TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.3K photos
1.46K videos
209 files
4.02K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ETHIOPIA

በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ግጭት ከተቀሰቀሰ በኃላ እስካሁን ምን ሆነ (እጅግ በጥቂቱ) ?

- ህወሓት ቆቦና የአካባቢው ቦታዎችን መቆጣጠሩን ተከትሎ ከፍተኛ የሰው ቁጥር ሰላም እና ደህንነት ፍለጋ ወደ አጎራባች ከተሞች እንዲፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

- እንደ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል በመቐለ በተፈፀመ የአየር ጥቃት 4 ሰዎች ተገድለዋል ፤ 2ቱ ህፃናት ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት ግን ንፁሃንን ዒላማ ያደረገ ጥቃት እንደማይፈፅም በመግለፅ የወጡ ክሶችን አስተባብሎ ነበር።

- ህወሓት በአፋር ክልል " ያሎ " በኩል በሰነዘረው የከባድ መሳሪያ ጥቃት በአካባቢው ንፁሃን ነዋሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የዱብቲ ጠቅለላ ሆስፒታል የገለፀ ሲሆን በጥቃቱ ህፃናት ተገድለዋል። አንዲት እናት ሁለት ህፃናት ልጆቿ በከባድ መሳሪያ ጥቃት ተገድለውባታል። የቆሰሉም በርከት ያሉ ናቸው።

- የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር እንደገለፀው " ወለህ " አካባቢ ህወሓት 10 ሰላማዊ ሰዎችን በግፍ መግደሉን፣ ከሟቾች መካከል አንዲት እናት ከነ ልጆቿ እንደምትገኝበት ገልጿል። በተጨማሪ ቡድኑ ወደ ወለህ መጠለያ ጣቢያ በመግባት 25 ሰዎችን መግደሉን አስተዳደሩ ገልጿል።

- ህወሓት በአፍሪካ ህብረት (AU) መሪነት ለሰላም ንግግር ዝግጁ መሆኑ በገለፀ በሰዓታት ውስጥ ይዟቸው በሚገኙ የራያ ቆቦ ወረዳዎች በንፁሃን ላይ ጥቃት መዘንዘሩን ነዋሪዎች መግለፃቸውን ቪኦኤ ዘግቧል። ህወሓቶች በቀበሌ 02 ሰው መግደላቸው፣ ማቁሰላቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል። ከጥቂት ቀናት በፊትም አራዱም ላይ ሰላማዊ ሰው መግደላቸውን ገልፀዋል። ባለፉት 18 ቀናት ሌሎች ያልታጠቁ ንፀሃን ሰዎችን መግደላቸውና በተጨማሪ ዝርፊያ እንደፈፀሙ ለሬድዮ ጣቢያው ገልፀዋል።

- የመቐለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል እንደገለፀው 2 ጊዜ በተፈፀመ የአየር ጥቃት 10 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የመጀመሪያዎቹን ተጎጂዎች ለመርዳት በተሰበሰቡበት ወቅት በተፈፀመ ጥቃት የተገደሉ ናቸው ብሏል። (ይህ የሆነው ትላንት ነው)

- UN OCHA በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ዳግም ባገረሸ ግጭት በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን አመልክቷል።

እንደ UN OCHA መረጃ ፦

👉 በአማራ ፣ አፋር፣ እና ትግራይ ክልሎች በ10 ሺዎች መፈናቀለቸውን ገልጿል።

👉 የሰብዓዊ እርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ መግባት እንዳቆሙ፣ ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ በረራ እንደተቋረጠ መሆኑን ገልጿል።

👉 በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ለመገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

👉 በመርሳ ከተማ በ5 ት/ቤቶች አብዛኞቹ #ህፃናት እና #ሴቶች ከቆቦ እና አካባቢው ተፈናቅለው ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን ለእነሱ ምግብ እና ምግብ ያልሆኑ ድጋፎችን ማሰራጨት ጀምራለሁ ብሏል።

- የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ለቪኦኤ ሬድዮ በሰጠው ቃል በዞኑ የተፈናቃዮች ቁጥር እጅግ እየጨመረ መሆኑን ገልጾ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጿል። መርሳ በሚገኙ ት/ቤቶቹ ውስጥ ያሉት ሴቶች እና ህፃናት ሲሆኑ ወንዶች ወጣቶች እንዲገቡ አልተደረገም። በአጠቃላይ ወልድያ እና መርሳ ከተሞች ላይ 92,400 ተፈናቃይ አለ።

- ጦርነቱ ዳግም ካገረሸ ወዲህ በርካታ ንብረቶች ወድመዋል።

- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ወደ ባህርዳር ቢሮው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መልዕክቶች እየመጡለት ሲሆን አካባቢዎቹ ላይ ምቹ ሆኔታ ሲፈጠር ምርመራ አድርጎ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።

NB. የተዘረዘሩት ክስተቶች ግጭት ዳግም ካገረሸ ወዲህ #በተለያዩ_ጊዜያቶች የተሰሙ ናቸው።

የሰላም ሂደቱ ምን ያህል ተስፋ ሰጪ ነው ?

የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብረት (AU) መሪነት ለሰላማዊ ንግግር ዝግጁ መሆኑን ከሳምንታት በፊት ገልጾ ነበር።

ህወሓት በአፍሪካ ህብረት (AU) አፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዜዳንት ኦባሳንጆ ላይ እምነት እንደሌለውና በሂደቱ መተማመን እንደሌለው ሲገልፅ ከቆየ በኃላ ከቀናት በፊት በህብረቱ መሪነት ለሚደረግ የሰላም ንግግር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

ይህንን የህወሓት የሰላም ሂደት መቀበል እና ግጭት ለማቆም ዝግጅቱነት እንዳለው መግለፁን በተመለከተ በርካታ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን የተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ውሳኔውን በማድነቅ የሰላም ሂደቱ እንዲፋጠን ጥሪ አቅርበዋል።

ዳግም ያገረሸው ጦርነት ግን አሁንም አልቆመም።

የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ህወሓት ላወጣው መግለጫ በግልፅ ቀጥተኛ ምላሽ ባይሰጥም ትላንት ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋር በተወያዩበት ወቅት መንግስት ለአፍሪካ ህብረት የሰላም ሂደት ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ቁርጠኛ መሆኑን በዩናይትድ ኪንግደም ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ የሆነ መፍትሄ እንዲያገኝ መንግስት ዝግጁነት እንደነበረው ነገር ግን ህወሓት በቅርቡ ወረራ መፈፀሙን ኤምባሲው ዛሬ አመልክቷል።

አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስት ግጭቱ እንዲፈታ የሚያምንበት ብቸኛ አማራች ሰለማዊ መፍትሄ መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ አልጀዚራ ላይ ባወጡት ፅሁፍ መንግስት በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ለሰላም ውይይት ዝግጁ እንደሆነ አስታውሰው ህወሓት የሰላም ጥሪ ገፍቶ ጦርነት ከፍቷል ብለዋል።

ህወሓት የጀመረውን ጥቃት በማቆምም ወደ ሰላም ድርድር እንዲመለስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት ስር ለሚደረገው ድርድር ፍላጎቱን ማሳየቱን ተከትሎ በቃሉ እንዲፀና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከዝምታው በመውጣት የመንግስትን የሰላም አማራጭ በመደገፍ ህወሓት ታጣቂዎቹን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ድርድር እንዲገባ ጫና ማድረግ አለበት ሲሉም አሳውቀዋል።

ህወሓት ወደሰላም እንዲመለስና ሰላምን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና ማድረግ ያለበት አሁን ነው ያሉት አምባሳደሩ ይህ ካልሆነ መንግስት ህዝብን የመጠበቅ ግዴታ ስላለበት ግዴታውን ይወጣል ብለዋል።

ከቀናት በፊት " ህወሓት " ፤ በአፍሪካ ኅብረት (AU) የሚመራ ተዓማኒ የሰላም ሒደት እንደሚጠብቅ ፤ በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ፤ ለድርድሩ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ፣ ለአፋጣኝ እና በሁለቱም ወገኖች ስምምነት ተግባራዊ ለሚደረግ የተኩስ አቁም ዝግጁ መሆኑን መግለፁ እንዲሁም ለግጭት ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ማምጣት የሚቻለድ በሰላማዊ ውይይት ብቻ እንደሆነ እግጠኛ መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል።

@tikvahethiopia