TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
አባታዊ የደስታ መልዕክት !

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በወቅታዊ ጉዳይ አባታዊ የደስታ መልእክት አስተላልፈዋል።

ከመልዕክታቸው የተወሰደ ፦

" ውድ ወገኖቻችን ጦርነትን የሰሙ ጆሮዎቻችን ዛሬ #ሰላምን እና #እርቅን በመስማታቸው ደስታችን ወደር የሌለው መሆኑን ለኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያውያት ልጆቻችን ለመግለጽ እንወዳለን።

አገራችን ኢትዮጵያን ከአስከፊ የጦርነት ታሪክ ለማውጣት፣ እግዚአብሔር በሰጣት መልካም ዕድል፣ የተፈጥሮና የሃይማኖት ሀብት እንድታድግ ሰላምን መናፈቅና የሰላም መልእክተኛ መሆን ያስፈልጋል።

ሀሳብ የበላይ ሲሆን የጦር መሣሪያ የእርሻ መሣሪያ ወደ መሆን ይለወጣል። እኛም በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪያችንን እያስተላለፍን የቆየን እንደመሆኑ መጠን በዚህ መልካም የምሥራች ደስ ብሎናል።

አሁንም ኢትዮጵያውያን በሙሉ አገሩ የሁላችን ነውና ልንጠብቀው፤ አለመግባባታችንን በውይይት ልንፈታው ፤ ቃላችንን ከመሬት ላይ አሳርፈን እርቁን እውነተኛ ልናደርገው ይገባናል።

#ወጣቶች ሲሞቱ ሳይሆን ተምረው ሲመረቁ ፤ ተዋደው ጋብቻ ሲመሠርቱ ለማየት እንናፍቃለን።

የተዘጉ ደጆች ሁሉ በምሕረት እንዲከፈቱ ፤ የተጨነቁ ሁሉ ፀሐይ እንዲወጣላቸው በብርቱ እንሻለን።

ለዚህ እርቀ ሰላም መምጣት በብርቱ የደከሙትን የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላትንና የሰላም ጥሪ የተቀበሉት ልጆቻችንን እግዚአብሔር አምላካችን ዐስበ ሐዋርያትን እንዲከፍልልን እንመኛለን። ለሞቱት ዕረፍተ ነፍስን ለታመሙት ፍጹም ጤንነት እንዲሰጥልን እንለምናለን። "

(የቅዱስነታቸው መልዕክት ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia