🔴 " ደመወዛችን ተቆርጦ 15 ,000 ብር የሚከፈላቸው 5 ,000 ብር ነው የገባላቸው፡፡ ለ6 ወራት ደመወዛችን በስርዓት እየተከፈለን አይደለም " - ሠራተኞች
🔵 " ጥሩ ቅሬታ ነው። ድርጅቱ ደመወዝ የሚከፍለው ብር ሲኖር ነው " - የናሁ ቴሌቪዥን አስተዳደር
የናሁ ቴሌቪዥን ሠራተኞች የወር መወዛቸው በወቅቱ እንደማይፈጸም፣ ጊዜው ካፈ በኋላ ራሱ ከደመወዛቸው ከግማሽ በላይ ተቆርጦ እንደሚደርሳቸው፣ ደመወዛቸው ባለመከፈሉ ብድር ጭምር እንደገቡ፣ ድርጅቱ አጥጋቢ ምላሽ በመስጠት ፋንታ እያንጓጠጣቸው መሆኑን በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ስሞታ አሰምተዋል፡፡
ሠራተኞቹ ያቀረቡት ዝርዝር እሮሮ ምንድን ነው?
" ደመወዛችን ተቆርጦ 15 ሺሕ ብር የሚከፈላቸው 5 ሺሕ ብር ነው የገባላቸው። ላለፉት ስድስት ወራት የሰራንበት ደመወዝ በትክክል እየተከፈለን አይደለም፡፡ አሁን ለምሳሌ የጥቅምት ወር ደመወዝ ዛሬ ነው የገባልን።
ወቅቱን ተላልፎ እንኳ 13 ሺሕ ብር የሚከፈለን ሰዎች ተቆርጦ 6,500 ብር ነው የገባልን፡፡ ወሩን ሥራ ገብተናል፡፡ ግን ‘ፊርማ አልፈረማችሁም’ ተብሎ ነው የተቆረጠው፡፡ ለዜናም፣ ለጥቆማም ልናናግር ወጥተን ያረፈድነው ሰዓት አይቆጠርልንም፡፡
የሐምሌን ደመወዝ ራሱ ‘ከባንክ ተበደሩና ውሰዱ እኛ እንከፍላን’ ነበር ያሉን፡፡ የሐምሌ ደመወዛችን ባለመፈጸሙ አቢሲኒያ ብድር ገብተናል፡ ግን እስካሁን እለተከፈለንም፡፡
የነሐሴ ወር ደመወዝ ደግሞ 20 ፐርሰንት ተቀንሶ ነው የገባው፡፡ ቀሪውን ራሱ እስካሁን አልሰጡንም፡፡ የመስከረም ደግሞ ጥቅምት 20 ነው የተከፈለን፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ አሁን ደግሞ ደመወዛችን ከግማሽ በታች ተቆርጦ ነው የገባው፡፡
ከ10 ሺሕ ብር እስከ 3,000 ብር ነው የተቆረጠብን፡፡ ይህ ሲደረግ ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ አናውቅም፡፡ ብቻ ደመወዛችን ሲገባ ግን ተቆርጧል፡፡ ስንናገርም ‘ከፈለጋችሁ ውጡ ከፈለጋችሁ ተቀመጡ’ ነው የምንባለው።
ድርጊቱ ከአቅማችን በላይ ሆኗል። እስከ ሰባት ዓመት የሰሩ ጓደኞቻችንን ‘እንዳትመጡ’ ብለዋቸዋል። አንዷ ወር ሙሉ የሠራችበት ተቆርጦ 1,000 ሺሕ ብር ነው የገባላት ከ10 ሺሕ ብር ደመወዟ። ‘ምን ታመጣላችሁ ብትፈልጉ ውጡ’ ነው የሚሉት።
ሰው ለመቀነስ ፈልገው ከሆነ እንኳ በአግባቡ ምክንያቱ ተጠቅሶ፣ ደብዳቤ ተፅፎ፣ ለሠራተኛው የሚገባው ሁሉ ተሰጥቶ ነው የሚሆነው። ከዚህ ግን ማናጀሩ ‘ኑ’ ብሎ ‘ካሁን ወዲያ እንዳትመጡ’ ነው የሚለው " ብለዋል።
የሌሎች ደመወዝ በትክክል እየተፈጸመ ከሆነ የእናንተ ለብቻው ለምን በወቅቱና ሳይቆረጥ አልተፈጸመም? ምን የተለዬ ምክንያት ኖሮ ነው የእናንተ ብቻ እንዲህ የተደረገው? በሚል ላቀረብነው ጥያቄ ምላሻቸው፣ " እነርሱ የሚሉት ‘አቴንዳንስ በትክክል አልፈረማችሁም’ ነው፡፡ ግን ሰዓት አልፎም ቢሆን ፈርመናል " የሚል ነው።
“ ደመወዝ ሊቆረጥ የሚችለው በተሸረረፈው ሰዓት ነው፡፡ ሦስት ቀን ያልፈረመ የአንድ ቀን ይቆረጣል ነው የሚለው ሕጉ” ሲሉ አክለው፣ " እኛ ግን ለምሳሌ 4 ሰዓት ገብተን ቢሮ ውለን የሙሉ ቀን ደመዝ ነው የሚቆረጥብን " ብለዋል።
ቅሬታው ያላቸው 14 ሰዎች እንደሆኑ፣ ከድርጅቱ ደመወዝ ያልተቆረጠባቸው አራት ወይም አምስት ሰዎች እንደሆኑ አስረድተው፣ ድርጅቱ በአግባቡ እንዲያስተዳድራቸው ጠይቀዋል።
ሠራተኞቹ ያቀረቡትን ቅሬታ በመንገር እውነት ነው ? ከሆነ ለምን እንደህ ተደረገ ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ የጠየቃቸው የናሁ ቴሌቪዥን አስተዳደር አቶ ኢዶሳ ቀጀላ፣ " ጥሩ ቅሬታ ነው። ድርጅቱ ደመወዝ የሚከፍለው ብር ሲኖር ነው " የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የድርጅቱ አስተዳደር አክለው ምን አሉ ?
" ብዙ ነገሮች ኪሳራ ላይ ስለጣሉን ብዙ ክፍያ ውጪ ላይ ስለሚያዝብንና ከከስተመሮቻችን ጋር ያሉትን ሴልሶች ቶሎ ኮሌክት ለማድረግ ስለማንችል/ ስለምንቸገር ደመወዝ ቆይተን ልንከፍል እንችላለን።
አንደኛ ደመወዝ ይቆያል። ሁለተኛ ደግሞ በአግባቡ ሥራ ያልገቡ ሰዎችን አቴንዳንሳቸው ኮሌክት ተደርጎ ይገባና ስንት ቀን ሥራ ገብተዋል? ተብሎ ነው ደመወዝ የሚከፈለው።
አሁን ‘ደመወዝ በአግባቡ አልተከፈለንም፣ ተቆረጠ’ የሚሉ ሠራተኞች በወር ውስጥ ስንት ቀን ገብተው እንደፈረሙ አቴንዳንሳቸው ታይቶ ነው ደመወዝ የተከፈላቸው እንጂ ሠራተኞች ስለሆኑ ብቻ 30 ቀናት ታስቦ አይሰጥም።
ስለዚህ የተቆረጠባቸው ሰዎች አሉ። እነርሱም በአግባቡ ያልገቡና አቴንዳንስ ያልፈረሙ ለድርጅቱ ሥራ ያልሰሩ ሰዎች ናቸው " ሲሉ ተናግረዋል።
ደመወዝ ሊቆረጥባቸው የሚገባው በሸራረፉት ሰዓት ሆኖ እያለ ሰዓት አሳልፈው ቢሮ ቢገቡም የሙሉ ቀን መቆረጡ ቅር እንዳሰኛቸው ሠራተኞቹ ገልጸዋል፤ ይህን ማድረጉ አግባብ ነው? ስንል ላቀረበው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።
ምን አሉ ?
"አንድ ሠራተኛ ድርጅቱ በሚያውቀው መልክ ነው ገብቶ የሚወጣው እንጂ ሥራ ስለሌለ 4 ሰዓት መግባት የለም።
የቢሮ መግቢያ ሰዓት ከ2፡30 ይጀምራል። እስከ 3፡30 እኛ እዚያ እንቆያለን አቴንዳንስ ከዚያ በኋላ ይነሳል” ያሉት የድርጅቱ አሰሰተዳዳሪ፣ “እስከ 4 ሰዓት ያልገባ ሠራተኛ ገብቶ እንዲሰራ አንፈልግም፤ አንፈቅድም።
አጋጣሚ ሆኖ ችግር ካጋጠመ ደውሎ ማሳወቅ፣ ማስፈቀድ ይኖርበታል። እንደዚህ የሚያደርጉ ሠራተኞች በጥሩ ትራት ይደረጋሉ።
እንደፈለጉ ለሚገቡና ለሚወጡ ሠራተኞች ደመወዛቸውንም አንከፍልም፤ እሱም ብቻ ሳይሆን አስተዳደራዊ እርምጃም እንወስድባቸዋለን። ይህን ሕጉም ስርዓቱም ይፈቅዳል” በማለት ነው የመለሱት።
ድርጅቱ ሠራተኛ ለመቀነስ ፈልጎም ከሆነ በደብዳቤ እንጅ ‘ውጡ’ ተብሎ “ተጥላልተን” መሆን የለበትም የሚል ቅሬታ ሠራተኞቹ አላቸው፤ ይህን ማድረግስ ለምን አስፈለገ? በሚል ቲክቫህ ላቀረበው ጥየያቄ፣ “ይህን አላደረግነውም” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM