TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
" ለጅቡቲ ጉምሩክ ደብዳቤ ፅፈናል " - የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን

በጅቡቲ ጉምሩክ የወደብ ጭነት መዘግየት ችግር የተፈጠረ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አሳውቋል።

የጂቡቲ ጉምሩክ " ከ20 ሺህ ዶላር በታች የክፍያ ደረሰኝ የያዙ ጭነቶች ወደ ኢትዮጵያ #እንዳያልፉ " በሚል መመሪያ እቃዎች እንዳይንቀሳቀሱ እንዳገደ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዘርይሁን አሰፋ በሰጡት ቃል ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ለጅቡቲ ጉምሩክ ደብዳቤ መፃፉን ገልጸዋል።

" ኢትዮጵያ እቃዎችን በጂቡቲ ወደብ በኩል የምታዘዋውር መሆኑን ተከትሎ መሰል ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ " ይጠበቃል ያሉት አቶ ዘርይሁን " እቃ አስመጭዎች ለደረሰባቸው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ስራዎች እየተሰሩ ናቸው " ብለዋል።

" በጂቡቲ 2 ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች አሉን " ያሉት ዳይሬክተሩ ችግሩ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚሻ አስረድተዋል፡፡ 

ችግሩ ከ3 ሳምንታት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን ተከትሎ ጭነቶች ወደብ ላይ በሚቆዩበት ወቅት ከሚከፈለው ገንዘብ መጠን ጋር ተያይዞ ጉዳቱ የከፋ መሆኑን አስረድተዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፤ ይህ መረጃ #ባለቤትነቱ የአሐዱ ኤፍ ኤም 94.3 ሬድዮ ጣቢያ መሆኑን ያሳውቃል።

@tikvahethiopia
" የኤችአይቪ/ኤድስ የሥርጭት ምጣኔ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል " - አቶ ፍቃዱ ያደታ

ወጣቶችን ጨምሮ ለበሽታው ተጋላጭ ተብለው በተለዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ እየታየ ያለው የኤችአይቪ/ኤድስ የሥርጭት ምጣኔ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነግሯል።

የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭት ፦

* በቀን ሠራተኞች፣
* በሴተኛ አዳሪዎች፣
* በረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣
* በአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ላይ ያለው የሥርጭት ምጣኔ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።

በጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪ/ኤድስና ቫይራል ሄፒታይተስ የመከላከልና የመቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈቃዱ ያደታ ምን አሉ ?

- የኤችአይቪ ሥርጭት በኢትዮጵያ ከአንድ ፐርሰንት በታች ዝቅ ቢልም የሥርጭት ምጣኔው ከክልል ወደ ክልል የተለያየ ነው።

- ከፍተኛ ሥርጭት ካለባቸው ክልሎች መካከል ፦
• ጋምቤላ ክልል የመጀመሪያው ሆኖ 3.69 በመቶ፣
• አዲስ አበባ ከተማ 3.17 በመቶ፣
• ሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 3 በመቶ የሥርጭት ምጣኔ አላቸው።
• በሶማሌ ክልል ዝቅተኛ የቫይረስ ሥርጭት ነው ያለው።

- በግጭት ምክንያት #የሚፈናቀሉ ማኅበረሰቦችና የተለያዩ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ/ኤድስ ዘርፈ ብዙ ማስተግበሪያ ዳይሬክተር ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ ምን አሉ ?

✦ በአገር ደረጃ የሥጋት ቀጣና ተብለው የተለዩ አካባቢዎች አሉ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት 121 ወረዳዎች 48 ወረዳዎች በትኩረት የሚሠራባቸው ናቸው።

✦ ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አሉ እነዚህ። ፦
° አፍላ ወጣቶች፣
° የትዳር አጋራቸውን የፈቱና የሞቱባቸው፣
° ሴተኛ አዳሪዎች ሲሆነ ለእነዚህ አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።

✦ ከቦታ ወደ ቦታ የበሽታው ሥርጭት የተለያየ ነው። በአዲስ አበባ የሥርጭት ምጣኔው 3.4 በመቶ ነው።

✦ የመዘናጋት ሁኔታዎች በሰፊው እየተስተዋሉ ነው። ሞት በመቀነሱ ምክንያት " ኤችአይቪ/ኤድስ የለም " የሚሉ ሰዎች ተበራክተዋል።

