TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.7K photos
1.49K videos
211 files
4.06K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
የተማሪ ሊዲያ አበራ ጉዳይ ...

በደቡብ ክልል ሀላባ ቁሊቶ ከተማ በሚገኘው የሀለባ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ #ሊዲያ_አበራ የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ/ም ከትምህርት ቤቷ ተወስዳ ከታሰረች በኋላ ጉዳዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኗል።

ሊዲያ ከታሰራች በኋላ ለ5 ቀናት ፍርድ ቤት ሳትቀርብ መቆየቷን እና በእስር ቤት ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባት አባቷ አቶ አበራ ሻሞሮ እንዲሁም ጠበቃዋ አቶ አበባየሁ ጌታ እንዳገለፁለት ቢቢሲ አማርኛው አገልግሎት በድረገፁ አስነብቧል።

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሕግ እና ፖሊስ ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ወ/ሮ ታሪኳ ጌታቸው የ14 ዓመቷ ተማሪን ጉዳይ ኮሚሽኑ እየተከታተለ መሆኑን ገልፀዋል።

የሊዲያ እስር ምክንያት ምንድን ነው ?

በሀላባ ቁሊቶ 30 ዓመታት የኖሩት አቶ አበራ ሻሞሮ፣ ሁለት ሴት ልጆች የሃላባ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የ10ኛ እና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።

ሊዲያ የካቲት 22/2015 ዓ.ም. በመደበኛ ትምህርቷ ላይ ተገኝታ ነበር።

በዚያን ዕለት ሊዲያ በምትማርበት ክፍል ውስጥ አንዲት ተማሪ መውደቋ የነገሮች ሁሉ መነሻ ነው።

👉 ጉዳዩን በተመለከት ሰሜ አይጠቀስ ያሉ የሀላባ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሰጡት ቃል ፦

" ተማሪዋ የወደቀችው ሊዲያ መተት አሰርታባት ነው በሚል በተፈጠረ ግርግር የትምህርት ቤቱ ሥራ በጊዜያዊነት ተስተጓግሎ ነበር።

ከጥቂት ጊዜ በኋላም ፖሊሶች ወደ ትምህርት ቤቱ መጡ።

ያለምንም መጥሪያ...ፖሊሶች መጥተው ከነዩኒፎርሟ፣ ከነደብተሯ እያለቀሰች” ከትምህርት ቤት ወሰዷል።

ይህ በጣም አሳሳቢ እና የሚያሳዝን ነው። "

👉 የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ወንድሙ መርጋም የሰጡት ቃል ፦

" በዚያን ዕለት ሌላም ተማሪ መውደቋ ለሊዲያ እስር ምክንያት ሆኗል። ሆኖም ታዳጊዋ ላይ ቀደም ብሎ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው አቤቱታ ያቀርቡባት ነበር።

ከእሷ ጋር አብረን ምግብ በልተናል የሚሉ 8 ተማሪዎች ወላጆች ቅሬታ አቅርበዋል፤ ትምህርት ቤቱ እርምጃ ይውሰድ የሚል ጫናም እየበረታ መጥቶ ነበር።

በዚህ ሳቢያ ትምህርት ቤቱ የቅሬታ አቅራቢ ተማሪዎች ወላጆች ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲወስዱ አድርጓል።

በትምህርት ቤት ውስጥ ከእሷ [ሊዲያ] ጋራ ግንኙነት ነበረን፣ ምግብ በልተናል ያሉ 8 ተማሪዎች ወድቀዋል ፤ ይሄ ነገር ከእሷ ጋር ግንኙነት አለው? ወይስ የለውም ? የሚለውን ለማጣራት ነው ክስ ተመስርቶ በዚያው እየታየ ያለው።

በዕለቱ ተማሪዎች ስለተረበሹ እና እርምጃ መውሰድ ስላለብን...ለፖሊስ ልጅቷን በአፋጣኝ ይዛችሁ ብትሄዱ የተሻለ ይሆናል ያልነው። "

ሆኖም ይህ በሊዲያ ላይ የቀረበው ቅሬታ በእህቷ ላይ አልተሰማም ተብሏል።

👉 የሊዲያ ጠበቃ አቶ አበባየሁ ጌታ ፦

" ሊዲያ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰደች በኋላ ከሕግ ውጪ ለ5 ቀናት ፍርድ ቤት ሳትቀርብ ታስራ ቆይታለች።

ከአምስት (5) ቀናት በኋላ ሃላባ መጀመሪያ ፍርድ ቤት ካለ ጠበቃ ጋር ቀርባ የ14 ቀናት ቀጥሮ ለምርመራ ከተሰጠ በኋላ ወደ ሃላባ ቁሊቶ ማረሚያ ቤት ተወስዳለች።

ይህ ድርጊት ከሕግ ጋር የሚጻረር ነው። ለአካለ መጠን ያልደረሰ ሰው በወንጀል ሲጠረጠር ከቤተሰቦቹ ጋር ቆይቶ ለምርመራ ሲፈልግ እንደሚጠራ በሕግ ተደንግጓል።

በተጠረጠረችበት ወንጀል #ጥፋተኛ ሆና ብትገኝ እንኳን የማረሚያ ቤት እስር እንደማይፈረድባት የወንጀል ሕጉ ያስቀምጣል።

በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ላይ ለሃላባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ተጠይቋል። ይግባኙም የታዳጊዋ አያያዝ እንዲሁም ለቀናት በእስር ላይ እንድትቆይ መደረጉ ተገቢ አይደለም የሚል ነው።

የሊዲያ ከሳሾች ጉዳት ደርሶብናል ያሉት ተማሪዎች ወላጆች ሲሆኑ ልጆቻችንን ላይ ባደረገችባቸው መተት/ድግምት አፍዝዛ ጉዳት አድርሳባቸዋለች የሚል ማመልከቻ አቅርበው ነው የተከሰሰችው።

ክሱ ተሰራ በተባለው መተት / ድግምት ተጎድተው ሕክምና ላይ የሚገኙ ተማሪዎች አሉ ይላል።

ሊዲያም ባለፈው አርብ አግኝተናት አናግረናት ነበር። በወቅቱም ንቅሳት ካለብሽ እናይሻለን በሚል እርቃኗን እንደፈተሿት ተናግራለች።

ሊዲያ እስሩ በተፈጸመባቸው የመጀመሪያዎቹ ቀናት ታለቅስ ነበር። አሁን መምህራን፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቿ እና ሌሎች ሰዎች እየጠየቋት በመሆኑ በጥሩ ሞራል ላይ ትገኛለች።

በኢትዮጵያ ሕግ ድግምት ፣ ጥንቆላ፣ እኔ አውቅልሃለሁ ባይነት፣ መንፈስ መጥራት እና መሰል ወንጀሎች የሚዳኙበት ድንጋጌ አለ።

ሆኖም እነዚህ ወንጀሎች ጥቅምን ለማግኘት በማሰብ እና የሌላን ሰው ገንዘብ ለማግኘት የሚፈጸም እንጂ የግል ጥቅም ምን እንደሆነ በማታውቅ ታዳጊ ልጅ፣ ገንዘብ ያለበትን እጠቁማቸኋለሁ ባላለችበት ሁኔታ. . . [ሕጉ] ይህንን ሁኔታ ሊቀበለው አይችለም።

ሰዎችን ለማፍዘዝ የተለያዩ ዱቄት መሰል ምርቶችን ማምረት፣ መሸጥ እና ማሰተላለፍ ወንጀል ነው ሊዲያ ግን ይህንን ሁሉ አላደረገችም።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሕይወቷ የሚያሰጉ ዛቻዎች እና ማስፈራሪያዎች እየተዘዋወሩ ነው። በደረሰባት የሥነ ልቦና ጫና ምክንያት ከሥነ ልቦና ጫናው ተላቃ ትምህርቷን ትቀጥላለች ማለት ይከብዳል። "

👉 የሊዲያ አባት አቶ አበራ ሻሞሮ ፦

" ... የልጄ እስር የተወረወረ ዱብ ዕዳ ነው። ልጆቼ በትምህርታቸው ከአጠቃላይ ተማሪ ተሸላሚ ናቸው። እያጠኑ የሚያድሩ ናቸው።

የተቀረውን የትምህርት ጊዜ ሌላ አካባቢ እንዲጨርሱ እየሞከርኩ ነው።

ልጄም በማረሚያ ቤት ባነጋገርኩበት ወቅት መቼ ነው ከዚህ የምወጣው? ብላ ጠይዋኛለች። "

👉 ጉዳዩን በተመለከተ የሀላባ ዞን የቁሊቶ ከተማ አሰተዳደር ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ከቀናት በፊት በፌስቡክ ገጹ ይህን ብሏል ፦

" ... በከተማችን በሙሰሊም ሴት ተማሪዎች ላይ ድግምት አሲራለች ተብላ በታሰረች ተማሪ ሊዲያ አበራ በተያያዥ ጉዳይ በአቶ ናስር በሀላባ በዚህም ጉዳይ መሰል ተያያዥነት ያላቸው ግለሰቦችም ጭምር ተይዘው በምርመራ ሂደት በማረሚያ መኖራቸው ይታወቃል።

በታሰሩበት ኬዝ እንዳንድ አክቲቪስቶች ጉዳዩን ወደ ሓይማኖታዊ ለማስመሰል በማጦዝ የሚሞክሩ እንዳላችሁ በማሕበራዊ ሚዲያ እየታየ ያለው ሁኔታ በፖሊስ እና በምርመራ ባለሙያዎች ሂደቱ እየተጣራና ማንም በተጠረጠረበት ወንጀል ታሰሮ አንደሚጣራ የሚታወቅ  ስለሆነ ሁሉም ማህበረሰብ በትዕግስት እንዲጠብቅ ስንል እናሳስባችኋለን።

#ይህንን_ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውንም  አካል በህግ የምንጠይቅ መሆኑን እናውቃለን። "

የመረጃ ምንጭ ፦ ቢቢሲ የአማርኛው አገልግሎት / የሀላባ ዞን የቁሊቶ ከተማ አሰተዳደር ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ናቸው።

@tikvahethiopia