TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.89K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
በለገጣፎ ለገዳዲ ቤት ማፍረሱ ዛሬም ቀጥሏል‼️

የለገጣፎ -ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር አረንጓዴ ቦታዎችን፥ የወንዝ ዳርቻዎችን፥ ከፈቃድ ውጭ የተያዙ እና ካሳ ተከፍሎባቸው ግንባታ የተካሄደባቸው ናቸው ያላቸውን ቤቶች እያፈረሰ ነው።

ቤት ማፍረሱ በትናንት ማክሰኞ ዕለት የተጀመረ ሲሆን የከተማው ከንቲባ የሆኑት በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ፈርሰው የሕዝብ መናፈሻ ይሆናሉ ማለታቸው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በዛ ያለ ቁጥር ያላቸው ተጨማሪ ቤቶች እንደሚፈርሱ የሚጠበቅ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች እርምጃው ዱብ ዕዳ ሆኖብናል ይላሉ።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ ከአርሶ አደር መሬት ገዝቶ፤ ጎጆ ቀልሶ በስፍራው መኖር ሲጀምር አካባቢው ከሞላ ጎደል በማሣዎች የተከበበ፣ መሠረት ልማት የናፍቀው እንደነበር የሚገልፀው አንዋር አህመድ ቤቶቻቸው በትናንትናው ዕለት ከፈረሱባቸው አባወራዎች አንዱ ነው።

እኛ ስንገባ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ራሱ አልተዋቀረም ነበር የሚለው አንዋር፤ ለቤቱ ካርታ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ባይሳካም "ውሃና መብራት አስገብተናል፣ የቤት ቁጥር ተሰጥቶናል፣ የመሬት ግብር እንከፍላለን" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

መንደሩን የሚያቋርጡ መንገዶች በሚቀየሱበት ወቅት ኗሪዎች ሁለት፣ ሦስት ጊዜ ቤቶቻቸውን እና አጥሮቻቸውን አፍረሰው መሥራታቸውን የሚያስታውሰው አንዋር፤ የአሁኑ እርምጃ ፈጣን እንዲሁም የነዋሪዎቹን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ እንደሆነ ይናገራል።

"ይህ የመኖሪያ መንደር እንደሆነ ይታወቃል፤ አረንጓዴ መናፈሻ ይሁን የሚለው አዲስ ማስተር ፕላን እዚያው ቢሮ ቁጭ ብለው የወሰኑት ነገር ነው። ምንም ሳያወያዩን ነው ድንገት ውሳኔ ይዘው የመጡት።"

በወርሃ የካቲት መባቻ የ'ውጡ' ትዕዛዝ እንደደረሰው ለቢቢሲ የገለፀው አንዋር፤ አስር አባላት ያሉትን ቤተሰቡን ይዞ የትም ለመሄድ እንዳልቻለ ይገልፃል።

እንደአንዋር ገለፃ ቤቶቻቸውን ያጡ አንዳንድ ነዋሪዎች በእምነት ተቋማት ተጠልለዋል።

"ያለምንም ቅደም ሁኔታ ነው ያፈረርሱብን። ዕቃችን እስክንሸክፍ እንኳ ጊዜ አልሰጡንም" ሲል ጨምሮ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በአካባቢው መሬት ገዝታ መኖር ከጀመረች ስምንት ዓመት እንደሞላት ለቢቢሲ የገለፀች ሌላ ነዋሪ፤ የመኖሪያ ቤቷ ባይፈርስም በስጋት መወጠሯ እንዳልቀረ ታስረዳለች።

"ትናንትና ብዙ ሕፃናት ሜዳ ላይ ሲወድቁ አይቻለሁ" የምትለው ነዋሪ ይህም ያለፈቃድ የሚሠሩ ቤቶችን አስመልክቶ "ሰማይ ላይ ነው እንጅ ምድር ላይ ጨረቃ የለም" በሚል ከመንግሥት ተሰጥቷል የምትለውን ተስፋ እና መተማመኛን የናደ እንደሆነባት ትናገራለች።

"ዱብ ዕዳ ነው የሆነብን፤ የት እንሄዳለን?"

በስፍራው አስራ ዘጠኝ ዓመት መኖሩን ለቢቢሲ የነገረ ሌላ ነዋሪ በበኩሉ የከተማው አስተዳደር ለገበሬው ካሳ የተከፈለበት ቦታ ላይ የተሠሩ ቤቶችን ነው የማፈርሰው ማለቱን እውነት አይደለም ይላል።

"ይሄ ቤት የተሰራው በ1992 ነው። ማዘጋጃው የተሰራው ከዓመታት በኋላ ነው። የት ሆነው ነው የከፈሉት? ለገበሬው ካሳ የከፈልንበት መሬት ላይ ነው የሰፈራችሁት ነው የሚሉን። እዚህች መሬት ላይ ለአንድም ገበሬ ምንም አልተከፈልም። ግምት ሳይከፍሉ በነፃ ለመውሰድ ነው ለገበሬው ከፍለናል የሚሉት" ይላል።

አንዋር የራሱን ልጆች ዋቢ አድርጎ፥ የከተማው አስተዳደር ተማሪ ሕፃናት የጀመሩትን የትምህርት ዓመት እስኪጠናቀቅ ቢታገሳቸው መልካም እንደነበር ይገልፃል። መንግስት ተፈናቃዮችን ለማቋቋም፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመሰብሰብ እየጣሩ እንዳሉ በሚናገሩበት ሰዓት እርሱ እና ጎረቤቶቹ ቤት አልባ የሆኑበትን እርምጃ ግራ የሚያጋባ ነው ይላል።

"እንደዜግነታችን እንኳ መጠለያ እንኳ አዘጋጅተውልን እዚህ ጋ እንኳ መቀመጥ ትችላለችሁ ባላሉበት ሁኔታ ነው ያፈረሱብን።

ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰብ ደግሞ የአካባቢው አስተዳደር "ለይዞታችን ካርታ እንሰጣችኋለን መረጃ አምጡ በማለት መረጃ ሲሰባሰብ ቆይቷል" በማለት ያስረዳሉ።

አንዳንድ ግለሰቦች እንደሚሉት ቤታቸው እንደሚፈርስ #ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ከ10 ቀን እንደማይበልጥና ይህም ቤት ፈልጎ ለመልቀቅ በቂ ጊዜ እንዳይደለ አስረድተዋል።

"መንግሥት በርቱ #ህጋዊ እናደርገላችኋለን እያለን እስካሁን ለመብራትና ውሃ የከፈልነው ብቻ ከመቶ ሺህ ብር ይበልጣል። ሆኖም ድንገት በሰባት ቀን ውስጥ ቤታችሁን አፍረሱ ተባልን። እኛ ማፍረስ ስላልቻልን መንግሥት እያፈረሰው ነው" ብለዋል።

ሌላኛዉ አስተያት ሰጭ እንደገለጹት ደግሞ "ሚስቴ ከወለደች ሦስት ቀኗ ነዉ። ከቤት ተባርራ ጎዳና ላይ ነች። ቤቱን ሲያፈርሱት እባካችሁ ሚስቴ ከወለደች ሦስት ቀኗ ነዉ ትንሽ ታገሱኝ ስል 'ምን አገባኝ ከእኔ #አልወለደች' ሲል አንደኛው ምላሽ ሰጠኝ። እኔም የሚሰማ መንግሥት ይኖራል ብዬ ለአቤቱታ ትቻት መጣሁ። ሜዳ ላይ በተወጠረ ሸራ ውስጥ ነው ያለችው። ምን እንደሆነች አላውቅም" ሲሉ የተሰማቸውን #ሐዘን ይገልፃሉ።

ትናንት ቤታቸዉ የፈረሰባቸዉ ግለሰቦች ዛሬ ጠዋት ተሰባስበዉ ወደ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ቢሮ ቢያመሩም እሳቸዉን ማናገር አትችሉም ተብለው ወደ ክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ መላካቸውን ነግረውናል። ነገር ግን ከክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮም ያገኙት ምላሽ "ቤታችሁ ከመፍረስ አይድንም። ልንተባበራችሁ አንችልም" የሚል መሆኑን ገልጸውልናል።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ በመቀጠል ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ቢያመሩም "ጉዳያችሁን እዛዉ ጨርሱ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸዉ ለቢቢሲ ተናገረዋል።

"መንግሥት ጎዳና የወጡትን #እንሰብስብ ሲል ደስ ብሎን እኛም ገንዘብ እያዋጣን ነበር። ነገር ግን በምትኩ ቤታችን የተቀመጥነውን #ወደጎዳና እያባረርን ነዉ። እቃ እራሱ ማውጣት አልቻልንም ከነቤታችን ነዉ እየፈረሰ ያለው" ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ።

በዛሬው ዕለትም የማፍረስ ተግባሩ የቀጠለ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰቦች በቤተ ክርስትያንና በመስኪዶች ተጠልለው ማደራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን በሚገኙ ከተሞች የህገ ወጥ ግንባታ መስፋፋት እንዳለ በጥናት ማረጋገጡን የኦሮሚያ ክልል የከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቆ እንደነበር ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቦ ነበር።

በዚህም በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር 67 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት እና በቤት ደረጃ ከ12ሺ በላይ ቤቶች በህገወጥ መንገድ መገንባታቸውን መለየታቸውን ተገልጾ ነበር።

ምንጭ፦ BBC
@tsegabwolde @tikvahethiopia