✦ ከ20 እስከ 25 ዓመት ዕድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች " ሞት የለም " በማለት የመዘናጋት ሁኔታዎች እያሳዩ ነው።

✦ በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የሥርጭት ምጣኔ 0.91 በመቶ ነው። በዚህ ሥሌት ከ610‚350 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ኤችአይቪ/ኤድስ በደማቸው እንደሚገኝና ከእነዚህ ውስጥም 8‚257 ያህሉ አዲስ የተያዙ፣ እንዲሁም ከ11 ሺሕ በላይ ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ በአገር ደረጃ ይሞታሉ።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ይህ መረጃ #ባለቤትነቱ የሪፖርተር ጋዜጣ መሆኑን ያሳውቃል።

@tikvahethiopia
" የባህል ህክምና እንሰጣለን የሚሉ አጭበርባሪ ግለሰቦች እየተበራከቱ ነው " - የአ/አ ባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማህበር

የአዲስ አበባ ባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማህበር ፤ የባህል ህክምና እንሰጣለን የሚሉ አጭበርባሪ ግለሰቦች እየተበራከቱ ነው ብሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ፌስ ቡክ እና ቴሌግራም ያሉ ማኅበራዊ መገናኛዎችን በመጠቀም " የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ነን " የሚሉ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡

እነዚህ መድሃኒት አዋቂ ነን የሚሉ ሰዎች መድሃኒት እናዘጋጅላቸዋለን የሚሏቸው ጉዳዮች ያልተለመዱና " መድሃኒት " ይፈታቸዋል የማይባሉ ዓይነት ናቸው፡፡

ለምሳሌ ፦
- ለገበያ፣
- ለስልጣን፣
- ለግርማ ሞገስ፣
- ትዳር እምቢ ላለው፣
- ወደ ውጭ ለሚጓዝ፣
- ሎተሪ እንዲደርሳችሁ
- ለቤቲንግ
- ለእቁብ
- ለድምፅ ወዘተ.  የሚሉ አጓጊ ቃላትን ይጠቀማሉ ተብሏል።

መድሃኒት አዋቂ ነን ከሚሉት ሰዎች " መርጌታ " የሚል መንፈሳዊ ማዕረግን የሚጠቀሙት ብዙዎቹ ሲሆኑ በመቶ ሽዎች ተከታዮች ባሏቸው የማኅበራዊ መገናኛዎች ላይ ስልክ ቁጥሮቻቸውን ከመለጠፍ ባለፈ የሥራ አድራሻቸውን በግልጽ አያስቀምጡም ተብሏል።

ስልክ ሲደወልላቸው " ምን መድሃኒት ትልጋለህ ? " ብለው ይጠይቁና ለማንኛውም ዓይነት ችግር መፍትሔ እንዳላቸው ይናገራሉ ፤ ባለጉዳዩ ክፍያ #በባንክ እንዲያስገባ መድሃኒቱንም በመልክተኛ እንደሚልኩ ይገልጻሉ።

በዚህ መልኩ በርካታ ማጭበርበሮች የደረሰባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው ተነግሯል።

ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የአዲስ አበባ የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ማህበር ፕሬዝዳንት መሪጌታ መንግሥቱ ፤ እንዲህ ያለ ሥራ የሚሠሩ አጭበርባሪዎች መበራከታቸውን ጠቁመዋል፡፡

