TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.4K photos
1.48K videos
209 files
4.04K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ሾኔ

ከ500 በላይ የሾኔ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ላይ እንደሚገኙ ተሰማ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፤ ሐዲያ ዞን ሾኔ ከተማ ፣ ላለፉት 3 ወራት የተቋረጠባቸው ደመወዝ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን የገለጹ የሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሠራተኞች በሥራ ማቆም አድማ ላይ እንደሚገኙ ቪኦኤ አማርኛ ዘግቧል።

በጊዜያዊ ውል የተቀጠሩትን ጨምሮ ከ500 በላይ የሆስፒታሉ ጠቅላላ ሠራተኞች እንደተስማሙበት በጠቀሱት በዚሁ የሥራ ማቆም አድማ ምክንያት ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆን ሕዝብ አገልግሎት ይሰጣል የተባለው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሉ ሥራ ከአቆመ 7 ቀን እንዳለፈው ሠራተኞቹ ተናግረዋል፡፡

አንድ ስማቸውን ለደህንነታቸው ሲባል እንዲገለፅ ያልፈለጉ የሆስፒታሉ ሰራተኛ ፤ " የባጀት እጥረት እየተባለ፣ ከባጀቱም ከፍቶ አሁን ደግሞ የነሃሴ ፣ መስከረም ሙሉ ወር ደመወዝ አልተከፈለም። አምናም ደሞዝ ሳይከፈል ቀርቶ ብዙ ባለሞያዎች ስራ ለቀው ሲሄዱ ነበር። እኛ ያለነውም ደመወዝ ሳይከፈለን ስራ መስራት አንችልም ብለን ነው ለቀን የወጣነው " ሲሉ ተናግረዋል።

" ለረሃብ እና ለአደጋ ተጋልጠናል፤ ደመወዝ ሳይከፈል እንዴት እንሰራለን ? እኛ እየተራብን ምንድነው የምንሰራው መጀመሪያ እኛ እራሱ መታከም አለብን ፣ እኛ መዳን አለብን ብለን ነው ያቆምነው፤ ከሁለት ዓመት በፊትም ያልተከፈለ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አለ የሁለት ወር ክፍያ የት እንደሄደም አይታወቅም። ማንም ባለሙያውን እንደ ባለሙያ እየቆጠረው አይደለም በሚል ነው በቁጣ ለቀን የወጣው " ሲሉ አክለዋል።

" በከተማው ሌላ ሆስፒታል የሌለ ሲሆን ያሉት የተወሰኑ ጤና ጣቢያዎች ነበሩ እነሱም ከተዘጉ ቆይተዋል። ለምን ተዘጋ ? የሚል አካልም የለም " ብለዋል።

የሆስፒታሉ የተኝቶ ታካሚዎች ክፍል አስተባባሪ ዶ/ር ፋብዩ አየለ ፤ " ከ7 ቀን በፊት የድንገተኛ ክፍል ብቻ የተወሰኑ ሰዎች ተመርጠው ይሰሩ ነበር ፤ ይከፈላችኃል ተባለ ዛሬ ነገ ሲባል 72 ሰዓት ሆነ የሚከፍል የለም ከዛ በኃላ ነው ሁሉንም ክፍሎች ለመዝጋት የወሰኑት። አብዛኛው ሰራተኛ ከሌላ ቦታ የመጣ አለ፤ የቤት ኪራይ፣ የሚበላ የሚጠጣ ያጣ አለ የሚከፍለውን ያጣው አብዛኛው ሰራተኛ ወደ ቤት ሄዷል ቤተሰቡ ጋር እዚህ ተወላጅ የሆነውም ቤት ኪራይ፣ መብላት መጠጣት አለ 3 ወር ሙሉ አልተከፈለንም። አሁንም እየጠየቅን ነው ልንከፍል አንችልም የተሰጠን ብር ጎሏል አይነት ነገር ነው የሚያወሩት " ብለዋል።

ዶ/ር ፋብዩ ፤ ከዚህ ቀደምም 2012 የሁለት ወር የትርፍ ሰዓት ክፍያ መበላቱን፣ በ2015 የጥቅምት ወር በተመሳሳይ እንዳልተከፈለ አስታውሰው አሁን በጣም ሲከፋ ሰራተኛው ስራ ማቆሙን ጠቁመዋል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ተድላ አካሉ፤ ሆስፒታሉ ሥራ ማቆሙን አረጋግጠዋል።

