TIKVAH-ETHIOPIA
1.53M subscribers
58.8K photos
1.49K videos
211 files
4.07K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#ኢትዮጵያ #ረቂቅአዋጅ

በመሣሪያ ላይ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓት ማቋረጥን የሚፈቅድ ረቂቅ ሕግ በጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ተካቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደቀረበ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።

መሣሪያ ላይ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ማቋረጥ የሚቻለው የታማሚዎችን የልብና የመተንፈሻ አካላት የአሠራር ሥርዓት መመለስ በማይችልበት ደረጃ ሥራቸውን ሲያቆሙ፣ ወይም የአንጎል ሞት ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 14 ተደንግጓል፡፡

ዝርዝር አፈጻጸም የጤና ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ እንደሚወሰን ተመላክቷል፡፡  

በማይድን በሽታ የሚሠቃዩና የሕይወታቸውን ፍፃሜ የሚጠባበቁ ሰዎችን ሥቃይ ለመቀነስ የሚሰጥ የጤና አገልግሎት በረቂቅ አዋጁ የተካተተ ሲሆን፣ በጤና ባለሙያ ወይም ሥልጠና ባገኘ ማንኛውም ግለሰብ (አካላት) ሊሰጥ እንደሚችል በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 13 ተደንግጓል፡፡

" ሆስፒስ " እየተባለ የሚጠራው አገልግሎቱ የሚሰጠው ተገልጋይ የቅርብ ዘመዶቹ ስለታካሚው የበሽታ ክብደት፣ ደረጃና ስለሚያስከትው ውጤት ሊያውቁ እንደሚገባ በረቂቅ አዋጁ ተዘርዝሯል፡፡

በማንኛውም ሁኔታ የተገልጋይን ሕይወት የሚያሳጥር ሕክምና ተግባር መፈጸምን ይከለክላል ይላል፡፡

በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው በክፍል ሦስት በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሥር ከተዘረዘሩት ውስጥ፣ ስለሆስፒስ ወይም በማይድን በሽታ የሕይወታቸው ፍፃሜ የሚጠባበቁ ሰዎች የሚሰጥ አገልግሎትና በመሣሪያ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓት ስለሚቋረጥበት ሁኔታ በተመለከተ ይገኝበታል፡፡

የጤና አገልግሎቶች አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ በ12 ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን፣ ጠቅላላ ድንጋጌዎች ስለአጠቃላይ የጤና አገልግሎት፣ ስለመብትና ግዴታ፣ ስለጤና አገልግሎት አሰጣጥ፣ ስለልዩ የጤና አገልግሎቶችና ሌሎች 60 አንቀጾች ተካተውበታል፡፡

የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 5/2017 ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጤና ማኅበራት ልማትና ባህል ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

ሆስፒስ ማለት ምን ማለት ነው ?

በሕይወት መትረፍ የማይችሉ ሰዎች የሚሰጣቸው የሕክምና አገልግሎት ነው።

ታካሚው ስለሕመሙ እንዲያውቅ የሚደረግበትና ቤተሰብ (አስታማሚ) እንደሚቀበሉት የሥነ ልቦና ድጋፍና ምክር የሚገኙበትን አገልግሎት ያካተተ ነው።

የጤና ባለሙያዎች ምን አስተያየት ሰጡ ?

- ከዚህ ቀደም በመሣሪያ የታገዙ ታማሚዎች ሕይወታቸው እንደማይተርፍ እየታወቀ፣ መሣሪያውን ለመንቀል ከሥነ ምግባር አኳያ ለመወሰን ይከብድ ነበር።

- በመሣሪያ ላይ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓት የሚቋረጥበት ሁኔታ የሕግ ማዕቀፍ የለውም የተወሰነ የአንጎል ክፍል እየሠራ ነገር ግን መሣሪያው እየተነፈሰላቸው እስከ 2 እና 3 ዓመታት በሕክምና የሚቆዩ ታማሚዎች ይኖራሉ።

- በመሣሪያ ብቻ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓት የሚቋረጥበትን ሁኔታ ውሳኔ ለመስጠት ማረጋገጫ በሚሰጡ ሆስፒታሎች የሥነ ምግባር ኮሚቴ መኖር አለበት።

- ጉዳዩ በባለሙያ ብቻ መወሰን የሌለበት በመሆኑ በየጤና ተቋማቱ ራሱን የቻለ የሥነ ምግባር ኮሚቴ መቋቋም ይገባዋል።

(#ሪፖርተር_ጋዜጣ)

@tikvahethiopia
#ረቂቅአዋጅ

የከተማ መሬትን በድርድር በሊዝ ማስተላለፍ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ሊቀርብ ነው።

የከተማ መሬትን ከጨረታ እና ከምደባ በተጨማሪ #በድርድር በሊዝ ማስተላለፍ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ሊቀርብ መሆኑን ' ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ' አስነብቧል።

አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ፤ ከተሞች በምደባ ለማቅረብ ካዘጋጁት መሬት መጠን ውስጥ፤ ቢያንስ 20 በመቶውን ለቤት ግንባታ አገልግሎት መዋል እንዳለባቸው ግዴታ ይጥላል። 

" የከተማ መሬትን በሊዝ ስለመያዝ " እንደወጣ የተገለጸው ይህ አዋጅ፤ ነገ በሚካሄድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ እንዲቀርብ አጀንዳ ተይዞለታል።

ረቂቅ አዋጁ " መሬትን በድርድር በሊዝ ለማስተላለፍ " ምን ይላል ?

➡️ ረቂቅ አዋጁ መሬትን በድርድር በሊዝ ለማስተላለፍ የሚፈቅደው ድንጋጌ ይገኝበታል።

➡️ 13 ዓመት ያስቆጠረው ነባሩ አዋጁ፤ የከተማ ቦታ በሊዝ እንዲያዝ የሚፈቀደው በጨረታ ወይም በምደባ ስልት ብቻ ነበር።

➡️ በአዲሱ አዋጅ የተካተተው ' የድርድር ' ስልት፤ በጨረታ እና በምደባ አግባብ ለተጠቃሚ ሊተላለፉ በማይችሉ የከተማ መሬቶች ላይ፤ አንድ አልሚ " ለተለዩ ሀገራዊ ፋይዳ ላላቸው አገልግሎቶች " መሬት በሊዝ ይዞ ማልማት የሚፈቀድበት ነው። 

➡️ ይህ ተግባራዊ የሚደረገው " አግባብ ያለው አካል " ከአልሚዎች ጋር በሚያስቀምጠው " የልማት እቅድ መሰረት " እና " ከአልሚው ጋር በመደራደር " ነው።

➡️ የከተማ መሬት በድርድር ሊተላለፍ የሚችለው " ሀገራዊ እና ክልላዊ የከተማ ልማት ስፓሻል ፕላንን " መሰረት በማድረግ ነው ይላል ረቂቅ አዋጁ።

➡️ በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ ለሚቀርቡ የልማት ጥያቄዎች፤ መሬት በድርድር አግባብ ሊተላለፍ እንደሚችል በአዲሱ አዋጅ ተደንጓል።

➡️ በፌደራል መንግስት ለሚተዳደሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለከፍተኛ የትምህርት እና የጤና ተቋማት እንዲሁም ለምርምር ዘርፍ ፕሮጀክቶች የከተማ መሬት በድርድር ሊተላለፍ እንደሚችል ተዘርዝሯል።

➡️ የአገልግሎት ዘርፉን የሚደግፉ ባለኮከብ ሆቴሎች እና ለቱሪስት ልማት ለሚውሉ ሪዞርቶችም የሚቀርቡ የመሬት ጥያቄዎች በድርድር አሰራር ሊስተናገዱ ይችላሉ።

➡️ በግሉ ዘርፍ አሊያም በመንግስትና በግሉ ዘርፍ በሽርክና ሊለሙ የሚችሉ የከተማ መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶችም፤ በዚሁ የመሬት አሰጣጥ አግባብ እንደሚስተናገዱ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

➡️ ለሪል ስቴት ወይም ለቤት ልማት የሚቀርቡ የመሬት ጥያቄዎች፣ የግዙፍ የገበያ ማዕከላት (ሞል) ፕሮጀክቶች፣ ትላልቅ የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች እና ማከፈፋያዎች፣ ለዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ህንጻ ግንባታዎች የሚውሉ ቦታዎች፤ በተመሳሳይ መልኩ በድርድር ማግኘት እንደሚቻልም ተመላክቷል።

➡️ በድርድር አግባብ የሚስተናገዱ ፕሮጀክቶች " የሚመጣዉ ልማት ይዘት፣ ስፋትና ጥልቀት፤ ለልማት በተመረጠው ቦታ ነባር ተጠቃሚ የሆኑ ባለይዞታዎች መስተንግዶና ተጠቃሚነት፣ በዙሪያ ባሉ ማህበረሰቦች ተጠቃሚነትና ጉዳት ቅነሳ እንዲሁም የመሰረተ ልማት አቅርቦት ድርሻ " ከግምት ውስጥ እንደሚገባ የአዋጅ ረቂቁ አትቷል።

➡️ የከተማ ቦታ በድርድር አግባብ እንዲተላለፍ የሚደረገው፤ በክልሎች፣ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ አስተዳደሮች " ካቢኔ ሲወሰን ብቻ " ነው።

➡️ መሬት በድርድር የማስተላለፊያ ዋጋ፤ ከአካባቢው አማካይ የሊዝ ጨረታ ዋጋ በታች መሆን እንደሌለበትም በአዲሱ አዋጅ ተደንግጓል። 

በምደባ ስለሚሰጥ የከተማ መሬትስ ምን ይላል ?

🔴 አዲሱ ድንጋጌ ' ከተሞች በምደባ ለማቅረብ ካዘጋጁት የመሬት መጠን " ውስጥ " ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆነውን " ለቤት ግንባታ አገልግሎት መዋል እንዳለባቸው ግዴታ ይጥላል።

🔴 በአንድ ከተማ በመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበር፣ በጋራ መኖሪያ ቤት ልማት ፕሮግራም ወይም በተናጠል የከተማ መሬትን በምደባ ተጠቃሚ የሆነ ግለሰብ፤ በዚያው ከተማ " ለሁለተኛ ጊዜ በምደባ ተጠቃሚ እንዳይሆን " የሚያግድ አዲስ ድንጋጌም ተካቷል።

🔴 በአዲሱ አዋጅ፤ መሬት በጨረታ የሚያሸነፉ ግለሰቦች ለሚያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶች ላይ ማሻሻያ ተደርጎበታል። እስካሁን በስራ ላይ ባለው የሊዝ አዋጅ፤ አንድ ተጫራች የመሬት ጨረታ አሸናፊ የሚሆነው፤ ባቀረበው የጨረታ ዋጋ እና የቅድመ ክፍያ መጠን ላይ ተመስርቶ በሚደረግ ስሌት ከፍተኛውን ነጥብ ሲያገኝ ነው። በአዋጅ ረቂቁ ላይ ይህ ተቀይሮ የሊዝ ጨረታ አሸናፊዎች የሚለዩት፤ ከጨረታ ዋጋ እና የቅድሚያ ክፍያ በተጨማሪ የሊዝ ክፍያ ማጠናቀቂያ ጊዜ ተሰልቶ በሚገኘው የድምር ውጤት ነው። የጨረታ ዋጋ 65 በመቶ፣ የቅድሚያ ክፍያ 20 በመቶ እና የሊዝ ክፍያ ማጠናቀቂያ 15 በመቶ ነጥብ ይኖራቸዋል።

ተጨማሪ መረጃ ፦

🔵 አዲሱ አዋጅ የሊዝ መነሻ ዋጋ የሚከለስበትን ጊዜ ከ2 ዓመት ወደ 3 ዓመት ከፍ አድርጎታል።

NB. " የሊዝ መነሻ ዋጋ " ማለት ዋና ዋና የመሰረተ-ልማት አውታሮች የመዘርጊያ ወጪን፣ ነባር ግንባታዎችና ንብረቶችን ለማንሳት የሚያስፈልገውን ወጪና ለልማት ተነሺዎች የሚከፈል ካሳአን እና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን መስፈርቶች ታሳቢ ያደረገ የመሬት ዝቅተኛ ዋጋ ነው።

🔵 ረቂቁ የመሸጋገሪያ ድንጋጌም ያያዘ ሲሆን አዋጁ ከመውጣቱ በፊት አግባብ ላለው አካል ለቀረቡ የከተማ መሬት ጥያቄዎች የሚሆን አንቀጽ አስቀምጧል። እነዚህ ጥያቄዎች አዋጁ ከጸናበት ቀን ጀምሮ እስከ 6 ወራት ድረስ፤ በነባሩ አዋጅ እና አዋጁን መሰረት አድርገው በወጡ ደንብ እና መመሪያዎች ውሳኔ የሚያገኙ እንደሚሆን ገልጿል።

ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የ ' ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ' ድረገጽ ነው።

ፎቶ ፦ ፋይል

@tikvahethiopia
#ረቂቅአዋጅ

የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ለማሻሻል የወጣው ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል።

የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ምን ይዟል ? ምን ዋና ዋና ማሻሻያ ተደርጓል ?

🔵 ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የስራ አመራር ቦርድ አሰያየም እና አወቃቀር ጋር በተያያዘ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

በአዋጁ የተዘረጋው የቦርድ አሰያየምና አወቃቀር የተንዛዛ እና ረጅም ሂደትን የሚከተል መሆኑ ከዘርፉ ተለዋዋጭ ሁኔታ አንጻር አብሮ የማይሄድ መሆኑ፣ ይህም ባለሥልጣኑ መደበኛ ተልእኮዎችንና አስቸኳይ ውሳኔዎችን ከመስጠት አንጻር የመፈጸም አቅሙን የሚያስተጓጉል መሆኑ፣ እንዲሁም በነባሩ አዋጅ የተካተተው የቦርድ አባላት ስብጥር ከባለሥልጣኑ ሬጉላቶሪ ሚና ጋር በተያያዘ የጥቅም ግጭትን የሚፈጥር ሆኖ መገኘቱ እንደክፍተት ተገልጿል።

የተደረጉ ማሻሻያዎች ፦

" አንቀፅ 9/5/ሀ/ የቦርዱ አባላት ለመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ቅርበትና አግባብነት ካላቸው የተለያዩ አካላት እና የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ይሆናሉ " በሚል በረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ የተደረገበት ሲሆን የቦርድ አወቃቀር ላይ አስቻይ ያልሆኑ ገደቦች እንዲሻሻሉ ተደርጓል፡፡

🔵 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የስራ አመራር ቦርድ በወሳኝ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

በረቂቁ ማብራሪያ ላይ ፥ " በመርህ ደረጃ የባለሥልጣኑ ስራ አመራር ቦርድ ባለሥልጣኑን በፖሊሲ የሚመራ አካል ቢሆንም፣ በአዋጁ አንቀፅ 13(2) መሰረት በዕለት ተዕለት የሚከወኑ የሬጉላቶሪ ሥራዎች በቦርድ እንዲከናወኑ ተደርጓል " ይላል።

" በተጨማሪም የሀገርን ደህንነት ወይም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ የሚያደፈርስ ዘገባ በማናቸውም መገናኛ ብዙሃንና በማናቸውም ጊዜ ቢሰራጭ በአንቀፅ 81 መሰረት ፈቃድ የማገድ፣ የመሰረዝና አለማደስን የተመለከተ አስተዳደራዊ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ለቦርድ ተሰጥቷል " ሲል ያብራራል።

" ስለሆነም አዋጁ ቦርዱ ከሚጠበቅበት የፖሊሲ አቅጣጫ ሰጪነት ሚና ውጭ በዕለት ተዕለት የሬጉላቶሪ ተግባርና ሃላፊነት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡  ይህም ባለሥልጣኑ በህግ የተሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ መስጠት እንዳይችል ገድቦታል " ይላል።

" በተመሳሳይ የሚዲያውን አውድ ታሳቢ ያላደረገ የውሳኔዎች መዘግየት በዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ በሀገር ደህንነት ላይ አሉታዊ ጎኑ አመዝኖ ይታያል " ሲክ አክሏል።

የተደረጉ ማሻሻያዎች ፡-

" የፈቃድ አለማደስ፣ የፈቃድ ማገድ፣ ወይም የፈቃድ መሠረዝ የሚያስከትሉ ውሳኔዎችን የመወሰን ሥልጣን የባለሥልጣኑ ቦርድ ይሆናል" የሚለው ድንጋጌ ተሻሽሏል።

የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ከባድ የገንዘብ ቅጣት ወይም አንድ ፕሮግራም ማገድ ወይም መሰረዝ የሚያስከትሉ ውሳኔዎችን የመወሰን ሥልጣን
#የባለሥልጣኑ_ይሆናል፡፡

ረቂቁ " ባለሥልጣኑ የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ መሰረዝ፣ ከባድ የገንዘብ ቅጣት ወይም አንድ ፕሮግራም መሰረዝ የሚያስከትል ቅጣት የሚዳርግ ክስ ሲቀርብለት ባለፈቃዱ ወይም የምዝገባ የምስክር ወረቀት የተሰጠው መገናኛ ብዙሃን በጉዳዩ ላይ ያለውን ምላሽ በፅሁፍ በ7 የስራ ቀናት ውስጥ ለባለሥልጣኑ እንዲያቀርብ እድል ሊሰጠው ይገባል "  ይላል።

