TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.3K photos
1.47K videos
209 files
4.03K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
TIKVAH-ETHIOPIA
" ቅዱሱን ቅርስ መጠበቅና የአባቶቻችንን አደራ እንዳንበላ በአካባቢው የጦርነት ድምጽ እንዳይሰማ መደረግ አለበት " - ብፁዕነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በጦርነት ምክንያት  የአደጋ ስጋት ላይ መሆናቸውን አሳወቀች። ቤተክርስቲያኗ ፤ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የሚገኙት የቅዱስ ላላበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በ900 ዓመታት ውስጥ ብዙ መከራን…
#ላሊበላ

" ' ቫይብሬሽን ትንሽ ነበረ የሚባለው ' ሲተኮስ ይሄ እውነታ ነው እዚያ ያሉ ኮሚቴዎችም ያረጋገጡት ነው... ቤተ ሙዚየሙ መግቢያ መድኃኒዓለም ግን ጥይት መትቶታል። ጥይቷ አጥሯ ላይ እንደተሰካች ናት " - አቶ አበባው አያሌው

(በኢዮብ ትኩዬ)

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ስለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያንና ቅርስ ጉዳት ደርሷል ስለሚባለው ጉዳይ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአማራ ፤ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያንና ቅርስ ዙሪያ በፋኖ ታጣቂዎችና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ሰሞኑን ተደረገ በተባለ የተኩስ ልውውጥ በቅርሱ ላይ ጉዳት እንደደረሰ ፣ ከባድ መሳሪያ እየተተኮሰ በመሆኑ ከፍተኛ ንዝረት እንዳለ በዚህም ቅርሱ አደጋ እንተጋረጠበት የተለያዩ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያው ሲንሸራሸሩ ተስተውለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ በበኩላቸው በሰጡት መግለጫ " ቅዱስ ቅርሱ " አደጋ ላይ እንደሆነ ገልጸው ነበር።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በበኩሉ ፦
* በቅርሱ ላይ የደረሰ ጉዳት አለ ?
* ስለ ጉዳዩ የሚወጡት መረጃዎች ምን ያህል እውነተኛነት አላቸው ?
* አዲስ ስንጥቅ አለ ? የሚሉትን ጥያቄዎችና አጠቃላይ ስለጉዳዩ ያለው ማብራሪያ ምን እንደሆነ ለቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጥያቄ አቅርቧል።

በቅርሱ ላይ የደረሰ ጉዳት አለ ወይስ የለም ? ተብሎ በመጀመሪያ ጥያቄ የቀረበላቸው የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይይሬክተር አቶ አበባው አያሌው ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም በቦታው ኮሚቴ ተልኮ ተረጋግጧል ያሉትን ሁኔታ ከማብራራት ጀምረው እንደሚከተለው ገልጸዋል።

" ላሊበላ አካባቢ ግጭት ነበረ። ከዚያ በመነሳት ነው ' በጥይት ተመቷል ' ይሉ የነበረው " ሲሉ ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም 7 ሰዎች ያሉበት (ከደብሩ ካህናት 3 ሰዎች፣ ከላሊበላ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት 3 ሰዎች፣ በቦታው ከሚገኝ የቅርስ ባለሥልጣን 1 ሰው) ኮሚቴ ተዋቅሮ ከ3፡00 እስከ 6፡40 ገደማ ዞረው ቅርሱን አይተዋል ብለዋል።

በዚህም የሰሜን ምሥራቅ ግሩፕ ኮሚቴ ፦
- ቤተ አማኑኤልን፣
- ቤተ ሊባኖስ፣
- ቤተ ገብርኤል ያሉባቹውን ቦታዎች ተመክተዋል ነው ያሉት።

አቶ አበባው አክለውም ፤ " ' በቤተ ገብርኤል አናቱ ላይ ጥይት አርፏል' የሚል ነው ወሬው እዛ ሲወራ የነበረው " ብለው፣ "ቤተ ገብርኤል ተወጥቶ ታይቷል። ጥይት ያረፈበት ምንም ነገር የለም " ሲሉ ተናግረዋል።

2ኛው ደግሞ ' ቤተ ሊባኖስ አካባቢ ጥይት ተተኮሰ ' የሚል ነገር እንደነበር ገልጸው፣ " እዛም ላይ ምንም ምልክት የለም። እንዳውም ጥገና እየሰራንበት ነው። 'ቤተ አማኑኤል ላይ ደግሞ የመጠለያውን ብረቱን ጥይት መትቶታል' የሚል ነው፣ ምንም የተመታ የለም። በቦታው የነበሩ ጥበቃዎች አሉ ፣ የተመታ ነገር የለም፣ ግን ሲተኮስ #ቫይብሬሽን ስለነበረው ቃቃ ይል ነበር መጠለያው ከዚያ ውጭ ምንም ነገር የለም " ሲሉ ከኮሚቴዎቹ ያገኙትን ምላሽ አስረድተዋል።

ከሰሜን ምሥራቅ ግሩፕ ቀጥሎ የደቡብ ምዕራብ ግሩፕ ደግሞ ፦
- ቤተ መድኃኒዓለም፣
- ቤተ ማርያም፣
- ቤተ ጎለጎልታ ያሉበትን ቦታ እንደተመለከተ፣ እዚያ ሲባል የነበረው ደግሞ 'የቤተ መድኃኒዓለምን መጠለያ ብረቱን መትቶታል' የሚል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ " ጥይት ሲያርፍ ምልክት ይኖረዋል። ግን ዙረው አይተዋል። ምንም ነገር የለም " ብለዋል።