በተለይ የድንገተኛ ክፍልና ማዋለጃ ክፍል አገልግሎት ሲሰጡ የነበረ ሲሆን ከ3 ቀን በፊት አንስቶ እሱም እንደተቋረጠ ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪ ሆስፒታሉ አገልግሎት እየሰጠ ባለመሆኑ ወደሌሎች አካባቢዎች ለመሄድ መገደዱን ጠቁመዋል።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ መለሰ ተሰማ ሆስፒታሉ ሥራ ማቆሙን ባይክዱም መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

የሐዲያ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታከለ ኦልባሞ ከሬድዮ ጣቢያው ስልክ ሲደወልላቸው #ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ጠቅሰው " እዚያው ሆስፒታሉን ጠይቁ " የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ ከ600 ሺህ በላይ ህዝብ ተደራሽ ያደርጋል፣ በቀንም እስከ 200 ታካሚ ያስተናግዳል የተባለለት ሆስፒታል ስራ በመቆሙ ህዝቡ እንግልት እየደረሰበት ይገኛል።

መረጃው የቪኦኤ ሬድዮ (ዮናታን ዘብዲዮስ) ነው።

@tikvahethiopia
#ሚዛን_ቴፒ_ዩኒቨርሲቲ #ኦዲት

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በ2014 ዓ / ም በጀት ዓመት ሲንከባለሉ የቆዩ የሒሳብ ጉድለት እንዳሉበት በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ወጪ አስተደደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታውቋል።

ይህንን ያስታወቀው የዩኒቨርሲቲውን የ2014 ዓ/ም በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ሕጋዊነትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው።

የዩኒቨርሲቲው የሒሳብ የኦዲት ጉድለቶች ተብለው በቋሚ ኮሚቴው የቀረቡት ምንድናቸው ?

- ለዩኒቨርሲቲው ማስፋፊያ ቦታ ለባለ ይዞታዎች ካሳ ቢከፈልም እስካሁን ከቦታው አልተነሱም። ለባለ ይዞታዎቹ የካሳ ክፍያ ቢፈጸምላቸውም ምንም ዓይነት ሰነድ (ካርታ) አላቀረቡም ፤ ግለሰቦቹ በመሬቱ ላይ ያላቸው ሀብትና ንብረት በሚመለከተው አካል ሳይረጋገጥ ክፍያ ተፈፅሟል። ተነሺዎቹ በገቡት ውል መሠረት የካሳ ክፍያው በተፈጸመ በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ይዞታቸውን እንዲለቁ ቢጠበቅም፣ አንድም ግለሰብ ቦታውን አለቀቀም።

- ከተጋባዥ መምህራን ያልተሰበሰበ ቅድመ ግብር ፣ ለአካዴሚክ የሕክም እና ባለሙያዎች ከደንብና ከመመርያው ውጪ " ቶፕ አፕ " ተብሎ በድምሩ ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ቢጠየቅም እስካሁን ድረስ ግን አልተስተካከለም።

- በሥራ ገበታቸው እያሉ #ስብሰባ (ኮንፈረንስ) ለ2 ቀናት ለተሳተፉ ሠራተኞች የ18 ቀናት የውሎ አበል በቀን 171 ብር ተሠልቶ ያላግባብ ተከፍሏቸዋል።

- የተሟላ መረጃ ሳይቀርብ በወጪ መመዝገብ፣ ቀኑን በመጨመር ያላግባብ የውሎ አበል መክፈል፣ ከቀረበ ማስረጃ በላይ አስበልጦ መክፈልና የተሽከርካሪ ዕቃዎች  ግዥ ሲፈጸም ያለ ደረሰኝ (በዱቤ) ሽያጭ ደረሰኝ 3,259,439 ብር ክፍያ ተፈፅሟል።

- በግባንታ ላይ ያሉ ' 12 ፕሮጀክቶች ' በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለአገልግሎት አልዋሉም። ተቋራጮቹ በገቡት ውል መሠረት መሥራታቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ከግንባታ ክፍል በተገኘው መረጃ መሠረት በርካታ ክፍተቶች ተገኝተዋል።

ከዚህ ውስጥ ፦

* ሉሲ ኮንስትራክሽን የተሰኘ የኮንስትራክሽን ኩባንያ 233,432,359.95 ብር ለቴፒ ካምፓስ የመማሪያ ሕንፃ ግንባታና ለመምህራን አዳራሽ ሚያዝያ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲያጠናቀቅ በውሉ ቢገለጽም፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ግንባታው 56 በመቶ ላይ ብቻ ይገኛል።

* ኮንስትራክሽን ተቋራጩ (ሉሲ) በ73,652,906.05 ሳንቲም ለጂምናዚየም ግንባታ ሐምሌ 11 ቀን 2008 ዓ.ም.  ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 15 ቀን 2012 ማጠናቀቅ እንደሚገባው፣ ተቋራጩ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ሳይጨርስ ሌላ ፕሮጀክት ተሰጥቶታል።

* የውኃ አቅርቦት ግንባታ በ 300,283,120.83 ብር በጀት ሉሲ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ግንባታውን እንዲያጠናቅቅ ፕሮጀክቱ ቢሰጠውም፣ ግንባታው እስካሁን አሥር በመቶ  ላይ ይገኛል።

- ለግንባታና ለጥገና ለተደራጁ ማኅበራት ቅድመ ክፍያ ሲሰጥ ካደራጇቸው የመንግሥት ተቋማት የዋስትና ደብዳቤ ሳያቀርቡ 4,918,356.18 ብር ተከፍሏል።

በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ዕርምጃ ያልወሰደበት #ከ46_ሚሊዮን_ብር_በላይ የሚሆን የበጀት ጉደለት ቢኖርም ማስተካከያ የተደረገበት የበጀት ጉድለት አንድ በመቶ/1% አይሆንም ተብሏል።

ቋሚ ኮሚቴው ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የኦዲት ግኝት አስተያየቶችን ለማረም እያደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑን ከዚህ በኋላ ኃላፊነታቸውን በማይወጡ ኃላፊዎች ላይ ተገቢው ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት፣ ሕጎችንና መመርያዎችን ማክበር እንደሚገባ አሳስቧል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤ ምን አለ ?

- በዩኒቨርሲቲው ሕጋዊ ሒደትን ያልተከተለ የግንባታ ፕሮጀክቶች ውል፣ ተገቢ ያለሆነ የአበል ክፍያ፣ ለባለ ይዞታዎች ያለ በቂ መረጃ የተከፈለ የቦታ ካሳ ክፍያና ያለ በቂ የአዋጭነት ጥናት የተጀመሩ የገቢ ማመንጫ ሥራዎች በኦዲት ግኝት ተረጋግጧል።

- በተያዘላቸው ጊዜ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መኖር፣ በማዕቀፍ መከናወን የነበረባቸው ግዥዎች በግለሰብ መፈጸማቸው፣ ሕጋዊ ደረሰኝ ያልተገኘላቸው ግዥዎች መኖራቸውን ጨምሮ፣ በዩኒቨርሲቲው ዕርምጃ ያልተወሰደበት የኦዲት ግኝት ከ59 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲደርስ አድርጎታል።

- ዩኒቨርሲቲው የውስጥ ቁጥጥርና የኦዲት ሥርዓት ደካማ በመሆኑ፣ ከ200 ሺሕ ብር በላይ ወደ ግለሰብ ኪስ እንደገባና ሕጋዊ ሒደቱን ባልተከተለ ግዥ መንግሥት ከ1.9 ሚሊዮን ብር በላይ አጥቷል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ ምን አሉ ?

- የኦዲት ግኝቶችን ለማረም ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው።

- በዩኒቨርሲቲው የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ የበጀት እጥረት፣ የፀጥታ ችግርና የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ መናር ምክንያቶችች ናቸው።

- የበጀት እና የንብረት አጠቃቀምን ለማስተካከል የዕውቀት ክፍተት አለ፤ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን የሰው ኃይል የማብቃት ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።

- የካሳ ክፍያ የተከፈለባቸው ከ60 በላይ ይዞታዎች ውስጥ 46 ያህሉን ዩኒቨርሲቲው ተረክቧል። ሕግና ሥርዓትን በጣሱ ግለሰቦች ላይ የዕርምት ዕርምጃ እየተወሰደባቸው ነው።

መረጃው ከሪፖርተር ጋዜጣ የተገኘ ነው።

@tikvahethiopia