TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.4K photos
1.47K videos
209 files
4.03K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#update የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን⬇️

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን #ወደነበረበት የሚመልስ ረቂቅ ዕቅድ ተዘጋጀ። ለመጀመርያ ጊዜ በአዲስ አበባ የፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ይቋቋማል

በግንቦት 1997 ዓ.ም. ከተካሄደው #ምርጫ በኋላ በተፈጠረው ቀውስ ወደ #ፌዴራል መንግሥት የተዘዋወረውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ወደ ከተማው አስተዳደር መመለስ የሚያስችል ረቂቅ ዕቅድ ተዘጋጀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አደረጃጀትና መዋቅር ጥናት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ባካሄደው ጥናት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሱ የሆነ አዲስ የፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እንዲመሠርት ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ባከናወነው ጥናት ላይ የመጀመርያ ዙር ውይይት ረቡዕ መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ፣ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አስተዳደር ቢሮ›› የተሰኘ አዲስ የካቢኔ አባል የሚሆን ተቋም እንዲመሠረት ሐሳብ ቀርቧል፡፡

ይህ አዲስ ተቋም ላለፉት 14 ዓመታትአስተዳደር በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ሆኖ የቆየውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በድጋሚ ወደ ከተማው በመመለስ፣ የከተማውን ደንብ ማስከበር አገልግሎትና በክፍለ ከተማና በወረዳ የሚቋቋሙትን የፀጥታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶችን አቅፎ ይይዛል፡፡

#የአዲስ አበባ ከተማ የፀጥታና ቢሮ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለከተማ #አስተዳደሩ ከንቲባ ይሆናል ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አደረጃጀትና መዋቅር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ ፍቃዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተዘጋጀው ጥናት ለካቢኔ ቀርቦ ይሁንታ ካገኘ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ቀርቦ ሲፀድቅ ተግባራዊ ይሆናል፡፡

በቀረበው ረቂቅ ጥናት ላይ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 2 እና በቻርተሩ 95 አንቀጽ 10 መሠረት፣ አዲስ አበባ ከተማ ራሱን የማስተዳደር #መብት አለው፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል፣ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፤›› ሲል ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ደንግጓል፡፡

ረቂቅ ጥናቱን ያቀረቡት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ቤተ ማርያም መኮንን እንዳሉት፣ አዲስ አበባ ከተማ እስካሁን የራሱ የፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የለውም፡፡

‹‹ራሱን የቻለ የፀጥታ መዋቅር ባለመኖሩ የከተማውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ባደረገ መንገድ ባለመደራጀቱ፣ የፀጥታ ተቋማቱ በተለያየ መዋቅር እንዲመሩ ሆኗል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ቤተ ማርያም፣ ‹‹አዲስ የፀጥታ አስተዳደር መዋቅር ተግባራዊ ሲሆን ይህ ችግር ይፈታል፤›› ብለዋል፡፡

በአዲሱ መዋቅር መሠረት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክፍለ ከተማና የወረዳ የፀጥታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች፣ በማዕከል፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ ያሉ የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤቶች በቢሮው ሥር ይተዳደራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ዓመታት የፍትሕ፣ የፀጥታ፣ የሰላም፣ የመልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች መነሳታቸውን ያስታወሱት ደግሞ፣ የከተማው ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ ኤፍሬም ግዛው ናቸው፡፡

ከነዋሪዎች የሚነሱትን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት፣ የከተማውን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ አዲሱ መዋቅር ወሳኝ ድርሻ እንዳለው አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡

ይህ ጥናት እንዲካሄድ መመርያ የሰጠው የከተማ አስተዳደር ካቢኔ በመሆኑ፣ በሒደት ላይ ያሉ ሥራዎች ሲጠናቀቁ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር
@tsegabwolde @tikvahethiopia