TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.91K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#አማራ

ቤተሰቦቻቸው በአማራ ክልል የሚገኙ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት በክልሉ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት በየዕለቱ የበርካታ ሰዎች ህይወት እያለፈ፣ ንብረት እየወደመ ፣ ቀድሞም የደቂቀው ኢኮኖሚና የኑሮ ሁኔታ እየባሰበት እየሄደ መሆኑን ገለፁ።

ለችግሮች መፍትሄ እንዲፈለግም ጠይቀዋል።

ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ ቤተሰቦቻቸው ጎጃም ውስጥ እንደሚኖሩ የገለፁ አንድ የቤተሰባችን አባል፤ " ህዝቡ በሰላም እጦት መሰቃየት ከጀመረ ወራት ተቆጠሩ " ብለዋል።

እሳቸው ባላቸው መረጃም በጦርነቱ በርካታ ሲቪል ሰዎች ሰለባ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ቤተሰቦቻቸው ባሉበት አካባቢ ያለው ግጭት አንዴ እየቀዘቀዘ ዳግም ደግሞ እያገረሸ ወራት መቆጠሩን በመግለፅ ሁኔታው ለእርሻ፣ ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አዳጋች እንደሆነና በዚህም ህዝቡ ሁለንተናዊ ስቃይ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

" ያለፉት ዓመታት ጦርነት ያሳጣንን ማስታወስ ይገባል " ያሉት እኚሁ ግለሰብ በአስቸኳይ ሰላማዊ መፍትሄ ተገኝቶ ህዝቡ በተለይ ገበሬው ወደቀደመው ስራ ካልተመለሰ ቀጣይ የሚመጣው ቀውስ እጅግ የከፋ ነው ብለዋል።

ደብረ ማርቆስ ውስጥ እናት እና አባቷ እንዳሉ የገለፀች የአዲስ አበባ የቲክቫህ ቤተሰብ አባል ስለ ቤተሰቦቿ መጨነቅ ከጀመረች ወራት እንዳለፈ ተናግራለች።

" ዘውትር እንቅልፍ የለኝም፤ ከዛሬ ነገ ምን ይፈጠራል እያልኩኝ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከወደኩ ይኸው ሳምንታት አልፈዋል " ብላለች።

ጦርነቱ የሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ከመሆኑም በላይ ኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ነው የምትለው ይህች የቤተሰባችን አባል መፍትሄ እንዲፈለግ ርብርብ ይደረግ ስትል ተማፅናለች።

ሌላው አንድ በአማራ ክልል ቤተሰቦቹ የሚገኙ የቲክቫህ ቤተሰብ አባል፤ እሱን ጨምሮ ሌሎችም ያለ አንዳች ጥፋት " የፋኖ ደጋፊ ናችሁ " በሚል ለእስር ተዳርገው እንደነበር በመግለፅ ጦርነቱ እየፈጠረው ያለው ቀውስ ሁለንተናዊ ነው ብሏል።

በርካቶች አሁንም በጥርጣሬ ብቻ በእስር እየማቀቁ፣ ቤተሰብም እየተሰቃየ ነው፣ ይህንን ስሜት በቦታው ላይ ካልሆነ ማንም አይረዳውምና ስቃዩና መከራው ያበቃ ዘንድ መፍትሄ እንዲፈለግ ተማፅኗል።

ሌላው አንድ የሚወዳቸውን ሰዎች በዚሁ ጦርነት የተነጠቀ የቤተሰባችን አባል #አሉታዊ ነው ያለውን የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ የተቃወመ ሲሆን ለተገደሉት ለተገፉት ወገኖች ፍትህ ጠይቋል።

" #አንዳንዶች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ብቻ ቀኑን ሙሉ ሲሰዳደቡ፣ ሲበሻሸቁ፣ በዘፈን፣ በድለቃ ፣ በወሬ የሚጮሁ ከግጭት ቀጠናው ፍፁም የራቁ፣ ወንድም እህታቸውን እናት አባታቸውን ያላጡ፣ የሰላምን አየር እየተነፈሱ ያሉ፤ ጦርነት ምን እንደሆነ ፈፅሞ የማይያውቁ ናቸው " ብሏል።

" የአማራ ህዝብ ኢንተርኔት ካጣ ወራት አልፎታል፣ የሰላም እጦቱ ሰለባ እሱ ነው፤ #አንዳንዶቹ አንድም ቀን የጥይት ድምፅ ሰምተው የማያውቁ፣ ሰው ያልሞተባቸው ናቸው " ሲል ተችቷል።

ከምንም በላይ እየተካሄደ ባለው ግጭት ያለ ሃጢያታቸው ነፍሳቸውን ለተነጠቁ ንፁሃን ወገኖች፣ በሀዘን ላይ ለሚገኙ ቤተሰቦች፣ ለተጎዱ፣ ለተገፉ ወገኖች ሁሉ ፍትሕ ይስፈን፤ ንፁሃንን የገደሉ፣ ያስገደሉ፣ ትዕዛዝ ያስተላለፉ ሁሉም ጥፋተኞች ይጠየቁ፤ በዚህ ጉዳይ ሁሉም ድምፁን ሊያሰማ ይገባል ሲል አሳስቧል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በቀጣይም ከቤተሰቦቹ የሚደርሱትን መልዕክቶች እያሰባሰበ ያቀርባል።

@tikvahethiopia