አንድ ያሳዩአቸው የመጠለያው አናት ሸራ ከጎኑ ቀዳዳ አለ ' ተመትቶ ነው ' የሚል ነው፣ ያቺ ደግሞ ሸራ ቀዶ መግባትም ብዙም ትልቅ ችግር እንደማይኖረው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ጎለጎልታ፣ ቤተ ደናግል እንዲሁም ቤተ ጊዮርጊስ ምንም የተኩስ ምልክት እንደሌለ ተናግረዋል።

አክለውም ፣ ' ትንሽ #ቫይብሬሽን ነበረ ' የሚባለው ሲተኮስ ይሄ እውነታ ነው እዚያ ያሉት ኮሚቴዎችም ያረጋገጡት ነው" ብለው፣ የአካባቢው ማኅበሰሰብ የደብሩ ካህናት ሆነው አጠቃለሁ የሚለውን ኃይል በግዝትም ቢሆን ወደ ቅርሱ እንዳይጠጋ ማድረግ፣ በመንግሥት በኩል ቅርስ ጥበቃም፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮም ምንም አይነት ታጣቂ ቡድን በአካባቢው እንዳይኖር ለማድረግ መስራት፣ ከዚያ ውጭ ደግሞ ቤተ ክህነትም ሆነ የመንግሥት አካላት መግለጫ ሲያወጡ ጠይቀው እንዲያወጡ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከኮሚትዎቹ ጋር መወያየታቸውን አስረድተዋል።

ኮሚቴው ቦታው ላይ ተገኝቶ ሳይመለከት የቆየበት ምክንያትን ሲያስረዱም አቶ አበባው ፤ " #ሀዘን ሆኖ ነው አካባቢው ያዘገየነው። ብዙ ሰው አልቋል። በቦታው ድንኳን አለ፣ እንዲያው በትኩሱ ተነሱና እዩ ከምንላቸው ብለን ነው " ብለዋል።

አክለው " ቅርስ ፖለቲካ አይሆንም፣ ያኔ የነበሩ ሰዎች ቅርሱን ለእኛ አውርሰውናል ሲሆን እንጠብቀዋለን እንጂ በእኛ የፖለቲካ ንትርክ ውስጥ ቅርስን አናስገባም፣ ከፖለቲካም ከምንም በላይ ነው፣ መተኪያ የለውም፣ ይህን ማንም ማሰብ አለበት" ነው ያሉት።

" ከዚያ ውጭ ቀጣይ የምንሰራው ንዝረቱ ካለ ምን አስከትሏል የሚለውን ነው። እያንዳንዷን ስንጥቅ እናውቅምታለን። አዲስ ስንጥቅ ካለ እናሳውቃለን " ሲሉ ገልጸዋል።

ባደረጋችሁት ዳሰሳ አሁን አዲስ ስንጥቅ የለም? የሚል ጥያቄ ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ለቀረበላቸው ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ፣ "የላሊበላን ያሉትን ስንጥቆች ካህናቱም ያውቋቸዋል። እዚያ ያለው ጽሕፈት ቤት ኃላፊም ያውቀዋል። የእኛም ባለሙያ ያውቀዋል። አዲስ ስንጥቅ የለም ኢን ኬዝ ግን ቫይብሬሽኑ ስንጥቅ አስፍቶ ይሆን እንዴ? የሚለውን ለማረጋገጥ 3ዲ ስካን እናወጣለን። አሁን ያለውን እናያለን፣ እናነጻጽራለን እንጅ ላሊበላ ስንጥቅ በስንጥቅ ነው 22 ቦታዎች ተሰንጥቀው እየተጠገኑ ነው" ብለዋል።

አቶ አበባው በሰጡት አክለው ማብራሪያ፣ "ተመታ የሚባለው ቤተ ሙዚየሙ መግቢያ መድኃኒዓለምን ግን ጥይት መትቶታል። ጥይቷም አጥሯ ላይ እንደተሰካች ናት፣ እሷን ነው እያነሱ ሲበትኑ የነበረው ያ ደግሞ አጥሯ ላይ ግንብ ነው በ2012 ዓ.ም የተሰራ ነው" ብለዋል።

አክለውም፣ " ሁለተኛ ጥይት ያለችው ቤተ ደናግል ማርያም ጋ ኢህአዴግ ሰቆጣ ሲገባ የደርግ ወታደሮች እዛ ገብተው ነበር ይተኩሱ ነበር እሷም አለች" ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ስለጉዳዩ ምን ማብራሪያ እንዳላቸው የተደረግልው ሙከራ አልተሳካም። ይሁን እንጅ ጉዳዩን በተመለከተ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ቅዱስ ቅርሱ አደጋ ላይ እንደሆነና ልንታደገው እንደሚገባ ገልጸው ነበር።

የብፁዕነታቸው መግለጫ በተመለከተ ምን ምላሽ እንዳላቸው ከቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አበባው፣ "አቡነ ኤርሚያስ ትልቅ ሰው ናቸው ግን ሰው ሊያሳስታቸው ይችላል። ሁሉም ልጆቻቸው ናቸው ፤ እዚያ ያሉት በኮሚቴው የተገመገመው ትክክል አልነበረም የሚል ነው ፤ እርሳቸውም ትንሽ ቹኩለዋል " ብለዋል።

አክለውም ፣ " በመንግሥት በኩልም ግጭት የለም በቦታው ላይ ማለት ትክክል አልነበረም ግጭት ነበረ በእርግጥ " ያሉት አቶ አበባው ፣ " እርሳቸው በተፈጥሯቸው የእውነት ሰው ናቸው ከመቆርቆር የተነሳ ሊሆን ይችላል። መቆርቆሩንም እንወደዋለን " ብለዋል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethiopia