TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.6K photos
1.43K videos
206 files
3.97K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
በነጆው ጥቃት ከተገደሉት አንዱ የማዕድን ኩባንያው ባለቤት ነበር፦
.
.
ትናንት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ ሁምነ ዋቀዮ በተባለ ቀበሌ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት #የአምስት ሰዎች መገደላቸውን የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቆ ነበር።

ማክሰኞ ዕለት በታጠቂዎቹ ጥቃት የተገደሉት አምስት ሰዎች ሰንራይዝ በሚባል በአካባቢው የማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ለተሰማራ ኩባንያ የሚሰሩ እንደነበር ታውቋል።

በጥቃቱ የተገደሉት ሦስት ኢትዮጵያዊያን እና ሁለት የውጪ ሀገራት ዜጎች ሲሆኑ እነሱም የህንድና የጃፓን ዜግነት ያላቸው እንደሆ የአካባቢው ኮማንድ ፖስት አባል የሆኑት አቶ #አደም_ኢስማኤል ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ከተገደሉት አራቱ ወንዶች ሲሆኑ አንዷ የውጪ ዜጋ ሴት ናት።

እነዚህ የጥቃቱ ሰለባዎች ከማዕድን ኩባንያው ጋር ይሰሩ የነበሩ ሲሆን አንደኛው የኩባንያው ባለቤት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

አቶ #አለማየሁ_በቀለ ይህንን የማዕድን ማውጣት ሥራ ለመጀመር #ሦስት ዓመታትን የፈጀ ጥናት ማከናወኑንና የምርት ሥራውን ለመጀመር በተቃረበበት ወቅት ከአራት ባልደረቦቹ ጋር በታጣቂዎቹ መገደሉን የቅርብ ጓደኛው አቶ አቦማ አምሳሉ ለቢቢሲ ተናግሯል።

አቶ አለማየሁ ከአንድ ወር በፊትም በሥራው አካባቢ በድንጋይ በተፈጸመ ጥቃት በመኪናው ላይ የመሰባበር ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፤ ከአካባቢው ወጣቶችና ህብረተሰብ ጋር ለመግባባትና ከሥራው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ለመወያየት ዕቅድ እንደነበረው ጓደኛው አቶ አቦማ ያስታውሳል።

አቶ አለማየሁ በቀለ ተወልዶ ያደገው ጊምቢ ውስጥ ሲሆን ነዋሪነቱ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነበር። እንዲሁም ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት፤ የመጀመሪያ ልጁም ገና አምስት ዓመቱ እንደሆነ አብሮ አደግ ጓደኛው ጨምሮ ገልጿል።

ከአቶ አለማየሁ ጋር አብረው በጥቃቱ ከተገደሉት አንደኛው የመኪናው ሹፌር ሲሆን ሌሎቹ ግን በማዕድን ሥራው የሚረዱት ባለሙያዎች ነበሩ። ጃፓናዊቷና ሕንዳዊው ሥራውን ለማቀላጠፍ በዕውቀትና በልምዳቸው እንዲያግዙት የቀጠራቸው ባለሙያዎች እንደሆኑም ተገልጿል።

ግድያው ከተፈጸመ በኋላ የወጡ መረጃዎች የድርጊቱ ፈጻሚዎች ማንነታቸው እንዳልታወቀ የያመለከቱ ቢሆንም አመሻሽ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ታጣቂዎቹ "ኦነግ ሸኔ" የተባለው ቡድን አባላት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ ጀነራል ረታ በላቸው እንደተናገሩት፤ አምስቱን ሰዎች በመግደል መኪናቸውን ያቃጠሉት "በአካባቢው እየተዳከመ የመጣው የሸኔ ቡድን አባላት ናቸው" በማለት የጸጥታ ኃይሉም አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

ግድያውንና ምክትል ኮሚሽነሩ የተናገሩትን በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ የኦነግ ቃል አቀባይ የሆኑትን አቶ ቶሌራ አደባን ቢቢሲ ጠይቆ "የድርጅቱን ወታደሮች በተመለከተ የዕርቅ ኮሚቴው የያዘው ጉዳይ በመሆኑ ሃሳብ መስጠት አንችልም" ብለዋል።

ነገር ግን በተፈጸመው ግድያ እጅጉን ማዘናቸውንና አስፈላጊው ማጣራት መደረግ እንዳለበት አቶ ቶሌራ ጨምረው ተናገረዋል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በምዕራብ ኦሮሚያ ከሚፈጸሙ ጥቃቶችና የጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ የኦነግ ስም በሚነሳበት ጊዜ ድርጅቱ በሚሰጠው ምላሽ ላይ መንግሥት ላይ ክስ ያቀርብ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከዚህ ተቆጥቧል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ
@tsegabwolde @tikvahethiopia