውም በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት ሲያደርግ የዋለ ሲሆን፥ በነገው እለትም ውይይት ከተደረገበት በኋላ አዲሱ የመዋቅር አደረጃጀት ረቂቅ አዋጅ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

ምክ ቤቱ በተጨማሪ በእስካሁን ቆይታው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት የተለያዩ ውሳኔዎችን ያስተላለፈ ሲሆን የተለያዩ አዋጆችንም አፅድቋል፡፡

ከነዚህም መካከል የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ፣ የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የጠቅላይ አቃቤ ህግን ለማቋቋም የወጣ አዋጅና ሌሎችም አዋጆች በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።

ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ
@tsegabwolde @tikvahethiopia