TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
መቆሚያው የት ነው ?

ባለፉት ዓመት ንፁሃን ዜጎች በተለይ ህፃናት እና ሴቶች እጅግ በጣም አረመኔያዊ በሆነ መንገድ ሲጨፈጨፉ ፣ ሲሳደዱ፣ ከገዛ ቤታቸው ሲፈናቀሉ አይተናል።

ይህን ተከትሎም በርካቶች ሀዘናቸውን እና ቁጣቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ገፆች ላይ ያጋራሉ ፤ ከልባቸው ተጠያቂነት እንዲሰፍን ይወተውታሉ። መንግስት ተቀዳሚ ስራው የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሆነ ደጋግመው ያሳስባሉ።

በአንፃሩ የንፁሃንን ሞት እንዲሁም ጭፍጨፋ ለፖለቲካ መጠቀሚያ እንዲሁም በውስጣቸው ያለውን ጥላቻ ለማንፀባረቅ የሚጠቀሙም ብዙ ናቸው።

አንድ ቦታ ላይ ችግር ሲፈጠር እኩል ከማውገዝ ይልቅ ጉዳዩን ለማብራራት እና ለማስረዳት ወንጀለኞችንም ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ከሀዘንም በላይ ሀዘን ላይ የሚጥል ነው።

ለአብነት ፦ ወደ ኃላ ብዙ ሳንሄድ ከሰሞኑን በጋምቤላ ዜጎች ሲገደሉ ተመልክተናል ፤ ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን ሰዎች ናቸው የተገደሉት ይህን እኩል ማውገዝ ሲጠበቅ የተወሰነ ወገን ብቻውን ስለፍትህ ሲጮህ ነበር።

ቀጠለ ፦ በአማራ ክልል ውስጥ አንድ እጅግ አሰቃቂ ቪድዮ ወጣ ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን ህገወጥ እና አረመኔያዊ ግድያ መሆኑን እርግጥ ነው የተወሰነ ወገን ፍትህ እያለ ጮኸ ፤ ድርጊቱን እኩል ከማውገዝ ጥፋተኞች እንዲጠየቁ ከመጠየቅ ይልቅ ጉዳዩን ለመተንተን እና አድበስብሶ ለማለፍ የጣሩ ሰዎች ብዙ ታይተዋል። ጭራሽ በሌላ በኩል ከሰውነታቸው ይልቅ የማን ወገን ናቸው በሚል የሚከራከሩ ሁሉ ነበሩ ፤ በግልፅ በሚታዩ ሰዎች በጥይት ተረፍርፈው የተገደሉት የሰው ልጆች ሳያሳዝናቸው ጥፋተኞቹን ከለላ ሊሰጡ የሞከሩ በርካታ ነበሩ። ይህ ምን ያህል ከሰውነት እየራቅን እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

ቀጠለ ፦ ምዕራብ ወለጋ ዜጎች በተለይ አንዳች ጥፋት የሌለባቸው ምስኪን ህፃናት እና ሴቶች እጅግ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ተገደሉ ጉዳዩን ለማብራራት ብቅ ያሉ አልጠፉም ፤ እንዴት ምንም ነገር የማይውቁት ጨቅላ ህፃናት አያሳዝኑንም ? ይህ ንፁሃን ላይ የተፈፀመ ግፍ ማብራሪያ ይፈልጋል ? የዛሬውን ጥቃት ከትላንትናው ጋር በማነፃፀር ለማቅለል የጣሩም በርካቶች ናቸው። ጉዳዩን እንዴት ታስጮሃላቹ ለማለት የዳዳቸው ፤ ዓለም ማወቁ ያስከፋቸውም አልጠፉም።

ትንሽ ወደኃላ ብንመለስ በትግራዩ በኃላም ወደ አማራ እና አፋር በተስፋፋው አስከፊ ጦርነት ወቅት ሴቶች አልተደፈሩም ፤ ንፁሃንም አልተገደሉም ሁሉም ነገር ውሸት ነው እያሉ ሲያላግጡ የነበሩም ብዙ ናቸው።

