TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.6K photos
1.43K videos
206 files
3.97K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#መምህራን

" ለልማት በሚል ከደመወዛችን እየተቆረጠብን ነው " - መምህራን

" እውነት ነው። ከህግ አግባብ ውጪ የመምህራን ደመወዝ እየተቆረጠ ነው " - የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር

የደመወዝ በወቅቱ አመከፈል፣ የጥቅማጥቅም ክፍያ አለማግኘት ችግር ባልተቀረፈበት ሁኔታ፣ ያለፈቃዳቸው ከደመወዝ ለልማት በሚል እየተቆረጠባቸው መሆኑን መምህራን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል አማረሩ።

መምህራኑ በሰጡት ቃል፣ " ለልማት በሚል እስከ 50 በመቶ ከደመወዛችን እየተቆረጠብን ነው። የወር አስቤዛን በቅጡ ከማይሸፍን ደመወዝ ላይ እየተቆረጠ እንዴት ቤተሰብ እናስተዳድር ? " ሲሉ ጠይቀዋል።

ይህ የመንግስት ድርጊት ሰንበትበት እንዳለ ገልጸው፣ ጭራሽ ቤተሰብ ማስተዳደር አቅቷቸው በብድር እየማቀቁ በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

መምህራኑ ያቀረቡት ቅሬታ እውነት ነው ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ ያቀረበለት የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር፣ " እውነት ነው ችንሩን በደንብ ነው የምናውቀው "  ብሏል።

የማኀበሩ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አበበ በሰጡት ቃል፣ " በየክልሉ የተለያየ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ። ያለመምህራን ፈቃድ የደመወዝ  ቆረጣም በጣም #ትክክል ያልሆነ፣ #ጉልበተኝነት የበዛበት፣ #ሰሚ ያጣ ነው " ብለዋል።

ታዲያ ለቅሬታው ማኀበሩ ምን እየሰራ ነው ? ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ " ትክክል አይደለም ብለን እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድርሰናል። ባለፈው ነሐሴ ወር በነበረን ውይይት " የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አሁንም በተለይ ዳውሮ ዞን የሚገኙ መምህራን እንደሚያለቅሱ፣ ማኀበሩም ለትምህርት ሚኒስቴር እንዳሳወቀ፣ ትምህርት ሚኒስቴርም ያለፈቃዳቸው ደመወዝ እንዳይቆረጥ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ ደብዳቤ እንደጻፈ፣ ክልሉም ደመወዛቸው እንዳይቆረጥ ለሚመለከተው አካል እንዳሳወቀ አስረድተዋል።

" ዞኑ ላይ 'ለማዕከል ግንባታ' በሚል ለዛ ነው ደመወዛቸው እየተቆረጠ ያለው። መምህራኑም እዚህ ድረስ መጡ። እኛም ለእንባ ጠባቂ ተቋም ደብዳቤ ጻፍን። የተለያዩ አካላትን ለመድረስ ጥረት አደረጉ። ግን እንባ ጠባቂም ምን ያህል ኃላፊነቱን እንደተወጣ አላውቅም " ነው ያሉት።

" በእኛ በኩል ያላረግነው ነገር የለም " ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ " ግን አሁን ህግ የሌለ በሚስል ሁኔታ የመምህራን ደመወዝ እየተቆረጠ ነው " ብለዋል።

መምህራኑ ደመወዛቸውን ቀድመው ለተለያዩ ፕሮግራሞች ከፋፍለው የሚጠቀሙበት ብቸኛ ገቢያቸው እንደሆነ ገልጸው፣ " መካከል ላይ ደመወዝ ሲቆረጥ ምስቅልቅል ይወጣል " ሲሉ አስረድተዋል።

" ይህንን የማያይ ምን አይነት የዞን አመራር እንዳለ አይገባኝም በበኩሌ። እጅግ በጣም ጫፍ የወጣ ስልጣን መጠቀም እንደሆነ ነው የምረዳው። መምህራን እየተሰቃዩ ነው የሚያዳምጣቸው አጥተዋል " ሲሉ አክለዋል።

ምን ያህል መምህራን ናቸው ደመወዝ የተቆረጠባቸው ? ለሚለው ጥያቄ አቶ ሽመልስ፣ " ለምሳሌ ዳውሮ ላይ የዞኑ መምህራን በሙሉ ተቆርጦባቸዋል። ኦሮሚያ ላይ የ230 ሺህ መምህር ይቆረጣል ደመወዙ " ነው ያሉት።

የሚቆረጠው መጠን በሁሉም ቦታ እንደየሁኔታው እንደሚለያይ አስረድተው፣ የክልል መንግስታት በማናለብኝነት ደመወዝ መቁረጥ አግባብነት እንደሌለው ቆም ብለው እንዲያስቡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመምህራኑን ቅሬታ በተመለከተ ምን ሀሳብ እንዳለው በቀጣይ የመረጃ የምናደርሳችሀ ይሆናል።

#TikvahErhiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia