TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#update በምዕራብ ኦሮሚያ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የጦር መሪ የሆነው ኩምሳ ዲሪባ ወይም መሮ፤ በምዕራቡ ክፍል የሚገኘው የኦነግ ጦር የትጥቅ ትግል ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናገረ።

መንግሥትን እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን ለማስታረቅ ተዋቅሮ የነበረው ኮሚቴ ትናንት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ባቀረበበት መድረክ ላይ የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከአሁን በኋላ ኦነግ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ የጦር ኃይል አይኖረውም ማለታቸውን ተከትሎ ነው የጦሩ መሪ ይህን የተናገረው።በምዕራብ ኦሮሚያ የጦር መሪ የሆነው ኩምሳ ዲሪባ ወይም መሮ፤ ''የተለወጠ ነገር የለም'' በማለት ከኦነግ ሊቀ መንበር በተለየ መልኩ የኦነግ ጦር የትጥቅ ትግል ማድረጉን እንደሚቀጥል ለቢቢሲ ተናግሯል።

መሮ መከላከያው፣ ፖሊስ እና የደህንነት አካሉ ሙሉ በሙሉ የፓርቲ ወገንተኝነቱን አቁሞ የሕዝብ ወገንተኝነቱን እስካላረጋገጠ ድረስ የመንግሥትን ጥሪ አንቀበልም ብሏል። ''እኛ ለፓርቲ ወግኖ ህዝብን የሚጎዳ የመከላከያ አካል መሆን አንሻም'' ሲል ከዚህ በፊት ከመንግሥት ጋር በተደረሰው ስምምነት የግንባሩ ታጣቂዎች ከመንግሥት የጸጥታና የመከላከያ ኃይል ጋር ለማካተት የቀረበውን ሃሳብ መሮ ውድቅ አድርጎታል።

ጨምሮም ''ለጊዜያዊ ጥቅም ተብሎ በንግግር ተሸፋፍኖ የሚያልፍ ነገር አያዛልቅም። ነገ እሳት መነሳቱ አይቀርም። ዘላቂ መፍትሄ በሚሰጡ ምክክሮች ላይ ለመወያየት ግን ዝግጁ ነን'' በማለት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል።መንግሥትን እና ኦነግን ለማስታረቅ ተዋቅሮ የነበረው ኮሚቴም ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት መሳሪያ አንገበው ጫካ ገብተው የነበሩ የኦነግ ወታደሮች በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንዲቀጥሉ ወይም ወደሚዘጋጅላቸው ስፍራ ለስልጠና እንዲገቡ ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ አስታውሷል።

ኮሚቴው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በተገኙበት ነው ሪፖርቱን ያቀረበው። ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኦነግ ከአሁን በኋላ ጦር አንግቦ የሚንቀሳቀስ ሠራዊት አይኖረውም፤ መንግሥት ሕግ ለማስከበር የሚወስደውን እርምጃም እንደግፋለን ብለዋል።

የአስታራቂ ኮሚቴውን ሪፖርት ያቀረቡት አቶ #በቀለ_ገርባ ሲሆኑ ባቀረቡት ሪፖርት ውስጥ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አንስተዋል። ኦነግ ከአሁን በኋላ #ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ጦር ስለማይኖረው ኮሚቴው የተቋቋመበትን ዓላማ ማሳካቱን ጠቅሰው፤ ኮሚቴው በኦነግ እና በመንግሥት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ታስረው የነበሩ ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቋል። በተጨማሪውም ኮሚቴው ኦነግ በሰላማዊ መንገድ ፖለቲካዊ ትግሉን ለመቀጠል በሚያደርገው እንቅስቃሴ የመንግሥት ድጋፍ እንዳይለይ እና የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደተዘጋጀላቸው ስፍራ የገቡ የኦነግ ጦር አባላት ቃል የተገባላቸው ሁሉ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ኮሚቴው ጠይቋል።

Via #BBC
@tsegabwolde @tikvahethiopia