TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.8K photos
1.49K videos
211 files
4.07K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
ከቲክቫህ ቤተሰብ አባላት ፦

(የፀጥታ ጉዳዮች)

ከቀናት ለፊት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ቤተሰቦቻችን በተለይ በወለጋ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ፣ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ባሉ ችግሮች ንፁሃንን ሰለባ እየሆኑ እንደሚገኙ ፣ ሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ የጠራቸው ተማሪዎች መንገድ በመዘጋቱ በእግር ለመጓዝ እንደተገደዱ መግለፃቸው አይዘነጋም።

በእርግጥ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ያለው የፀጥታ ችግር ዘላቂ እና አስተማማኝ መፍትሄ ሳያገኝ የበርካታ ንፁሃንን ህይወት እየቀጠፈ እንሆ አመታት አልፈዋል ፤ አሁንም ቀጥሏል ፤ በፀጥታ ችግሩ ሳቢያ ኢኮኖሚው ተጎድቷል፣ ገበሬዎች ማረስ እንዳችሉ ሆነዋል በርካቶች የሰው እጅ ጠባቂ ሊሆኑ ተገደዋል።

ከሰሞኑን ደግሞ የፀጥታ ችግሩ እስከ ትልቋ የነቀምቴ ከተማ ደርሶ ነበር።

ባለፈው እሁድ ዕለት በከተማይቱ መንግስት 'ሸኔ' ሲል በሽብርተኝነት የፈረጀው እራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ወደ ከተማይቱ ዘልቆ በመግባት ከመንግስት የፀጥታ ኃይል ጋር #የተኩስ ልልውጥ አድርጎ ነበር።

በዕለቱ የደረሱ ጉዳቶች ስለመኖራቸው (ትክክለኛውን ለመግለፅ ቢያስቸግርም) ፣  ነገር ግን ሁኔታውን የፀጥታ ኃይሉ መቆጣጠር እንደቻለ ከቤተሰቦቻችን ተገልጾልናል።

ይህን ያህል በትልቅ ከተማ ውስጥ የተኩስ ልውውጥ እስኪደረግ የፀጥታና ደህንነት ኃይሉ ምን ይሰራ ነበር የሚለው " ትልቁ ጥያቄያቸው " እንደሆነ ቤተሰቦቻችን ነግረውናል።

የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ለማህበረሰቡ እና ለመላ ለአገልግሎት ሰጪዎች ባሰራጨው አጭር መልዕክት ፤ በቅርቡ ነቀምቴ ከተማ ውስጥ በሸኔ ቡድን የፀጥታ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር ገልጾ ችግሩ በፀጥታ ኃይሉ ቅንጅት ፣ በከተማው ህዝብ ተሳትፎ እንዲረጋጋ መድረጉን አመልክቷል።

ነቀምቴ ከተማ አሁን ላይ ሰላም በመሆኗ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣ የአገልግሎት ሰጪዎች (የትራንስፖርት ፣ ባንክ ...የመሳሰሉ) ወደ ስራ ተመልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ የከተማው አስተዳደር አሳስቧል።

                                 --------

በአ/አ - ሀዋሳ ፈጣን መንገድ ላይ " መቂ " አካባቢ ምንድነው የሆነው ?

ከትናንትና በስቲያ ምሽት 2 ሰአት አከባቢ ከአ/አ ወደ ሃዋሳ በሚወስደው ፈጣን መንገድ ላይ መቂ አከባቢ ሲጓዙ በነበሩ ተሳፋሪዎች ላይ በታጣቂዎች ተኩስ ተከፍቶ የሰዎች ህይወት ስለማለፉ አንድ የቤተሰባችን አባል ገልጿል።

ይህንን ክስተት የገለፀው የሻሸመኔ፤ ቲክቫህ ቤተሰብ አባል ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ " ወንድም እና እህት መሞታቸውን አረጋግጫለሁ " ብሏል።

በወቅቱ ከተሳፋሪዎቹ አንዷ የእሱ #እህት እንደነበረች በመግለፅ በጥቃቱ ሳቢያ የቆሰሉ ሰዎች እንደነበሩ አመልክቷል።

ሟቾቹ የሻሸመኔ ከተማ 04 ቀበሌ ውሃ ልማት አካባቢ ነዋሪዎች እንደሆኑ ጠቁሟል።

የኸው ቤተሰባችን በዚያው ሰአት ከአዲስ አበባ እቃ ጭነው ሲመጡ የነበሩ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን እንደሰማ ገልጿል።

እስካሁን በዚህ ጉዳይ ከመንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም።
 
                                 --------

በአሶሳ ምንድነው ያለው ?

" አሶሳ ፍፁም ሰላም ነች "

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ ከተማ ከሀሙስ ከሰአት ጀምሮ ኔትዎርክ፣ ሲስተም ፣ መብራት ጠፍቶ ነበር።

ትላንት ከሰዓት ኔትወርክ / ሲስተም የተመለሰ ሲሆን ይህ መልዕክት እስከተላከበት ሰዓት መብራት የለም።

አንድ የአሶሳ የቤተሰባችን አባል በላከው መልዕክት ፤ " ስለጉዳዩ ከመንግስት በኩል የተነገረ ምክንያት የለም " ያለ ሲሆን " አሶሳ ከተማ ግን ባለፉት 6 ቀናት ከባንኮች መዘጋት በስተቀር  እጅግ ሰላማዊና መደበኛ የስራ እንቅስቃሴዎች አንዳሉ ናቸው። " ብሏል።

በኔትወርክ መጥፋት ምክንያት የተጨነቁ ቤተሰቦችም ሁሉም ነገር ሰላም ስለሆነ ጭንቀት እንዳይገባቸው መልዕክት አስተላልፏል።

ከሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል " ምዕራብ ወለጋ " አካባቢ ካለው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በአሶሳ ኔትዎርክ መቋረጡ ያሳሰባቸው በርካቶች ሲሆኑ አሶሳ ከተማና አካባቢው ላይ ኔትዎርክ ከመቋረጥ በዘለለ / አሁን ላይ ኔትዎርክ ተመልሷል / ሁሉም ነገር #ሰላም ነው።

በሌላ በኩል፦ በአሶሳ ዞን #ባንባሲ ወረዳ ከወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ (ወረዳው የስጋት ቀጠና በመሆኑ ምክንያት) ከቀናት በፊት የታወጀው የሰዓት እላፊ ተግባራዊ እየሆነ ነው።

ለማስታወስ ያህል ፦

- እግረኞች ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ምንም እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም።

- ሞተር ሳይክሎችና 3 እግር ተሽከርካሪዎች ከምሽቱ 1:00 - ንጋቱ 12:00 ሰዓት ምንም እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም።

- ማንኛውም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሻይ ቡና፣ ምግብ ፣ ሪስቶራንት፣ መጠጥ ቤቶች እና ወ.ዘ.ተ ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም።

በተጨማሪ ፦ ማንኛውም የጸጥታ አካል ከተመደበው #መደበኛ_ሠራዊት_ውጪ የተጣለውን የሰዓት እላፊ ገደብ አልፎ ሲንቀሳቀስ ከተገኘ በቁጥጥር ስር ይውላል።

@tikvahethiopia