TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.4K photos
1.47K videos
209 files
4.04K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ኮሬ #ዳርባማናና

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ዳርባ ማናና ወረዳ 2 ወጣቶች መገደላቸውን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከአከባቢው ነዋሪዎች ለማወቅ ችሏል።

አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የቀድሞ አማሮ ልዩ ወረዳ ባለሥልጣን ደግሞ ፤ ወጣቶቹ የተገደሉት ሲጠፉ የነበሩ መከላከያ ሠራዊትን ለማስመለጥ ሞክራችኋል ተብለው እንደሆነ ተናግረዋል።

በመንግስት የፀጥታ ኃይል የተገደለው አንደኛው ወጣት ሳሙኤል ሰለሞን እንደሚባልና ይኸው ወጣት ቀጥታ ሞተር ሳይክል ላይ እንደነበር ተመቶ እንደተገደለ ገልጸዋል።

ሌላኛው አቡለ ጸጋዬ የተባለ ወጣት ጉጂ ቦሬ ወደ ተባለ ካምፕ ከተወሰደ ከቀናት በኃላ ስቃይ ተፈፅሞበት መገደሉን ገልጸዋል።

ቃላቸውን የሰጡ አንድ የአካባቢው ነዋሪ  በበኩላቸው ፦

* ከመከላከያ ሲኮበልሉ የነበሩ አባሎችን ሲፈልጉ የነበሩ የመንግሥት ሠራዊቶች ሁለት በሞተር ሲጓዙ የነበሩ ወጣቶችን ኮሬ ዞን ሸሮ ቀበሌ ሙራ ማንቻ የሚባል ቦታ ምሽት አራት ሰዓት ላይ እንዳገኟቸው ገልጸዋል።

* አንዱ ከጸጥታ ኃይሎቹ በተተኮሰ ጥይት ወዲያው እንደሞተ ፣ ሌላኛውን ደግሞ ለማምለጥ ሲሞክር ይዘውት ወደ ሌላ ቦታ ወስደውት እንደነበር ፤ በኃላም እሁድ 7 ሰዓት ላይ እንደተረሸነ መስማታቸውን ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተፈጸመ ስለተባለው ግድያ ምን ምላሽ እንዳላቸው የኮሬ ዞን ምክትል ፖሊስ አዛዥ አቶ ሲዳሞ ማደቦን ጠይቋል።

ምክትል ፖሊስ አዛዡ  ፤ " በዚህ ነገር ላይ እኔ መግለጫ መስጠት አልችልም፣ ምክንያቱም ወጣቶች በሆነውም ባልሆነውም ቅሬታ ሊያቀርቡ ይችላሉ። መንግሥት እንደ መንግሥት እርምጃ ሊወስድ ይችላል " ብለዋል።

አክለውም፣ " የምሰጠው ነገር ከሕግ ጋር ሊጋጭ ስለሚችል ተነጋግረን ነው መረጃ የምንሰጠው " ሲሉ አክለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ጥያቄ ለዞኑ ፓሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አራርሶ ነጋሽ አቅርቧል።

ሁለት ወጣቶች በጸጥታ ኃይል ለምን እንደተገደሉ ሲጠየቁ ከአሥር ደቂቃ በኋላ እንዲደወል ቀጠሮ ቢሰጡም በቀጠሮው ሰዓት በድጋሚ ሲደወል ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም።

በተጨማሪ፦ " እባክዎ ስልክዎን ያንሱና ምላሽ በመስጠት ኃላፊነትዎን ይወጡ። የወከሉት ሕዝብ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እየተተኮሰበት እየተገደለ እንደሆነ እየገለፀልን ነው ፤ በዚህ ጉዳይም ከ10 ደቂቃ በኋላ ደውሉ ብለው ነበር " ተብሎ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ለተላከላቸው የጽሑፍ መልዕክትም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ከዚህ ባለፈ ፦

- የኮሬ ዞን ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ አየለ ስልክ ባላማንሳታቸው፣

- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ "ስብሰባ ላይ ነኝ" በማለታቸውና በድጋሚ ሲድልወልም ስልክ ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ለማካተት አልቻልንም።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) የክልሉ ቅርንጫፍ በበኩሉ፣ ስለሁለቱ ወጣቶች እስካሁን መረጃ ባይደርሰውም በዞኑ ባለው የጸጥታ ችግር ነዋሪዎች እየተደበደቡ መሆኑን ከዚህ በፊትም እንደተከታተለ አስረድቷል።

ዘገባው በአ/አ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።

@tikvahethiopia