" በራሴ ሥም መርጌታ መንግስቱ የባህል መድሃኒት አዋቂ " የሚል ገጽ ተከፍቶ ሰዎች እየተጭበረበሩ ነው ብለዋል፡፡

ከመንግስት ጋር እየተነጋገርን እነዚህን አጭበርባሪዎች ለማስታገስ እየሞከርን ነውም ሲሉ ተናግረዋል።

እነዚህ " መድሃኒት " አዋቂ ነን ብለው የሚያስተዋውቁ ሰዎች እንፈውሳቸዋለን የሚሏቸው በግልጽ መድሃኒት እንደሌላቸው የተነገረላቸው በሽታዎች ለምሳሌ ፦ ኤች አይ ቪ. እና ካንሰር ... ወዘተ. እንዲሁም እንደ በሽታ ሊታዩ የማይችሉ ወይም በሽታ ስለመሆናቸው ያልተረጋገጡ ለሆኑ ነገሮች ለምሳሌ ፦
* ራዕይ ለማዬት፣
* ሌሊት ሽንቱ ለሚያመልጠው፣
* ለወር አበባ፣
* ለንቃተ ህሊና፣
* ትምህርት ለማይገባው፣
* ለሥራ ዕድል፣
* ለመስተፋቅር ወዘተ. የሚሉ አሉ፡፡ ህክምና ፈላጊዎች እንዲህ መሰል በሆኑ አጭበርባሪዎች እንዳይታለሉ ሲሉ መሪጌታ መንግሥቱ (የአ/አ የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ማህበር ፕሬዝዳንት) ተናግረዋል።

ይህ መረጃ #ባለቤትነቱ የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ሬድዮ ' እውነትን ፍለጋ ' የተሰኘ ፕሮግራም / ደሳለኝ ስዩም ነው።

@tikvahethiopia
#AddisAbaba

" ፈተናውን ብዙዎቹ ሊያልፉ ይችላል የሚል ግምት ነው የተያዘው " - የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሚኖሩ ዳይሬክተሮች እና ቡድን መሪዎች መካከል #ተመሳሳይ የብሔር ማንነት ያላቸው አመራሮች ብዛት ከ40 በመቶ እንዳይበልጥ ሊያደርግ መሆኑ ተሰምቷል።

በቅርቡ ለሚተገብረው #የሠራተኞች_ድልድል ሲባል ከ14 ሺህ በላይ የከተማ አስተደደሩ ሠራተኞች ነገ አርብ ታኅሣሥ 12/2016 ዓ.ም. ለፈተና ይቀመጣሉ።

ከማዕከል እስከ ወረዳ ያሉት ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ባለፉት ሳምንታት ከሠራተኞቹ ጋር ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል ተብሏል።

163 ሺህ ገደማ ሠራተኞች በስሩ ያሉት አስተዳደሩ ፤ በሚተገበረው ለውጥ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል የከተማዋን የመንግሥት ሠራተኞችን በአዲስ መልኩ መደልደል የሚለው ይገኝበታል።

ለለውጡ ትግበራ ተብሎ የተዘጋጀ #የሥልጠና_ሰነድ ምን ይላል ?

-አሁን በመጀመሪያው ዙር ድልድል እንዲተገበርባቸው የተመረጡት አስራ ስድስት (16) ተቋማት ናቸው። ከእነዚህም መካከል ፦

* የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር፣
* ቤቶች ልማት እና አስተዳደር፣ ትራንስፖርት፣
* ፐብሊክ ሰርቨሲ እና ሰው ሀብት ልማት፣
* ፕላን እና ልማት፣
* ሥራ እና ክህሎት፣
* ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮዎች
* ቤቶች ኮርፖሬሽን፣
* ኅብረት ሥራ ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎች የከተማይቱ ኤጀንሲዎች እና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ይገኙበታል።

- የተዘረዘሩት መስሪያ ቤቶች ድልድል የሚደረግባቸው በማዕከል ቢሮዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ላይ ባሉ ጽህፈት ቤቶቻቸው ጭምር ነው።

የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ጣሰው ገብሬ ምን አሉ ?

° ከላይ የዘረዘሩት መስሪያ ቤቶች ለመጀመሪያው ዙር ትግበራ የተመረጡት ብዙ ተገልጋይ የሚያስተናግዱ እንዲሁም ብልሹ አሰራር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብዙ መጓደል ያለባቸው በመሆናቸው ነው።

° የሠራተኞች ድልድል ከመከናወኑ በፊት የእነዚህ መ/ቤቶች ሠራተኞች ለፈተና ይቀመጣሉ።

° ፈተና ለመስጠት የታቀደው የሠራተኞቹን የብቃት ደረጃ ለማረጋገጥ ነው።

° ፈተናው የባህሪ እና የቴክኒክ ምዘናዎችን የያዘ ነው። የሚሰጠው የቴክኒክ ምዘና ሠራተኞቹ ከሚሠሩት ሥራ ጋር ግንኙነት ያለው ነው። የባህሪው ፈተና ደግሞ አገልግሎት አሰጣጡን የሚፈታተኑ የባህሪ ችግሮች ስላሉ ያንን ክፍተት ለመሙላት አመላካች እንዲሆን ተስቦ የተዘጋጀ ነው።

° የምዘና ፈተናው የተዘጋጀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በጋራ ትብብር ነው።

° ፈተናው የሚሰጠው በዩኒቨርስቲ / በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው።

° እስካሁን ባለው መረጃም ነገ ፈተናውን የሚወስዱ ሠራተኞች ቁጥር ከ14 ሺህ በላይ ነው።

° ፈተናውን የማያልፉ ሠራተኞች እንዳይኖሩ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ እንዲያጠኑ ተነግሯል። ፈተናው ለማለፍ በሚያስቸግር መንገድ በጣም የተወሳሰበ፣ አብስትራክት እና ንድፈ ሀሳባዊ የሆነ ሳይሆን የሠራተኞችን አቅም ለመለካት አመላካች ሆኖ ነው የተዘጋጀ ነው።

° ብዙዎቹ ሊያልፉ ይችላል የሚል ግምት ነው የተያዘው።

የሪፎርም ሥልጠና ሰነዱ ምን ይላል ?

- የከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎች ፈተናውን ለማለፍ ከ50 በመቶ በላይ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል።

- ከዚህ የማለፊያ ውጤት በታች የሆነ ነጥብ ያገኘ ባለሙያ ከደረጃው ዝቅ ብሎ ባሉት የአስተዳደር እርከኖች ላይ ይመደባል።

- ለዳይሬክተሮች እና ለቡድን መሪዎች የተቀመጠው የፈተና ማለፊያ ነጥብ 60 በመቶ ነው። ይህን ነጥብ የማያስመዘግቡ አመራሮች ለዳይሬክተርነት ወይም ለቡድን መሪነት ኃላፊነት #መወዳደር_አልችሉም

ዶ/ር ጣሰው ገብሬ ፦

ሠራተኞች ፈተናውን ማያልፉ ከሆነ ዝቅ ተደርገው ሊመደቡ ይችላሉ። ድልድሉ ሲያልቅ ሌሎች አማራጮች ታይተው ምን ሊደረግ እንደሚችል የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ መፍትሄ ይፈለግላቸዋል።

በአዲስ መልኩ #ሠራተኞች ሲደለደሉ ከፈተናም በተጨማሪ ሌሎች መስፈርቶችን ይኖራሉ።

- ሰነዱ የሠራተኞች ድልድልን በተመለከተ " ትኩረትን የሚሹ አዳዲስ ጉዳዮች " በሚል ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ጉዳይ ነው።

- ድልድሉ ሲከናወን " ሕብረ ብሔራዊነትና አካታችነት በጥንቃቄ " መተግበር እንዳለበት በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

- " አካታችነትና ፍትሐዊነትን " በሚመለከተው የሰነዱ ክፍል ላይ በዳይሬክተርነት እና ቡድን መሪነት የሥራ መደቦች ላይ አመራሮች ሲመደቡ " የሜሪት ሥርዓት " ይጠበቃል።

- የአመራሮች ድልድል "የብሔር ብሔረሰብ ስብጥርን ባካተተ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ " ይከናወናል።

- በመ/ቤቱ ካሉ የሥራ መደቦች መካከል በተመሳሳይ ማንነት የተያዙት ከ40 በመቶ መብለጥ የለባቸውም።

- መ/ቤቶቹ ድልድሉን ሲያከናውኑ ይህንን #የብሔር ስብጥሩን ለመጠበቅ እንዲችሉ " ብቃት ያላቸውን ሠራተኞች ከሌሎች መ/ ቤቶች በመለየት በዝውውር እንዲሟሉ " ይደረጋል።

ዶ/ር ጣሰው ገብሬ ፦

ከ40% መብለጥ የለበትም በሚል የተቀመጠው አሠራር፤ የሚተገበረው የቡድን መሪዎች እንዲሁም የዳይሬክተሮች ድልድል ላይ ብቻ ነው።

በዚህ ድልድል ወደ #ሠራተኛው የወረደ እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም። የድልድል ደንቡ ውስጥም የለም።

የተመሳሳይ ማንነት ያላቸው ከተወሰነ ፐርሰንት በላይ መሆን የለበትም የሚለው ለዳይሬክተሮች እና ለቡድን መሪዎች ነው።

ከተማዋ የአገሪቱ ዋና ከተማ ናት። ብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ያሉባት ስለሆነች ያንን ሥዕል የሚያሳይ እንዲሆን መደረግ ስላለበት የተቀመጠ ነገር ነው።

