TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.4K photos
1.47K videos
209 files
4.04K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
የሀሰት ዋጋው‼️

እሳት፣ ውሃ፣ እውነትና ሃሰት የሚባሉ ጓደኛሞች ነበሩ። በዚህ ጓደኝነታቸው ግን ሃሰት ብዙም አልተደሰተም። ጥምረቱም ደስተኛ አላደረገውም። ስለዚህም #አንድነታቸውን ማበላሸት ፈልጎ እንዲህ አለ፤ «ለምን ወደ አንድ ስፍራ ተጉዘን እያንዳንዳችን የራሳችንን ግዛት አንመሰርትም? ስለዚህ ተነስተን አብረን እንጓዝ።»

ሁሉም በሃሳቡ ተስማምተው ሲሄዱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ #ሀሰት ወደ #ውሃ ጠጋ ብሎ «እሳት ሳሩን፣ ደኑንና ቁጥቋጦውን የሚያቃጥል ቀንደኛ ጠላታችን ስለሆነ ለምንድነው ከእርሱ ጋር ግዛት ፍለጋ የምንሄደው?» አለው። ውሃም «ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?» ሲል መልሶ ጠየቀው።

ሃሰትም ቀበል አድርጎ «ልንገድለው እንደሚገባ ግልፅ ነው፤ እሳትን የማጥፋት ብቸኛ ኃይል ያለህ ደግሞ አንተ ነህ። እናም ቁጭ ሲል ጠብቀህ እላዩ ላይ ራስህን በመርጨት አጥፋው» አለው። ውሃም «ራሴን መሬቱ ላይ ከረጨሁ ተመልሼ ውሃ መሆን አልችልም» አለ። ሀሰትም «ችግር የለውም፤ ተረጭተህ እንዳትበታተን የተወሰኑ ድንጋዮች በዙሪያህ አኖርና በኋላ እሰበስብሃለሁ» አለው።

በዚህ ጊዜ የተሸረበበትን ተንኮል ያልጠረጠረው እሳት ቁጭ ሲል፤ ውሃው አንድ ጊዜ በላዩ ላይ ሲረጭ ሃሰት ድንጋዮች ዙሪያውን አድርጎ ውሃውን ከሰበሰበውና እሳትን ካስወገዱ በኋላ አብረው መጓዝ ጀመሩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሃሰት ውሃውን «ለምን እዚህ ገደል አፋፍ ላይ ቁጭ ብለህ በተፈጥሮ ውበት አትዝናናም?» አለው። ውሃም አፋፉ ላይ ቁጭ ሲል ሃሰት ቀስ ብሎ ተነስቶ ውሃ የተቀመጠባቸውን ድንጋዮች ከስሩ ሲለቅማቸው ውሃው በዚያው ተበታትኖ ጠፋ።

በመጨረሻም ሃሰት እውነትን ማጥፋት ነበረበትና ወደ አንድ ትልቅ ተራራ በተቃረቡ ጊዜ ሃሰት እውነትን ከተራራው ግርጌ ቁጭ በል ብሎት ከተራራው አናት ላይ ትልቅ አለት ቁልቁል በመልቀቅ እውነትን ሊጨፈልቀው ሲል እውነት ቀልጠፍ ብሎ ማምለጥ በመቻሉ አለቱ ተንከባሎ ሲፈረካከስ ከውስጡ አልማዝ፣ ወርቅና ልዩ ልዩ የከበሩ ማዕድናት ወጡ። ሃሰትም የእውነትን አስከሬን ሊመለከት በመጣ ጊዜ እነዚህን ሁሉ የከበሩ ድንጋዮች አየ። እናም «እነዚህ ሁሉ ከየት መጡ?» ብሎ ጠየቀ። እውነትም «አለቱ እላዬ ላይ ሲወድቅ እነዚህ ማዕድናት ወጡ» ሲል መለሰለት። በዚህ ጊዜ ሃሰት «አሁን ደግሞ እኔ ከተራራው ግርጌ ልቀመጥና አንተ አለቱን በላዬ ላይ ልቀቅብኝ» አለው። እናም እውነት ወደ ተራራው ጫፍ ወጥቶ ትልቅ አለት ወደታች በለቀቀ ጊዜ አለቱ የሃሰት አናት ላይ አርፎ ሃሰትን ጨፈላልቆ ገደለው። ይህ የሚያሳየው ሀሰት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍልና እውነት ፈተና ቢገጥመውም በመጨረሻ አሸናፊ እንደሚሆን ነው። በተለይ አሁን በሀገራችን የሀሰት መረጃ እያደረሰ ካለው ጉዳት ጋር ስናነጻጽረው ትልቅ መልዕክት ይሰጠናል።
የማገናዘብና ትክክለኛውን መረጃ አውቆ ወደ ተግባር መግባት ላይ ብዙዎች ችግር አለባቸው። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ የሀሰት ወሬ ነው። ይህንን አድርግና ይህንን ታገኛለህ የሚለው የተሳሳተ መስመር ብዙዎችን ባልተገባ መንገድ እንዲጓዙ አድርጓቸዋል። ሰው በሰው ላይ በክፋት አስነስቷል። እውነቱ እንደ እውነትነቱ መጨረሻ ማሸነፉን የሚዘነጋ ሰው አይጠፋም።

በእርግጥ በሌሎች ስህተት ውስጥ አለመሳተፍ ዋጋ ይኖረው ይሆናል። ልክ እንደ እሳት ማለት ነው። ነገር ግን እንደ በሀሰት ዝም ብሎ ሰዎችን ማባላትና ማገዳደል መጨረሻው ራስን ለጉዳት ይዳርጋል፡፡ የህግ ተጠያቂነትም ያስከትላል። በአገሪቱ ውስጥ እሳትን የሆኑ፣ ሀሰትን የሆኑ እንዲሁም እውነትን የሆኑ ሰዎች አሉ።

እሳትን የሆኑት የሚደረገውን የማያውቁ የራሳቸውን አለም ብቻ የሚኖሩ ናቸው። ሀሰትን የሆኑት ደግሞ የሰዎች ሰላም ማጣትና መባላት የሚያስደስታቸው፤ ሁሉ ነገር የእኔ ብቻ የሚሉ፤ ‹‹እኔ ከሌለሁ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው እንስሳ ናቸው። እውነትን የሆኑት ግን ለአንዲት አገር ለውጥ የቆሙና የአገር መለወጥ የእኔ ለውጥ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው።

በአንድ አገር ውስጥ የተለያየ ፍላጎት፣ የተለያየ ርዕዮተ አለምና፣ የተለያየ የትግል ስልት ይኖራል። ሆኖም አንድ ነገር ላይ ግን መግባባት ያስፈልጋል። የሁሉም ጥረት እውነትን ለመገንባት መስራት መሆን አለበት። ምናልባት አንዳንዶቹ ይህ እውነት ተግባራዊ ሆኖ ላያዩት ይችላሉ። ግን አሻራቸው ይኖርበታል። ለቀጣይ ትውልድም መልካም ታሪክ ማስተላለፍ ይችላሉ። በእውነት ለመኖርና ሃገርን ለመገንባት እውነትን መስራት ነው የሚያስፈልገው።

«ልታየው የምትፈልገውን ለውጥ መጀመሪያ አንተው ራስህ ሁነው» እንዲል ማኅተመ ጋንዲ፤ ለለውጥ በቆረጡ፣ መለወጥ እንችላለን ብለውም በሚያስቡ፣ ከዕለት ጉዳይ አልፈው ታላቁን ሥዕል ለማየት በሚችሉ ሰዎች እውነትን ገንብቶ አገርን በለውጥ ጎዳና ውስጥ ለማስኬድ መጣር ይገባል። ለዚህ ደግሞ ስለ እውነት ሁሉም በእኩል ደረጃ፣ አቅም፣ ችሎታ፣ ዕውቀት እና ሥልጣን መሟገትና መስራት አለበት። ምክንያቱም ሀሰተኞች ለራሳቸውም ሆነ ለአገር አይጠቅሙም፤ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸው በእውነት መረታት ነው፡፡

ምንጭ፦ አዲስ ዘመን
@tsegabwolde @tikvahethiopia