TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
57.8K photos
1.44K videos
207 files
3.99K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
#አማራ_ክልል ከትጥቅ ግጭት ጋር በተያያዘ #አሳሳቢነታቸው የቀጠለ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተላከልን መግለጫ ከላይ ተያይዟል። @tikvahethiopia
#አማራ

በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች ውስጥ ንጹሐን ሰዎች መገደላቸውንና የአካል ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ ጎዳና ላይ የነበሩ ሰዎች ማቆያ መገኘቱ ይፋ ተደርጓል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የታሰሩ ሰዎችም የተጠረጠሩበት ወንጀል ምርመራ በአስቸኳይ በማጠናቀቅ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ ተጠይቋል።

ኮሚሽኑ ዛሬ መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች ንጹሐን ሰዎች መገደላቸውን እና የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ፦
- ከነዋሪዎች፣
- ከተጎጂዎች፣
- ከተጎጂ ቤተሰቦች
- ከዐይን ምስክሮች ባሰባሰባቸው መረጃዎች መሠረት የትጥቅ ግጭቱ ወደ ክልሉ ልዩ ልዩ ወረዳዎች መስፋፋቱን ተረድቷል" ሲል የጠቀሰው መግለጫው፣ "በነዋሪዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ተባብሶ ቀጥሏል" ብሏል።

" ለምሳሌ ከነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በተለይም ፦
- በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረማርቆስ ከተማ፣
- በሰሜን ጎጃም ዞን አዴትና መራዊ፣
- በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር፣
- በማእከላዊ ጎንደር ዞን ደልጊ፣
- በሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ፣ ሸዋ ሮቢት እና አንጾኪያ ከተሞች እና በአካባቢዎቻቸው በሚገኙ አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች በግጭቱ ዐውድ በርካታ ሲቪል ሰዎች መሞታቸውን " አስታውቋል።

ኢሰመኮ አክሎ፣ " ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና የንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው ለመረዳት ተችሏል " ብሏል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው፣ " በተኩስ ልውውጦች ወይም በከባድ መሣሪያ ተኩስ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል በመንገድና በእርሻ ሥራ ላይ እንዲሁም በቤታቸው ውስጥ የነበሩ ሰዎች ጭምር የሚገኙ መሆኑን ቤተሰቦች እና የዐይን ምስክሮች ያስረዳሉ " ሲል አስገንዝቧል።

" በዚሁ የግጭቱ ዐውድ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከሕግ/ፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች (extrajudicial killings) እጅግ አሳሳቢ ነው "ም ብሏል።

" ለምሳሌ ከሐምሌ 24 እስከ ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በተለይም ፦
- በአዴት፣
- በደብረማረቆስ፣
- በደብረ ታቦር፣
- በጅጋ፣
- በለሚ፣
- በማጀቴ፣
- በመራዊ፣
- በመርጦ ለማርያምና ሸዋ ሮቢት ከተሞች ተስፋፍተው በተፈጸሙ ከሕግ/ፍርድ ውጪ የሆኑ #ግድያዎች ሰለባ " የሆኑ ሰዎች እንዳሉ መግለጫው ያስረዳል።

ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች " በተፈጸመ ከሕግ አግባብ ውጭ ከሆኑ ሰዎች መካከል ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ የተያዙ ሰዎች፣ በግጭቱ ወቅት መንገድ ላይ የተገኙ እና ያልታጠቁ ሰዎች፣ ' የጦር መሣሪያ ደብቃችኋል አምጡ ' በሚል የተያዙ ሰዎች፣ የሰዓት እላፊ ገደቦችን ተላልፈው የተገኙ ሲቪል ሰዎችና በቁጥጥር ስር የዋሉ የታጣቂው ቡድን (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚታወቀው) አባላት የሚገኙበት ሲሆን፤ በኮሚሽኑ እና በአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርዱ አማካኝነት የተሟላ ምርመራ ሊደረግበት የሚያስፈልግ ነው " ይላል መግለጫው።

" ከዚህ በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ኮማንድ ፖስት በይፋ ካሳወቃቸው እስሮችና ቦታዎች ውጪ በተለይ በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ጊዜ ዐውዱ የተስፋፋና የዘፈቀደ እስር የተፈጸመ "ም ተመላክቷል።

ኮሚሽኑ ይህን ሲያብራራም፣ "ለምሳሌ በአማራ ክልል ፦
- በባሕር ዳር፣
- በደብረ ታቦር፣
- በደብረ ማርቆስ፣
- በፍኖተ ሰላም፣
- በጎንደር፣
- በላሊበላ፣
- በመካነሰላም፣
- በቆቦ እና በሸዋ ሮቢት ከተሞች፤ በኦሮሚያ ክልል በተለይ #በሸገር ከተማ እና #በአዲስ_አበባ ከተማ የተፈጸሙ የዘፈቀደ እስሮች ይገኙበታል " ሲል አክሏል።

" ከእነዚህ ታሳሪዎች ውስጥ በደቡብ ክልል ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ግቢ (በተለምዶ አቦስቶ በመባል የሚታወቀው ቦታ) የነበሩ ታሳሪዎችን ጨምሮ ከተለያየ ጊዜ መጠን በኋላ የተለቀቁ መኖራቸውን ማወቅ የተቻለ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ገና ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ሰዎች ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ " ነው ያለው።

እንደ ኮሚሽኑ መግለጫ፣ " በመንግሥት የጸጥታ አካላት የሚታሰሩ ሰዎች በአብዛኛው ' ለታጣቂ ቡድኑ ድጋፍ ታደርጋላችሁ ' እና/ወይም 'የጦር መሣሪያ ደብቃችኋል ' በሚል ምክንያት ነው " ብሏል።

አክሎም ፣ " በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ ውስጥ ሲዳ አዋሽ ወረዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ጊዜያዊ ማቆያ ማእከል ውስጥ ተይዘው የነበሩ " ሰዎች ማረጋገጡን አስታውቋል።

" ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊትና በኋላም ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ውሏቸውን ጎዳና ያደረጉ ነዋሪዎች ከጎዳና ላይ ተነስተው እንዲቆዩ የሚደረግበት ቦታ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው ፤ በቅርቡ ወደ ማእከሉ ከተወሰዱት ውስጥ 29 ሰዎች በመታወቂያ ካርዳቸው ተለይተው እንዲለቀቁ መደረጉን " አትቷል።

አክሎም ፤ " የተወሰኑት ደግሞ በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ወደየመጡበት አካባቢዎች እንዲመለሱ የተደረገ መሆኑን፣ በጣቢያው ውስጥ ተከስቶ የነበረው ተላላፊ በሽታ በቁጥጥር ስር የዋለ መሆኑን ኮሚሽኑ በክትትሉ ተመልክቷል " ብሏል።

ኮሚሽኑ በመጨረሻም የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ጨምሮ ፤ " በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የታሰሩ ሰዎችም የተጠረጠሩበት ወንጀል ምርመራ በአስቸኳይ በማጠናቀቅ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ " ሲል ጠይቋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ መረጃውን ያዘጋጀው #ከኢሰመኮ በተላከለት መግለጫ ነው።

@tikvahethiopia