ይህ የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርምና የሠራተኞች ድልድል እስከ ታኅሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ለማጠናቀቅ በጊዜያዊነት ዕቅድ ተይዟል።

ይህ መረጃ #ባለቤትነቱ የቢቢሲ አማርኛ አገልግሎት ነው።

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#Ethiopia በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ትላንት በተጠናቀቀው የካቲት ወር በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካቶች ተገድለዋል። ጉዳትም ደርሷል። ቲክቫህ ኢትዮጵያ በወሩ ስለነበሩት ሁኔታዎች ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለማግኘት እጅግ በርካታ ቀናትን የወሰደ ሙከራ ቢያደርግም ምንም ምላሽ የሚሰጠ አካል አላገኘም። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ግን ስለነበሩት ሁኔታዎች…
#AmharaRegion

° " ህዝቡ በታጠቁ ቡድኖች ነው ለጥቃት የተዳረገው በገዛ ከተማው ነው መአት ያወረደበት ... ጥቃት ፈፃሚዎቹ ከአጎራባች ' ሸኔ ' ናቸው " - የአጣዬ ከተማ ከንቲባ

° " #ሀሰት_ነው የኦሮሞ አርሶ አደሮች እንጂ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላት አይደሉም " " - አባገዳ አህመድ ማህመድ

በአማራ ክልል ፤ የሰሜን ሸዋን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርን በሚያጎራብቱ አካባቢዎች ላይ ግጭት ከጀመረ ከሳምንት በላይ ሆኖታል።

በተደጋጋሚ ፦
- የሰዎች ደም በሚፈስበት፣
- ንብረት በሚወድምበት ፣
- ሰዎች ቄያቸውን ለቀው በሚፈናቀሉበት በዚህ ቀጠና ባለፈው የካቲት ወር ውስጥም በርካቶች መገደላቸው ይታወሳል።

አሁን ደግሞ #ከ8_ቀናት በፊት የተቀሰቀሰው ግጭት እጅግ መባባሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በመነሻው ላይ በሁለቱም በኩል እርስ በእርስ መወነጃጀል ያለ ሲሆን በኤፍራታ ግድምና ቀወት ውስጥ ግጭቱ ከፍቶ መዋሉ ነው የተሰማው።

በሁለቱም በኩል ያሉት ነዋሪዎች ፣ የአጣዬ ከንቲባ ፣ የአካባቢው አባገዳ ምን አሉ ?

በኤፍራታ ግድም ወረዳ የአላላ ከተማ ነዋሪ ፤ ጦርነት ከተጀመረ 8 ቀን መያዙን ፣  ብዙ ቤቶች መቃጠላቸውን ገልጸዋል።

ነዋሪው " የአርሶ አደሮች ዱቄት ሳይቀር ፣ በግ ፣ ፍየል ፣ ግመል ፣ አህያ፣ ከብት በሙሉ ሙልጭ አድርገው ወስደውብናል። ኃላሸት የሚባል ሰውም ገድለውብናል እኛው ክልል ላይ ገብተው " ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ካደረጉ በኃላ ህዝቡ ተሬ እና ዘንቦ ወደሚባለው አካባቢ በለበሰው ልብስ ሸሽቶ ተጠልሎ እንደሚገኝ ገልጸዋል። " በተከታታይ 18 ሰዎችን ገድለውብናል "ም ብለዋል።

በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰንበቴ ነዋሪ ፤ " እስከ ጅሌ ጥሙጋ ባርሲሳ ፣ ካራ ሌንጫ ፣ መከና ወይም አጣዬ ከተማ ዙሪያ ባሉ ቀበሌዎች ከትላንትና ጀምሮ ተኩስ ነበር። ትላንት አንዲት ሴት እንዲሁም ግመልና ከብቶችም ተመተው ነበር ግጭቱ የቀጠለው በዚህ ነው፤ አንድ ሰው ሲሞት ሁለት ሰው ቆስለዋል፤ አንዱ ወደ አዳማ ተልኳል። ዛሬ ደግሞ 4 ሰው ሲሞት 3 ሰው ቆስሏል " ብለዋል።

