TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.9K photos
1.44K videos
207 files
4K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
ይነበብ!

#TIKVAH_ETH የፌስቡክ፣ የትዊተር፣ የኢንስታግራም ገፅ የለውም። በቤተሰባችን ስም የሚለጠፉ መረጃዎች እና መልዕክቶች በሙሉ እኛን የሚወክሉ አይደሉም!

ውድ ቤተሰቦቻችን ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን፣ ከቤተሰባችን አባላት፣ መረጃዎችን #እያሰባሰብን የምናስቀምጠው፦

ሚዛናዊ፣ ሁሉን በእኩል የሚያይ ስለ ነገ የሀገሪቱ ሁኔታ የሚያስብ፤ የሚጨነቅ፣ በምክንያት የሚያምን፣ ቅሬታውን በማስረጃ የሚያሳምን፣ በማህበራዊ ሚዲያ ያልተጨበጡ ወሬዎች የማይደናገር፣ የተረጋጋ፣ ሀገሪቷን ችግር ላይ ከሚጥል ወገንተኛ አካሄድ የነፃ አመለካከት፣ ነባራዊውን የሀገሪቱን ሁኔታ የሚረዳ፣ ቤተሰብ ለመፍጠር በማሰብ ነው።

በተጨማሪም የቲክቫህ ቤተሰብ አባላት የሆናችሁ ሰራተኞች በስራችሁ ላይ፣ ተማሪዎችም በትምህርታችሁ ላይ አትኩሮታችሁን አድርጋችሁ በቀን በተወሰነ ሰዓት ክፍተት የተፈጠሩ አዳዲስ ጉዳዮችን፣ የቤተሰባችን አባላት ያጋሩትን፣ በሚዲያዎች ሽፋን የተሰጣቸውን ጉዳዮችን እጅግ በአጭሩ ሳትሰለቹ እንድታነቡ ለማድረግ ነው።

እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መረጃ ለማግኘት የምትገሉትን ረጅም ሰዓት፣ እግረ መንገድም የምትመለከቷቸውን የጥላቻ ንግግሮችን ለማስቀረትም ያለመ ነው። በተጨማሪም ከአፀያፊ፣ የሰዎችን ክብር ከሚነኩ አስተያየቶች፣ ለግጭት ከሚያነሳሱ፣ አእምሯቹን ከሚረብሹ መልእክቶች እንድትርቁ ለማድረግ ነው።

ለቲክቫህ ቤተሰቦች መረጃዎች አይደበቁም፤ እንደወረዱም አይቀርቡም፤ እጅግ ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ ከመገናኛ ብዙሃን የምንሰማውን፣ የምናነበውን፣ ከቤተሰባችን አባላትም የሚላኩትን መረጃዎች በጥንቃቄ እናጋራለን።

እጅግ አደገኛ ጊዜ ላይ እንደምንገኝ ሁላችሁም የምታውቁት ነው። ማህበራዊ ሚዲያው ሀገር እያተራመሰ ነው፤ ለዚህም በቂ ማስረጃ ማቅረብ እንችላለን። እኛ የቲክቫህ ቤተሰብ አባላት ስለምን እንደዚህ ያለ ነገር ውስጥ፤ ነገ ሊፀፅተን በሚችል ጉዳይ ላይ እንሳተፋለን? በፍፁም አናደርገውም! መረጃዎች ስናጋራ፣ ለፀጥታ እና ደህንነት፣ ለመንግስትም ችግር ሲኖር በገፃችን ጥቆማ ስንሠጥ የምንጠነቀቀውም ያለ ምክንያት አይደለም።

ለምሳሌ፦

ከዚህ ቀደም (ከሁለት ዓመት በፊት) ቲክቫህ ኢትዮጵያ የሚታወቀው ቀጥታ የቤተሰቡን አባላት መልዕክቶችን እንደዋረደ እያጣራ በማጋራት ነው፤ በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች እና ወጣቶች ላይ በማተኮር ያላቸውን ጥያቄዎች፣ ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸው ተቃውሞዎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በዜጎች ላይ የሚደርሱ በደሎች፣ ፍትሃዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን፣ በየተቋማት ውሥጥ በሰራተኞች ላይ የሚፈፀሙ በደሎችን ወዘተ...

በዛን ሠዓት እንኳን በድፍረት፣ ያለምንም ፍራቻ፣ ለማንም ሳንወግን ስናቀርብ፣ የናተንም መልዕክቶች ስናጋራ ነበር። ዛሬም አንደ አንድ የሀገሪቱ ዜጋ የትኛውም አካል መንግስት ላይ ቅሬታ ሲኖረው፣ ተበድያለሁ ካለ፣ የትኛውም ወገን ተቃውሞ ሲኖረው በቀጥታ እናቀርባለን። እኛ ከሚቀያየረው ፓርቲ ወይም መንግስት አልያም ሀገር አስተዳዳሪ ጋር ሳይሆን ከህዝቡ ጋር ነን!

ነገር ግን ጊዜ ወዲህ ነገሮች በሙሉ መልካቸውን ቀይረዋል (ለአብነት ዘንድሮ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተፈጠረውን መመልከት በቂ ነው)፣ እያንዳንዱ ጉዳይ ወደ ብሄር ይቀየራል፣ ወደ ሃይማኖት ይዞራል። ይህ ነው ፈታኙ ሰዓት! አንድ ቦታ በሚሰጥ እና በሚነገር መረጃ ሌላ ቦታ ከፍተኛ እልቂት ሲፈፀም በተደጋጋሚ አይተናል።

በሀሰተኛ መረጃ ሰዎች ሲገደሉ፣ አለመረጋጋት ሲፈጠር፣ ሰዎች ሲፈናቀሉ፣ የእርስ በእርስ ግጭት ሲቀሰቀስ ሰምተናል። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ በርካታ ጉዳዮች እየተመዘዙ እንደሆነ እየተመለከትን ነው እያንዳንዱን ነገር እንደ ከዚህ ቀደሙ እንደወረደ ይቅረብ ከተባለ ችግር አባባሽ እንጂ ችግር ፈቺ ቤተሰብ ልንሆን አንችልም።

ይህንን ያልተረዱ፤ አንዳንዶች ሆን ብለው፣ ምናልባትም ከሰላም ይልቅ እልቂት የሚፈልጉ፣ ሀገራችን እንድትፈርስ የሚፈልጉ፣ ሰላም ውለን ሰላም ስናድር የሚያማቸው፤ እንቅልፍ የሚነሳቸው ግለሰቦች እያንዳንዱን ብሄር ከየአቅጣጫው እየጠራን ነገሮች እንድናጋጋል ይፈልጋሉ፤ በፍፁም የሌለብንን፣ ወደፊትም የማይኖርብንን የሀይማኖት፣ የብሄር ወገንተኝነት ሊለጥፉብን ይፈልጋሉ እኛ እንዲህ ባለማድረጋችን፣ ለነሱ አጀንዳ ባለመመቸታችን ስድብ ያከናንቡናል፤ የጥላቻ ንግግሮችን ያዘንብቡናል።

እነሱ የሚሉት ካልሆነ ሌላው ጠላታቸው፣ የነሱ መረጃ ካልሆነ ዘረኝነት እና ወገንተኛ እንደሆነ አድርገው ይነግሩናል፤ የቤተባችንን ስም ለማጥፋት ይደክማሉ። ልፉ ሲላቸው 😊 ነገር ግን የቲክቫህ ባለቤቶች የሆኑ አባላት ( 508,500 በላይ ) ሁሉም ወጥቶ አልቆ አንድ ሰው ቢቀር እንኳን ሀገራችንን ወገናችንን አደጋ ላይ ለሚጥል ጉዳይ በፍፁም አንገዛም። ውድ ቤተሰቦቻችን ያለምንም ግፊት እና ማስታወቂያ ከ1 ተነስተን ግማሽ ሚሊዮን መድረሳችንን አትዘንጉት። ብቻችን ብንቀር እንኳን ሀገራችንን ሊያሳጣን፣ ህዝብን ከህዝብ ሊያፋጅብን ይችላል ከምንላቸው ጉዳዮች በሙሉ እንደራቅን እንቀጥላለን።

እኛ ሀገር በማተራመስ ውስጥ እጃችንን አናስገባም! ግጭት በማጋጋል ውስጥ አንሳተፍም! ብሄር ከብሄር፤ ሃይማኖት ከሃይማኖት በሚያጋጭ አፀያፊ ድርጊት እጃችን አይገባም ይህን በማድርጋችን ቅር የሚሰኝ ካለ የቤተሰባችን አባል መሆን አይገባውም። በኃላፊነት ቲክቫህ የኔ ነው ለሚሉ የቤተሰባችን አባላት መረጃዎችን በከፍተኛ ጥንቃቄ እናቀርባለን። በድጋሚ መልስ ብላችሁ ከሁለት ዓመት የነበረውን የሀገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት እና አሁን ያለውን ተመልከቱና ፍርዱን ስጡ!

ከ2 ዓመት በፊት እንደምናደርገው መረጃ እንደደረሰን፣ ከሚዲያዎች እንዳነበብን፣ እንደወረደ አናጋራም፤ ከናተ የተሻለ የሀገሪቱን ፈተና እና ከፊት ያለውን አደጋ የተረዳ አካል ያለ አይመስለንም። በመሆኑም እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ የቤተሰባችን አባላት #ብቻ ሚዛናዊ፣ ሁሉን አቀፍ፣ እውነተኛ፣ ገለልተኛ መረጃዎች እያሰባሰብን እንድታነቡ እንሰራለን።

እኛ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰቦች በየጊዜው የሃይማኖት ካርድ እየተመዘዘ፣ የብሄር ካርድ እየተመዘዘ እልቂት ውስጥ እንድንገባ፤ ሀገራችን ፈርሳ ሀገር አልባ ሊያደርገን በሚችል የማህበራዊ ሚዲያ አጀንዳ በፍፁም ተጠልፈን አንወድቅም!

508,500+☺️የቲክቫህ ቤተሰቦች፣ 508,500+☺️የቲክቫህ ኢትዮጵያ ባለቤቶች!

Addis Abeba,Ethiopia
[email protected]
0919743630
@tsegabtikvah
@tsegabwolde
@tikvahethiopia

@tikvahethiopiaBot 👈 የቤተሰባችን ሀሳብ መቀበያ!