ውድ ቤተሰቦቻችን ፤ ይህ የቅርብ ጊዜው ነው ባለፉት ዓመታት ምን ሲሆን እንደነበር ከናተ አንዳች የተደበቀ አይደለም ፤ በአንድ ሀገር ውስጥ አንዱ ቦታ ሰው እያለቀሰ ሌላው እየተደሰተ በሰው ሀዘን እያላገጠ ፤ እንዴት የአንድ ሀገር ዜጎች ነን ማለት ይቻላል ? ሌላው ይቅር እኩል መደሰት ባንችል እኩል ማዘን እንዴት ያቅተናል ? የግድ ሀዘን ሁሉም ጋር መድረስ አለበት ? ከሰውነት ተራ እየወጣን ነው ፤ ያለፈው መማሪያ ሆኖ ዛሬ ካልታረምን የነገው ያስፈራል።

ስለዚህ መቆሚያው የት ነው ? ብለን ነገ ሳይሆን ዛሬ ልጓም ልናበጅለት ይገባል። ሁሉም ዜጋ ለፍትህ እና ለንፁሃን እኩል ካልቆመ ለውጥ ሊመጣ አይችልም።

ሌላው ይቅር ቢያንስ ለቀጣዩ ትውልድ ፤ ለታዳዊዎቹ ስንል ውስጣችን መፍተሽ ይኖርብናል ፤ እውነት የሰው ልጅ ሞት ስቃይ በሰውነቱ ብቻ ይሰማኛል ? ወይስ የኔ ብሄር፣ ዘመድ ፣ ጓደኛ ፣ ተመሳሳይ ሃይማኖት መሆን አለበት ለማዘን ? ደግመን ደጋግመን ራሳችንን መጠየቅ አለብን።

በሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅ ፣ ምዕራብ ሀገራችን ክፍል ስንቶች ወጥተው ቀሩ፣ የስንቶች ተስፋ መና ሆኖ ቀረ፣ የስንት እናቶች እና አባቶች እንባ ፈሰሰ፣ ስንት ትንንሽ ልጆች ያለቤተሰብ ቀሩ፣ ስንት ወጣቶች ረገፉ፣ ስንት ወገኖቻችን ሜዳ ላይ ወደቁ ፍትህ ለሁሉም ተጎጂዎች ይገባል።

የዜጎች ደህነት እንዲሁም በህይወት የመኖር ዋስትና በመግለጫ ጋጋታ አይጠበቅም ፤ አይረጋገጥምና ሁሉም መሬት ላይ የሚታይ ስራ ሰርቶ ፣ የሚከፈለው ዋጋ ተከፍሎ ንፁሃንን መጠበቅ፤ የተበደሉትን መካስ ፤ ያዘኑ የዜጎችን እንባ ማበስ እንዲሁም ደግሞ ህግና ስርዓት ነው የሚያስተዳድረን ከተባለ ጥፋተኞችን ፣ ከላይ እስከታች ያሉ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡትን መቅጣት ያስፈልጋል። ወሬ ያለተግባር ምንም ለውጥ አያመጣም።

በዚሁ አጋጣሚ ፥ #ልጆች_ያላችሁ የቲክቫህ አባላት ወላጆች ልጆቻችሁ የሚያዩትን እና የሚሰሙትን ነገር እንድትቆጣጠሩ ይሁን ፤ የማህበራዊ ሚዲያው በጥላቻ በአስከፊ ድርጊቶች፣ ምስሎች ፣ ቪድዮዎች ተሞልቷል። ቢያንስ ቀጣዩን ትውልድ መታደግ ይገባል በጥላቻ ታውሮ እንዳያድግ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል።

(Tikvah Family)

@tikvahethiopia