ዋነኛው እቅዳቸው የጅሌ ጥሙጋ ከተማ #ሰንበቴን " እንይዛለን ፣ እናጠፋለን " የሚል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አንድ የአጣዬ ነዋሪ ደግሞ ፤ ሰሞኑን ግጭት ተባብሶ ዛሬ አጣዬን በተኩስ ልውውጥ ሲያናውጥ መዋሉን ፣ 5 ሰው መገደሉም. ጥቃት ፈፃሚዎቹ የታጠቁ አካላት " ሸኔ " ናቸው ብለዋል።

ሌላው የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ፣ የሰንበቴ ነዋሪ " ግጭቱ የጀመረው #መጋቢት_አንድ ላይ ነው። ይህም በጅሌጥሙጋ ኮላሽ የሚባል ስፍራ 1 ሰው ገድለው 2 ሰው አቁስለው ከብቶችንም ነድተው ከሄዱ በኃላ ነው ግጭቱን የተስፋፋው " ሲሉ ተናግረዋል።

" ከባልች ቀበሌ እስከ ሰንበቴ እና መከና አጣዬ ድረስ ጦርነት ነው። የዛሬውን ለየት ያደረገው ታጣቂዎቹ #ከሰሜን_ሸዋ ተሰባስበው ፤ እራሳቸውን አደራጀትው ሌሊቱን በተሽከርካሪዎች ተጉዘው መጥተው ውጊያ መክፈታቸው ነው " ሲሉ አክለዋል።

ባለፉት 10 ቀናት 29 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረው የተወሰዱት ከብቶችና የወደመው ንብረትም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ አስተያየት #አልቀበልም ያሉት የአላላ ነዋሪው ፤ " አማራው ሲያጠፋ በአማራው አጥፊውን መዞ ለህግ ማቅረብ፤ ከኦሮሞውም ሲያጠፋ አጥፊውን መዞ ለህግ ማቅረብ ሰላም የሚያሰፍነው ይሄ ብቻ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

" በህግ እና በሽምግልና  ነገሩ መክሰም አለበት እነሱ የሚሉት ከጨፋ ጀምሮ እስከ ሸዋሮቢት ድረስ የኦሮሞ ቦታ ነው። አጣዬም #የኛ_ነች ፤ አላላም ፣ ሞላሌም ፣ ማጀቴም ... ሁሉም የኛ ነው የሚሉት። መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ችግሩን ሊፈታው ይገባል " ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን #አባገዳ አህመድ ማህመድ " መንገድ የለም። ከጅሌ ጥሙጋ እና አርጡማ ፋርሲ ወረዳዎች እንዲሁም ከዞን መገናኘት አልቻልንም " ብለዋል።

" በዚህ ምክንያት የሃይማኖት አባቶች እና አባ ገዳዎች ተሰባስበው መፍትሄው ምንድነው ? ለማለት መንገዱ ተከፍቶ ለህዝቡ ምግብ ለማድረስ ፣ የቆሰሉትንም ወደ ህክምና ቦታ ለመውሰድ ጥረት ላይ ነን። መንገድ ከተዘጋ 1 ወር ሊሆነው ነው። እኛም ሆነ መንግሥታዊ አመራሩ ሄደን ማየት አልቻልንም። የአማራ ክልልም #ታጣቂዎቹን_ስለሚፈሯቸው ቀርበው ለማነጋገር አልተቻለም። እኛ ጋር ያሉትን #ወሰናችሁን አልፋችሁ አትሂዱ እያልን እየመከርናቸው ነው ። " ገልጸዋል።

ነዋሪዎችና የአካባቢው አስተዳደሮች ጥቃቱን የከፈቱት " ሸኔ (የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት) " ናቸው ቢሉም አባገዳ አህመድ " ሀሰት ነው " ብለዋል።

" ሀሰት ነው የኦሮሞ አርሶ አደሮች እንጂ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላት አይደሉም። የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት እዚህ አልገባም። እየተዋጋ ያለው እራሱ ነዋሪው ነው " ብለዋል።

የአጣዬ ከተማ ከንቲባው ተመስገን ተስፋ ፤ ከተማዋና ህዝቡ በታጠቁ ቡድኖች ነው ለጥቃት የተዳረጉት ብለዋል።

አጣዬ ላይ ' #ወረራ ' መፈፀሙን ገልጸው " ሰውም አልቋል፤ ሚሊሻውም የሚችለውን ያህል ሞከረ አለቀ " ብለዋል።

ይህን የሚፈፅሙት ከአጎራባች  " #ሸኔ በሏቸው " ሲሉ የጠሯቸውን የታጠቁ ኃይሎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

" ዋናው መፍትሄ መንግሥት ጠንከር ብሎ #እርምጃ መውሰድ ያለበት ላይ እርምጃ መውሰድ ፤ ይሄ ነበረ መፍትሄው  አሁን ባለው መንገድ ፣ #በእሹሩሩ ሰውም አለቀ " ብለዋል።

#የአጣዬ_ህዝብ የገዛ ከተማው ላይ እንዳለ መአት እንደወረደበት የገለጹት ከንቲባው " እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ መንግስት ቢደርስልን ጥሩ ነው " ሲሉ ተናግረዋል።

ከኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር በኩል ለጥፋቱ ለችገሩ " የፋኖ ታጣቂዎችን " ተጠያቂ ሲያደርጉ ከሰሜን ሸዋ ዞን በኩል ደግሞ " ሸኔን (የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት) " ተጠያቂ ያደርጋሉ።

NB. ባለፉት አምስት ዓመታት አጣዬ ከ10 ጊዜ በላይ የመቃጠል አደጋ አስተናግዳለች።

እስካሁን የአማራ ክልል መንግሥት ስለ ጉዳዩ ያለው ነገር የለም።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ይህ መረጃ #ባለቤትነቱ የቪ.ኦ.ኤ. ራድዮ (ጋዜጠኛ መስፍን አራጌ) መሆኑን ይገልጻል።

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
" በፈንጂ እና በድማሚት ቢሞከረም ሊሳካ አልቻለም " - የከበሩ ማዕድናት አምራች ማህበር ከ12 ቀናት በፊት በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ፤ የኦፓል ማዕድን ለማውጣት ቁፋሮ ላይ እያሉ ዋሻ የተናደባቸው ሰዎች የሚወጡበት መፍትሔ አሁንም ድረስ አለመገኘቱን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር እና የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ተናግሯል። ትላንት የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው በመገኘት የዋሻውን የላይኛው…
በደቡብ ወሎ ዞን፤ በደላንታ ወረዳ የመአድን ቁፋሮዉ ዳግም መጀመሩ ተነገረ።

በደላንታ ወረዳ አለኋት ቀበሌ " ቆቅ ውሀ " እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የኦፓል ማዕድን ለማውጣት ቁፋሮ ላይ የነበሩ ሰዎች ዋሻ ተደርምሶባቸው እንደነበር ይታወሳል።

የሰዎቹን ህይወት ለማዳን ሲደረግ የነበረው ጥረት በመቋረጡ የተጎጂ ቤተሰቦች ተስፋ በመቁረጥ ለቅሶ መቀመጣቸውም መነገሩ አይዘነጋም።

አሁን ላይ የአካባቢው ማሕበረሰብ ተስፋ በመቁረጥ እና እርሙን በማውጣት ወደ መደበኛው የኦፓል ማዕድን የማውጣት ስራ የተሰማራ መሆኑ ተሰምቷል።

የደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የማዕድን ስራዎች ፈቃድ መስጠትና ማስተዳደር ቡድን መሪ አቶ በሪሁን ማህብረሰቡ ተስፋ ቆርጦና እርሙን አውጥቶ ወደ መደበኛው የኦፓል ማዕድን የማውጣት ስራ ገብቷል ብለዋል።

ከተፈጠረው አደጋ ለምን መማር አልተቻለም ? አሁን ላይስ ማዕድን ለማውጣት ከበፊቱ በተለየ ጥቅም ላይ የሚውል የተሻለ መሳሪያ አለ ወይ ? ተብለው የተጠየቁት ኃላፊው ፥ " የአካባቢው ማሕበረሰብ ኑሮውን የሚያስተዳድረው የኦፓል ማዕድን በማውጣት በመሆኑ ያለ ምንም መሳሪያ ቀደም ሲል በነበረው በባህላዊ መንገድ ስራውን እያከናወነ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ መረጃ #ባለቤትነቱ የአሐዱ ሬድዮ 94.3 እና ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው።

@tikvahethiopia