TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
የመሮ ምክትል የሰላም ጥሪውን ተቀበለ‼️

የ'ጓድ' መሮ ምክትል እና 'ዲነራስ' በሚለው የትግል ስም የሚታወቀው ሁንዴ ዴሬሳ ከቀናት በፊት የአባ ገዳዎችን ጥሪ ተከትለው የጦር አባላቱን ይዞ ወደ ተዘጋጀለት ስፍራ ገብቷል።

ሁንዴ ዴሬሳ የአባ ገዳዎችን የሰላም ጥሪ የተቀበለውና ወደ ተዘጋጀው ስፍራ የገባ የመጀመሪያው የኦነግ የጦር አዛዥ ነው ተብሏል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ምክትል ጦር አዛዥ የሆነው ሁንዴ ዴሬሳ ወደፊትም ቢሆን በኦሮሞ እና የኦሮሚያ መብትን ለማስከበር መታገላችንን እንቀጥላለን ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ቅዳሜ ዕለት በአባ ገዳዎች አቀባበል ተደርጎለት የነበረው የጦር አዛዡ ተከታዮቹ በአምቦ ሰንቀሌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ቆይታ ካደረጉ በኋላ ዛሬ ወደ ጦላይ የወታደር ማሰልጠኛ ማዕከል መሄዳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የጦር አዛዥ የሆነው መሮ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ''ወደፊት መራራ ትግል ማድረጋችንን እንቀጥላለን። ብቻዬን ብቀር እንኳ ትግል ማድረጌን እቀጥላለሁ እቅዴም ይሄው ነው" ሲል መናገሩ ይታወሳል።

ሁንዴ ዴሬሳ እንዴት የአባ ገዳዎችን ጥሪ ለመቀበል እንደቻለ ሲያብራራ ''ይህ የህዝብ ፍላጎት ነው። ህዝቡ የሚፈልገው ይህን ነው። 'በኦሮሞ ጉዳይ ላይ ኑ አብራን እንሥራ' ብለው ጥሪ ስላቀረቡልን ከሠራዊቱ ጋር ከተወያየን በኋላ ጥያቄያቸውን ተቀብለናል'' ብሏል።

''የኦነግ የምዕራብ ኦሮሚያ ዞን በሁለት ተከፍሎ ነው የሚተዳደረው። ከጊምቢ በታች መሮ ነው ትዕዛዝ የሚሰጠው። ከጊምቢ በላይ እንደ ነቀምቴ፣ ሻምቡ እና ምዕራብ ሸዋ ደግሞ ትዕዛዝ የምሰጠው እኔ ነኝ'' የሚለው ሁንዴ የዕዝ ተዋረዱን ሲያስረዳ ''መሮ ከሊቀመንበሩ [#ዳውድ_ኢብሳ] ትዕዛዝ ይቀበልና ለእኛ ያስተላልፋል'' ብሏል።

የሁንዴ የትግል አጋር እና አዛዥ የሆነው ኩምሳ ዲሪባ ወይም መሮ "የእርቅ የተባለው ኮሚቴ እኔን በአካል አግኝተው ለማነጋገር ፍላጎት የላቸውም። ትኩረት ያደረጉት ጦሩን አንድ በአንድ እጁን እንዲሰጥ ማድረግ ላይ ነው" በሚል እና በሌሎች ምክያቶች ጥሪውን እንደማይቀበል አርብ ዕለት ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

በዚህ ላይ ሁንዴ አስተያየቱን እንዲሰጥ ተጠይቆ ''ይህን ትግል ህዝቡ የሚፈልግ ከሆነ አንድ መቶ ዓመት እንኳ በትግል ላይ እንቆያለን። የምንታገለው ለህዝቡ እስከሆነ ድረስ ህዝቡ የምፈልገው ሰላማዊ ትግል ነው እስካለ ድረስ የህዝቡን ስሜት ማዳመጥ ይኖርብናል። እሱ [መሮ] የግል አቋሙ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ማዳመጥ ያለብን የግል ስሜታችንን ሳይሆን የህዝቡን ፍላጎት ነው'' በማለት ''የአባ ገዳዎችን ጥሪ ከሰማን በኋላ ከመሮ ጋር ተገናኝተን ተነጋግረን ነበር። የእርቅ ጥሪውን ከተቀበልን በኋላ ሃሳቡን ቀየረ'' ሲል የነበረውን ሁኔታ ገልጿል።

የመሮን ውሳኔ በተመለከተም ''ሽንፈት መሰለው፤ ሰው የሚለውን መቀበል ላይ ትንሽ #ድክመት አለበት። #ብቸኝነትም ያጠቃዋል፤ ከዚህ ውጪስ ሌላ ችግር የለበትም" ብሏል።

መሮ ከቀናት በፊት ለቢቢሲ እንደተናገረው ''ከዚህ የተለየን ጦር 5 በመቶ እንኳ አይሆንም። 95 በመቶ አሁንም እንደታጠቀ ነው የሚገኘው" ብሎ ነበር። የመሮ ምክትል የሆነው ሁንዴ እንደሚለው ከሆነ ግን የእርቅ ጥሪውን ተቀብለው የወጡ የኦነግ ወታደሮች በጫካ ከሚገኙት ይበልጣሉ።

''በእኔ ስር የነበሩ የሠራዊት አባላት በሙሉ የእርቅ ጥሪውን በደስታ ተቀብለውታል፤ በጫካ የቀሩት አባላት 'የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ እስኪመለስ እንታገላለን የሚሉት ናቸው'' በማለት ተናግሯል።

በኦነግ ጦር አባላት መካከል የእርቅ ጥሪውን እንቀበል፤ አንቀበል በሚል የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሯል ወይ ብለን ለጠየቅነው ጥያቄ፤ ሁንዴ ሲመልስ ''ይህ በደንብ ያለ ነው። እኔ እንደማውቀው እንኳ ሦስት ቦታ ተከስቷል'' ብሏል።

ምንጭ፦ BBC አማርኛ
@tsegabwolde @tikvahethiopia