TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
"የአነግ #አባል ስለሆነ የታሰረ #የለም" የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን
.
.
በፖለቲካ ምክንያት ታስረው ከነበሩና ኋላ ከተፈቱት መካከል የሆነችው #ጫልቱ_ታከለ ከሶስት ቀን በፊት በምዕራብ ወለጋ ሻምቡ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ተይዛ እስር ላይ ትገኛለች።

ጫልቱ ብቻ ሳትሆን የቤጊ ወረዳ አባ ገዳ ጌታቸው ተርፋን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሰዎች እንደታሰሩ የጫልቱ እናት ወ/ሮ አስካለ አብዲ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ማክሰኞ ማታ ቤት ውስጥ የመከላከያ ሃይል አባላት መጥተው በቁጥጥር ስር እንደዋለች ተናግረዋል።

በምን ምክንያት የታሰረች ይመስልዎታል ተብሎ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄም የታሰረችበትን ምክንያት በትክክል ባያውቁም "ኦነግ ስለሆነች ይመስለኛል። ሌላ ጥፋት ያለባት አይመስለኝም። ለራሷም ስንት አመት ተሰቃይታ ነው የወጣችው" ብለዋል።

ጫልቱ ከአመታት በፊት የሃገርን ፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት በሚል ተከሳ 12 አመት ተፈርዶባት 8 ዓመት ከ45 ቀን ታስራ በአመክሮ ወጥታለች።እንደገና በሽብር ተከሳ 11 ወር ከታሰረች በኋላ መንግስት ከወራት በፊት እስረኞችን ሲለቅ እሷም ክሷ ተቋርጦ ከእስር መውጣቷ የሚታወስ ነው።

ጫልቱ ወደ ትውልድ ቦታዋ ሻምቡ ከሄደች አንድ ወር እንዳስቆጠረች የሚናገሩት እናቷ በሻምቡ ባለው የኦነግ ፅህፈት ቤት ሊቀ መንበር ሆና ለአንድ ሳምንት ሰርታለች።
የኮማንድ ፖስቱን መምጣት ተከትሎ ቤቷ እንዳለችም ወ/ሮ አስካለ ጨምረው አስረድተዋል።

የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ በበኩላቸው ግለሰቦቹ የታሰሩት በወንጀል ተጠርጥረው እንጂ የኦነግ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ስለሆኑ አይደለም ብለዋል።

"የኦነግ አባል ስለሆነ የታሰረ የለም፤ የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ለአንድ ወንጀል ሽፋን መሆን አይችልም" ብለዋል።

እስካሁን ለምን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡም ተጠይቀው " ያለኝ መረጃ በቅርቡ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ነው" ብለዋል።

ከባለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ አለመረጋጋትና ግጭቶች የበረከቱ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ተሰማርቷል።

በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ የተሰማሩ ታጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ ሊታገሉ የመጡ ናቸው በሚል የክልሉ ፀጥታ ኃይል የሚደርሱ ግድያዎችና ዘረፋዎች ማስቆም አቅቶት እንደነበር የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ብርሃኑ ጁላ የመከላከያ ሚኒስቴርን ግማሽ አመት የስራ ክንውን ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ እለት ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል።

በአካባቢው ፖሊሶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች መገደላቸውንና ዝርፊያዎች እንደደረሱ የተናገሩት ጄኔራል ብርሃኑ "በውትድርና ዘመኔ በራስ ሕዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ዘግናኝ ጥቃት ተፈፅሞ ያየሁት በምዕራብ ወለጋ ነው" ብለዋል።

ምንም እንኳን የአካባቢውን ፀጥታ ማስከበር ሃላፊነት የክልሉ ኃይል ቢሆንም ነገሩ ከአቅም በላይ በመሆኑ የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ተሰማርቶ የማረጋጋትና ወደ ሰላም የማምጣት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ምንጭ፦ BBC አማርኛ
@tsegabwolde @tikvahethiopia