" በተወሰኑት ውሳኔዎች ቅር የተሰኘ ባለፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት የተሰጠው የመገናኛ ብዙሃን ውሳኔው በደረሰው በ14 የሥራ ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለቦርዱ ሊያቀርብ ይችላል፤ ቦርዱ አቤቱታው በደረሰው በ30 የሥራ ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለበት " በሚል በረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡

🔵 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አሿሿምን በተመለከተ ማሻሻያ ተደርጓል።

" የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በቦርዱ ተመልምሎ በመንግስት አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሰየማል " የሚለው ድንጋጌ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡

የተደረገው ማሻሻያ፡-

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል፡፡

🔵 ከብሮድካስት አገልግሎት ባለፈቃድ ግዴታዎች ጋር በተያያዘም ማሻሻያ ተደርጓል።

የረቂቁ ማብራሪያ ላይ " በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ከቀጥታ ሥርጭት ውጭ የማናቸውም ፕሮግራም ይዘት በጣቢያው ከመሠራጨቱ በፊት ሕግን የሚያከብር መሆኑን የማረጋገጥ፤ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ይህ ድንጋጌ በቀጥታ ስርጭት ወቅት ህገወጥ ይዘቶች ከተሰራጩ የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎችን ተጠያቂ የማያደርግ በመሆኑ፣ አስፈላጊውን ኤዲቶሪያል ጥንቃቄ እንዳያደርጉ ያደርጋል፡፡

በመሆኑም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በሚፃረር እና በሀገር ሉአላዊነት ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ እንደ ጦርነት ጥሪ እና የጥላቻ ንግግር የመሳሰሉ ይዘቶች እንዲሰራጩ መንገድ ይከፍታል፡፡

በመሆኑም ይህን ለመከላከል የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመውሰድ ማሻሻል አስፈልጓል " ብሏል።

የተደረገው ማሻሻያ፡-

የማናቸውም ፕሮግራም ይዘት በብሮድካስት አገልግሎት ጣቢያው ከመሠራጨቱ በፊት ሕግን የሚያከብር መሆኑን የማረጋገጥ፤ በሚል በረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
#ረቂቅአዋጅ

የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅን ለማሻሻል ያለመ ረቂቅ አዋጅ ትላንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።

ረቂቁ ምን ይዟል ?

🔵 የአፍ መፍቻ ቋንቋ እንደ ትምህርት አይነትነት እና እንደ ማስተማሪያ ቋንቋነት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ የሚሰጥ ሆኖ እንደ ትምህርት አይነትነትና እንደ ማስተማሪያ ቋንቋነት መሰጠቱ የሚያበቃበትን የክፍል ደረጃ ክልሎች ይወስናሉ።

🔵 የእንግሊዘኛ ቋንቋን በማስተማሪያነት ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ማስተማር ግዴታ ነው። ክልሎች ግን ከዚያ በፊትም የማስተማሪያ ቋንቋ ማድረግ ከፈለጉ ይችላሉ።

🔵 ተማሪዎች ቢያንስ 3 ቋንቋዎችን እንዲማሩ ይደረጋል። የአፈጻጸም መመሪያ በቀጣይ ይወጣል።

🔵 አንድ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ከፌደራል መንግስት የስራ ቋንቋዎች መካከል የተማሪን አልያም የወላጅን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ ከ3ኛ-10ኛ ክፍል ድረስ እንዲማሩ ይደረጋል።

🔵 በአጠቃላይ አንድ ተጨማሪ የውጭ ቋንቋ ክልሎች በሚመርጡት መሰረት ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ በአማራጭነት ይሰጣል። የእንግሊዘኛ ቋንቋ ደግሞ ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ እንደ አንድ የትምህርት አይነት ይሰጣል።

🔵የተማሪዎች ምዘናን በሚመለከት ደግሞ እስከ 1ኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ የሚባለው እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ ተማሪዎችን በደረጃ ማስቀመጥን ይከለክላል፡፡

