TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.8K photos
1.49K videos
211 files
4.06K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል‼️

ባለፈው ሳምንት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያሶ ከተማ በፈፀመ ጥቃት #ስምንት የአንድ ቤተሰብ አባላት #መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ህዳር 11 ቀን 2011 ማታ ከሶስት ሰዓት በኋላ ታጣቂዎች የቤተሰብ አባላቱን በጥይት ገድለው ቤታቸውንም እንዳቃጠሉ በጥቃቱ ባለቤታቸውንና የባለቤታቸውን ወንድሞች ያጡት የስምንት ልጆች እናት ወ/ሮ #ልኪቱ_ተፈራ ይናገራሉ።

"መጀመሪያ ተኩስ ከከፈቱብን በኋላ ቤት ውስጥ ጭድ ጨምረው እሳት ለኮሱብን። እኔና ልጆቼ በጓሮ በር በኩል አመለጥን። ሌሎቹ ግን እዚያው ተቃጠሉ" በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

ልጃቸው አቶ ወጋሪ ፈይሳ በመኖሪያ ቤታቸው በወቅቱ ሃያ አንድ የቤተሰብ አባላት እንደነበሩና ቤታቸውም ፖሊስ ጣቢያ አቅራቢያ በመሆኑ ደህንነት ተሰምቷቸው እንደነበር ይናገራል።

ነገር ግን ያልጠበቁት ነገር መከሰቱንና በተፈጠረው ነገርም ህፃናት ልጆች ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ እንዳሉም ይገልፃሉ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ ከተማው ውስጥ ግድያ ስለ መከሰቱ መረጃ እንዳላቸው ነገር ግን ዝርዝር ጉዳዮችን እንደማያውቁ ገልፀዋል።

ከጥቃቱ የተረፉ የቤተሰቡ አባላት ሸሽተው የተጠለሉበት አዋሳኝ የምሥራቅ ወለጋ ሃሮ ሊሙ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጋሮማ ቶሎሳ ግድያው ስለመፈፀሙ ማረጋገጫ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አባቴ ፈይሳ ዲሳሳ፣ ወንድሙ ዲንሳ ዲሳሳን ጨምሮ ስምንት የአጎቶቼ ልጆችን አጥተናል። ግድያው በጣም አሰቃቂ ነበር" ይላሉ አቶ ዋጋሪ።

በተመሳሳይ እለት የቤተሰብ አባላቱን ግድያ ጨምሮ በያሶ ከተማ በተፈፀመ ጥቃት አርባ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ኗሪዎችና የአዋሳኝ ወረዳ አስተዳዳሪው ቢናገሩም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊው አቶ ሙሳ ግን አስር ሰው ብቻ ስለመገደሉ መረጃ እንዳላቸው ይገልፃሉ።

ሆኖም ግን ጉዳዩን በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ እንደሚያስፈልጋቸው "መንገድ በመዘጋቱ ነገሮችን በቅርበት ማጣራት አልቻልንም" በማለት ተናግረዋል።

አቶ ሙሳ እንደሚሉት የረቡዕ ጥቃት ከመፈፀሙ ከጥቂት ቀናት በፊት ሁለት የመንግሥት ሰራተኞች ተገድለዋል። አርብ እለትም ደግሞ በካማሼ ሌሎች ሦስት ሰዎች መሞታቸውንም ገልፀዋል።

በያሶ ጥቃቱን የፈፀሙት ታጣቂዎች ከመሆናቸው በዘለለ ስለታጣቂዎቹ እስካሁን ምንም የተረጋገጠ መረጃ እንደሌለ አቶ ሙሳ ይናገራሉ።

'ያፈነገጡ የኦነግ ታጣቂዎች' ለአካባቢው ስጋት እየሆኑ እንደሆነ አቶ ሙሳ ቢናገሩም ያነጋገርናቸው ኗሪዎች እና የአዋሳኝ ወረዳ ሃላፊዎች ግን በአካባቢው #የኦነግ ታጣቂ እንደሌለ ገልፀዋል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አራት የካማሺ ዞን ሃላፊዎች አሶሳ ከተማ ስብሰባ ቆይተው ወደ ካማሺ በመመለስ ላይ ሳሉ በተከፈተባቸው ተኩስ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት ብዙዎች መገደላቸውንና ወደ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት ግን ነገሮችን #ለመቆጣጠር በያሶ ከተማ ፌደራል ፖሊስ፤ በካማሽ ደግሞ መከላከያ ሠራዊት እንደገባ አቶ ሙሳ ገልፀዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ
@tsegabwolde @tikvahethiopia