TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.7K photos
1.49K videos
211 files
4.06K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ደራ_ወረዳ #ትኩረት

በደራ ወረዳ ያለው የፀጥታ ችግር አሁንም #አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ፣ የሰዎች ህይወት እያለፈ ፣ ንብረትም እየወደመ መሆኑን ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

የደራ ወረዳ ነዋሪዎች በሰጡት ጥቆማ አንድ የቀድሞ የኦሮሚያ ፖሊስ አባል የልጆቻቸው እናት የሆነች ሚስታቸውን ከ " ኦነግ ሸኔ " ታጣቂዎች ጋር በመወገን ገድለዋል ብለዋል።

አንድ ቃላቸውን ለ ' ቲክቫህ ኢትዮጵያ ' የሰጡ የሟች የቅርብ ቤተሰብ ነኝ ያሉ ግለሰብ ፤ " በደራ ጁሩ የተባለ አካባቢ አንድ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል የፓሊስ አባል ከኦነግ ሸኔ ጋር በመወገን የአራት ልጆቹን እናትና የ5 ወር ነፍሰጡር ሚስቱን ገድሏል " ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላኛው የሟች የቅርብ ቤተሰብ ይህ ግድያ በጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ፤ " ጁሩ " የተባለ አካባቢ ላይ እንደትፈጸመ አስረድተው፣ " የሟቿን እናት ጨምሮ ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ጉዳት ደርሶባቸዋል። እኛም ልባችን ተሰብሮ አለን " ብለዋል።

በሌላ በኩል ፤ ሌላኛው የዓይን እማኝ #ጥቅምት_9 በገለጹት መሠረት፣ በደራ ወረዳ " ቆሮ ግንደ በርበሬ " ቀበሌ የኦነግ ሸኔ ጦር አካባቢውን እና መንደሩን ካቃጠለ 2 ሴቶችን እና አንድ ወንድ ገድሏል ሲሉ ከሰዋል።

እንደ ነዋሪው ገለፃ ን በታጣቂ ቡድኑ የተገደሉት ፀጋ እምነት፣ ጌታው አቤቱ እና ለግዜው ስሟን ያላወቁት ሴት ናቸው።

እኚሁ እማኝ ፤ " በመንግሥት ይሁንታ #የደራ_ህዝብ ከፍተኛ የዘር የፍጅት እየደረሰበት ነው " ብለዋል።

ይኸው ዘገባ እየተዘጋጀበት እስከነበረበት ጊዜ ድረስ ታጣቂ ቡድኑ ያለበትን ሁኔታ ሲያስሩዱም፣ " አሁንም በተለያዩ ቀበሌዎች እንደቀጠለ ነው። መንግሥት ምንም እርምጃ አልወሰደም። አድማሱን እያሰፋ ይገኛል " ነው ያሉት።

እኚሁን ምንጭ ጨምሮ ሌሎች የኦሮሚያ እና የአማራ ተወላጅ የደራ ወረዳ ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በገለጹት መሠረት ፣  አሙማ ገንዶ፣ ኢሉ ጎደ ጨፌ ፣ ሀርቡ ደሶ ፣ ዴኙ ወቤንሶ ፣ ጁሩ ዳዳ፣ ሀቼ ኩሳዬ፣ ካራ፣ ጎዲማ ሶስት ዋርካ፣ ጊሊ ወዲሳ፣  ቆሮ ግንደ በርበሬ፣ በዮ ኖኖ፣ ደንቢ ብርጄ፣ ባቡ ድሬ፣ ወሬ ገበሮ፣ መንቃታ፣ የተባሉና ላሎችም ቀበሌዎች እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) በታጣቂ ቡድኑ ስር ናቸው ይላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ቃላቸውን በስልክ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡ የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ፣ መከላከያ በአካባቢው እንዳለ፣ እንደ አጠቃላይ ግን ነዋሪው የጸጥታ ችግር ውስጥ እንደሆነ አስረድተው ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል።

ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው ፤ " ፋኖ ታጣቂዎችም አልፎ አልፎ ጥቃት እያደረሱ  ነው። በመካከል እየተጎዳ ያለው ንጹሐኑ ነው። መንግሥት እርምጃ ቢወስድ ምን አለ ? " ሲሉ ተይቀው ተጨማሪ ሀሳብ ለመስጠት ተቆጥበዋል።

የደራ ወረዳ ነዋሪዎች ባለፉት ሳምንታት በርካታ ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ እንደታገቱ ፣ ከእገታ ለመለቀቅም ከ500 እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እየተጠየቀባቸው እንደነበር፣ በጥቃቱ ከ200 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ፣ በርካታ ቤቶች እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናት እንደተቃጠሉ መግለፃቸው ይታወሳል።

የኦሮሚያ ተወላጆችም ፤ " የፋኖ ታጣቂዎች በርካታ ቁጥራቸው ገና በትክክል ያልታወቀ ሰዎችን ገድለዋል " ማለታቸው አይዘነጋም።

መንግሥት " ኦነግ ሸኔ " እያለ በሚጠራው የታጣቂ ቡድን ታገቱ የተባሉ ሰዎች ከምን እንደደረሱ፣ የሟቾች ቁጥር ስንት እንደሆነ፣ የቤት ቃጠሎ ጥቃቱ እንደቆመና እንዳልቆመ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ላቀረበው ጥያቄ ፣ " ከ500 ሺህ እስከ 1 ሚሊየን ብር የከፈሉ ተለቀዋል፣ ያልከፈሉትን ገድሏል " ብለዋል ሁኔታውን ሲከታተሉ የነበሩ ታማኝ ምንጭ።

ሌሎች ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የሚሰነዝሩትን ግድያ፣ ቃጠሎ፣ እገታ እንዳላቆሙ የሟቾችን ቁጥር ማወቅ እንዳልተቻለ ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደተገደሉ አስረድተው፣ ይህን ልጓም ያጣ ጥቃት መንግሥት ቸል ብሎታል የዓለም መንግሥታት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይወቁልን ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፤ ደረሰ እና አልቆምመ የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ምን ምላሽ እንዳላቸው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የደራ ወረዳ አስተዳዳሪ ለአቶ ሺበሺን በስልክና በአጭር ጽሑፍ እንዲያብራሩ ጥያቄ ቢያቀርብም #ምላሽ_ለመስጠት_ፈቃደኛ_አልሆኑም

አቶ ሺበሺ ከዚህ በፊት ጉዳዩን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ችግሩን ለመቅረፍ የጸጥታ ኃይል እጥረት እንዳለ አስረድተው ነበር።

በተጨማሪ ከዞኑ አስተዳደር፣ ከክልሉ የጸጥታ ቢሮ የተደረገው ተመሳሳይ ሙከራ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፤ በደራ ስላለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ያነጋገረ ሲሆን " ክትትል ተጀምሯል ግን ገና አላለቀም " የሚል አጭር ምላሽ አግኝቷል።

መረጃው በአ/አ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ተጠናቅሮ የቀረበ ነው።

@tikvahethiopia