🔵 ከክፍል ወደ ክፍል መዘዋወርን በሚመለከት በሁሉም የትምህርት እርከኖች ከክፍል ወደ ክፍል ማለፍ የሚቻለው ተማሪዎች በሁሉም ትምህርት አይነቶች 50 ከመቶ እና ከዛ በላይ ውጤት ሲያመጡ ብቻ ነው።

🔵 ክልላዊ ፈተናዎችን ማለፍ ያልቻሉ ተፈታኞች ከሁለት ጊዜ በላይ በነጻ ፈተና ላይ መቀመጥ አይችሉም። ተፈታኞች በግላቸው እንዲፈተኑ ይደረጋል።

🔵 የመምህራንን ትምህርት እና ስልጠና ጉዳዮችን በሚመለከት ሴቶች ለመምህርነት ስልጠና በሚወዳደሩበት ጊዜ ለምልመላ የሚያስፈልጉትን አጥጋቢ መስፈርት አሟልተው በውድድር ወቅት ከወንዶች ጋር እኩል ነጥብ በሚያገኙበት ወቅት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ይደረጋል።

🔵 አንድ መምህር በስራ ላይ እያለ በመንግስት ወጪ ደረጃውን የሚሻሽል ስልጠና ከወሰደ ለእያንዳንዱ የስልጠና ዓመት አንድ ዓመት በሙያው ማገልግል ግዴታ አለበት።

🔵 ወሲባዊ ጥቃትን የሚመለከቱ ወንጀሎች መፈጸሙ ተረጋግጦ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ መሆኑ የተረጋገጠበት ሰው በማንኛውም የትምህርት ተቋም ውስጥ በመምህርነት እንዳይቀጠር ይታገዳል።

🔵 የግል ትምህርት ቤትን ማቋቋም በሚመለከት፥
° በፍርድ ቤት የመክሰር ውሳኔ የተሰጠበት ወይም እዳ መክፈል ያልቻለ ሰው ፣
° ትምህርት ቤቱን ለማቋቋም ፈቃድ ከሚጠይቀው አመልካች ውስጥ ድርሻ ያለው ሰው
° በወሲባዊ ወንጀል አልያም በህጻናት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ጥፋተኛ መሆናቸው በፍርድ ቤት የተወሰበት ሰው ፈቃድ ማግኘት አይችልም።

🔵 ሀገር አቀፍ የትምህርት ፈንድ እንዲቋቋም አዋጁ ይፈቅዳል ይላል፡፡

ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የአል አይን አማርኛ አገልግሎት ነው።

@tikvahethiopia
#ነዳጅ #ረቂቅአዋጅ

🔴" ዋናው ነገር ኮንትሮባንድ ንግድ መስራታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከባንኮች ብድር መውሰጃ እንደሆነ አረጋግጠናል " - የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት

🔵 " ለኮንትሮባንድ ንግድና ብድር ማግኛ ብሎ የገባው ኩባንያ ስርዓት ይይዛል " - ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር

በህገወጥ የነዳጅ ግብይት የታየዘ ግለሰብ ነዳጁ ተወርሶ ከ3 ዓመት በማይበልጥ እስራትና እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ።

ረቂቁ ምን ይላል ?

- አዲስ የነዳጅ ምርት አከፋፋዮች ስራ ለመጀመር ቢያንስ 500 ሺህ ሊትር የነዳጅ ውጤቶች መያዝ የሚችል ማከማቻ / ዴፖ እና 4 ማደያዎችን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ያስገድዳል።

- በስራ ላይ ያሉ ማደያዎች ደግሞ አዋጁ ከሚጸድቅበት ጊዜ ጀምሮ ለአዲስ አከፋፋዮች የተጣሉትን ግዴታዎች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።

- አዲስ ጀማሪ ሆኑ ነባሮቹ በ3 ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ 6 ማደያዎችን የመገንባት ግዴታ አለባቸው።

- የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጭ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው ቦታና የግብይት ስርዓት ውጭ ሲሸጥ የተገኘ ወይም አደጋ ያስከትላሉ በተባሉ መያዣዎች ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ የተያዘው የነዳጅ ውጤት ተወርሶ ከ3 ዓመት በማይበልጥ እስርና ከብር 50 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ የሚደርስ ቅጣት ይፈጸምበታል።

- መንግሥት ከሚያወጣው የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ተመን ውጪ በተደጋጋሚ የመገበያየት ወንጀል እንዲሁም የነዳጅ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር መቀላቀል እስከ 3 ዓመት እስርና እስከ 300 ሺህ ብር ቅጣት ያስጥላል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ እስመለአለም ምህረቱ ምን አሉ ?

አሁን አሁን ወደነዳጅ አቅራቢነት ስራ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እየታየ ነው ብለዋል።

በድርጅቱ በተደረገው ጥናት ይህ ፍላጎት የኮንትሮባንድ ንግድ እና ከባንክ ብድር ለመወሰድ ተብሎ የሚደረግ እንደሆነ ተደርሶበታል ሲሉ ገልጸዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው ፥ በዚህ 9 እና 10 ዓመት ውስጥ ከነበሩት 8 ወይም 9 ካምፓኒዎች አሁን 59 መድረሳቸውን ጠቁመዋል።

3ቱ የመንግሥት ገንዘብ አባክነው በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ናቸው።

56ቱ ካምፓኒዎችን በማርኬትሼር በመደልደል ነዳጅ እየተሰጠ መሆኑን የገለጹ ሲሆን " ይህ ሁኔታ እራሱ እስካሁን ስምምነት የሌለበት ሁልጊዜ ጭቅጭቅ ያለበት ድርጊት ነው " ብለዋል።

ወደ ነዳጅ ግብይት አዲስ የሚገቡ ካምፓኒዎችን በተመለከተ ምንድነው አላማቸው ? ለምንድነው እንዲህ እያደገ የመጣው የሚለው መጠናቱን ገልጸዋል።

በጥናቱ ውጤትም " ዋናው ነገር ኮንትሮባንድ መስራታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከባንኮች ብድር መውሰጃ እንደሆነ ነው የተረጋገጠው " ብለዋል።

እነዚህ የነዳጅ ካምፓኒዎች ባንኮች ጋር ሄደው ብድር በሚጠይቁበት ጊዜ ባንኮቹ " ከናተ ጋር ያላቸው የሥራ አፈጻጸም ይጻፍልን " እየተባለ ደብዳቤ እንደሚጻፍ ገልጸዋል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ምን አሉ ?

° አዋጁ አላማ መንግሥት በየዓመቱ በሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጣበትን ለነዳጅ ምርት በአግባቡ ለማስተዳደር ነው።

° በመንግሥት በኩል የነዳጅ አቅርቦትን የማበራከት አላማ የለም።

° አዋጁ በእያንዳዱ የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ባሉት ተዋናዮች ላይ የህግ ሪስትሪክሽኖችን ይጥላል። የአቅራቢ፣ የማደያ ... ግዴታዎች አሉ።

° ግብይታችን ችግር አለበት። የአቅርቦት ችግር ሳይኖር ስርጭት ላይ ትልቅ ችግር አለ። የታሰበላቸው ቦታ ያለመድረስን በተመለከተ በክልሎች የሚቀርበው ቅሬታ ገሚሱ ትክክል ነው።

° ነዳጅ አለ !! ሳምንት ሁለት ሳምንት ገበያ ማስራብ ፣ በነዳጅ ማደያዎች ውስጥ ነዳጅ ይዞ ' ቤንዚን የለም ፤ ናፍጣ የለም ' ብሎ መለጠፍ ይሄ ደግሞ ተጠያቂነት የማያስከትልበት ሴክተራል ባህሪው እንዲቀየር ይታሰባል፤ ይፈለጋል በመንግሥት በኩል ለዛም ነው ይሄ አዋጅ የሚወጣው።

° ከዚህ በኃላ ንግድን አንከለክልም እናሰፋዋለን ፤ ግብይቱ እንዲሳለጥ እንፈልጋለን ነገር ግን ለኮንትሮባንድ ንግድና ብድር ማግኛ ብሎ የገባው ኩባንያ ስርዓት ይይዛል።

° የነዳጅ ኮታ እና ስርጭት ላይ ፍትሃዊ ስርዓት ለመፍጠር ይሰራል።

° ከአቅርቦት እና ስርጭት ይልቅ ማስተዳደሩ ከባድ ነው።

° ነዳጅ እያላቸው ዘግተው የሚቀመጡ ማደያዎች በስፋት አሉ። የቅጣት መጠኑ ላይ ጠንካራ ስራ ይሰራል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ መረጃውን ከሪፖርተር እንዲሁም ከህ/ተ/ም/ቤት የቀጥታ ስርጭት ማግኘቱን ይገልጻል።

#ኢትዮጵያ #ነዳጅ #ረቂቅአዋጅ

@tikvahethiopia